የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ሶስተኛ ጉባዔ ተከናወነ

ከሰኔ ፳፮ እስከ ፰ ፪ ሺህ ፯ ዓ. ም  (July 3rd to July 5th 2015) በዋሺንግተን ዲሲ የተካሄደው የሸንጎው ሦስተኛ ጉባዔ  በጥሩ ሁኔታ ተካሂዷል። ጉባዔው ሸንጎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያካሄዳቸውን ዘርፈ ብዙ ስራዎችና የልዩ ልዩ የስራ ግብረ ኃይሎች ሪፖርት ገምግሞ በሚቀጥሉት ዓመታት ትኩረት ለሚያደርግባቸው ግቦች ስኬታማነት፤ የሰው፤ የገንዘብና ሌላ ቁሳቁስ፤ የመረጃ፤ የመገናኛና የሕዝብ ግንኙነት፤ የዲፕሎማሲ፤ የወጣቶችና ሴቶች ተሳፎ፤ በሃገር ቤትና በውጭ ከሚንቀሳቀሱ መሰል ድርጅቶች ጋር የግንኙነት አቅሙን ለማጠናከር… ወዘተ ከመቸውም የበለጠ ጥረት እንደሚያደርግ ወስኗል።

አንደሚታወቀው  ሸንጎ እንዲመሰረት ያስገደደው ዋና የፖለቲካ አደረጃጀትና የአመራር ክፍተት የተበታተነውና እርስ በእርሱ የሚጠላለፈው አገር ወዳድ ተቃዋሚ ኃይል ተባብሮ፤ ተመካክሮ፤ ተናቦ፤ ተደራጅቶ፤ ብቁነት ያለው አመራር መስርቶና የጋራ ሰነድ አዘጋጅቶ በተከታታይ ትውልድና ታሪክ ሊጠቀስ የሚችል አስተዋፆ ለማድረግ ሲችል ብቻ ነው የሚል እምነት ስላለው ነው።

አሁንም እንዳለፉት ሃያ አራት አመታት የሚታየው የፖለቲካ ሁኔታ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጥንካሬ ይልቅ የተቃዋሚው ዘርፍ መፍረክረክ፤ መከፋፈል፤ መጋጨት፤ መነታረክ፤ አለመተማመን፤ መጠላለፍ፤ ራሱን ለሰርጎ ገቦች ማጋለጥ… ወዘተ ነው። በጉባዔው ትንተናና እምነት የተቃዋሚው ኃይል አብሮና ተባብሮ ለመስራት አለመወሰን ለአፋኙ፤ በዝባዡና፤ ጠባብ ጎሰኛው አምባገነን የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት በገንዘብ ሊገዛው የማይችል አስተዋፆ እያደረገለት ነው። በመግለጫውና ሃተታው እንደምናብራራው ተሳስቦና ተቻችሎ በአንድነት ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ሰብሳቢ የሆኑ የአንድነት ኃይሎች በሙሉ የሚጋሯቸው፤ ለጋራ ሰነድ ዝግጅት ጠቃሚ ይሆናሉ ብለን የምንገምታቸው አስኳል ጉዳዮች አሉ።

ለዚህ ይጠቅማል ብለን የምንገምተው በሸንጎ ውስጥ የተጣመሩት የፖለቲካና የማህበረሰብ ድርጅቶችና የታወቁ አገር ወዳድ ግለሰቦች ተስማምተውና ተጋርተው የሚመሩባቸውን አምስት መርሆዎች መገምገም ነው። እነዚህም፤

አንድ፤ በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ በመላው ሕዝቧ የሥልጣን ባለቤትነትና ሉዑላዊነት ጽኑ ዕምነት ማስተጋባት፤

ሁለት፤ በሕግ ፊት የሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች እኩልነትንና የሰብአዊ መብቶች መከበር ወሳኝ መሆናቸውን መቀበል፤

ሶስት፤ ፍትኅ የሰፈነበትና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ሥርዓት መመስረት አስፈላጊ መሆኑን ማመን፤

አራት፤ በድርጅቶች ውስጥና መሃከል ዴሞክራሲያዊነትን መመሪያ አድርጎ በስራ ላይ ማዋልና፤

አምስት፤ በስልጣን ላይ የሚገኘው የህወሓት/ኢህአደግ አገዛዝ ለዴሞክራሲ መስፈን፤ ለእርጋታ፤ ለሰላም፤ ለዘላቂና ፍትሃዊ እድገት እንቅፋት የሆነ ስርዓት በመሆኑ መወገድ እንዳለበት መቀበልና ያልተቆጠበ ጥረትና አስተዋፆ ማድረግ ናቸው።

ጉባዔው፤ እነዚህን ግቦች ስኬታማ ለማድረግ የመጀመሪያዎቹ ጊዜ የማይሰጡ ትኩረቶች ኢትዮጵያን ከመፈራረስ (አገር ለማዳን) እና ሕዝቧን ከእርስ በእርስ እልቂት ለማዳን በአንድነት መነሳት ነው የሚል ነው። ኢትዮጵያ ከጠፋች ሌላው ትግል ትርጉም የለውም ከሚል ስምምነት ላይ ደርሰናል።

ጉባዔው እነዚህ መርሆዎች አሁንም አግባብ እንዳላቸው ተቀብሎ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ በጥናቶች የተደገፈ ጥልቀትና ስፋት ያለው ሰፊ ውይይት አድርጓል። ከእነዚህ መካከል ትኩረት የሰጣቸው አስኳል ጉዳዮች የግንቦቱ የይስሙላ “ምርጫ” ትርጉመቢስነት፤ የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚው ጎራ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፤ አገር ቤትና ውጭ ከሚገኙ የአንድነት ዘርፍ የተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግ ሰፊና ጠንካራ የሆነ ግንባር መስርቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አግባብ ያለው አማራጭና የጋራ ሰነድ በማዘጋጀት፤ ወጣቶችና ሴቶች በሰፊው የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት፤ በብሄር/ብሄረሰብና በየክልሉ ስም ተደራጅተውና ታጥቀው ትግል እናካሂዳለን የሚሉት ቡድኖች ከኢትዮጵያ አንድነት አንፃር እንዴት እንደሚታዩ በመዳሰስ፤ በአፍሪካ ቀንድና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱት ሁኔታዎች፤ ለምሳሌ፤ የሃገራት መፈራረስ፤ የሽብርተኛነት መስፋፋትና የኃያላን መንግሥታት ሚና በኢትዮጵያ ላይ ያለው ጫና ምን አስከትሏል፤ ያስከትላል እና የወደፊቱ የትግል ስልታችን ምን መሆን አለበት… ወዘተ በሚሉት ላይ ነው።

