ያልተቀደሰው ጋብቻ (ኢህአዴግ፣ ፋና፣ ኢብኮ፣ ምርጫ ቦርድ) -ጌታቸው ሺፈራው

(ኢህአዴግ፣ ፋና፣ ኢብኮ፣ ምርጫ ቦርድ)

ጌታቸው ሺፈራው

በአንድ ወቅት ኢህአዴግ ‹‹የሚወዳደረኝ ተቃዋሚ ጠፋ›› ብሎ ቀልዶ ነበር፡፡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተበታትነው የነበሩት ተቃዋሚዎች ቅንጅትን ፈጥረው 1997 ምርጫ ላይ ሲያሸንፉት ደግሞ ቀልዱን ረስቶት ወደ ምርጫ የሚያመራውን መንገድ ሁሉ ለመዝጋት መታተር ያዘ፡፡ የፀረ ሽብር፣ የፕሬስ፣ የሲቪክ ማህበራት….አዋጆች ‹‹ከእኔ ጋር ለመወዳደር አቅም የላቸውም፡፡›› ይላቸው የነበሩትን ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ የሚያመሩበትን መንገድ የሚዘጉ መሰናክሎች ሆኑ፡፡ ያም ሆኖ ግን በእነ ኢዴፓ፣ የአየለ ጫሚሶው ‹‹ቅንጅት››ና መሰል ፓርቲዎች በመታጀብ ምርጫን ለይስሙላነት መጠቀሙን ቀጥሏል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ሳያሸንፍም ቢሆን አሸንፈሃል የሚለው ‹‹ምርጫ ቦርድ›› ጋር እጅና ጓንቶ ሆኖ ይሰራል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ ያልሆነውን ኢህአዴግን ብቸኛ አማራጭነ አድርገው የሚያቀርት ኢቲቪና ፋና አሉ፡፡ ሚዲያና ምርጫ ቦርድ ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ተቃዋሚዎችን በህዝብ አይን ማሳነስ ዋነኛ ስራቸው ሆኗል፡፡ በተለይ ምርጫ በተቃረበ ቁጥር ኢህአዴግ፣ ፋና፣ ኢብኮ፣ ምርጫ ቦርድ ሆነው በአንድነት በተቃዋሚዎች ላይ መዝመታቸው የተለመደ ነው፡፡

የኢህአዴግ፣ የፋና፣ የኢብኮና የምርጫ ቦርድ ጥምረት በዚህ አመትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህጋዊ እውቅና አግኝተው በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ረስቶ ‹‹ህገ ወጥ፣ አሸባሪ…›› እያለ መክሰስና ስም ማጥፋቱን የመጀመሪያ ስልት አድርጎ ውስዶታል፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህን የኢህአዴግ ፍረጃ ተንተርሶ መኢአድ፣ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ ላይ ምርጫ ቦርድ እሱ የማያገባውን ጥያቄ እያነሳ ‹‹ህገ ወጦች ናችሁ›› እያለ በሆነ ባልሆነው ሲጠምዳቸው ከርሟል፡፡ ኢቲቪ (ኢብኮ) እና ፋና ምርጫ ቦርድ እና ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ላይ የሚለጥፉትን ስም፣ የሚያነሱትን ክስ ደጋግመው ለህዝብ ያሰማሉ፡፡

አሁን አሁን ደግሞ እነዚህ ያልተቀደሰ ጋብቻ የፈፀሙት አካላት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አንጃ እስከመፍጠር ደርሰዋል፡፡ ለዚህ ያልተመቹዋቸውን ፓርቲዎች ደግሞ ክፍተት በመፈለግ ለመክሰስና ስም ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሰሩ ነው፡፡ በእነዚህ አካላት የስም ማጥፋት መዝገብ እየተፈለገላቸው ካሉ ፓርቲዎች መካከል ሰማያዊ ፓርቲ አንዱ ነው፡፡

