ይገረም አለሙ
ይህ በርዕስነት የተጠቀምኩበት አባባል በደቡብ ምዕራብ የሀገራችን ክፋል ሸካ ዞን በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚነገር ነው፡፡አባባሉ በአካባቢው ቋንቋ ሲነገር ለጆሮ ይጥማል፣ ቀልብ ይስባል፣ እንዲህ ወደ አማርኛ ተመልሶም ቢሆን መልእክቱ ግልጽና በቀላሉ ለመረዳት የማያስቸግር ነው።
ተፈጥሮው ሆኖበት እንጂ የሚቀለው አቡጀዲው ነበር፣ ጉቶው ግን ከባድ ነው፣ እንደውም የጦሩን ጫፍ ሊያጥፈው ሲብስም ሊሰብረው ይችላል፡ነገር ግን ጦሩ የተሰራው ከመጥረቢያ ብረት ሆነና መጥረቢያው ደግሞ ተፈጥሮውም ለጉቶ መፍለጥ፣ የኖረውም ከጉቶ ጋር ሲታገል በመሆኑ አቡጀዲውን አያውቀውምና ወደ ለመደው ግን ጠንካራና አስቸገሪ ወደ ሆነው ጉቶ መሄዱን ነው የሚመርጠው፡፡
የህውኃት መስራቾች ለሥልጣን ሲሉ ጫካ መግባታቸውን ብሶት የወለደን በሚል ማስመሰያ ጋርደው ዱር ገደሉን መኖሪያቸው አድርገው፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻቸውን ገድለው፣ በዛው መጠን የትግል ጓዶቻቸውን ካጠገባቸው አጥተው ለሥልጣን የበቁ በመሆኑ ሰላማዊ ትግል ብሎ ነገር አያውቁም፤ በልዩነት ተከባብሮ መኖርንም ሆነ የዓላማም ሆነ የአደረጃጅት ልዩነት ካላቸው ጋር ውይይት ብሎ ነገር አያስቡትም፤ከፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በላይ የአንድ ሀገር ልጅነት ሚዛን የሚደፋ መሆኑ አይገባቸውም፡፡ ከመጥረቢያ ብረት የተሰራው ጦር ወደ ቀላሉ አቡጀዲ ሲወረወር ወደ ጠንካራው ጉቶ እንደሚሄደው ሁሉ ወያኔዎችም የህይወት ጥፋት፣ የሀገር ሀብት ውድመት፣ የትውልድ ተወቃሽነት፣ የህግና የታሪክ ተጠያቂነት በማያስከትለው የሰላማዊ ትግል መንገድ የሰለጠነ ፖለቲካ እናራምድ ሲባሉ እነርሱ የሚታያቸው ትናንት ለቤተ መንግሥት ዛሬ ለከበርቴነት ያበቃቸውና 24 ዓመት በሥልጣን የቆዩበት የሀይሉ/የጡንቻው መንገድ ነው፡፡
ተፈጥሮአቸው ይህ በመሆኑም ነው ስለ ሰላም የሚያዜሙትን፣ ሰላማዊ ትግል መርሀችን ብቻ ሳይሆን እምነታችን ነው ብለው ሁሉን ችለው የሚንፈራገጡትን፤ህገ መንግሥቱን መሰረት አድርገውና በቃል የሚነገረውን ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ተማምነው ብዕራቸውን ለዴሞክራሲ ምስረታ ዘብ ያቆሙትን ወዘተ ጸረ ሰላም፣ አሸባሪ፤ወዘተ በማለት መወንጀልና ማሰርን ስራቸው ያደርጉት፡፡
ዝናር ታጥቀው፣ ጠብ-መንጅ አንግበው ከደደቢት በረሀ እስከ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የደረሱት ነባር ታጋዮች መተካካት እያሉ እንዳንድ ጠብ-መንጃ ያልጨበጡ አዳዲሶችን ቢያሳዩንም የሚተኩት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዶክትሪን ታንጸውና በህውኃት ጸበል ተጠምቀው በመሆኑ ራሳቸው ይለወጣሉ አንጂ ወያኔን አይለውጡትም፡፡ ስለሆነም የመጥረቢያው ብረት ወደ ጦር በመቀየሩ ተፈጥሮውን ሊተው እንዳልቻለው ሁሉ ከጫካ ሳይሆን ከከተማ የተገኙ አንዳንድ ሰዎች በወያኔ ውስጥ መታየት ወያኔ የተወለደበትንና ያደገበትን ማንነቱን ሊለውጠው አልቻልም፡፡
