August 11, 2015
11 mins read

ለኢትዮጵያዊውስ ማን አለው?

በያሬድ ታዬ መኮንን፤ ቶሮንቶ

ቶሮንቶ ከመጣሁ ሶስተኛ ሳምንቴን ያዝኩኝ፡፡ ቀኑን ሙሉ፤ ከሰሜን ደቡብ፤ ከምስራቅ ምእራብ ሳካልለው ውዬ፤ መጀመሪያ በጓደኛዬ ቤት፤ አሁን ደግሞ መንግስት በሰጠኝ፤ በቶሮንቶ፤ ኦንቴርዮ ጎዳና ላይ በሚገኘውና እኔና ሌላ አንድ ሰው በምንጋራው ክፍል ጣሪያ ስር ሆኜ፤ ወደጣሪያው አንጋጥጬ፤ የኢትዮጵያና የካናዳ ህይወቴን፤ እንዲሁም ነጻነቴን ማሰላሰል ይዣለሁ፡፡ ነጻነት እንዴት ይጥማል፡፡ ድህነት አንድ ነገር ነው፡፡ መራብም አንድ ነገር ነው፡፡ ሰው ግን ነጻነቱንና ክብሩን እንዴት ባገሩ ይነፈጋል፡፡ እነሆ በማያውቁን፤ በማላውቃቸው፤ በሰው አገር የተሰጠኝን ክብርና እንክብካቤ እያጣጣምኩ ሳለሁ፤ የሩቅ ጓደኛዬ የነገረኝ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡  ይህ የሩቅ ጓደኛዬ አውነተኛ ታሪክ ነው ብሎ ያጫወተኝን፤ እኔም የተቀበልኩትን ገጠመኝ ላጫውታችሁ፡፡

እውነት መሆኑን እንዴት ተቀበልከው፤ ያላችሁኝ እንደሆነ ኢትዮጵያ ሃገሬ ውስጥ እንኳን ይሄ ይቅርና፤ ወያኔ “ተቃዋሚዎችም መርጠውኛል”  ብሎን ተቀብለነው የለም እንዴ? መቼ ነው ያለው፤ ለምትሉኝ ደግሞ አሁን ባሳለፍነው ምርጫ 2007፤ በአይኔ ያየሁት፤ ምናልባትም ብዙዎቻችሁ በሶሻል ሜዲያ ያነበባችሁ፤ እና ያሰገረማችሁ የምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው፤ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች፤ ከ1000 መራጮች መካከል ኢህአዴግ፤ 1000 ከ1000 ተብሎ በምርጫው ጣቢያ ሲለጠፍ፤ አስቡት እንግዲህ፤ ይህ 1000 መራጭ የተቃዋሚ ተመራጭ ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ መሆኑን፡፡ እንግዲህ ይህንንም አምነን “አሜን” ብለን ተቀብለን የለም ወይ? እንግዲህ የጓደኛዬንም የህይወት ገጠመኝ አምኜዋለሁ፡፡

የወያኔን ጉድ እስቲ ይሁን ብለን እንለፈውና ወደዋናው ታሪክ እንመለስ፡፡ በነገራችን ላይ ስም መጥቀስ ስላላስፈለገኝ፤ ጓደኛዬ እያልኩ በመተረኬ፤ ቅር አይበላችሁ፡፡ ያው እንደምታውቁት ጊዜው አስቸጋሪ ስለሆነ ስም ባይጠቀስ ይሻላል ብዬ ነው፡፡

ይህ ጓደኛዬ እና አንድ የስራ ባልደረባው ከስራ በኋላ መሸትሸት ሲል ለመዝናናት፤ 22 አካባቢ ወደሚገኙት የመዝናኛ ቤቶች ጎራ ይላሉ፡፡ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላኛው በመቀያየር ሲዝናኑ ይቆዩና፤ አትላስ አካባቢ ወደሚገኝ አንድ ታዋቂ የጭፈራ ቤት (በተለምዶ ክለብ) ይገባሉ፡፡ በክለቡ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች የነበሩ ሲሆን፤ ከእነዚህም መሀከል ከወደምስራቅ አካባቢ የመጡም (በግምት ቻይናውያን ይመስሉታል) ነበሩበት፡፡ ሙዚቃው ቀጠለ፤ ጨዋታውም ደራ፡፡ መቼስ በዳንስ ውዝዋዜ መሀል መነካካት አይጠፋም፤ የጓደኛዬ ጓደኛ ከአንዱ ቻይናዊ ጋር ይነካካል፡፡ ከዚያም ይቅርታ ጠይቆ ጨዋታውን ይቀጥላል፡፡ ቻይናዊው ጉዳዩን በቀላሉ አልተመለከተውም፡፡ “ሳታውቅ ሳይሆን እንደው ነገር ስትፈልገኝ ነው” በማለት እምቧ ከረዮውን አቀለጠው፡፡ ሰዎች ነገሩን ለማረጋጋት ቢሞክሩም፤ አጅሬ ቻይና ካልደበደብኩት ብሎ ሰፈሩን ቀውጢ አደረገው፡፡ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ መሆን በጀመረበት ሰዓት፤ የሀገሬው ፈላጭ ቆራጭ፣ ምንም ቢያደርግ ጠያቂ የሌለው፣ ማሰር፣ መደብደብ ካሻውም መግደል መብት የተሰጠው፤ መቼስ ታውቁታላችሁ ስለማን እያወራሁ እንዳለ፤ የወያኔ አካል የሆነው፡ ፈደራል ፖሊስ መጣ፡፡ ግርግሩም ቀዝቀዝ እያለ ሁሉም በመረጋጋት ስሜት ባሉበት ሁኔታ፤ ቻይናዊው ፌዴራሉን ሲመለከት የልብልብ ተሰምቶት ኖሮ፤ እጁን ሰንዝሮ የጓደኛዬን ጓደኛ በቡጢ ቢለውስ፡፡ ያኛውስ ከማን አንሶ በእጁ በሶ አልጨበጠ መልሶ ቢቦቅሰውስ፡፡ ታዲያ ይኽኔ ነበር ግራ የሚያጋባውና ማንነትን የሚፈታተነው ጉዳይ የተከሰተው፡፡