የይስሙላውን “ምርጫ” በተመለከተ ሸንጎ ምርጫው ከመካሄዱ ከአንድ ዓመት በፊት የምርጫው ሂደት ነጻ፤ ፍትሃዊና አግባብ ያለው እንዲሆን ከተፈለገ ዘጠኝ ነጥቦችን ያቀፈ ቅድመ ሁኔታዎችና ዝግጅቶች መሟላትና መተግበር እንደነበረባቸው ገልጾ ነበር፡፤ ሆኖም አንዳቸውም ስራ ላይ እንዳልዋሉ አስታውሶ፤ ጉባዔው ህወሓት በበላይነት የሚያሽከረክረው ኢህአዴግ የመንግሥት ለውጥ በምርጫ እንዲካሄድ የማይፈቅድና በሕገ መንግሥቱ መመሪያ መሰረት የሚደረገው የሰላማዊ ትግል ጭላንጭል ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋ ተስማምቶበታል። በሕገ መንግሥቱና በዓለም ህጎች መሰረት የመንግሥት ለውጥ በሰላም ሊደረግ አይችልም ብሎ ጭካኔውን፤ አፈናውን፤ ግድያውንና ማሳደዱን ከመቸውም በሚዘገንን ደረጃ የሚያካሂደው ህወሓት የሚያዘውና የሚቆጣጠረው ኢህአዴግ የሚያሳየው ባህርይና ድርጊት ካለፉት ስህተቶች ሊማር አለመቻሉን፤ የበላይ አለቆቹና ተተኪዎቹ ራሳቸው በፈጠሩት የጥላቻና የቂም በቀል ርእዮት ተበክለው በፍርሃት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ መሆኑን፤ ይህ ፍርሃት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የበከለው መሆኑን… ወዘተ ያሳያል።

የማህበረሰብ ሆነ የፖለቲካ፤ የኃይማኖት ሆነ የሰብአዊ መብቶች መከበር ጠበቃ የሆነ ግለሰብና ተቋም ድምፁን ሲያሰማ የሚደርስበት ተከታታይ ክስና የሃሰት መረጃ “ሽብርተኛ ነህ/ነሽ” የሚል ብቻ ነው። በጥላቻና በቂም በቀል የተበከሉት የህወሓት መስራቾችና ተተኪዎች በተደጋጋሚ ሊያስታውሱን የሚሞክሩት ሃቅ “እኛ በትጥቅ ትግል መስዋእት ከፍለን ያገኘነውን ስልጣን” ልትነጥቁን የምትችሉት እናንተም ተመሳሳይ ትግል አካሂዳችሁ ብቻ ነው የሚል እብሪተኛና ትምክህተኛ የሆነ ብሂል ነው። ይህ አብሪትና ትምክህተኛነት ሁለት የማያሻሙና መፈታት ያለባቸው ችግሮችን ያንፀባርቃሉ፤

አንድ፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመንግሥት አመራርና ስርዓት ለውጥ ወይንም ሽግግር በሰላም ሊተገበር አለማቻሉን፤ ይኼም ለዲሞክራሲ ምስረታ ማነቆ መሆኑን፤

ሁለት፤ በሃገር ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነትና በውጭ ወረራ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ በህይወቱና በኃብቱ ብዙ መስዋእት መክፈሉ፤ መራቆቱ፤ መድከሙ፤ መማረሩ፤ ክብሩን መገፈፉ፤ ሉዐላዊነቱና ትሥስሩ መውደሙ ናቸው።

ጉባዔው ይኼ ዑደት (Cycle) እና ሁከት (Cycle of Violence) ልክ እንደ ተራ ነገር የተለመደ መሆኑ ለሃገራችን ህልውና ዘላቂነትና ለስብጥር ሕዝቧ አብሮና ተቻችሎ ማደግና መኖር ፀር መሆኑንና አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ መክፈት ብልህነት መሆኑን ተስማምቶበታል። አዲስ ፖለቲካ ስንል፤ ከጥላቻና ከቂም በቀል የፖለቲካ ባህል ወደ መቻቻል፤ መወያየት፤ መከባበር፤ መደማመጥ፤ አብሮ ችግሮችን ወደ መፍታት፤ መደጋገፍ… ወዘተ ባህል እንዙር ማለታችን ነው። የህወሓት/ኢህአዴግን የጥላቻ ባህል ይዘን ዲሞክራሳዊ ስርዓት ልንመሰርት አንችልም።

ህወሓት ይኼን የተያያዘ ጊዜ ያለፈበት የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ ባህል ይዞ መቀጠሉ ለተገንጣዮችና ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ ለሚመኙ የውጭ ኃይሎችና ለሽብርተኛነት በር ከፍቷል። የይስሙላው ምርጫ ያባባሰው ይኼን የማይካድ ሁከት ነው። ይኼን በተመለከተ፤ ኢትዮጵያን አፍኖ ለሚገዛው  ቡድን አሳፋሪ ሁኖ ያገኘነው ክስተት ገዢው ፓርቲ ከ547 የፓርላማ ወንበሮች “424 አሸንፊያለሁ” ብሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማቅረቡ ብቻ ሳይሆን የቀሩትን ወንበሮች ራሱ ለፈጠራቸው፤ ታማኝና ታዛዥ ለሆኑ ተጠላፊ ፓርቲዎች መስጠቱ ነው። የዛሬ አምስት ዓመት “በ 99.6” አሸነፍኩ ያለውን የዓለም ሕዝብ ያልተቀበለውን ውጤት ከፍ አድርጎ “መቶ በመቶ አሸነፍኩ” ሲል ስርዓቱን በሕዝብ ድምፅና በሰላም ለመለወጥ አትችሉም የሚል የማያሻማ መልእክት አቅርቦልናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጥንብ ባለበት  ጂብ አይጠፋም  

