የካቲት 26 ቀን፣ 2007 እ.ኢ.አ.
ጥንት አባቶቻችን እንደሚሉት “ነገርን ነገር ያነሳዋል…” ነውና፤ በአንድ ያልታሰበ አጋጣሚ እንደቀልድ ከአንድ የምወደው የቀድሞ ወዳጄ ጋር በዋዛ ፈዛዛ ያደረኳቸው ጨዋታዎች፤ እውነትም በምንወዳትና በምንሳሳላት ሃገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት እየተከናወነ የሚገኘውን ነባራዊ እውነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ስለመሰለኝ፤ ይህንኑ ለአንባቢያን ፍርድ ማቅረብን ወደድሁ። ነገሩ እንዲህ ነው…!
የዛሬ ሁለት ወር አካባቢነው። ከአመታት በፊት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳለን የቅርብ ወዳጄ የነበረ ጓደኛዬን ፌስቡክ ላይ ባጋጣሚ አገኘሁት። ለአመታት ሳንገናኝ በመቆየታችን ናፍቆታችንን ለመወጣት ይመስላል፤ በጓደኝነት ያሳለፍናቸውን ጊዜአት በትዝታ መልክ እያስታወስን ስናወጋ ለሳአታት ቆይተን ነበር። ይህ ወዳጄ ዝምተኛ የሚባሉ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል የሚመደብ ሲሆን፤ እንደኔ በሚቀርቡት ወዳጆቹ ግን በጨዋታ መሃል ሳይታሰብ ጣል በሚያደርጋቸው አስቂኝ ቃላቶቹ ይታወቃል። እንደነገረኝ ከሆነ በአሁኑ ሰአት ከዩኒቨርሲቲ በተመረቀበት ሙያ እያገለገለ ሳይሆን፤ ያዋጣል ብሎ ባሰበው የንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል። በመሆኑም አንድ መለስተኛ ህንፃንና ሁለት የንግድ ድርጅቶችን በባለቤትነት ያስተዳድራል። ይህ ወዳጄ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባትም ሆኗል። በኔ ግምት እንደተመረጡት ቁንጮ ባለስልጣናት የናጠጠ ሃብታም ባይሆንም፤ ጥሩ ኑሮን ይኖራሉ ከሚባሉት ጥቂት ዜጐች ተርታ የሚመደብ ይመስለኛል።
ባልሳሳት ለአንድ ሰአት ያክል ፌስቡክ ላይ በፅሁፍ በመመላለስ እንዳወጋን፤ ጓደኛዬ “የበለጠ እየተያየን ብናወጋ የተሻለ ይሆናል” በሚል እሳቤ፤ ወደ ስካይፕ እንድንሄድ ጠየቀኝ። እኔም ተስማምቼ ጨዋታችንን በስካይፕ ቀጠልን። በአካል ስመለከተው በፅሁፍ የነገረኝ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዳለ ሰው የተመቸው አይመስልም። በውስጤ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብዬ እያሰላሰልኩ ጨዋታችንን ቀጠልን።