እንዲህ ነው የሆነው፡፡ ከፌዴራል ፖሊሶቹ መሀከል ሁለቱ ተንደርድረው መሃል በመግባት አንደኛው ቻይናዊውን ወደ ጎን ሲያደርገው፤ ሌላኛው የጓደኛዬን ጓደኛ በዚያ በያዘው የሚያቃጥል ቆመጥ (መቼስ የቀመሰ ያውቃታል) ሲዠልጠው ለተመለከተ ማንኛውም ሰው፤ እጅግ በጣም አስገራሚና አሳዛኝ ነበር፡፡ ቻይናዊውም ለካስ ይኼን አውቆ ኖሯል እንደዛ የልብልብ ተሰምቶት ቦክስ የሰነዘረው፡፡ ለጓደኛዬ ጉዳዩን ዝም ብሎ መመልከት አልሆንለት ቢለው፤ ጠጋ ብሎ በልመና መልክ ለማግባባት እየሞከረ፤ “ኽረ እባካችሁ ተውት እሱ ምንም አላጠፋም” በማለት ለማስረዳት ቢሞክር፤ አንተስ የት ይቀርልሃል ብለው ያላንዳች ማመንታት የዚያች ቆመጥ ተቋዳሽ በማድረግ፤ ሦስት አራት ጊዜ ካቀመሱት በኋላ፤ ቻይናዊውን በክብር ከይቅርታ ጋር ወደ ውስጥ እንዲገባ በምልክት (ያው እንደምታውቁት ቋንቋ ችግር ነው) ይነግሩት እና ጓደኛዬን እና ጓደኛውን በያዙት ፒክ አፕ መኪና ጭነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ፡፡

ለመዝናናት የወጡት እኚህ ኢትዮጵያውያን፤ በገዛ ሀገራቸው ክብር ተነግፏቸው፤ ለውጭ ዜጋ ጎንበስ ቀና ባለማለታቸው የመዝናኛ ጊዜያቸውን በፖሊስ ጣቢያ አሳልፈው፤ እንዲህ አይነት ነገር እንዳይለመዳቸው ከማስጠንቀቂያ ጋር በበነጋታው መለቀቃቸውን የነገረኝ፤ እጅግ በንዴት እና በቁጭት መንፈስ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ክስተቶች በተለያየ መንገድ ያጋጠመን ሰዎች እንኖር ይሆናል፡፡ ያላጋጠማችሁም ወደፊት ቢያጋጥማችሁ ግር አይበላችሁ፡፡ እንደው ነገርን ነገር አነሳውና ነው እንጅ፤ ከዚህም የባሰ ብዙ አይተናል ሰምተናል፡፡

ሁሌም ውስጤን የሚያንገበግበው ነገር ቢኖር፤ ቢያንስ ለሌሎች ዜጎች ሀገራችን ላይ የሚሰጣቸውን ክብር ያክል እንኳን ሰው በሀገሩ የማይሰጠው ከሆነ ለኢትዮጵያዊውስ ማን አለው? ማንስ አለሁልክ፤ አይዞህ ይለዋል?