ስለሆነም፤ የጉባዔው ዘገባና ድምዳሜ አንድና፤ አንድ ብቻ ነው። ይኼውም፤ ሕግ መንግሥቱ የሚፈቅደው የምርጫ ሂደትና ለሃገሪቱ ሕዝብ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው የተቋቋሙት ተቋሞች–የምርጫ ቦርድ፤ ፍርድ ቤቶች፤ የፌደራል ፖሊስ፤ መገናኛ፤ ደህንነት፤ መከላከያ…ወዘተ–ለገዢው ፓርቲ ማፈኛና መቆጣጠሪያ፤ መቆያና የኃብት ማካበቻ መሳሪያዎች ሁነዋል የሚል ነው። የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ መሳሪያ መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል። በአለፉት አምስት ምርጫዎች ህወሓት/ኢህአዴግ ከዓለም የምርጫ መስፈርቶች ጋር የተጻረረ፤ እውነተኛ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያፈራረሰ፤ መሪዎችን ያሳደደ፤ ያሰረና፤ ምርጫውን ካሸነፈ በኋላም የገደለ፤ በመግደልና በማሳደድ ላይ ያለ፤ የሕዝብ እምቢተኛነት ሲከሰት ችግሩን ሁሉ በአፈናና በመሳሪያ ኃይል እፈታለሁ የሚል አምባገነናዊ አገዛዝ ሆኗል። በአጭሩ፤ ህወሓት በበላይነት የሚያሽከረክረው አገዛዝ ሃገሪቱን ለከፋ አደጋ ያጋለጠና የእርስ በእርስ ጥላቻና እልቂት እንዲካሄድ ያመቻቸ ሆኖ አግኝተነዋል።

በጉባዔው ዘገባ፤ ዲሞክራሳዊ ለውጥ ጊዜ የማይሰጥ አስቸኳይ ጉዳይ ሆኗል። ጉባዔው ለማጠናከር የፈልገው መልእክት፤ ህወሓት የሚያካሂደው “የከፋፍለህ ግዛው”፤ የብሄር/ብሄረሰብና የኃይማኖት ጥላቻና ጎሳዊ አድልዎ ለሃገራችን አንድነትና ሉዐላዊነት” እና ለመቶ ሚሊዮን ሕዝቦቿ ሰላም፤ ደህንነት፤ አብሮና ተሳስሮ መኖር ዋናው አደጋ ፈጣሪ ሆኗል። ለማጠናከር፤ ጉባዔው ከዚህ ዘገባና ድምዳሜ ለመድረስ ያመዛዘናቸውን አደገኛ ሁኔታዎች በአጭሩ እናቅርባለን።

ሌላውን ሁሉ መረጃ ወደ ጎን ትተን፤ ባውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት “የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ዓመታዊ” ሪፖርትን፤ ባለፈው ዓመት መጨረሻ (2014) የወጣውን  የ አሜሪካ ኢንተለጀንሰ መስሪያ ቤት ያዘጋጀውን ዘገባ( “U.S. National Intelligence Council Documentary on the TPLF”) እና መንግስታዊ ያልሁነው ፈንድ ፎር ፒሰ (The Fund for Peace, )  በውድቀት አፋፍ ላይ የሚገኙ መንግስታት (“Failed and Failing States”  ) በሚል ያቀርቧቸውን አስጊ ሁኔታዎች እንጠቅሳለን።

አንድ፤ የገንዘብና የተፈጥሮ ኃብት ዘረፋህወሓት እንደ ፓርቲ የሚቆጣጠራቸውና የፈጠራቸው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ተቋሞች–ለምሳሌ ኤፈርት የተባለው ሞኖፖሊ፤ በበላይነት የሚቆጣጠረው መንግሥት፤ ጥቂት ምርጥ ግለሰቦች፤ የስለላ፤ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ የበላዮች አብዛኛውን ዘመናዊ ኢኮኖሚ ተቆጣጥረውታል። የጠባብ ጎሳ የበላይነትን ከኢኮኖሚና የተፈጥሮ ኃብት ባለቤትነትና የበላይነት ጋር አጣምረውታል። ገቢና ኃብት የሚገኝባቸውን ምንጮች ሙሉ በሙሉ የራሳቸው የግልና የቡድን አድርገውታል። ህወሓት የነጋዴዎች፤ የኪራይ ሰብሳቢዎች፤ የአትራፊዎችና የዘራፊዎች ስብስብ ቡድን ሆኗል። ሌላውን “አጥፊ ተቃዋሚ” እያለ በመወንጀል እራሱ ወንጀለኛ ከሆነ አመታት አልፈውታል።

ይኼን ነው፤ ዶኪውሜንተሪው “Ethnocracy combined with Plutocracy” ኢትዮጵያ በዓለም እርዳታ ከሚያገኙ ሃገሮች መካከል አራተኛውን ደረጃ፤ በአፍሪካ አንደኛውን ደረጃ ይዛ ሕዝቧን ለመመገብ አልቻለችም። ከሚለገሰው ግዙፍ እርዳታ ምን ያህሉ ድህነትን ለማጥፋት እንደሚውል አናውቅም። የምናውቀው የህወሓት የበላዮችና ጥቂት አጋሮቻቸው ታይቶ የማይታወቅ ድርጅታዊ ምዝበራ እያካሄዱ፤ ኃብት እንዳካበቱና በልጆቻቸውና በሌላ ዘዴ ብዙ ቢሊየን ዶላር ከሃገር እንዳሸሹ፤ የግል ኩባንያዎች እንዳቋቋሙ ተደርሶበታል። Global Financial Integrity, 2000-2009 ባወጣው ዘገባ $11.7 ቢሊዮን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰርቆ ወደ ውጭ ተልኳል፤ በዚህ ዓመት መጀመሪያ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት እምቤኪ የመራው ግብረ ኃይል ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ከኢትዮጵያ ተሰርቆ የሸሸው $10 ቢሊየን ነው። ህወሓት የማይክደ $21 ቢሊየን ዶላር ከሃገር ተሰርቆ ሸሽቷል። ስንት የስራ እድል ይፈጥር ነበር? ለዚህ ተጠያቂው ማን እንደሆነ አከራካሪ አይሆንም።