በቅርቡ እስካሁን ለሰማያዊ ፓርቲ ምንም አይነት ሽፋን ሰጥተው የማያውቁት ፋና እና ኢቲቪ (ኢብኮ) በአንድ ቀን ልዩነት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነቱ ጋር ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር፡፡ የፋናው ‹‹ሞጋች›› ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ ብሩክ ኢ/ር ይልቃልን፣ እንዲሁም ኢብኮ (ኢቲቪ) አቶ ዮናታን ተስፋዬን አነጋግረው ነበር፡፡ ሆኖም የሁለቱም ቃለ መጠይቅ ሳይቀርብ የቀረ ሲሆን ፋና ‹‹ፋይሉ ጠፍቶብኝ ነው፡፡ ሌላ ቀን ቃለ መጠይቅ እንዳጋለን›› የሚል መልስ ሰጠ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ሁለቱም ሚዲያዎች የአመራሮቹን ሀሳብ አፋልሰው ያቀርባሉ በሚል ቀረጻ አድርገው ስነበር ‹‹ችግር የለም፡፡ እኛ ጋር ስላለ ውሰድ›› ቢሉትም ‹‹እናንተ የቀረጻችሁት ለሚዲያ አይሆንም›› በሚል ሳያቀርቡት ቀርተዋል፡፡ የሚገርመው በፕሮግራሙ ወቅት ሰማያዊ ፓርቲን በመክሰሻነት ሊቀርቡ የነበሩት ሰማያዊ ፓርቲ ቀርጾ በሚዲያ ያስተላለፋቸው ድምጾች መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ በተለያዩ ጊዜያት የሰማያዊ አመራሮች ያደረጓቸውን ንግግሮች ከኢንተርኔት ተለቅመው በመሞገቻነት ሲቀርቡ ይህኛው ግን ‹‹ለሚዲያ አይሆንም!›› ተብሏል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ፋና እንደፈለገ ቆራርጦ፣ ከፍቶ እንዳያቀርብ ሰማያዊ ሙሉውን ይለቀዋል፡፡ ከዚህ በላይ ግን ሌላም ምክንያት ነበረው፡፡ ፋናዎች ከኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ጋር በጋራ ያቀዱትን አላማ የሚያሳካ አልነበረም፡፡

በተመሳሳይ ኢቲቪ (ኢብኮ) ቅዳሜ ጥር 16/2007 ዓ.ም ጠዋት ማታ ከ2 ሰዓት ዜና በኋላ የሚቀርብ ቃለ መጠይቅ ነው ብሎ ዮናታን ጋር ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር፡፡ እሱም ቢሆን ሳያስተላልፈው ቀርቷል፡፡ ከዚህ ይልቅ በአንድ ወቅት የህዝብ ግንኙነቱ ከሌላ ጋዜጣ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ መሰረት በማድረግ (አብዛኛዎቹ ጋዜጣው ላይም የሉም) ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ህዝቡ የምርጫ ካርድ እንዳይወስድ እየቀሰቀሰ ነው፣ ምርጫውን የሚጠቀምበት አመፅ ለማንሳት ነው….›› የመሳሰሉ ክሶችን አቅርቧል፡፡

ፋና እና ኢቲቪ (ኢብኮ) ከሁለቱ አመራሮች ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ አግኝቼ እንዳዳመጥኩት ሁለቱም ‹‹ሚዲያዎች›› ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ከጥያቄዎች መካከል አብዛኛዎቹ ‹‹ሰማያዊ ምርጫውን የሚፈልገው አመፅ ለማስነሳት ነው፣ የቀለም አብዮት ማስነሳት ትፈልጋላችሁ፣ ለምርጫ ቦርድ እውቅና አትሰጡም፣ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን አትፈልጉም….›› የሚሉ ለኢህአዴግና ለምርጫ ቦርድ ክስ የሚያመቹ ክፍተቶችን ያስገኛሉ ተብለው የታሰቡ (ምን አልባትም የተቀነባበሩ) ጥያቄዎችን ናቸው፡፡ ሆኖም ሁለቱም አመራሮች የሰጡት ቃለ መጠይቅ ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ በሚፈልጉት መልክ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ሰማያዊን በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ያሳውቃል ተብሎ በኢህአዴግ አመራሮች ዘንድ ስለታሰበበትም ይመስላል በሁለቱም ሚዲያዎች እንዳይቀርብ ተደርጓል፡፡

