ሔኖክ ያሬድ
የዘንድሮው ትንሣኤ በዓል ሊከበር አንድ ሳምንት ቀርቶታል፡፡ የሚያዝያን አራተኛ ቀንን ይጠብቃል፡፡ ዛሬ መጋቢት 27 ቀን ሆሳዕና ከእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና ዋና በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡
ክርስቶስ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ይታሰብበታል፡፡ በወቅቱ ተሰባስበው የነበሩት የዘንባባና የወይራ ዝንጣፊ ይዘው በደስታ በዝማሬ ‹‹ሆሳዕና የዳዊት ልጅ›› እያሉ በምስጋና ተቀብለውታል፡፡
‹‹ሆሳዕና›› የአራማይስጥ (አራማይክ) ቃል ሲሆን ፍችውም ‹‹አድነን›› ማለት ነው፡፡ በዕብራይስጥም በግእዝም ተመሳሳይ ፍች አለው፡፡ በዚያ ዘመን አይሁዶች በሮማውያን ቀንበር ውስጥ ወድቀው ነበርና ምድራዊ ንጉሥ መጥቶ ነፃ እንደሚያወጣቸውና እንደሚያድናቸው ይጠብቁ ነበር፡፡ በመጻሕፍት እንደተጻፈው፣ በዚሁ ቀን እንዲሁ እግዚእ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቶ ሃይማኖት የንግድ ቦታ አይደለም በማለት ቁጣውን ያሳየበትና ነጋዴዎችንና ቀራጮችንም ያባረረበት ነበር፡፡
ቤተመቅደሱ የጸሎት ቤት መሆኑን ያወጀበትና ክብሩንም የገለጸበት ነው፡፡ የሆሳዕና ሥርዓት ዐቢይ ጾም በተጀመረ በስምንተኛው ሳምንት፣ ከትንሣኤ (ፋሲካ) አንድ ሳምንት በፊት የሚከበረው ሆሳዕና ከጌታ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሆሳዕና እሑድ በሁለት ነገሮች ይዘከራል፡፡ አንደኛው በቅዳሴ ጊዜ ‹‹ያለ ሕማምና ያለ ደዌ፣ ያለ ድካምም ለከርሞም ያድርሰን ያድርሳችሁ›› እያሉ ካህናቱ ዘንባባ የሚያድሉበት ሲሆን፣ ሁለተኛው ካህናቱና ምዕመናኑ በቤተ ክርስቲያኑ ዙርያ የሚያደርጉት ዑደት ነው፡፡ ‹‹በታወቀችው በዓላችን መለከቱን ንፉ›› እያሉ የቅዱስ ያሬድ መዝሙር እየተዘመረ በዐራቱም ማዕዘናት ዕለቱን በተመለከተ ዐራቱ ወንጌላት እየተነበቡ ይከበራል፡፡
ዕለቱ የሰሙነ ሕማማት ዋዜማ ስለሆነና ሰሙነ ሕማማት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ‹‹የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ›› መታሰቢያ ሳምንት በመሆኑ ጸሎተ ቡራኬ ለሙታን የፍትሐት ጸሎት ስለማይፈጸምበት በሆሳዕና እሑድ በሳምንቱ ውስጥ ለሚያርፉት የሚገባው ሁሉ አስቀድሞ ይፈጸማል፡፡
ከሆሳዕና በኋላ ከትንሣኤ በፊት ያሉት ሰሙነ ሕማማትና ዓርብ ስቅለት በተለይ በጾምና በስግደት የሚከበሩ ናቸው፡፡ በወይራ ቅጠል ጥብጠባ በማሳረጊያው ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት ከሆሳዕና ሰኞ እስከ ጸሎተ ኀሙስ ያሉት ቀናት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩትን 5500 ዓመታት (አምስት ተኩል ቀናት) “የዓመተ ፍዳ” መታሰቢያ ሆነው ተሠርተዋል፡፡ ሆሳዕና ባህላዊ ገጽታዎች የሚታዩበት ነው፡፡ በሁሉም የአገሪቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ምእመናኑ እየተገኙ የዘንባባ ዝንጣፊ ከመያዝ ባሻገር፣ ከአዋቂ እስከ ሕፃን በዘንባባው ቅጠል ለጣታቸው ቀለበት፣ ለእጃቸው እንደ አልቦ፣ ለራሳቸው እንደ አክሊል የሚጠለቅ አድርገው ያዘጋጃሉ፡፡ ምዕመናኑም የመስቀል ምልክት በመሥራት በቤታቸው ይሰቅሉታል፡፡
በሆሳዕና እሑድ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁነት በማስታወስ በአንዳንድ አድባራት ተመሳሳይ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርዒቱ የተካሄደው ከ109 ዓመት በፊት ነበር፡፡ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት” በሚለው የትዝታ ድርሳናቸው እንደጻፉት፣ የሆሳዕና በዓል በአክሱም ሥርዓት ዓይነት ሆኖ እንጦጦ ላይ መከበር የተጀመረው በ1898 ዓ.ም መጋቢት 30 በሆሳዕና ዕለት ነው፡፡ ከአክሱም የመጡ አንድ መምህር ከበዓሉ ቀን ቀደም ብለው ጀምረው የሥነ ሥርዓቱን አፈጻጸም ለደብሩ ካህናትና ለሕፃናት መዝሙር አስጠንተዋል፡፡
በበዓሉ ዕለት አንዲቱን የበቅሎ ግልገል በወርቅ ጥልፍ የተለጠፈ ባለመረሻት (የበቅሎ የማዕርግ ልብስ፣ በልዩ ልዩ ሐሮች ተጠልፎ የተዘጋጀ ወርቀ ዘቦ) ኮርቻ ተጭኖባት ድባብ ደብበውላትና አጅበዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን አመጡዋት፡፡ ዑደት ተደረገ፡፡ ከአክሱም የመጣው ያ የሆሳዕና በዓል ሥነ ሥርዓት ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መኳንንትም ሁሉ ባሉበት መከበሩ ተመዝግቧል፡፡