ሁለት፤ የዘር ፍጅት፤ ማጽዳት ዘመቻ (Genocide and ethnic cleansing) የህወሓት  መሪዎችና ተተኪዎች ሌሎች ጠባብ ጎሰኞችን አሳምነው በአማራው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የተቀነባበረና ተከታታይ የዘር ፍጅት ዘመቻ አካሂደዋል፤ አሁንም እያካሄዱ ነው። የብሄር ጥላቻን እንደ ትግል ስልት ተጠቅመው ሌላውን በጥላቻ በክለውታል። ወጣቱ ትውልድ እንዲያምን የተገደደው ጥላቻን፤  የራስን ጥቅም የበላይነት…ወዘተ እንጅ አገራዊና ብሄራዊ ፍቅርንና ጥቅምን አይደለም።

ህወሓት ከጅምሩ፤ የትግራይን ሕዝብ “ያዳከመው፤ ያደኸየው፤ ያገለለውና ያጠቃው የአማራው ብሄርረሰብ ነው” በሚል ብሂል፤ የጥላቻ ጦርነት ሲያካሂድ ቆይቷል። ዘገባዎችና መረጃዎች የሚያሳዩት በጅጅጋ፤ በደቡብ ሸዋ፤ በጉራ ፈርዳ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በጋምቤላ፤ በወልቃይት ጠገዴና ሌሎች ቦታዎች የሚዘገንንና በፍርድ የሚያስጠይቅ ፍጅት አካሂደዋል። የራሱ የገዢው ፓርቲ የሕዝብ ቆጠራ ያሳየው ቢያንስ ሁለት ሚሊየን አምስት መቶ ሽህ የአማራ ሕዝብ በጥቂት አመታት ውስጥ የት እንደደረሰ አይታወቅም፤ ሌሎች (ለምሳሌ ኢኮንሚስቱ ዶር ብርሃኑ አበጋዝ በምርምር የተደገፈ ማስረጃ) ይኼ ቁጥር ከአምስት ሚሊየን በላይ ሕዝብ መሆኑን ያሳያል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ይህ ሕዝብ የት ደረሰ፤ ተሰደደ፤ ተገደለ፤ ማንነቱን እንዲለውጥ ሆነ? ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂው ማነው? በኛ አመለካከት ህወሓትና አጋሮቹ መሆናቸው አያከራክርም።

በተጨማሪ፤ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ችግሮችን በሰላምና በመደራደር በመፍታት ፋንታ በአኟክና (2003)፤ በኦጋዴን ኢትዮጵያዊ ሶማሌ ሕዝብ ላይ (በተደጋጋሚ)፤ የሚዘገንን፤ በቪዲዮ የተቀረጸ በፌደራል ፖሊስ የተመራ በዘር ፍጆት የሚመደብ ወንጀሎች ፈጽሟል። በተጨማሪ፤ በተራው የጋምቤላ፤ የኦሞ ሸለቆና ሌሎች ነዋሪዎች ላይ ሂውማን ራይትሰ ዋች፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ኢንተርናሽናል ሪቨርስ፣ ኦክላንድ ኢንስቲትዩት ፣ ጋርዲያን ጋዜጣና ሌሎቹም (Human Rights Watch, Genocide Watch, Amnesty International, International Rivers, Oakland Institute, the Guardian and others) የመዘገቡት የመሬት ነጠቃና ከዚህ ጋር የተያያዘው ነዋሪዎችን ከቀያቸው የማባረር ወንጀል በተደጋጋሚ ተፈጽሟል። ገዢው ፓርቲ እነዚህን የመሳሰሉ ወንጀሎች ሲፈፅም “በልማትና በፀጥታ አስፈላጊነት” ስም ነው። በተጨማሪ፤ እየለየ በድብቅ የሚገድላቸው፤ የሚያስራቸው፤ የሚደበድባቸው፤ ንበረታቸውን የሚገፋቸው፤ እንዲሰደዱ የሚያስገድዳቸው የሃገር ፍቅር ያላቸውን፤ ደፋሮቹን፤ መሪ ለመሆን ብቃት ያላቸውን፤ ለፍትህና ለዲሞክራሲ የቆሙትን ነው። ምርጫውን “አሸነፍኩ” ካለ በኋላ የገደላቸው ደፋርና አገር ወዳድ መሪዎች ምን ወንጀል ሰሩ? ማን ገደላቸው፤ በማን ትእዛዝ? የገደሉት ለምን አልተያዙም? የተገደሉበት ዋና ምክንያት ለህወሓት ተወዳዳሪ የሆነ አገር ወዳድና በፍትህ የሚያምን ትውልድ እንዳይፈጠር መቀጣጫ ለማድረግ ነው።

ሶስት፤ የሰብዓዊ መብቶች፤ የኃይማኖትና የፕሬስ ነጻነት አፈና— ከላይ እንዳቀረብነው፤ ያለፈው ምርጫ የፖለቲካ ምህዳር መዘጋት ነፀብራቅ ነው። አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዋች፣ ፍሪደም ሀውስ፤ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ሲፒጄ ያሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፡ የአውሮፓ ማህበርና ሌሎችም የሚጋሩት የኢትዮጵያ አገዛዝ ለማህበራዊ (ለሰብአዊ) መብቶች ፀር መሆኑንና ይኼ ሁኔታ ከቀጠለ ለሃገሪቱ መፈራረስና ለእርስ በእርስ ጦርነት መዘዝ መሆኑን ነው። ሲፒጄ (CPJ) ባደረገው ጥናት መሰረት “ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማፈንና ከሃገር እንዲለቁ በማድረግ፤ ከዓለም አራተኛ፤ ከአፍሪካ ሁለተኛ” መሆኗን በተደጋጋሚ አስምሮበታል። ሽብርተኛ ተብለው ከታሰሩት መካከል እስክንድር ደስታ፤ ተመስገን ደሳለኝ፤ ውብሸት ታየ፤ አንዱ ዓለም አራጌ፤ ሃብታሙ አያሌው፤ አቡበከር አህመድ፤ አብርሃ ደስታ፤ የሸዋስ አሰፋ፤ ዳንኤል ሽበሽና ሌሎች ብዙ ሽዎች የፖለቲካ እስረኞች ይገኙበታል። ቢያንስ ሰባ ዘጠኝ ጋዜጠኞች ከሃገር ተሰደዋል፤ ይኼ “በዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ” የያዘ ሃቅ ነው። ከላይ የጠቀስነው ዶኪሜንተሪ እንዳሳየው  የኢትዮጵያ መንግስት ከጋዳፊና ባለማችን ከታዩት ሌሎችም ጨካኝ አምባገነኖች የማይለይ መሆኑን ነው