በተለይ ‹‹ሞጋች›› የሚባለው ፕሮግራም አዘጋጅ ኢ/ር ይልቃል ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ወደሚፈልጉት ክፍፈት እንዳልገባ ሲያውቅ ‹‹ይህ አሁን የሚነግሩን ቀድሞ ስትሉት ከነበረው አቋም ይለያል፣ ተለሳለሳችሁ!›› ሲል ምን ይፈልግ እንደነበር ሳያስበውም ቢሆን ተናግሯል፡፡ ኢንጅነሩ በበኩሉ እሱም ሆነ ፓርቲው የተለየ አቋም እንዳልያዙ ብሩክ ከኢንተርኔት የወሰዳቸው ድምጾች ላይ የተነገሩት ነገሮች ምንም አይነት ስህተት እንደሌለባቸው ደግሞ ያስረግጣል፡፡ አሁንም ብሩክ ሌላ ድምጽ አሰምቶ ሰማያዊን ‹‹ህገ ወጥ›› ሊያደርግ ይሞክራል፡፡ ኢንጅነሩ ‹‹ምንም ስህተት የለበትም›› ብሎ ዳግመኛ ያስረግጣል፡፡ አቶ ብሩክ በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ በኩል ሰማያዊን ‹‹ህገ ወጥ›› የሚያሰኝ ክፍተት ለማግኘት ‹‹አገዛዝ ፈቅዶ መብት አይሰጥም›› የተባለበትን ድምጽ ሳይቀር ህገ ወጥ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ‹‹ምርጫ ቦርድን ትዘልፋላችሁ፣ ስብሰባዎችን ረግጣችሁ ትወጣላችሁ›› ይላል ብሩክ፤ ኢንጅነር ይልቃል በበኩሉ ‹‹አሁንም የሚሳሳት ከሆነ ደግመን ደጋግመን አቋርጠን እንወጣለን›› ብሎ አቋማቸውን ያስረግጣል፡፡

በአጠቃላይ ሁለቱም ሚዲያዎች ከሰማያዊ አመራሮች ጋር ያደረጓቸው ቃለ መጠይቆች ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ሰማያዊን ለመክሰስ ቀዳዳ የተፈለጉባቸው ይመስላሉ፡፡ ሆኖም አመራሮቹ ለክስ የሚመቹ ነገሮች ይልቅ ፓርቲውን የሚያስተዋውቁ መልሶችን በመስጠታቸው ጥያቄዎቹን ላወጧቸው የፓርቲ አመራሮች ኪሳራ እንደሆነ ገብቷዋልና እንዳይቀርቡ ተደርገዋል፡፡ የሁለቱ ሚዲያዎች ሆን ተብለው የተቀነባበሩ የሚመስሉ ጥያቄዎች፣ እንዲሁም ቃለ መጠይቁ ፓርቲውን መክሰስ ለሚፈልጉ አካላት የማይጠቅም በመሆኑ እንዳይተላለፍ መደረጉ አራቱ ተቋማት በጋራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የከፈቱትን ዘመቻ የሚያሳይ ነው፡፡

ሁለቱም ሚዲያዎች ከሰማያዊ አመራሮች ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ገዥውን ፓርቲና ምርጫ ቦርድን እንዳያጋልጥ ተብሎ ባይቀርብም ሁለቱም ለኢሳት እንደደረሰ ታውቋል፡፡ ከገዥው ፓርቲና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባበሩት ሁለቱ ‹‹ሚዲያዎች›› ለህዝብ እንዳይደርስ የታፈነው ድምጽ በኢሳት በኩል ለህዝብ እንደሚደርስ ይጠበቃልና ኢሳት ላይ ተከታትሎ ፍርድ መስጠት ይቻላል፡፡

aklog
Previous Story

የህወሓት ገመና ሲጋለጥ:- ሰብአዊ መብቶች ያልተከበሩበት የልማት ጎዳና ጥቅሙ ለጥቂቶች ብቻ ነው – አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

Next Story

ኡዝታዝ አቡበከር አህመድ በችሎት ዳኞችን ሞገተ

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ንብረቱ እንዲወረስ የሚደነግግ አዋጅ ቀረበ

ዮሐንስ አንበርብር በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት የመውረስ ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ 10 ዓመት ወደኃላ ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው፣ ንብረት በመንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ድንጋጌ የያዘ
Go toTop