ጥር 22፣ 2007 (ጃናዋሪ 30፣ 2015)
ባለፉት ወራቶች የህወሓትን የበላይነት ፍጹም በሆነ ደረጃ የሚያስተናግደው፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው የምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ መሰረት በሰላም የሚንቀሳቀሱትን አገር አቀፍ የሆኑ ሕብረ ብሄር ተወዳዳሪና የፖሊሲ አማራጭ ለመስጠት የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከፋፍሏል፤ ተጠላፊ ድርጅቶችን መስርቷል፤ “ይኼን፤ ያንን አላሟልችሁም” እያለ አንገላቷል፤ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉትን እናቶች፤ አባቶች፤ ወጣቶችና ሌሎች እንደ እንሰሳ ደብድቧል፤ አካለ ስንኩል አድርጓል፤ አዋክቧል፤ አሳዷል፤ አስሯል። የሰባ ዓመት ባልቴት የሚደበድብ ስርዓት በራሱና በሕዝቡ አይተማመንም ለማለት እንደፍራለን።
ሸንጎ፤ ይኼ በተከታታይነት ሲደረግ የቆየ አሰቃቂ የሰብአዊ መብቶች አፈናና ረገጣ ሆነ ተብሎ፤ በተለይ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብቶች መከበር፤ ለዲሞክራሳዊ ስርዓት መተካት፤ ለእውነተኛ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ስኬታማነት መዛባት፤ ለሃገሪቱ ሉአላውነት፤ ክብር፤ ነጻነት፤ እርጋታና ሰላም የቆሙትን–መኢአድን፤ አንድነትን፤ ሰማያዊ, እና ሌሎችን–ለማዳከምና ለማጥፋት የተደረገ እቅድ ነው ይላል። ለገዢው ፓርቲ ታማኝነት ያላቸውን ተቀጥላ ድርጅቶች ማቋቋሙ፤ በመጭው ምርጫ ፍፁም የበላይነትን እንዲያገኝ ለማድረግ የተደረገ ሴራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል። ህወሓት፤ ይኼው “በምርጫው የሚሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ” እያለ የዓለምን ህብረተሰብ ለማታለል ይሞክራል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለው፤ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ምርጫው የሚካሄደው፤ የገዢው ፓርቲና ተለጣፊዎቹ ከራሳቸው ጋር ብቻ የሚወዳደሩበት ይሆናል” የሚል ነው። ያለፈውን መድገም። ከአምባገነኑ ከመለስ ዜናዊ እልፈት በኋላ የዓለም ሕዝብ፤ በተለይ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የፖለቲካው ምህዳር ሰፋ ይል ይሆናል፡ሜዳው ለሁሉም አመች ይሆናል፤ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆነው የመገናኛ ብዙሃንና የማህበረሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ወዘተ የሚል ምኞት ነበር። አልሆነም። ስለዚህ፤ አገሪቱን ከከፋ አደጋ ለማዳን የሚፈልግ፤ በተለይ የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ ይኼን ሂደት ሊያወግዘው ይገባል እንላለን።