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላማዊ ትግል በካዮች እና መከላከያ ምክሮች! (ግርማ ሞገስ)

ህወሓት ሁሉንም ተቋሞች ለመቆጣጠር በተከተለው ዘዴ መሰረት፤ ስልጣን በያዘ ማግስት የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኃይማኖትን አመራር በቁጥጥሩ ስር እንዲውል አድርጓል፤ አግባብ ያላቸውን ፓትሪያርክ አስወግዶ ለህወሓት ታዛዥና ታማኝ የሆኑ የትግራይ ተወላጅ ሹሟል። እንደ ዋልድባ ያሉ የማይተኩ ገዳሞችን ህልውና ለማሳጣት ሞክሯል፤ የዋልድባ አባቶችና እናቶች የሚተዳደሩበትን መሬት ለስኳር አገዳ ማምረቻ እንዲውል አድርጓል። ኃይማኖትን የፖለቲካ የበላይነት መሳሪያ ማድረግ ለሃገሪቱ አደጋ ፈጥሯል፤ ለውጭ ኃይሎች መግቢያ ቀዳዳ ሆኗል። በተመሳሳይ፤ የእስልምና ኃይማኖት አመራር ህወሓት በሚፈልገው መንገድ እንዲቋቋምና እንዲመራ አድርጓል፤ መሪዎችንና አባላትን አስሯል።

ገዢው ፓርቲ አስደናቂ እድገት እያሳየሁ ነው በሚላት የምግብ ጥገኛ ሃገር፤ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል ለመፍጠር አልተቻለም። ዛሬ ሃገሪቱ ከምትታወቅባቸው አንዱ ወጣቱ ትውልድ በተከታታይ መሰደዱ ነው። በየዓመቱ፤ ብዙ ሽህ ወጣቶች በጅቡቲ፤ በሶማሊያ፤ በሰሜንና ደቡብ ሱዳን፤ በኬንያ ወይንም የመውጫ ፈቃድ አግኝተው በቦሌ ወደ ውጭ ይሰደዳሉ። ከወጡ በኋላ የህወሓት/ኢህአዴግ  አገዛዝ መብታቸውን አያስከብርም። የኢኮኖሚው አመራር በሕዝብ የበላይነት የሚመራ ካልሆነ፤ ሕዝብን የእድገት ማእከል ካላደረገና የእድገቱ ውጤት ለሕዝብ አገልግሎት ካልዋለ የኑሮው ቀውስና ስደቱ አያቆምም።

አራት፤ ከመንግሥት ባለቤትነት የመነጨ የመሬት ነጠቃ—አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተዳደረው በእርሻና ተመሳሳይ ስራ ነው። በገጠር ሆነ በከተማ የመሬት ባለቤትነት የዜግነት መታወቂያና የኑሮ መመኪያ ነው። ህወሓት በበላይነት የሚመራው አገዛዝ የተፈጥሮ ኃብትን በሙሉ “የመንግሥት ነው” በሚል ዘዴ መሬትን ለንግድና ለግል ጥቅም አውሎታል። የመሬት ቅርምት (Land Grab) ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያውያንን አንጡራ የተፈጥሮ ኃብት ለውጭ አገር ኢንቬስተሮች ቸርችሮታል። ሳውዲ ስታር፤ የህንዱ ካሩቱሪ፤ ሩች ሶያ፤ የህንድ ድንች አምራቾች ተቋምና ሌሎች ጋምቤላን ሙሉ በሙሉ ተቀራምተውታል ለማለት ይቻላል። ብዙ ሚሊየን ሄክታር ለም መሬትና ወንዝ ለውጭና በሃገር ቤት ታማኝ ለሆኑ አትራፊዎች ተቸርችሯል። በጋምቤላ ብቻ የታወቀው ለውጭ ኢንቬስትሮች የተሰጠውና የግል የሆነው መሬት በዝቅተኛ 650,000 ሄካታር በከፍተኛ 2,000,000 ሄክታር ይደርሳል። የከተማና የገጠር መሬት ለግል ትርፍና ለሙስና ቁልፍ ሆኗል። በከተማ ቦታ ምደባ፤ ስደተኛውም ተጠቃሚ ሁኖ የከተማ መሬትን ዋጋ የማይቀመስ አድርጎታል። ይኼ በፖለቲካ የበላይነት የሚወሰን የመሬት አስተዳደር ሁኔታ እስካልተለወጠ ድረስ ፍትሃዊ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ሊኖር አይችልም።

አምስት፤ የስለላ፤ የደህንነት፤ የመከላከያ፤ የፍርድና የፌደራል ፖሊስ ፍፁም የበላይነት —እነዚህና እንደ ጉምሩክ፤ መገናኛ ቁልፍ ሚና ያላቸው ተቋሞች የሚያገለግሉት ህወሓትን ነው። የፓርቲው ተቀጥላዎችና አገልጋዮች ከሆኑ ቆይተዋል። በ2009 የተገኘ መረጃ ያሳየው ከጠቅላላው የኢትዮጵያ የመከላከያ እዝ አስራ ሰባቱ ጀኔራሎችና አርባዎቹ ኮሎኔሎች የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ፤ አንድ የአገው ተወላጅና አንድ የአማራ ተወላጅ ጀኔራሎች ነበሩ። አንድም የኦሮሞ ጀኔራል የለም፤ በኮሎኔል ደረጃ ሌሎች ብሄረሰቦች አልተወከሉም። በፖለቲካው፤ በኢኮኖሚው፤ በባንኩና ፋይናንሱ፤ በመገናኛው፤ በአስተዳደሩ፤ በደህንነቱ፤ በመከላከያው፤ በፌደራል ፖሊሱ፤ በጉሙሩኩ ዘርፎች የፖሊሲና የውሳኔ ኃላፊዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው። እንደዚህ አይን ያወጣ አድልዎ የትም ሃገር አይታይም።