ለአመታት የተለየሁትንና ያላየሁትን ወዳጄን እያየሁት ማውራት በመቻሌ እጅግ ተደስቼ የነበረ ቢሆንም፤ ለጥቂት ደቂቃዎች ከተጫወትን በሗላ ምናልባትም ለወዳጄ አስጊ ሊሆን የሚችል ነገር ትዝ አለኝ። ነገሩ እንዲህ ነው፤ የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ አብሮኝ የሚሰራ አንድ ሐበሻ “ኢትዮጵያ ውስጥ በስካይፕ መነጋገር በህግ ያስቀጣል።” የሚል ህግ እንደተደነገገ የነገረኝን አስታወስኩ። መረጃውን ያካፈለኝ ባልደረባዬ እንደኔው ተሰዶ በውጭ ሃገር የሚኖር ስለነበረ ትክክለኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ ባልሆንም፤ ጉዳዩ ለወዳጄ ደህንነት ወሳኝ እንደሆነ ስለተረዳሁ፤ ስለመረጃው እውነትነት እርግጠኛ አለመሆኔን በመናገር እንዲያረጋግጥልኝ በጥያቄ አቀረብኩለት። “እኔምልህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በስካይፕ መነጋገር ክልክል አይደለም እንዴ !?” የመንግስታችንን አይምሬነት ስለምገነዘብ፤ እርሱም ቢያንስ ከእኔ በላይ ይጨነቅበታል ብዬ ያመንኩበት ወዳጄ፤ ፈጠን ብሎ “ባክህ እርሳው፤ መንግስታችን የሚያወጣው ህግ ከጐኑ ላጲስ አለው” ቢለኝ በጣም ተገረምኩ።
የተናገረውን በሚገባ የሰማሁት ቢሆንም፤ በመልሱ ግራ ስለተጋባሁ “ምን አልከኝ!?” አልኩት። ጓደኛዬም ነገሩ እንግዳ እንደሆነብኝ ስለተረዳ ጉሮሮውን ሳል ሳል አደረገና “ስለዚህ ጉዳይ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አስቤም አላውቅ። እውነትም ከሃገር ርቀሃል ጃል!” በማለት ጨዋታውን ቀጠለ። “በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ውስጥ የተደነገገ ማንኛውም ህግ ላጲስ ከጐኑ አለ እኮ ነው የምልክ! አልሰማህም እንዴ!?” ብሎ በመገረም ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰልኝ። ወዳጄ አሁንም ያን ቀልዱን አለመተዉን ለቅፅበት አሰብ አረኩና፤ ጨዋታውን እንዲቀጥልልኝ ስለፈለኩ “ኧረ በጭራሽ አልሰማሁም፤ ደግሞ ይህ ምን ማለት ይሆን!?” ፤ “አይ አንተ ልጅ አሁንም ቀልድህን አልተውክም ማለት ነው!?” ጠየኩት። ወዳጄም ፈገግ ካለ በሗላ፤ ቀጠለ “አየህ ባሁኑ ሰአት እዚህ ሃገር ላይ ማንኛውም ወንጀል ብትሰራ በህግ አትቀጣም።”፤ “ማለቴ የመንግስታችንን አስተዳደር እስካልተጋፋህ ድረስ።”
ብዙ ጊዜ በጨዋታ መሃል ቀልድ ቢጤ ጣል ማድረግ ስለሚወድ፤ አሁንም ይህንኑ የሚያደርግ መስሎኝ የነበረ ቢሆንም፤ እርሱ ግን ፊቱን አኮሳትሮ፣ ግንባሩን አቀጭሞ ንግግሩን ቀጠለ፤ “መንግስታችን ከህገ መንግስቱ ጀምሮ በርካታ ህጐችን በወረቀት ላይ በግልፅ አስፍሯል። ነገር ግን እነዚህን ህጐች ከመንግስት ጀምሮ ማንም አያከብራቸውም፤ አይተገብራቸውምም።” የሚያጫውተኝ ቁምነገር በቀልዱ የማቀው የቅርብ ወዳጄ የነበረ ሰው ያልተጠበቀ ሲሬስነት ጋር ተጣምረው፤ ለንግግሩ ሙሉ በሙሉ አትኩሮቴን እንድሰጥ ስላስገደዱኝ፤ ሳላስበው በተመስጥኦ ማዳመጥ ጀመርኩ። እርሱ ግን መናገሩን አላቋረጠም። “መንግስትን ጨምሮ ሁላችንም ህግ እንጥሳለን፤ ምክንያቱም የምንጠየቅበት መች እንደሆነ እናውቃለና!” በአትኩሮት አይን አይኔን እያየ ንግግሩን ቀጠለ፤ “እኔ ራሴ በቀን ብዙ ህጐችን እጥሳለሁ፤ ይህን ደግሞ መንግስት በሚገባ ያውቃል፤ ግን ማንም ጠይቆኝ አያውቅም።” “አየህ እኔ ልማታዊ ዜጋ ነኝ፤ ልማታዊ ዜጋ ታውቃለህ!?” በማለት ያልጠበኩትን ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ከእንቅልፌ የነቃሁ ያክል፤ “ኧረ በጭራሽ! ቀጥል!?” አልኩት። በርግጥ በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች “ልማታዊ ጋዜጠኞች” እንደሚባሉ ስለማውቅ፤ “ልማታዊ ዜጋ” ምን እንደሆነ መገመትና መናገር እችል ነበር። ነገር ግን ጨዋታውን የሚያቋርጥብኝ ስለመሰለኝ ባጭሩ “ቀጥል” አልኩት።
ጨዋታውን ለመስማት መጓጓቴ እንዳስገረመው ከፊቱ ላይ በሚነበብ መልኩ ቀና ብሎ ካየኝ በሗላ ንግግሩን ቀጠለ፤ “አየህ እኔ ‘ልማታዊ ዜጋ’ ስለሆንኩ፤ በመንግስታችን ስራ ጣልቃ አልገባም። ያሻውን ቢያደርግ አርሱ የኔ ጉዳይ አይደለም፤ አይመለከተኝምም።” እያዳመጥኩት እንደሆነ ከረጋገጠ በሗላ በተመስጥኦ ጨዋታውን ቀጠለ፤ “ገባህ ከእኔ የሚጠበቀው፤ የተፈቀደልኝን ብቻ እየሰራሁ እስከተፈቀደልኝ ድረስ ‘በሠላም’ መኖር ብቻ ነው። እንዳልኩህ በመንግስት የስራ ጉዳይ ውስጥ በፍፁም ጣልቃ መግባት የለብኝም፤ የኔ ስራም ለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነው፤ አለበለዚያ የምሰራቸው ወንጀሎች ያስጠይቁኛል።”
ለአፍታ አቀርቅሮ ካሰበ በሗላ፤ አትኩሮ እየተመለከተኝ ጨዋታውን ቀጠለ፤ “ሌላው የኔ ስራ ደግሞ፤ ምርጫ ሲደርስ መንግስትን መምረጥ፤ ዜጐች ቢበደሉ፤ ሃገር ቢቆረስ፤ ንፁህ ዜጋ ወንጀለኛ ተብሎ ቢፈረድበት፤ ሌላም ሌላም፤ ሁሉም ለኔ ጉዳዮቼ አይደሉም። ከኔ የሚጠበቀው መንግስት የሚፈልገውን እየሰራሁና እያስተጋባሁ ኑር እስከተባልኩ ድረስ መኖር ብቻ ነው።” እየሰማሁ ያለሁት ጉዳይ በጣም ግራ ስላጋባኝ፤ በአንድ በኩል የሰው ልጅ እንዴት በእንደዚህ የተሳሰ ሁኔታ መኖር ይችላል!? መለስ እልና ደግሞ ጓደኛዬን ድሮ ሳውቀው አደለም የማያምንበትን፤ አምኖ የተቀበለውን እንኳ በተገቢው መፈፀም እንደሚያጨናንቀው ነበር፤ አሁን ታዲያ ምን ነክቶት ይሆን!? ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን በውስጤ እያሰላሰልኩ፤ የራሴ አለም ውስጥ ሳላስበው ሰጥሜ አዳምጠው ነበር። እርሱ ግን ንግግሩን ቀጥሏል፤ “መንግስት ኢኮኖሚው በሁለትም በሶትም ዲጂት አደገ ካለ፤ እኔም ያንን አስተጋባለሁ፤ ቁጥር የኔ ጉዳይ አይደለም።”
በዝምታ አንገቱን አቀርቅሮ ለጥቂት ሴኮንዶች ጨዋታውን ሲያቋርጥብኝ፤ ያልሆኑ ጥያቄዎችን አምጥቼ ወዳጄን ያስከፋሁት ስለመሰለኝ፤ ነገሩን ወደ ሌላ ጨዋታ አቃልዬ ለማስቀየር በማሰብ፤ እሺ እና ቤተሰብ እንዴት ነው ባክህ!? አልኩኝ። እርሱ ግን ቀና ብሎ አይቶኝ ጨዋታውን ቀጠለ፤ “ንግድ ውስጥ እንዳለሁ ነግሬሃለሁ፤ አይደል!?” አለኝ። ደንገጥ ብዬ፤ በፍጥነት “አዎን ነግረኸኝ ነበር” አልኩ። “ታውቃለህ!?” አለኝ፤ “አንድ የመንግስት የበላይ ባለስልጣን ወይንም ወዳጁ፤ በማንኛውም ሰአት የኔ ቢዝነስን ሼር ሆልደር ልሁን ወይም ልግዛህ ካለኝ በደስታ እቀበላለሁ። ባይገርምህ እስካሁን ስንት የንግድ ድርጅቶች ቀያይሬአለሁ መሰለህ!” “ባክህ ተወኝ ብዙ አታሶራኝ እኔ ተመችቶኛል። ይልቁንስ የሚያሳዝኑኝ ድርጅታቸው ሲቀማ፤ እንደ አዲስ መጀሩ ታክቷቸው ነገር አለሙን እርግፍ አርገው የሚተዉት ሰዎች ናቸው።” “እኔ እንኳ በአዲስ መጀመር ምንም አይመስለኝም፤ ከንግዲህ እንዳትሰራ ካላሉኝ በስተቀር።” አለ ፈገግ ብሎ እየተመለከተኝ።
“አሁን ግልፅ ሆነልክ!?” ጠየቀኝ፤ ነገር ግን መልሴን ሳይጠብቅ ንግግሩን ቀጠለ፤ “ስለዚህ ህጉ ላጲስ አለው ያልኩህ ለዚህ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል እንደ እኔ አይነቱን ልማታዊ ዜጋ በህግ አያስጠይቀውም፤ አያስቀጣውምም።” “ለነገሩ ባለስልጣናቱንም አያስጠይቅም፤ ከዋናዎቹ ጋር እስካልተቃረኑ ድረስ።” “እስኪ በየ እስር ቤቱ የታጐረውን ዜጋ አስብ!!!? እውን እንደሚባለው ወንጀል ፈፅሞ ይመስልካል!?” “የትኞቹ ጋዜጠኞች ናቸው ወደ እስር ተወርውረው የተረሱት!?” “ፖለቲከኞቹስ ቢሆኑ!? ሁሉም የሚታሰሩ ይመስልሃል!?” “ስንቱ ከስራ ተባሮ ቦዘኔ ደሓ ሁኖ የቀረው ስራውን በአግባቡ ስለማይሰራ ይመስልሃል!?”
“ስለዚህ እመነኝ፤ እኔ ለልማታዊው መንግስታችን የምመች ልማታዊ ዜጋ ሆኛለሁ።” “መንግስታችን እንደኔ አይነቶቹ ዜጐች ከሌሉ ለህልውናው ስለሚሰጋ ይንከባከበናል። ስለዚህ አትጨነቅ።” “በርግጥ ይህን እንዳጫወትኩህ ከሰሙ ነገ ወደ እስር ቤት እንደምጓዝ አትጠራጠር። ለነገሩ አንተ ካልነገርካቸው በስተቀር የዛሬው ጨዋታችንን አይሰሙትም። ምክንያቱም አይከታተሉኝማ፤ አውቃለሁ።” “እነርሱ የሚከታተሉህ ‘ልማታዊ ዜጋ’ ካልሆንክ ብቻ ነው።”አለና ቀና ብሎ እያየኝ “አሁን ገባህ!? መንግስታችን የሚያወጣቸው ህጐችና መመሪያዎች ከጐናቸው ላጲስ አሏቸው።” “በላጲሱ ማጥፋት የሚችለው ግን መንግስታችን ብቻ ነው።” “እንዲያጠፋልክ የምታዘው ደግሞ አንተ ነህ፤ ‘ልማታዊ ዜጋ’ በመሆን።” “ይሄው ነው ወዳጄ።” አለኝ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!