አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ረቡዕ፤ ሚያዝያ ፯ ቀን ፳፻፯ ዓመተ ምህረት ( 04/15/2015 )
ከ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረቱ የየካቲት ሕዝባዊ መነሳሳት ጀምሮ፤ ለመብት፣ ለነፃነትና በሰላም ሠርቶ ለመኖር ያለው ትግል፤ ሳያርፍ በተከታታይ አሁንም እየተካሄደ ነው። በነዚህ ባለፉት ፵ ዓመታት፤ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፤ በትግሉ ከሕዝብ ጎን ተሰልፈው ሕይወታቸውን ሠጥተዋል። ቆራጥ የሕዝብ ጠበቃዎች ወጥተዋል፤ ሕይወታቸውን ላመኑበት ዓላማ በቆራጥነት በመሥጠት በጀግንነት ተቆጥረዋል። ትውልድ አልፎ ትውልድ ተተክቷል። በግለሰብ ደረጃ፤ አጥንት የሚሰብሩ፣ ደም የሚነውጡ፣ ልብ የሚነኩ፣ አንጀት የሚያንሰፈስፉ፣ ጀግንነት የተሞላባቸው ተግባራት ተከናውነዋል። ድርጅቶች ተነስተዋል፣ ወድቀዋል። በድርጅቶች ደረጃ፤ ሕዝባዊ ጉዳዮችን መልክ ባለው መንገድ አመቻችተው ባደባባይ አውጥተዋቸዋል። አባሎቻቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለውበታል። መሪዎቻቸው ከፍተኛ መሯሯጥን የኑሯቸው ማዕከል አድርገው መርተውበታል። በወቅቱ በተደረጉት ክንውኖች ላይ ጽሑፍት ጎርፈውባቸዋል። ግጥሞች ተደርሰውባቸዋል። መጽሐፍት ታትመውባቸዋል።
አሁንም እንድትናንቱ ትግሉ ቀጥሏል። አሁንም የነበሩት ጥያቄዎች ባሉበት ቆመዋል። አሁንም መብት፣ የሀገር ሰውነትና በሰላም ሠርቶ መኖር ማዕከላዊ ጥያቄዎች ናቸው። ለምን ወደፊት መሄድ አልተቻለም? ለምን ትግሉ ባህልና ቋሚ ሆኖ አብሮን ይኖራል? ለዚህ መልስ መሥጠት ቀላል አይደለም። በአንድነት፤ በሀገር ደረጃ፤ እስካሁ ካደረግነው ትግል ምን ትምህርት እናገኛለን? የሚለውን በመፈተሽ፤ የመጀመሪያውን ወደ ስኬት ለመሄድ የሚደረግ እርምጃ፤ መራመድ እንችላለን። ይህ የግድ መደረግ አለበት። ባንድ ጽሑፍ፣ ባንድ ውይይት፣ ባንድ ትዕይንተ ሕዝብ፣ ባንድ ምሽት፣ ባንድ ግጥም አይከናወንም። ካለፈው ካልተማርን፤ ያለፈውን ባለፈው መንገድ መድገማችን አያጠራጥርም። ለዚህም ይኼው ፵ ዓመት ባስቆጠረውና እየቀጠለ ባለው ትግላችን፤ እያስመሰከርነው ነው። የሚቀጥለው እንዲስተካከል፤ ያለፈው መመርመር፤ በጎና በጎ ያልሆኑ ጎኖቹ ተለይተው መውጣት፤ አለባቸው። እናም ለኛ ትምህርቱ ቢያንስ አሁን መጀመር አለበት። እስኪ እኔም፤ ለዚህ ከፍተኛ ትኩረት ተሠጥቶት፤ በብዙዎች ብዙ መጻፍ ባለበት ጉዳይ ላይ፤ በኔ አመለካከት ምን ነበርና ምን ትምህርት እንወስዳለን የሚለውን ልነካካ።
የ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረቱ የየካቲት ሕዝባዊ መነሳሳት የተከሰተው፤ የፖለቲካ ድርጅቶች በመድረክ ላይ በገሃድ ባልታዩበትና በአንድነት ተሰባስቦ የመታገል ልምዱ ባልዳበረበት ወቅት ነበር። በርግጥ የተማሪ ማኅበሩ፣ የአርሶ አደሮች በየቦታቸው በተደጋጋሚ ያደረጉት እንቅስቃሴ፣ አነስተኛ የነበረው የሠራተኛው ክፍል መነሳሳት፤ ለዚህ የ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረቱ የካቲት ሕዝባዊ መነሳሳት ያለጥርጥር መሠረቱ ነበር። ትልቁ ክፍተት የነበረው፤ ሀገራዊ ራዕይ ይዞ፣ ታዋቂነትን አንግቦ፣ መዋቅር ዘርጎቶ፣ ልምድና ዝግጅትን አከማችቶ፣ በሕዝቡ ዘንድ መርኀ-ግብሩን አሰምቶ፣ በቦታው የነበረውን ሕዝባዊ መነሳሳት መሪ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖሩ ነው። እናም ትክክለኛ ሕዝባዊ ጥያቄዎች የትግሉን አየር ሞልተው በተመሙበት ወቅት፤ የሕዝቡን መነሳሳት ቀዳዳ ተጠቅመው፤ ሥልጣን ወዳድ ወጣት መኮንኖች፤ ሕዝቡን አግልለው፣ ትግሉን አኮላሽተው፣ ሀገር ወዳድ ተማሪውን ፈጅተው፣ ሀገራችንን ደም በደም ለቃልቀው፣ የደም ጥማታቸውን ካረኩ በኋላ፤ በወራዳውና ሰው በላ አረመኔ መሪያቸው፤ በመንግሥቱ ኃይለማርያም አማካኝነት፤ ለአሁኖቹ ተረኛ ተባዮች አስረከቡን። በዚህ ደርጋማ መንግሥት ዘመን ትግሉ ምን መልክ ያዘ? በዚህ ወቅት ሌሎች ምን ያደርጉ ነበር? ምን እንገነዘባለን ነው ከወቅቱ የምናገው ትምህርት።
በወቅቱ ዋነኛ ተጫዋቾች ከነበሩት የትግል ድርጅቶች መካከል፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ( ኢሕአፓ )፣ የመላ ኢትዮጵያዊያን ሶሺያሊስት ንቅናቄ ( መኢሶን )፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ( ኢዲዩ )፣ ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ ( ተሓኤ – ጀብሃ )፣ ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ( ሕግሓኤ – ሸዓቢያ )፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ( ኦነግ )፣ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ( ትሕነግ – ህወሓት – ወያኔ )፣ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ትነግ – ጠርናፊት )፤ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ( ኦብነግ )፤ ነበሩበት። የኤርትራ ታጋይ ድርጅቶችን በነበሩበትና ባሉበት እተዋቸዋለሁ። ቀሪ ነፃ አውጪ ግንባሮችን ደግሞ፤ – ኦነግ፣ ትነግ፣ ኦብነግ – ነፃ ለመውጣት ያደረጉት ትግል ነበርና፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ልተቻቸውና ትግላቸውን ልመረምር መረጃውም ሆነ የሞራል ፍቃዱ የለኝም። በርግጥ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርን ( ትሕነግ – ህወሓት – ወያኔ ) በሚመለከት፤ ብዙ የምለው አለኝ። ለምን? የሚለው ጥያቄ ከተነሳ፤ ከነፃ አውጪነቱ ወጥቶ ኢትዮጵያን በሙሉ ወሮ በአምባገነንነት እየገዛ ነውና!
በወቅቱ የነበሩት ድርጅቶች፤ ሲነሱ ሁሉም ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ መብት፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ፣ እኩልነት በማለት ነበር። የትግል ዓላማቸው፣ ግባቸውና ዘዴያቸው ምን ነበር? ለምን አልተሳካላቸውም? እኒህ ናቸው በአንድነት በሀገራዊ መልኩ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች። ጎልቶ በትግል መድረኩ ላይ ከፍተኛ ሚና በተጫወተውና በመጠኑም ቢሆን አውቀዋለሁ በምለው በኢሕአፓ ልጀምር።