ቢያንስ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነው የደህንነቱን፤ የፌደራል፤ የልዩ ፖሊሱንና የመከላከያውን እዝ በበላይነት የሚመሩት ለህወሓት ታማኝ የሆኑ የትግራይ ብሄረሰብ አባላት ናቸው። ይኼ አይን ያወጣ  አድልኦ መሆኑ አያከራክርም።  ይኼ ለበላይነት የተዋቀረና እጅግ ጠባብ የሆነ  አመራር ለሃገሪቱ ደህንነትና ዘላቂነት፤ ለሕዝቧ ሉዐላዊነትና አንድነት፤ ለሕግ የበላይነትና ለዴሞክራሲ አደገኛ መሰናክል ፈጥሯል።  ህወሓት ይኼን የበላይነት ያጠናከረው ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተቋሞችን በማውደም፤ የኢትዮጵያን ታሪክ በማጥፋት፤ የትምህርት ይዘቱን ክልላዊና ጎሳዊ በማድረግ፤ አገር ወዳድ የሆኑ መምህራንን በማባረር፤ የጥላቻ ባህል ጥልቀትና ስፋት ይዞ አዲሱ ትውልድ እርስ በእርሱ እንዳይተማመንና ብሎም እንዲጋጭ በማድረግ ነው። ዛሬ ልክ ዩጎስላቪያ እንደሆነው፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያያይዙ ባህሎችና ልምዶች በህወሓት ወድመዋል ለማለት እንችላለን። ይኼ ሁኔታ ለእርስ በእርስ ግጭት፤ ለዘር ፍጅት፤ ለተገንጣይ ኃይሎችና ለውጭ ጠላቶች የጥቃት መግቢያ ሆኗል።

ስድስት፤ የውጭ መንግሥታት፤ በተለይ የአሜሪካ መንግሥት ሚና አሳሳቢነት–የምእራብ ሃገሮች፤ በተለይ የአሜሪካ መንግሥት ከሰብዓዊ መብቶች መከበር ይልቅ ለመረጋጋትና ለፀረ-ሽብርተኛነት ዘመቻ ቅድሚያ እየሰጠ አምባገነኑን የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ መደገፉ ለራሱ ጉዳት እንዳመጣ እናምናለን። የኢትዮጵያና የአሜሪካ ከመቶ አስር ዓመታት በላይ የቆየ ግንኙነት አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ሊቀጥል የሚችለው አፋኙን አገዛዝ በማውገዝና የሚሰጠው የገንዘብና ሌላ እርዳታ እንዲቆም በማድረግ እንጅ ድጋፉን በመቀጠል አይደለም። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ቀውስ ውስጥ መግባት፤ መባባስ፤ የሰብአዊ መብቶች መረገጥ፤ የኃይማኖት ነጻነት መታፈን፤ በፀረ-ሽብርተኛነት ሽፋን የገዢው ፓርቲ ሕዝብ አሸባሪ መሆን፤ የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ መባከን፤ ከመቶ በላይ የሚገመቱ በጎሳ የተደራጁና የታጠቁ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሃገሪቱ ሁኔታ ተባብሶ የመገንጠል ዓላማቸውን ስኬታማ ለማድረግ መዘጋጀት፤ ለልማት መዋል የሚችል ግዙፍ የሆነ ኃብት ከሃገር እየሸሸ መውጣቱ…ወዘተ ለአሜሪካም ዘላቂ “ጥቅም” ጉዳት እንደሚያመጣ እንገምታለን። ለዚህ አግባብ ያለው፤ የማያሻማ መልእክት ለኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ መስጠት ነው።

ጉባዔው በቅርቡ ሸንጎ ለፕሬዝደንት ኦባማ የጻፈውን ግልፅ ደብዳቤ መሰረት አድርጎ፤ የአሜሪካ መንግሥት ለሚከተሉት መተክሎች (Principles) እና እሴቶች ትኩረት እንዲሰጥ የዲፕሎማቲክ ዘመቻ ማካሄድ ይኖርበታል በሚል ተስማምቷል።

አንድ፤ የፖለቲካ እስረኞች፤ ጋዜጠኞች፤ ብሎገሮችና የኃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤ ጥቂቶቹን ለይስሙላ ፈትቶ ሌሎችን እያሰቃየ ነው፤

ሁለት፤ የመገናኛ ብዙሃን፤ የኃይማኖት፤ የመናገር፤ የመሰብሰብ፤ የመንቀሳቀስና የመደራጀት ነጻነት እንዲከበሩ፤ የማህበረሰብ ድርጅቶች እገባ እንዲቆም፤ የፀረ-ሽብርተኛው ሕግ እንዲነሳ፤

ሶስት፤ የፍርድ ቤት፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የመከላከያና የምርጫ ቦርድ ተቋሞች ከገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ ሁነው መላውን ሕብረተሰብ እንዲያገለግሉ፤

አራት፤ ነዋሪዎችን ከመሬታቸው እንዲገለሉ የሚደረገው ዘመቻ እንዲቆም፤

አምስት፤ በዘር ፍጅት የሚታወቁ ባለስልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡና የዘር ፍጅት ዘመቻው በአስቸኳይ እንዲቆም።

ከላይ የቀረቡት መተክሎች አሜሪካ የምታምንባቸው እሴቶች እንደመሆናቸው መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደተግባር ካልተተረጎሙ የአሜሪካ መንግሥት ለህወሓት/ኢህአዴግ የሚሰጠውን እርዳታ በጥንቃቄ መመርመር ይገባዋል። ጉባዔው  ይኼን በሚመለከት የሸንጎ አመራር ለፕሬዝደንት ኦባማ ልዩ ደብዳቤ እንዲፅፍ አሳስቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ዋርካ ምድር ነካ ንገሩት ለዋንዛ ፍቅር ለባለጌ ይመሥለዋል ዋዛ " መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

የትግል ስልት

ከላይ የቀረበውን ኃሳብና አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ጉባዔው ስለ ትግል ስልት ሰፊ ውይይት አድርጎ በሚከተለው ተስማምቷል። ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካውንና የማህበረሰቡን ነጻነት ተስፋ፤ ምኞትና የመንቀሳቀስ ምህዳር ሙሉ በሙሉ በመዝጋቱ በሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መብት መሰረት በሰላም ለውጥ ለማምጣት የማይቻል መሆኑን አምኗል። ጉባዔው፤ ተቃዋሚዎች፤ የተለያዩ የትግል ስልቶች ቢከተሉም፤ ኢትዮጵያን እንታደግ፤ ለአገራዊና ብሄራዊ ስሜት እንታገል፤ መጠላለፍ እናቁም፤ እንደጋገፍና እንተባበር ከሚሉ አገር ወዳድ ከሆኑ የአንድነት ኃይሎች ጋር አብሮ ለመስራት ያደረገውን ጥሪ አሁንም ያድሳል።

ሸንጎ በመግቢያው የቀረቡትን መርሆዎች ስኬታማ ለማደረግ ከዚህ በፊት በተከታታይና በቆራጥነት ያልተሞከሩ የትግል መንገዶች ሁሉ መስተናገድ አለባቸው የሚል እምነት አለው። በተጨማሪ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሲያስተጋባ ከቆየው የብሄር/ብሄረሰብና የኃይማኖት ከፋፋይነት፤ የጥላቻና የቂም በቀል የፖለቲካ ባህል ወደ ዴሞክራሲያዊ ባህል መሸጋገር ወሳኝ መሆኑን እናምናለን።

ምንም እንኳን የሃገሪቱ የተፈጥሮ ኃብትና እድገት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥቅም ይዋል፤ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ፣ የሀገር አንድነት ይጠበቅ…ወዘተ የሚል እምነት ይዘው ገዢውን ፓርቲ  ሲታገሉ ብዙ ታጋዮች ቢገደሉም፤ ቢታሰሩም፤ ቢደበደቡም፤ ከሃገር ቢሰደዱም፤ አሁንም በሃገር ቤት ሁነው የሚታገሉ አገር ወዳድ፤ ደፋርና ለውጥ ፈላጊዎች ብዙዎች ናቸው። እነዚህን ደፋር፤ ቆራጥና አገር ወዳድ  ወገኖቻችንን በማንኛውም መንገድ መደገፍ አቅማቸውንም ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት ማገዝ  አስፈላጊ ነው።

በመርሆዎቻችን መሰረት ኢትዮጵያውያንን ያማከለና ያሳተፈ  የተጠናከረ ሰላማዊ ትግል እንዲካሄድና አፋኙ አገዛዝ በዴሞክራሲያዊ  አስተዳደር እንዲተካ ያልተቆጠበ ጥረት እናደርጋለን።  በሰላማዊ ትግል እናምናለን የሚሉ የፖለቲካ፤ የማህበረሰብ፤ የኃይማኖት፤ የሞያና ሌሎች ድርጅቶች፤ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች የሚያካሂዱት ትግል ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የዓላማ አንድነት ተከትለው (ተከትለን) በትግል ስልት የተለያዩትንም ሲያካትቱ (ስናካትት) ነው። ጉባዔው የተለያዩ የትግል ስልቶች መኖራቸውን ተቀብሎ የትግሉን ዘላቂነትና ውጤታማነት የሚወስነው ሕዝብን ማእከል፤ አጋርና አሳታፊ ማድረግ ከቻለ መሆኑን አስምሮበታል። ሕዝብን ያሳተፈ፤ ሕዝብ በባለቤትነት የያዘው ትግል በምንም ሊጠቃ አይችልም። ዴሞክራሲያዊ  አስተዳደር አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው የሕዝብን አመኔታ ሲያገኝ ብቻ ነው የሚለውን ግብ ጉባዔው ተቀብሎታል። ትግሉ በከተማና በገጠር የተያያዘና የተቀነባበረ እንዲሆን ድርሻችን ከመወጣት ወደ ኋላ አንልም።

ለሰላማዊ ትግሉ ውጤታማነት  የሚጠቅመው የተሳሰረና የተቀነባበረ አመራር ያለው አገር አቀፍ እምቢተኛነት ነው የሚል እምነት አለን።  ለምሳሌ፤ ከተሜው፤ ገጠሬው፤ ወጣቱ፤ አዛውንቱ፤ ድሃው፤ ባለ ኃብቱ የተባበረበት የየካቲትን ወይንም የግንቦት ዘጠና ሰባትን የሚመስል የሕዝብ እምቢተኛነት ትግል፤ አንዱ ወገን ሲጠቃ ሌላው ድምፅ የማሰማት ትግል፤ የስራ ማቆም አድማ፤ ሰላማዊ ሰልፍ፤ የህወሓት/ኢህአዴግ የግል የንግድ ተቋሞች እቀባ፤ በሃገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች የዲፕሎማሲ ትብብር ገዢውን ፓርቲ የማጋለጥ ዘመቻ፤ የተጠናከረ የዘመናዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቅሞ ህወሓት/ኢህአዴግ ወጣቱን ትውልድ የሃገሩን ታሪክ፤ የጀግኖቿን ጀብዱ ስራ፤ የሕዝቡን ተቻችሎ መኖር ወዘተ የሃሰትና የሰው ሰራሽ ታሪክ መሰሪነት አውቆ ለሃገሩና ለወገኑ ተባብሮ የሚነሳበት ዘመቻ፤ በውጭ የሚገኘውን የህወሓት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ የማጋለጥና ሰላዮችን ለፍርድ የማቅረብ ዘመቻ፤ ከሃገር ተሰርቆ የሸሸውን ኃብት የማጋለጥና የማስመለስ ዘመቻ፤ በጥናትና ምርምር የተመሰረተ የእርቅና የሠላም ድርድር ዘመቻ፤ የአንድነት ኃይሎች መተባበርና ውጤት የሚያስገኝ ትግል ዘመቻ ወዘተ። እነዚህና ሌሎች በተከታታይነት ያልተሞከሩ የትግል ዘርፎች ናቸው። የህወሓት/ኢህአዴግን ፈቃደኛነት አይጠይቁም። ከላይ እንዳሳየነው፤ እብሪተኛው ገዢ ፓርቲ ለእርቅና ለሰላም የሚደረግ ጥሪን እንደማያስተናግድ እናምናለን። ሆኖም፤ ጥረቱ በጥላቻ፤ በቂም በቀልና በራስ ወዳድነት ለተበከለው የአዲስ ትውልድ ክፍል ትምህርታዊ ግብዓቶችን ያበረክታል፤ የዓለምን ሕብረተሰብ ልቦና ያንቀሳቅሳል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥት ለውጥ በመሳሪያ ብቻ እንጅ በመወያየትና በመደራደር አይታሰብምና ተቃዋሚዎች የሚፈልጉት ዲሞክራሲን ሳይሆን ስልጣንን ነው የሚለውን ከእውነቱ የራቀ  የህወሓት/ኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ የማይቀበሉ የአንድነት ኃይሎች እንዳሉ ያሳያል። እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ቆራጥነትና ተባባሪነት ያስፈልጋል፤ በፅሁፍ መቅረባቸው ብቻ በቂ አይደለም።