በሸንጎና በሌሎች አገር ወዳድና ዲሞክራሳዊ ኃይሎች ግምት ጠባብ ጎሰኛውና አምባገነኑ ህወሓት/ኢህአዴግ ተተኪ በማይገኝላቸው ኢትዮጵያ ባፈራቻቸው በአገር፤ በፍትህ፤ በህግ የበላይነት፤ በሰብአዊ መብቶች መከበር፤ በዲሞክራሳዊ ስርዓት መመስረት፤ በዘላቂና ፍትሃዊ እድገት አማራጭ ስኬታማ በመሆን የሚያምኑና ለዚህ መስዋእት ለመሆን የወሰኑ ታጋዮችና ወዳጆች ላይ የሚደረገው ግፍ የውጭ “ወራሪ” ከሚያደርገው ግፍ የተለየ አይደለም። በንፁህ ኢትዮጵያዊያን አዛውንቶች፤ በተለይ እናቶችና ወጣቶች ላይ የሚደረገው ክብርንና ሰብእነትን የሚገፍ በደል የደረሰው በፋሽስቱ ግራዚያኒ አገዛዝ ወቅት ነበር ከምንልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት የታየውና የሚያኮራውና ማንም ሊያቆመው የማይችለው ክስተት፤ ይኼ ጭካኔ በሚካሄድባት፤ “ታሪኳ የመቶ ዓመታት ታሪክ ነው፤ ሕዝቧ የተለያየ ነው፤ እኔ ከሌለሁ ይሕች ሃገር ትወድማለች” ወዘተ ብሎ ህወሓት/ኢህአዴግ በፈረደባት የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አርአያ ኢትዮጵያ አገር ወዳድነት፤ ኢትዮጵያዊነት፤ ከጎሳ በላይ ለሃገርና ለመላው ሕዝብ የማሰብ ባህል እያደገ መገኘቱ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ አገር ወዳድ የሆኑ ህብረ ብሄር ፓርቲዎችን ለማጥፋት የመንግሥት ተቋሞችን—የምርጫ ቦርድ፤ ፍርድ ቤቶች፤ የፌደራልና የመዘጋጃ ቤቶች ፖሊስ፤ ደህንነትና መከላከያ–ቢጠቀምም፤ ዙሮ ዙሮ በእነዚህ ተቋሞች የታቀፉት ግለሰቦች ለወገኖቻቸው፤ ለራሳቸውና ለሃገራቸው ይቆማሉ። በእኛና በውጭ ተመልካቾች ግምት፤ የህወሓት/ኢህአዴግ ጨካኝነትና ፀር-ሕዝብነት፤ ፀረ-ዲሞክራሳዊነት፤ ፀረ-ፍትህነት ወዘተ እያደገ ሲሄድ ለገዥው ፓርቲ አገልጋይና ታዛዢ እንዲሆኑ የተገደዱ ሁሉ ሚናቸው እየለየ፤ በውስጥ እየተከፋፈሉ፤ የሕዝቡን በደል እያዩ ሲሄዱ ወደ ሕዝቡ ጎራ ይገባሉ የሚል ግምት አለን። ተቃዋሚ ኃይሎች ለዚህ የሚያደርጉት ቅስቀሳ የሚያኮራና የሚደገፍ ነው እንላለን። በርቱበት፤ ግፉበት እንላለን። የህዝቡንም ትግል ወደተፈለገው ድል ለማድረስ እልህ አስጨራሹን ጉዞ ተባብረን በትግስት እንቀጥል፣ ለከፋፋዩና ለጥፋት መልክተኛው ህወሀት /ኢህአዴግ ሴራ በር አንክፈት እናላለን። እኛም ድርሻችን ለመወጣት ቆርጠና ተነስተናል።
“ሰውን በቁሙ ማቃጠልና መግደል” የሚለው ህወሓት/ኢህአዴግ
ሕዝብን የሚጨፈጭፍ ገዢ ፓርቲ በሚመራበት ስርዓት ሙሉ እምነት የለውም። ምርጫን እንደሌላው ሙስና አጭበርብሮ ከሕዝብ መስረቅ የተለመደ ባህሪው ነው። በሸንጎ ግምት፤ የገዢው ፓርቲ ራስን ማቆያ ዘዴ በተደጋጋሚ ታይቷል፤ በተለይ ከምርጫ ዘጠና ሰባት ወዲህ። ምን ዘዴዎች ይጠቀማል? መከፋፈል፤ ሰርጎ ገብቶ ታማኞችን በስልጣንና በገንዘብ ጥቅም መግዛት፤ ማስፈራራት፤ በዱላ መደብደብ፤ ማሰር፤ ሺባ ማድረግ፤ ማሳደድ፤ በምስጢር መግደል፤ ከሃገር እንዲወጡ ማስገደድ፤ የግል ኃብታቸውን መውረስ፤ “በቁማቸው እንዲሞቱ” ማድረግ ወዘተ። ዋናው ስትራተጅ የተቃዋሚው ክፍል እንዲደመሰስ፤ ባይደመሰስም፤ የተበታተንና ደካማ ኃይል እንዲሆን ለማድረግ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ፤ ኢትዮጵያን የብዙ የጎሳ ፓርቲዎች ስብስቦች አገር ያደረገበተ ዋና ምክንያት ለዲሞክራሲ ደንታ ስላለው አይደለም። እነዚህ የራሱ ፍጡራን የሆኑ ድርጅቶች ለራሱ መቆያ ስለሚረዱት ነው። በህብረ ብሄር አማራጮች ምትክ በብሄር/ብሄረሰብ የተደራጁትንና ተለጣፊ ድርጅቶችን መንከባከብ፤ እርስ በርሳቸው