ኢሕአፓ፤ በተማሪው ትግል ዋናውን ሚና ይጫወቱ የነበሩ ወጣቶች፣ በተማሪ ትግሉ መሪና አስተባባሪ የነበሩ ወጣቶች፤ በተለይም በውጭ ሀገር የነበሩ ታጋይ ተማሪዎችና በሠራተኛው ክፍልም የሠራተኛውን እንቅስቃሴ ይመሩና ያቀናጁ የነበሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ያቋቋሙት ፓርቲ ነበር። በትምህርት ዓለም ውስጥ ያጠኑትን የዓለም የፖለቲካ ሂደትና የተገነዘቡትን የፖለቲካ አሰላለፍ በመመርመር፤ በወቅቱ በነበረው የሶስተኛው ዓለም የነፃነት ንቅናቄና በሶቪየት ኅብረት የቅኝ ግዛቶች ድጋፍ በመመሰጥ፤ የሶሺያሊዝም አቀንቃኝነቱን ወስደው፤ ኮሚኒዝም ከነበርንበት አዘቅት የሚያወጣ መፍትሔ ብለን በመውሰድ፤ ትግሉን የሶሺያሊስት ንቅናቄ አድርገን ተነሳን። በወቅቱ የተነሱት ጉዳዮች፤ ማለትም የዴሞክራሲ መብቶች አለመከበር፣ የደሃ ልጅ የትምህርት ገበታ ዕድሉ መነፈጉ፣ ሕክምና ወደ ገጠር አለመዛመቱ፣ የሴቶች በእኩልነት በኅብረተሰቡ አለመገኘት፣ መሬት በጥቂት የመሬት ባለቤቶች ተይዞ ጢሰኛው ባላባቱ በፈቀደለትና በፈቀደው መንገድ የሚነዳው እስረኛ መሆኑ፣ የመሬቱ ባላባት የሆነው የገዥው መደብ አባልና በመሬቱ የሚለፋው ጢሰኛ፤ የትውልድ ሀረጋቸው አንድ አለመሆኑና ቋንቋቸው የተለያየ መሆኑ በሀገሪቱ ያስከተለው የመበላለጥ ልዩነት፣ የሃይማኖቶች በእኩልነት አለመመዘን፣ የሠራተኛው ክፍል በሕግ የሚተዳደርበት ትክክለኛ አሠራር አለመኖሩ፣ የግብር አሰባሰቡ አርሶ አደሩን መበደሉ፤ እኒህ ሁሉ ትክክለኛ ጥያቄዎች ነበሩ። እኒህን በማንሳትና ኮምኒዝምን በማወጅ መካከል የነበሩትን ደረጃዎች በሽምጥጥ በማለፍ የተደረገው ጉዞ፤ ተሰናከለ።
በአንጻሩ ደግሞ፤ ይህ በፖለቲካ ትግል ሂደቱ የተፈጠረው የኢሕአፓ ፓርቲ፤ የሚመረኮዝበት ኢትዮጵያዊ ታሪኩም ሆነ ልምዱ ስላልነበረው፤ መነሻና መድረሻ አድርጎ የወሰደው የሌሎች ሀገር ተመክሮዎችን ነበር። እናም፤ በወቅቱ በሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ ላይ የተመረኮዘ መፍትሔ ሳይሆን፤ ሌሎች ያራምዱት የነበረውን የሶሽያሊስት መርህ ተጠቅሞ፤ ከሀገራችን ጋር ባልተቀናጀ መንገድ ለመተግበር ተነሳ። የድርጅቱ ድክመት፤ ፍላጎቱና ጥረቱ ሳይሆን፤ የተጨባጭ ሁኔታውና ያደረገው ጥረት አለመጣጣም ነው። ፍጹም ኋላቀር በሆነች ሀገራችንና የላበደሩ ቁጥር ከዚህ ግባ በማይባልበት ደረጃ በነበረበት ወቅት፤ የሶሻሊዝምን ሥርዓት ለማንገሥ የተነሳው ኢሕአፓ፤ መሠረቱና ዕድገቱ በወጣት የከተማ ተማሪው ላይ ነበር። ይህ ክፍል በቆራጥነት ሕይወቱን ለትግሉ ሠጠ። ደርግ ደግሞ አረመኔነት በተሞላ አሰቃቂ መንገድ ይኼን ወጣት በላው። የዚህ ፓርቲያችን ተመክሮ ባጭሩ እንዲህ ነበር።
በወቅቱ በቦታው ሊያሳድገው የሚችለውን ኢትዮጵያዊ ሂደት ሳይከተል፤ በፍላጎቱ ላይ ብቻ ተመስርቶ ያደረገው ግስጋሴ፤ ውስን ሆኖ ቀረ። የድርጅት መሪዎች ዋና ተግባር፤ ወቅታዊ ለሆነው ጉዳይ ወቅታዊ የሆነ መልስ አዘጋጅተው፤ ተከታዮቻቸውን መምራት ነው። ለነበረው የፖለቲካ ጉዳይ፤ በኢሕአፓ አመራር የተሠጠው ትንታኔና መፍትሔ፤ ደረጃውን የጠበቀና ወቅታዊ አልነበረም። በርግጥ የደርግ በዚህ ድርጅት ላይ የተለየ ትኩረት ማድረጉና የህወሓት ሆን ብሎ ይኼን ድርጅት ለማጥፋት ያደረገው ጥረት ቀላል አልነበረም። ድርጅቱ፤ ዓላማው ላለመሳካቱ ምክንያት ፍለጋ ወደ ውጪ መመልከት የለበትም፤ ዋናው ምክንያት ከውስጥ ነበር። ወሳኝ የነበረው ውስጣዊ ማንነቱ ነበር። የመርኅ መሠረቱና የአመራሩ ችሎታ በቦታው አልተገኙም። እናም ድርጅቱ ሳይሳካለት ቀረ።