 

በትጥቅ መንገድ እንታገላለን ከሚሉት ውስጥ ከዓላማችን ጋር የሚመሳሰል ዓላማ ካላቸው ጋር መተባበር እንዳለብን ጉባዔው ተወያይቶ ተስማምቷል። ሆኖም፤ ሁሉም በትጥቅ ትግል ህወሓት/ኢህአዴግን የሚፈታተኑት ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ዘላቂነትና ጥቅም፤ ለመላው ሕዝቧ ሉዐላዊነት ትሥስርና እውነተኛ እኩልነት፤ ለፍትህና ለሕግ የበላይነትና ሁሉን የማህበረሰብ ክፍሎች ለሚወክል ዲሞክራሳዊ ስርዓት ይታገላሉ ማለት አይቻልም። በዚህ አኳያ ልናስብበት የሚገባን  ያለፈው የፖለቲካ ሂደት አንዱ ትምህርት አንድ አምባገነን አስወግዶ ሌላ አምባገነን መተካት እንዳይከተል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያሰፈልግ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግን በመጥላት ከታጠቁ ተገንጣይ ኃይሎች የሚከሰተውን የኢትዮጵያን መፈራረስ፤ አደጋ የእርስ በእርስ ግጭትና የዘር ፍጅት ሴራዎች ሙሉ በሙሉ እንቃወማለን።

ኤርትራን በተመለከተ

ኤርትራ ከጥንቱ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኣካል የሆነች ክፍለ-ሃገር ነች። ከ1890ቹ ጀምሮ ክፍለ-ሃገሪቱ የብዙ ፖለቲካ ምስቅልቅሎችና የትጥቅ ትግሎች ሰለባ ሆና እንደቆየች ኣይካድም። በዚህ ሂደት ህዝቡ የዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮ ስለመፃኢ ዕድሉ በነፃነት ሊወስንበት የቻለበት ሁኔታ ከተውንም አላገኘም። በ1993 (እ.አ.አ) በኢሳያስ ኣፈወርቂና በመለስ ዜናዊ ኣቀነባባሪነት ኤርትራ ተገንጥላ ‘ነፃ’ ሃገር እንድትባል መደረጉ የዚሁ ሂደት ኣካል ነው። ተካሄደ የተባለው ሬፈረንደም ተቃዋሚዎችን ያላሳተፈ፤ ህዝቡንም ምርጫ የሌለው ውሳኔ እንዲቀበል ያስገደደ፤ በጠብመንጃ ግፊት የተፈፀመ በመሆኑ ተቀባየነት የለውም። ስለዚህም ሸንጎው ኤርትራን እንደ ‘ነፃ’ ሃገር ሳይቀበል የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስኪመሰረት ድረስ ትግሉን ይቀጥላል።

ብሄራዊ መግባባት እርቅና ሰላም

በህወሓት ላይ የሚደረገው ልዩ ልዩ ትግልና ጫና እንዳለ ሆኖ፤ ጉባዔው ሰፊ ምርምርና ጥናት አድርጎ፤ ከህወሓት/ኢህአዴግ የጥላቻና የጎሳ ፖለቲካ ወደ ነጻና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ወደሚያሳትፍ ብሄራዊ መግባባት እርቅና ሰላም ውይይት መሸጋገር ለዴሞክራሲ ወሳኝ መሆኑን ተቀብሏል። ምንም እንኳን እብሪተኛው ህወሓት ለዚህ ዓይነቱ ድርድር ዝግጁና ፈቃደኛ አለመሆኑን ብናውቅም፤ የእርቅና ሰላም ጽንሰ ሃሳብ በሃገር ቤትና በውጭ ከፍተኛ ውይይት እንዲካሄድበት ጉባኤው አሳስቧል። ሸንጎ ለዚህ ለተቀደሰ አማራጭ ያልተቆጠበ ድጋፍና እርዳታ ያደርጋል።

በመጨረሻ ጉባዔው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያቀርበው አደራ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ለዴሞክራሲ፤ ለፍትህ፤ ለሕግ የበላይነት፤ ለመገናኛ ብዙሃን ነጻነት…ወዘተ ስኬታማነት እውን የሚሆነው በጋራ ዓላማ ላይ የተመሰረተ፤ የተቀነባበረ ሕዝባዊ ትግል ሲካሄድ ብቻ እንደሆነ ነው። ህወሓት ሊያፈራርሳቸው ቢሞክርም፤ አገር ቤት የሚንቀሳቀሱ የአንድነት ዘርፍና አካል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወሳኝ የሆነ ሚና ለመጫወት ስለሚችሉ ኢትዮጵያን ሆሉ የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፋችሁን ለግሷቸው፤ እኛም የተቻለንን እናደርጋለን እንላለን።  በተመሳሳይ፤ ሸንጎ በሃገር ቤትና በውጭ ከሚታገሉ የአንድነት ስብስቦችና ግለሰቦች ጋር ተባብሮ ለመስራትና ለመታገል ዝግጁ መሆኑን በድጋሜ ቃል ይገባል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

 

 

2 Comments

  1. የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ሶስተኛ ጉባዔ ተከናወነ

    Reoported by Shengo ከጉንጭ አልፋ ፍሬከርስኪ አውርቶ አደሮች መንደር

  2. ጉባዔ ጉባዔ ጉባዔ 25 years of ጉባዔ brought nothing to our people. Par time politics. Why don’t you try some thing different? Why don’t you stop this junk politics and join the recently launched fight for freedom?

    Let’s see … we had COEDF in 1991 but gone for good. We had another one known as the PARIS CONFERENCE . Gone and now so called SHENGO. Another do nothing organization. ጉባዔ ጉባዔ ጉባዔ probably planning another 25 years of ጉባዔ. That is it. Welcome to the club of ጉንጭ አልፋ ፍሬከርስኪ አውርቶ አደሮች. If your life depends on it , it is a free country.

Comments are closed.

Share