እንዲፎካካሩ ማድረግ ለህወሓት/ኢህአዴግ መቆያ ዋና መሳሪያነት አለው። የብሄር/ብሄረሰብ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሚሰረቱ የተደረገበት አቢይ ምክንያት ተቃዋሚ የሚባለው ኃይል በጎሳ ተከፋፍሎ ከራሱ ጎሳና ጥቅም ባሻገር ለመላው ሕዝብና ለሃገር እንዳያስብ ለማድረግ ነው። ለጎሳውና ለራሱ ጥቅም ብቻ ከቆመ ለገዢው ፓርቲ አደጋ አይሆንም። ስለሆነም፤ ገዢው ፓርቲ ከሁሉ በላይ የሚፈራው የተባበረ ሕብረ-ብሄር ድርጅቶችን ነው እንላለን። ሸንጎ ደግሞና ደጋግሞ አደራ የሚለው መከፋፈልን እንቋቋም፤ እርስ በርስ መወነጃጀልን ከፖለቲካ ባህላችን እናውጣ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚፈልገውን አናድርግ፤ ከወጥመዱ መጥቀን እንውጣ ነው። አሁንም ጥሪያችን ይኸው ነው።
የተቃዋሚው ክፍል አፈናውን ወደማይበገር ኃይል ሊለውጠው ይገባል
የህወሓት/ኢህአዴግና የእኛ ስሌት አይጣጣምም። ህወሓት/ኢህአዴግ መከፋፈል፤ ማሳደድ፤ ማዋረድ፤ ማሰርና ሌሎች አሰቃቂ የፖለቲካ መቆያዎች ዘላቂነት አላቸው የሚል ግምት እንዳለው አሳይቷል። በዚህ ዘዴ ሲጠቀም ሃያ አምስት አመታት ሊሆነው ነው። ሁኔታዎች የሚያሳዩት ግን ይህ የአምባገነን ዘዴ ገመናን ከማገለጥ የበለጠ አገሪቱ የገጠማትን መሰረታዊ ችግሮች–ለምሳሌ፤ የኑሮ ውድነንት፤ የምግብ ዋስትና ማጣትን፤ የስራ እድል መጥፋትን፤ በሃገር ኑሮ መሻሻልን፤ የሃገሪቱን የተፈጥሮ ኃብት ለኢትዮጵያዊያን ጥቅም ማዋልን፤ የጠባብ ጎሰኛ አድልዖ፤ ጉቦና ሙስናን ማጥፋትን፤ የሕዝብ ስርጭት መያያዝን–ወዘተ ለመፍታት አለመቻሉን ነው። እነዚህ ብሄራዊ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ፍትሃዊ ስርዓት ሲመሰረት ብቻ ነው። አገር ወዳና ለፍትህ የቆመው ተወዳዳሪ ወይንም ተቃዋሚ ኃይል አማራጮችን በማቅረብ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ይችላል የሚል ግምት አለን። ሆኖም፤ በሸንጎ ግምት፤ እያንዳንዱ አገር ውስጥ ሆነ ውጭ ያለ አገር ወዳድና ፍትህ ፈላጊ ተቃዋሚ የመቀበልና የታሪክ ግዴታውን የመወጣት ግዴታ ያለበት በተናጠል በመደራጀትና በመታገል አይደለም። በኢትዮጵያ ውስጥ በሃቅ የሚታየው ክፍተት በዓላማ አንድነት ላይ የተመሰረተ ህብረት፤ ቢቻል ውህደት ለመመስረት አለመቻሉ ነው። አሁን ያለው እድል በምንም ሊያመልጠን አይገባም። እንተባበር፤ እንፈላለግ፤ አንከፋፈል፤ የማይበገር ተቃዋሚ ኃይል እንፍጠር እንላለን።
በምርጫው “እንሳተፍ ፤ አንሳተፍ” ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ይታይ
ሸንጎ ዛሬ ባለው ሁኔታ በምርጫው አንሳተፍም፤ “ምንም አስተማማኝ ሁኔታ የለም፤ የፖለቲካው ምህዳር በሙሉ ተዘግቷል፤ በምርጫው መሳተፍ ለገዢው ፓርቲ የማይገባውን እውቅና መስጠት ነው” የሚሉትን ሃሳብ ውድቅ ነው አይልም። የሚሉት ሙሉ በሙሉ ይገባናል። በሌላ በኩል፤ በምርጫው መሳተፍ “የማሸነፍ ያለማሸነፍ ጉዳይ አይደለም። መሳተፍ አማራጮችን ለማቅረብና የሕዝብን ተሳትፎ ለማስፋፋትና ገዢውን ፓርቲ ለማጋለጥ ይረዳል። አንሳተፍም ባይነት ለገዢው ፓርቲ የፈለገውን ተቃዋሚ የለም የሚል ውሸት ያጠናክራል። ትግሉ የዲሞክራሲ ስርዓትን ለመመስረት እንጅ ጥቂት ወንበሮችን