ሁሉም ነገር ከራስ ነው የሚጀምረው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፍቅርም ቢሆን፣ አክብሮትም ቢሆን ለራስ ሰጥቶ ነው ወደሌላኛው የሚኬደው፡፡ እራሱን እና የራሱ የሆነውን የማያከብር፤ ሌላውን አከብራለሁ እጠብቃለሁ ቢል፤ ለእኔ እንደማስመሰል ነው የምቆጥረው፡፡ እዚህ ላይ የሌላ ሀገር ዜጎች አይከበሩ እያልኩኝ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሰው ከሀገሩ የበለጠ ጥበቃ እና ከለላ ሊያገኝ የሚችልበት የተሻለ ቦታ የት ነው ያለው? ያደጉት እና እኛን ጥለው የሄዱት ሀገራት ከሀገራቸው አልፈው በሰው ሀገር ስለሚገኙት እያንዳንዱ ዜጎቻቸው ክትትል በማድረግ፤ ያሉበትን ሁኔታ ሰላማዊነት ሲያረጋግጡ የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገራችን ውስጥ ግን ለሚከሰተው ማንኛውም ጉዳይ የዜጎቹን መብት ሊያስከበር የሚችል ስራ የመስራት ግዴታ የመንግስት አንዱ ሃላፊነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሰው ሀገር አለኝ ብሎ በሀገሩ ሰርቶ እና ተለውጦ፣ የዘር፣ የጎሳ፣ እንዲሁም የቀለም ልዩነት ሳይገጥመው መኖር ካልቻለ፤ ከመሰደድ ውጭ ምን አማራጭ ይኖረዋል? አስቡት እስቲ በሀገሩ ክብር ተነፍጎት በሰው ሀገር ተከብሮ የሚኖረውን ስትመለከቱ ምን ይሰማችኋል? እንደው ወያኔ የሀገር ትርጉም አልገባውም እንጂ ቢገባው ኖሮ ይሄንን ግጥም ያዜምልን ነበር፡-

ሀገርን ሀገር ያሰኘው
ሰው የተባለው ፍጡር  ነው!

ያሬድ ታዬ መኮንን፡ ሀምሌ/ነሀሴ፤ 2015፡ ቶሮንቶ

3 Comments

  1. weyane segeba and,yezowat yemeta quwanquwa alech

    semwam ክ tebalalech kkkkkkkk
    mindenew ክ????? ታውቀዋለክ,,, ነገርኩክ,,, አየኩክ,,, ወደደኩክ,, አሳየኩክ,, አመንኩክ,,,ታዘብኩክ,, አሣየኩክ

    የ አራዳ ቁዋንቁዋነው ? ማፈረያ ሁሉ !!!ሕ !!!!በል ነገርኩህ!! ታውቀዋለህ!!! አየሁህ!! መታሁህ !!!! ተማር !!!!

  2. ለኢትዮጵያዊውስ ማን አለው? በያሬድ ታዬ መኮንን፤ ከቶሮንቶ:: የሚለውን መጣጥፍ በጽሞና ነበር ያነበብኩት እርግጥ ነው ይህ የሱ ጓደኛ ገጠመኝ ነው :የኔን ገጠመኝ ላክልበት: እኔ ቤተሰብ ለማየት ከአምስት አመት በፊት ሄጄ በነበረበት ወቅት ሾላ ገቢያ አሊያም የካ ሚካኤል እየተባለ በሚጠራበት ሰፈር አንድ ቻይናዊ ሰው በሚያሽከረክረው መኪና አንድ ወጣት ሰው ከገጨ ቦሃላ ካመኪና ወርዶ ከተገጨበት ቦታ ሊነሳ የሞከረውን ወጣት በካልቾ ሲመታው በማያቴ በንዴት የቻይነውን ማጅራት በመያዜ በአካባቢው የነበሩት ፖሊሶች እንዴት ማጅራቱን ትይዛለህ ይህን የዊጪ ዜጋ እኮ ነው ቢሉኝ አታዩቱም ወይ ሰው መግጨቱ ሳያንስ ከመኪና ወርዶ ሲማታ ብላቸው:: እያየ አይሄድም ወይ ነበር መልሳቸው እኔንም ሌላው ፖሊስ እንዴት የውጪ ዜጋ ማጅራት ትይዛለህ ብሎ ወደጎን ሲወስደኝ እኔም የውጪ ዜጋ ነኝ በማለት ፓስፖርቴን እያሳየሁት ሳለ አንድ አብሮ አዴጌ የሆን የትራፊክ ፖሊስ በሞተር ሳይክል ሲያልፍ ተመልክቶ ሞኦተር ሳይክሉን በማቆም የገላገለኝና በሰላም ወደ ምሄድበት የሄድኩት::እኛ ያልገባን የኢተዮጵያ መንግስት የሚባሉት እኮ ጥርስ የሌላቸው አንበሳ መሆናቸውን ስላልገባን ነው የምኝቆጨው: በተረፈ ወደፊት ከተዎወቅን ቡና እየጠጣን ሌሎች ወጎችን አወጋሃለው ቶሮንቶ ከሆንክ:: ከተመቸህ ኦገስት 16/2015 ዳን ፎርዝ በሚገኘው በሂሩት ምግብ ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ ለታሰሩት የሂሊና እስረኞች የገንዘብ መዋጮ ስለሚደረግ እንድትገኝ እጋብዝሀለው እኔንም ልታገኘኝ ትችላለህ ምልክት ካስፈላገህ ገብስማ ጸጉር ያለኝ የጥቁር ቆንጆ::
    ታምራት

Comments are closed.

Previous Story

በባህር ዳር ቀበሌ 11 ወጣቶችና በፖሊሶች መካከል ግጭት ተፈጠረ * አባላቱ በገፍ እየከዱት በሚገኘው አየር ኀይል አለመተማመኑ ስር ሰዷል

FB IMG 1439247088442
Next Story

የማለዳ ወግ…ለአሚራና ቤተሰቦቿ የጎደለው ፍትህ … !

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop