ኢህአዴግን ለመጣል መጀመሪያ እኛ መውደቅ አለብን

(ኤርሚያስ አለማየሁ)

ኢህአዴግ በትረ ስልጣኑን ከተረከበበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ህዝባዊ ጥያቄዎች ተፈጥረው ሳይመለሱ ጥያቄዎቹ በጥያቄ ምልክት ውስጥ ተከበው በወረቀት ላይ እንደሠፈሩ ቀሩ፡፡ እጅግ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ያስቀመጡ ጥናታዊ ፅሁፎች በየምሁራኑ ተፅፈው በየትምህርት ተቋሙ ተነበቡ በየጋዜጣው እና በየመፅሔቱ ላይ ሠፈሩ በርካቶች አነበቧቸው አንባቢው ከንፈሩን መጠጠ ግና ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡ በርካታ የሠብዓዊ መብት ታጋዮች ህብረተሠቡን ሠብስበው በንግግራቸው በርካታ ህዝብን አስጨበጨቡ፤ ጭብጨባው ያልቃል የሠብዓዊ መብት ታጋዮቹ ግን ዛሬም ላይ ያወራሉ ሌላ አዳዲስ አጨብጫቢዎች ተፈጥረው ስለንግግር አጨበጨቡ፡፡ እዚህች ሐገር ላይ ከጭብጨባ በቀር ምንም አይነት ተስፋ ሠጪ ነገር ሊታይ አልቻለም፡፡

ኢህአዴግን በጋራ ካልታገልነው ከስልጣኑ አይወርድም በሚል እሳቤ በርካታ በነጠላ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የሐገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከነጠላነት ወደጋቢነት ተቀየሩ ነገር ግን ነጠላ የሆነ ለውጥ ለሐገራችን ህዝብ ሊያስመዘግቡ አልቻሉም ይልቁንስ ጋቢያቸውን አውልቀው በነጠላ መጓዝ ጀመሩ፡፡

ኢህአዴግ በሠለማዊ መንገድ ከስልጣን እንደማይለቅ እሙን ስለሆነ ያሉ የትጥቅ ትግልን ለመጀመር ፎክረው ነፍጥ አነሱ ግና እላያቸው ላይ አሸባሪ የሚል ተቀፅላ ከማግኘት ውጪ ለሐገራችን ፖለቲካ ኢምንት የሆነ ለውጥ ሲያመዘግቡ ለማየት አልታደልንም፡፡ እነርሱም ጫካ ነን ይላሉ ኢህአዴግም ምንሊክ ቤተመንግስት ነኝ እንዳለ አመታት እየመጡ ሔዱ፡፡
በተለያዩ የአለማችን ክፍል በስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሠላማዊ ሠልፍ በአሜሪካ እና በአውሮፓ መንግስታት ፅ/ቤቶች ፊት ለፊት አደረጉ በሠልፋቸውም ኃያላን ሐገራቱ በተለይም ዩ.ኤስ አሜሪካ ለኢትዮጵያው መንግስት የምታደርገውን ድጋፍ ታቆም ዘንድ ጠየቁ ከተቻለም ተፅእኖ እና ማዕቀብ መጣል እንዳለባት ተማፀኑ፡፡ በርካታ ሠልፎች ተደረጉ የውጭ መንግስታት ተወካዮች ሠልፈኞቹን ተስፋ ሠጥተው በተኑ ግና ምን ተፈጠረ? ምንም ጭራሽ ኦባማ ኢትዮጵያ ሄዶ አምባገነኖቹን የልብ ልብ ሰጥቷቸው ተመለሰ ኢህአዴግን ከውጭ ሆኖ ከመታገል ይልቅ የፓርቲው አባላት ከህዝብ ጎን ይቆሙ ዘንድ ስራ መሰራት እንዳለበት በማመን የፓርቲውን አባላት ለማሳመን ስራ ተጀመረ የተወሰኑት የኢህአዴግ አባላት ከድተው ወጡ ግና ኢህአዴግ አሁንም በስልጣን ላይ ነው፡፡ ስለነፃነት፣ ስለሐገር ፍቅር እና ስለኢትዮጵያዊነት በብዕራቸው የሠበኩ ጋዜጠኖች እና ጦማሪያን እነሲሳይ አጌና፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ፋሲል የኔዓለም፣ ሠርካለም ፋሲል፣ ውብሸት ታዬ፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ዘላለም ክብረት፣ ደረጄ ሀብተወልድ እና የመሳሰሉ ስለዚህች ሐገር ሲሉ ታሠሩ ገሚሶቹ ተፈትተው ለስደት ተዳረጉ ገሚሶቹ በእስር ላይ ይገኛሉ ግና ህልማቸው አሁንም አልተፈታም ብእራቸው ቤቱን ሊመታ አልቻለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጥቃትን እንደ ግጭት ማቅረብ የግፉአንን ጩኸት መቀማት ነው - ያሬድ ሃይለማሪያም