ለማግኘት አይደለም። ብንወድም ባንወድም፤ ሰርቆም ሆነ በማፈንና በማሰፈራራት ገዢው ፓርቲ ያሸንፋል። የወቅቱ አነጋጋሪ ጉዳይ “እንገባለን፤ አንገባም”፤ ፓርቲዎች ተከፋፈሉና ለምን የሚለውን ሂሳብ መወራረድ አይመስለንም። ይኼ የትም አያደርስም፤ የሚረዳው ህወሓት/ኢህአዴግን ነው። ቁም ነገሩ አምባገነኑን ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሕዝብ እምቢተኛነት ከስልጣን እንዲወርድ አብሮና ተባብሮ መስራት ነው እንላለን። ወሳኙ ኃይል የኢትዮጵያ ሕዝብ መተባበርና ደፍሮ ለመብቱና ለህልውናው መታገል ነው። ይኼን ማንም የውጭ ኃይል አይሰራውም፤ የታሪክ ባለአደራወቹ እኛው ኢትዮጵያዊያን ነን።
የውጭ አበዳሪ ድርጅቶችና የገዢው ፓርቲ ደጋፊ መንግሥታት፤ በተለይ አሜሪካና እንግሊዝ የሚፈለጉት እርጋታን፤ ሰላምንና የራስን ጥቅም ማስተናገድን ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ የሀገራቸውን ጥቅም ማስጠበቅ እንጂ ለሰብዊ መብቶች መከበርና ለዲሞክራሳዊ ስርዓት አማራጭነት ቅድሚያ የሚሰጡት ሆኖ አልተገኘም። ቀደም ሲል ስለ ምርጫው አስፈላጊነት ባወጣነው መግለጫ እንዳሳየነው፤ በምርጫው መሳተፍ የትግሉ አንድ አካል ነው። አንሳተፍም ወይንም እንሳተፋለን የሚሉት አቋሞች እንዳሉ ሆነው፤ ዋናው ትኩረት ተባብሮ አዲስ በሕብና ለሕዝብ ተገዢ የሆነ አማራጭ ስርዓት መመስረት ብቻ ነው። ለዚህ በተናጠል የመስራትን የፖለቲካ ባህል አቁሞ መተባበርን፤ ቢቻል በመዋሃድን መሰረት ማድረግ ነው። ይኼ ሲሆን፤ የውጭ አበዳሪዎችና መንግሥታትም አማራጭ መኖሩን ሲመለከቱ ለሀገራችን ሁኔታም ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጡት አንጠራጠርም።
ባለፉት ሳምንታት የተለያዩ የውጭ የሰብአዊ መብቶች መከበር ተቋሞች፤ ህወሓት/ኢህአዴግ በበላይነት የሚመራው መንግሥት ለሰብአዊ መብቶች ፀር መሆኑን፤ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት እንዳለባቸው፤ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት መከበር እንዳለበት፤ የፖለቲካው ምህዳር መከፈት እንዳለበት፤ ተቀናቃኝ ወይንም ተወዳዳሪ የሆኑ ፓርቲዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ መብታቸው እንደሆነ ወዘተ ዘገባና ሃሳቦች አቅርበዋል። አገሪቱን የፖለቲካ እስር ቤት አድርጎ “ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ” ለማካሄድ እንደማይቻል ሂውማን ራይትስ ወች ባቀረበው ሰፊ ትንተና አሳይቷል። ይኼን በሚመለከት በቅርቡ በኢትዮጵያ ለሚገኘው የለጋሶችና የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊ አገሮች አምባሳደሮች ስብስብ (Development Assistance Group/DAG) ለተባለው አካል የጻፍነውን በድጋሜ ከዚህ በታች እናሳያለን።
1.ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆነ የሃገር ውስጥና የውጭ ታዋቂ ታዛቢዎች የሚገኙበት ኮሚሺን ተቋቁሞ በኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን ድብደባ፤ አፈና፤ እስራትና ያልታወቁ ግድያዎች እንዲመረምሩ ማድረግ፤ በንጹህ ኢትዮጵያዊያን የአካል ጉዳት፤ አፈና፤ እስራትና ግድያ የፈጸሙ በሃላፊነት በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ፤ የዚህ አይነቱ አፈና እንዲቆም በግልና በይፋ ለኢትዮጵያ መንግሥት ሃላፊዎች መናገር፤