ተፈጥሮ በተመክሮም በተሞክሮም የሚለወጥ ባለመሆኑ ስለ ምርጫ እያወሩ ደም ገብረን ያገኘነውን ሥልጣን በስመ ዴሞክራሲ በምርጫ መንጠቅ ያምራችኋል ወይ ይላሉ፡፡ ስለ ዴሞክራሲ ሲነገር ስለአንባገነንት ያስባሉ፡፡ስለ መድብለ ፓርቲ እየደሰኮሩ ስለ አውራ ፓርቲ ይዘምራሉ፡፡ ስለ ሰላም እያወሩ ወንድ ከሆናችሁ እንደኛ ታግላችሁ ኑ በማለት ይሳለቃሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ነው አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ተካሂደው ለውጥ ሊታይ ቀርቶ አንዳቸውም ምርጫዎች በተወዳዳሪ ፓርቲዎች ስምምነት፤ በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት በአለም አቀፉ ማህበረሰብም ተቀባይነት ሊያገኙ ያልቻሉት፡፡
ስብሰባ፣ ግምገማ፣ ወርክ ሾፕ፣ ሥልጠና፣ የአቅም ግንባታ ወዘተ የወያኔ የእለት ተእለት ሥራ ቢሆንም ተፈጥሮ በስር ነቀል ለውጥ እንጂ በእነዚህ የሚሻሻል ባለመሆኑ ነው ወያኔ የደደቢቱና ወያኔ የቤተ መንግሥቱ ምንም ልዩነት የሌላቸው ሆነው የሰላሙን መንገድ ሲያሳዩዋቸው የጦርነቱ መንገድ የሚታያቸው፡፡
ወደ አቡጀዲ ሲወረውሩት ወደ ጉቶ የሚምዘገዘገው ጦር ተምሳሌት የሚመለከተው ወያኔን ብቻ አይደለም፡፡ በተቃውሞው ጎራ ተሰልፈው፤ ተባበርን ባሉ ማግስት መለያታቸውን የሚያውጁ፣ ፍቅር ሲሉዋቸው ጸብ የሚያነፈንፉ፤ ከመከባበር መናቆር የሚቀናቸው፤ በተግባሩ ሳይሆን በመፎከሩ ቀዳሚ የሌላቸው ወዘተ እነርሱም ተፈጥሮአቸው ሆኖ ነው ጥሩውን ሲሉዋቸው መጥፎውን መምረጣቸው፡፡
ደግሞ አንዳንዶች አሉ ተፈጥሮአቸውም ሆነ እድገታቸው መቃወም ብቻ ሆኖ ለድጋፍ ሲያስቡዋቸው ለትብብር ሲጠሩዋቸው ምክር ሲጠይቋቸው ምላሻቸው ተቃውሞ፣ ማጥላላት ማንኳሰስ የሆነ፡፡ ጸባያቸው ታውቆ ሲተዉ ደግሞ እኛ የለለንበት በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ፡፡ እንዲህም ሆነና ለውጥ እንደናፈቀን፣ ዴሞክራሲ እንዳማረን ኖረን እኛ ወደማንወደው ለወያኔ ግን ተፈጥሮው ወደ ሆነው ጦርነት ማምራት ግድ ሆነ፡፡ ብእር ሊጨብጡ የሚገባቸው እጆች ጠመንጃ ለመያዝ ተገደዱ፡፡ ስንት የሰሩና ወደ ፊትም ብዙ ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎች ያለ ተፈጥሮአቸው፤ ያለ ልምድና ፍላጎታቸው ዱር ቤቴ ለማለት ተገደዱ፡፡
ፍላጎት ዓላማችን ወያኔን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ማንሳት ብቻ ሳይሆን እየተረገዘ የሚጨነግፈው ዴሞክራሲ ለውልደትና ለእድገት እንዲበቃና ደራሲ አያልነህ ሙላቱ በአንድ ተውኔቱ እንደገለጸው በጋሜ የቀረችው ኢትዮጵያ ሹርባ ተሰርታ ማየት ከሆነ በሁሉም ዘንድ መሰረታዊ የሆነ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን የመጣንበት መንገድ ወደ ድል ጎዳና አላመራንም፡፡ በተፈጥሮም ይሁን በተሞክሮ ያዳበርነው አስተሳሰብ ለለውጥ አላበቃንም እናም ¾ አሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሀም ሊንከን የተናገሩት ተብሎ የሚጠቀሰው ይህ ዘመን የማያደበዝዘው አባባል ምክር የሚሆን ይመስለኛል፡፡
«አንድ ትውልድ ያልፍና ሌላ ትወልድ ይተካል፣ ዓለም/መሬት ግን ለዘለአለም ትኖራለች፡፡ ጸጥ ረጭ ያለው ያለፈው ግዜ ፍልሰፍናዎች (ዶግማስ) አውሎ ነፋሳዊ ለሆነው ለዛሬው ችግር ለመፍትሄነት አይመጥኑም፡፡ ጊዜያችን ችግር ያዘለ ስለሆነ በአዲስ ሁኔታ ማሰብና በአዲስ ሁኔታም መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ ማውረድ ይገባል፡፡ ያን ግዜ አገራችንን ለማዳን እንችላለን፡፡ ታሪክን ልናመልጥ አንችልም፣ ልንሸሸው አይሆንልንም፣ ክፉም ሰራን ደግ እንዘከራለን፣ (እንታወሳለን) ግለሰባዊ መታወቅ ወይም አለመታወቅ አንዳችንንም ሆነ ሁላችንን አያተርፈንም፣ የምናልፍበት እሳታዊ ፈተና (ፍርድ) በክብር ወይንም በውርደት ማለፋችንን ይመሰክራል»