የመላ ኢትዮጵያዊያን ሶሺያሊስት ንቅናቄ ( መኢሶን ) እንደ ኢሕአፓ ከተማሪው እንቅስቃሴ የበቀለ ንቅናቄ ነበር። በዚያ ውስጥ ግን የሥልጣን ጥማቱ ያናወዛቸው ግለሰቦች ተሰግስገውበት ስለነበር፤ በአቋራጭ ሥልጣን ለማግኘት፤ ተሽቀዳድመው ቤተ መንግሥት በመግባት፤ የደርግ አገልጋይ ሆኑ። ደርግን ተጠቅመን እንነግሣለን ሲሉ፤ ደርግ እንሱን የኢሕአፓ መግደያ መሣሪያ አድርጎ፤ የተማሪውን መከፋፈያ አድርጎ፤ የደሙ መጥረጊያ ጨርቅ አድርጎ ቀደማቸውና፤ ሰለባቸው። ከመኢሶን ከዚህ የበለጠ የምንማረው ያለ አይመስለኝም።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ( ኢዴኅ – ኢዲዩ ) የፖለቲካ መርኀ ግብሩ ዴሞክራሲያዊ እያለ ቢያትትም፤ ከፖለቲካ መስመር ይልቅ፤ ፀረ-ወታደር በመሆን የድሮውን ለመመለስ በችኮላ የተቋቋመ ድርጅት ነበር። በርግጥ የድሮውን የወደዱና የወታደሩን ያለቦታው ዙፋኑ ላይ መቀመጥ ያልተቀበሉ፤ ጄኖራሎች፣ ሀገረ ገዥዎች፣ መሳፍንታትና አምባሳደሮች በችኮላ ተቀላቅለውታል። ከዚያ ያለፈ ግን መርኀ-ግብሩን ተረድተውና ለዓላማው በመቆም የተሰለፉ የነበሩ አይመስለኝም። ባጭር ጊዜ ለነበረው እድገታቸው ተመጣጣኝ አመራር ሠጪ አካልና ማዕከላዊ አሰራር ስላልነበራቸው፤ ከደርግም ሆነ ከሌሎች ታጋይ ድርጅቶች በገጠማቸው ተቃውሞ ተመናምነው ጠፉ። ከዚህ በላይ ስለ ኢዴኅ ማለት አልችልም።
የቀረው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ( ትሕነግ – ህወሓት – ወያኔ ) ነው። ከአፄ ዮሐንስና ከትግራይ መሳፍንት ጋር የተያያዘው የትግራይ ወጣቶች የነፃነት ግንባር፤ ምንም እንኳ ከተማሪ ማኅበሩ የመጡ መሪዎችና ተከታዮች ቢኖሩበትም፤ ከጠባብ የትግራይ መሳፍንት ገዥነት ጋር የተያያዘ የነፃነት ትግል ነበር። ስለዚህ ይህን ግንባር ከተማሪ ትግሉ ጋር ማዛመድ ስህተት ነው። የዚህ ነፃ አውጪ ግንባር መሠረቱ የትግራይ ሪፑብሊክን መመሥረትና የአማራ ገዥነትን ማጣፋት ነው። በምንም መንገድ ከማርክሲዝምና ከላብ አደሩ አምባገነንነት ጋር ግንኙነት የለውም። ይህ ትግራይን ነፃ አድርጎ የራሷ ሀገር የመፍጠር ጉዳይ፤ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ፣ ከሀገር አቀፉ እንቅስቃሴ የተለየና በተቃዋሚነት የቆመ ነበር። ስለዚህም፤ ህወሓት በጠላትነት የፈረጃቸው፤ ደርግን ብቻ ሳይሆን፤ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ትነግ – ጠርናፊት )ን፣ ኢሕአፓን እና አማራን ነበር፤ አሁንም ነው። የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ትነግ – ጠርናፊት )ን ስላጠፋው ከቁጥር አስወጥቶታል። ኢሕአፓን በሚችለው መንገድ ወግቶታል። አማራውን አሁንም በማጥፋት ላይ ነው። የዚህ ድርጅት ተግባር ሕዝባዊም፤ ኢትዮጵያዊም አይደለም። ከዚህ የምንማረው ቢኖር፤ ይህ ድርጅት መጥፋት እንዳለበትና ይህም ባስቸኳይ መሆን እንዳለበት ነው።