2.የፖለቲካ ምህዳሩ በአስቸኳ እንዲከፈት፤ ተወዳዳሪ ወይንም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደልብ እንዲንቀሳቀሱ፤ አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ ሕዝብ እንዲቀሰቅሱ፤ ገንዝብ ለመሰብሰብ እንዲችሉና ቢሮዎች ለመክፈት እገባ እንዳይደረግባቸው በግልና በይፋ ለመንግሥት የበላዮች መናገር፤ ይኼ ካልሆነ የሚመጣውን አደጋ እንዲያውቁት ማስጠንቀቅ፤
3.የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ በግልና በይፋ መናገር፤
- የምርጫ ቦርዱ ከገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ጫና ማድረግ፤
- ፍርድ ቤቶችና ፖሊሶች ከገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ እንዲሆኑ ጫና ማድረግ፤
- ከገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ጋዜጠኞች ሚና እንዲከበር ጫና ማድረግ፤
- ለተወዳዳሪ፤ ወይንም ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ የሆነ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አገልግሎት እንዲያገኙ ጫና ማድረግ፤
- የፌደራል ፖሊስ፤ ደህንነትና መከላከያ ተቋሞች በምርጫው ጣልቃ እንዳይገቡ ማሳሰብ፤
- የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭና የአገር ሰብ አዊ መብት ድርጅቶችና የማህበረሰብ ተቋሞች ያለ ምንም ተፅእኖ እንዲንቀሳቀሱ ጫና ማድረግ፤
10.የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭና የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች እንዲጋበዙና ምርጫው ዓለም በሚቀበለው የምርጫ ሂደት መካሄዱን እንዲከታተሉ አስቀድሞ ስምምነት ላይ ማድረስ የሚሉ ይገኙበታል።
በአጭሩ፤ ሸንጎ ከላይ በጠቀስናቸውና ሌሎች ብሄራዊ ጉዳዮች እውን እንዲሆኑና በሀገራችን ውስጥ የስርአት ለውጥ እንዲመጣ ያልተቆጠበ ጥረቱን ይቀጥላል። ለተቃዋሚው ኃይልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደጋግመን አደራ የምንለው ዛሬ የተከሰተውን አፈናና መከራ ወደ አዲስ እድል መለወጥ የሁላችንም ግዴታ መሆኑን ነው። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ አብሮና ተባብሮ ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ እንደገና እናሳስባለን። ጊዜው የገዝውን ቡድን ከፋፍሎ የማጥቃት ሴራ አክሽፈን በጋራ የምንነሳበት፣ በጋራ የምንታገልበት ፣ ለትግሉ ያለንን ጽናት የምናሳይበት እናድርገው።
መከፋፈል ይቁም፤ አብሮና ተባብሮ መስራት ብሄራዊ ግዴታ ይሁን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