በተለያዩ አጋጣሚዎች ከህፃኑ ነብዩ አለማየሁ ጀምሮ እስከ አዛውንቱ ፕ/ር አስራት ወልደየስ ድረስ በተነሡ ግጭቶች እና ህዝባዊ ጥያቄዎች ምክንያትነት ህይወታቸው ዓለፈ አልቅሰን ቀበርናቸው እነርሱም ላይመለሱ ሔዱ እኛም ሐዘን ታቅፈን ከመቀመጥ ውጪ ኢህአዴግ ወርዶ ለማየት አልታደልንም፡፡ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የኢትዮጵያውያን ሙከራ ኢህአዴግን ለመጣል ተብለው የተደረጉ ቢሆኑም ውጤት ሲያመጡ ለማየት አልቻልንም ይህንን ያህል ከተለፋ ስለምን ኢህአዴግ ከስልጣኑ ሊወርድ አልቻለም ኢህአዴግ ባይወርድ እንኳን ለማየት የምንጓጓላት ኢትዮጵያ ልትፈጠር አልቻለችም ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በአንድ የጋዜጣ ፅሁፍ ከባድ ቢሆንም እንደዚህ ፀሐፊ እምነት ትግሉ ሁሉ ፍሬ አልባ የሆነው መሰረቱን የለቀቀ ትግል ስለነበረ ነው፡፡ በኔ እምነት ኢህአዴግን ከስልጣን ላይ አውርደን የተሻለች ዴሞክራሲያዊ፣ የጎሳዎች እኩልነት እንዲሁም ፍትሐዊ የሀብት ከፍፍል ያላትን ኢትዮጵያን መፍጠር የምንችለው ቀጣይ በተዘረዘሩት ነጥቦች ዙሪያ መስራት ስንችል ይመስለኛል፡፡

1. የህዝብ ልብ ውስጥ ለመግባት መስራት

በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ወደሠሜኑ የሀገራችን ክፍል ባቀናሁበት ወቅት ያገኘኋቸው ወጣቶችን ስለተለያዩ የሀገራችን የጋራ ጉዳዮች የማዋራት እድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ እነዚህ ወጣቶች ትምህርት ቀመስ ባይሆኑም በየመፅሔቱ እና ጋዜጣው ባይፅፉም በየማህበራዊ ድሕረ ገፁ ባይጦምሩም በሚኖሩበት አካባቢ በሚኖረው ህዝባቸው እና ወገናቸው ላይ የሚደርሱት ግፎች መነሻቸው የት እንደሆነ ግን ያውቁታል ስለእነርሱ መብት የሚታገል ስለመኖሩ ግን እርግጠኞች አይደሉም ማንስ ያሳውቃቸው? የትኛው ፓርቲስ ቀርቦ አይዟችሁ እኔ ስለእናንተ መብት የምታገል ነኝ አለ?