ለመንደርደሪያ ያህል ይኼን ካስቀመጥኩ በኋላ፤ አጠቃላይ በሆነ መልኩ ወደፊት የሚመለከት መፍትሔ በመጠቆም፤ ጽሑፌን አስራለሁ። የ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ቱ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መሠረታዊ ጥያቄዎች፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፣ መሬት ለአራሹ ይሁን፣ የሴቶች እኩልነት ይከበር፣ ሃይማኖት የግል ስለሆነ፤ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባ፣ ሁሉንም ሃይማኖቶች እኩል ይመልከት፣ ሕክምና በገጠር ይስፋፋ፣ የድሃ ልጅ ይማር፣ ለተራበው ወገናችን እርዳታ ይደረግለት፣ የገዥዎች ያላአግባብ በሀብት ማላገጥ ይቁም፣ የኑሮ ውድነት ይስተካከል፣ ለሠራተኛው ትክክለኛ ሕግ ወጥቶ በሕገ-ደንብ ይስተዳደርና የመሳሰሉት ነበሩ። እኒህ ሀገራዊ ጥያቄዎች ነበሩ። አሁንም አሉ። አሁንም ሀገራዊ ጥያቄዎች ናቸው። በአንድነት ተነስተን በአንድነት ለማስከበር የምንቆምላቸው ነበሩ። ያኔ አልተደረገም። አሁንም እየተደረገ አይደለም።
የያዝነው ትግል ውጤቱ እንዲቃና፤ እስካሁን ከተደረገው ትግል ተምረን፤ ትግሉን በተስተካከለ መንገድ ማካሄድ አለብን። ጥያቄዎቹ ቀለም ይቀቡና ሌላ መልክ ይያዙ እንጂ እኒሁ ናቸው። ተጎጅው ደግሞ ያው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ትግሉ የሕዝቡ ነውና የሕዝቡን ባለቤትነትና የበላይነት መቀበል ዋነኛ መሠረታዊ ግዴታ ነው። ቀጥሎ ደግሞ፤ ያለውን የሀገራችንን የፖለቲካ እውነታ በትክክል ተንትኖ፤ ለዚህ ወቅታዊ የፖለቲካ ሀቅ ትክክለኛ መፍትሔ ማቅረቡ ነው። በኔ እምነት፤ በኢትዮጵያ ያለው ወራሪ መንግሥት ነው። ይኼን ወራሪ መንግሥት መታገል ያለብን፤ ጥቂት መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ የትግል ዕሴቶችን በማውጣት፤ አንድ የኢትዮጵያዊያን ሕዝባዊ የነፃነት ንቅናቄ መሥርተን በመነሳት ነው። መታገያ ዕሴቶቻችን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት መከበሩ፣ የኢትዮጵያ ሀገራችን ዳር ደንበር መጠበቁ ለሙ መሬቷ ለኢትዮጵያዊያን መዋሉ፣ የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ መብት መከበሩ፣ እና የሕግ የበላይነት መረጋገጡ ናቸው። በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለነው በአንድነት በነዚህ ሀገራዊ አንገብጋቢ ዕሴቶቻችን ዙርያ በመሰባሰብ መነሳት አለብን።
ከነዚህ አንገብጋቢ ዕሴቶቻችን ውጪ ያለው ጉዳይ፤ በመሠረቱ የሕዝቡን የትግሉ ባለቤትነትና የበላይነት እስከተቀበልን ድረስ፤ በሂደት ሕዝቡ በትግሉ ስለሚያነሳቸውና መፍትሔ ስለሚሠጣቸው፤ ላሁኑ በቆይታ ይታያሉ። እናም በነዚህ ዙርያ ተጠማጥመን እንቅስቃሴውን በአንድነት በአንድ ድርጅት ከውጪ ያለነው እናካሂደው። ካለፈው እንማርና፤ ለዚሁ አንድ ጉዳይ፤ ባንድ ተሰልፈን፤ ቆመን እንቆጠር። መማር ማለት፤ ከትናንት ተሽሎ መገኘት ማለት ነው። መማር ማለት ባሉበት መርገጥ ማለት አይደለም። መማር ማለት ማደግ ማለት ነው።