መርሳት የሌለብን ሐቅ እነዚህ ወጣቶች የብዙሐኑ ኢትዮጵያውያን ነፀብራቅ ናቸው አዎ እነዚህ ወጣቶች 80 ከመቶ ናቸው፡፡ እነዚህ 80 ከመቶ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ለመግባት አዲስ አበባ አልያም ዋሺንግተን ላይ ሆኖ መንቀሳቀስ ፋይዳ ቢስ ነው እዛው ገበሬው መሐል ሰተት ብሎ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ገበሬውን በየአካባቢው አግኝቶ ችግሩ ምን እንደሆነ ማወያየት፣ ተስፋ እንዳለው መንገር ከተቻለም በስራ ማገዝ ስልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ያኔ እንዲህ ያደረገ የፖለቲካ መሪ እስር ቤት ቢገባ አንድም ቀን እስር ቤት ውስጥ እንደማያድር እርግጠኛ ነኝ፡፡ አልያማ ዋሺንግተን ተቀምጦ በፓልቶክ ቅስቀሳ ማድረግ ለአንድ ማንበብ እና መፃፍ ለማይችል ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቶሌ፤ የቦሌ መለማመጃ - መስፍን አረጋ

2. የኢህአዴግን ጭራ እየተከተሉ ከመቃወም መውጣት

በሐገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ እንደልማድ ከተያዙት አብይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ይህ የኢህአዴግን ጭራ እየተከተሉ የመቃወም አባዜ ነው፡፡ ዘወትር ገዢው ፓርቲ አውቆም ይሁን በስህተት የሚፈፅማቸውን እኩይ ተግባራት እየተከታተሉ የተቃውሞ መግለጫ ከማውጣት ልንወጣ ይገባል፡፡ የኢ/ር ሳሙኤል ጉዳይ ሲከሠት የተቃውሞ መግለጫ፤ በደሌ ቢራ የቴዲ አፍሮን ኮንሠርት ሠረዘ ሲባል መግለጫ፤ ኃይለመድህን አበራ ጥገኝነት ሲጠይቅ መግለጫ የፓርቲዎቹ ስራ ከእነደዚህ አይነት ትርኪ ምርኪ መግለጫዎች በላይ ሊዘል ይገባል፡፡ ግለሠቦች በተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ የሚንቀሳቀሱባት ሐገር እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ከማለት ወደህዝብ ወርዶ ህዝብን ማማከር የተሻለ ነው አሁን ላይ ህዝብን ካላዳመጡ መቼ ሊያዳምጡ ነው፡፡

3. ቅድሚያ ለሚሠጠው ቅድሚያ መስጠት

ሌላው ለሐገራችን ፖለቲካ ትንሳኤ አለመምጣት እንደምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል የአንዳንዶች በማያፀድቀውም ሆነ በማያስኮንነው የሚያርደርጉት መረጋገም እና መተቻቸት ነው፡፡ በተለይም ኢህአዴግን በመጣል ሊሻሻሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ኢህአዴግን ከመጣል አስቀድሞ እንደመከራከሪያነት ከማቅረብ ልንወጣ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ሠንደቅ ዓላማ አደረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ መሆኑ እሙን ነው ነገር ግን እርስ በእረስ ሠንደቅ አላማው ላይ ያለው አርማ ትክክል ነው ትክክል አይደለም የሚል ኢህአዴግን ሊጥል የማይችል ክርክር በማንሳት መፋጨት ትርጉም አልባ ነው፡፡ የጎሳ ጥያቄ፣ የቋንቋ ጉዳይ እና የመሳሰሉት ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች መፈታት ያለባቸው ከኢህአዴግ ህልፈት በኋላ እንጂ በዘመነ ኢህአዴግ እንፍታቸው ብንል ከመራራቅ በቀር ሊያቀራርቡ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉም ስለሆነም የመጀመሪያ እቅዳችን በኢትዮጵያ ህዝባዊ ተቀባይነት ያለው መንግስት ስለመመስረት መሆን አለበት፡፡

በእነደዚህ አይነት መልኩ መንቀሳቀስ ካልቻልን ግለሠቦችን ስናሳስር ስናስፈታ፣ ህዝብን ሠብስበን ንግግር ስናደርግ፣ ለፓርቲዎች የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ስንለምን እና ስንሠጥ ከመኖር ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ ኢህአዴግን ለመጣል መጀመሪያ እኛ መውደቅ አለብን::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራጭ መኖር ትሩፋት በኤኮኖሚና በፖለቲካ - ግርማ ሠይፉ

እኛ የዚህ ዘመን ልጆች ነን

1 Comment

Comments are closed.

Share