ታላቁ እስክንድር

ከኢዮኤል ፍሰሐ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የሰው ድሃ አይደለችም። በየጊዜው ሰው ይወጣላታል። በእሷ ፍቅር የከነፉ ልጆችን ሁሌም ቢሆን አታጣም። እማማ እንደዚህ አይነት ልጆቿን አምጣ ትወልዳቸዋለች። በእርግጥ ሁላችንም ተምጠን ብንወለድም ፣ ለእሷ ራሳቸውን አሳልፈው ሊሰጧት የተዘጋጁትን ግን ከሁላችንም በከፋ ምጥ ውስጥ ትወልዳችዋለች። ለዛሬ ከእነዚህ እማማ ኢትዮጲያ በከፋ ምጥ ውስጥ ከወለደቻቸው ጀግኖች መሃል የሚመደበውን እስክንድር እንቃኛለን።

እስክንድር ነጋ ከራሱ ይልቅ የሀገሩን ጥቅም የሚያስቀድም ፣ በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋርነት የማያጠቃው ፣ ለግለሰብ ልዕልና የሚታገል ፣ ነጻነትን አጥብቆ የሚፈልግና ለዛም ዋጋ እየከፈለ የሚገኝ ታጋይ ነው። እስክንድር ፣ ላመነበት ነገር ዋጋ እንደሚከፍል በተግባር ያሳየ ሰው ነው። ‹‹ለውጥ ያለመስዋዕትነት አይገኝም። ነጻነታችንን የምንፈልገው ከሆነ ደግሞ እያንዳንዳችን ዋጋ ልንከፍል ይገባል›› ይላል። ይህ ሰው ለነጻነቱ ሲሟገት ሚስቱና ልጆቹን በስደት ተነጥቆ ስጋውን ደግሞ ቃሊቲ አድርጎ ነው። ቃሊቲ ውስጥ ሆኖም ስጋው እንጂ መንፈሱ እንዳልታሰረ በሚገባ ያስታውቃል። አርቆ አሳቢነቱ ፣ አስተዋይነቱና ከአሉታዊ ነገሮች ውስጥ እንኳ አዎንታዊ ነገሮችን የማውጣት ብቃቱ ልዩ ነው። ሰውንም በሰውነቱ ያስተናግዳል። ሁሉንም ሰው በእኩል አይን ማየት ይችላል። እስክንድር ዘንድ ዶክተር ፣ ኢንጅነር ፣ አርቲስት ፣ ጋዜጠኛ ፣ አትሌት ወዘተ…… ሁሉም እኩል ናቸው። ለራሱ መቼም ቢሆን ከፍተኛ ግምት አይሰጥም። እኔ ምን ሰራሁ? ይህ ሁላ ሙገሳ አይገባኝም የሚል ሰው ነው። የፔን አዋርድ ተሸላሚ የሆነ ጊዜ ከወዳጆቼ ጋር በመሆን «እንኳን ደስ አለህ» ለማለት ቃሊቲ በተገኘንበት ጊዜ እንኳን እንዲህ ማለቱን አስታውሳለሁ፤
‹‹እኔ ምን ሰራሁ? ይህ ሽልማት እኮ የእኔ አይደለም። በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲሰፍን እየታገሉ የሚገኙት ውጤት ነው። እኔ ብቻዬን ምንም አላደረኩም። ስለዚህ እንደራሴ ሽልማት አድርጌ አልቆጥረውም።›› ይህን ሲለን እጅግ ተገረምኩ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰው በተፈጥሮው ልዩ ና ግለሰባዊ ነው መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

እሱ እየከፈለ የሚገኘውን ዋጋ እያየሁ እኔ ምን አደረኩ? ሲልም ተደመምኩ። ይህን ሲለን የታሰረ ሰው እንኳ አይመስልም። የመንፈስ ጥንካሬው አስገራሚ ነው። መንፈሱ ከቃሊቲ ውጪ እንደሚገኝ እስክንድርን ቃሊቲ ተገኝቶ የጠየቀው ሁሉ ይመሰክራል። ስጋውም ቢሆን አልተጎዳም። እስኬው ፤ ከጥሩ ተነጋሪነቱ ባሻገር ጥሩ አድማጭም ጭምር ነው። የሰውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትንም ያከብራል።
ትህትናው ደግሞ ልዩ ነው።

‹‹እስክንድር ማለት ቤተ-መጻሕፍት ነው።›› ስትል ባለቤቱ ሠርካለም ፋሲል የተናገረችው እውነት እንደሆነም መመስከር እችላለሁ። አዎ! እስክንድር ቤተ-መጻሕፍት ነው። ምን ያህል እውቀት እንዳለው ጠጋ ብላችሁ ስታናግሩት ታውቃላችሁ። እውቀቱን ለማካፈል ባለመሳሳቱ ደግሞ እውነተኛ ምሁር ብዬ እንድጠራው እገደዳለሁ። በአጭር ደቂቃዎች እንኳ ከእስክንድር አንደበት ብዙ ቁም ነገሮችን ቀስሞ መመለስ ይቻላል። ይህ ደግሞ የእስኬውን የእውቀት መጠን በሚገባ ያሳያል። እስኬው ቃሊቲ መሆኑ ክፉኛ ያበሳጫል። ከቃሊቲ ውጪ ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገሮችን መስራት ይችላል። ገዢዎቻችንም ይህን ስለተረዱ ክስ መስርተውበት 18 አመት ፅኑ እስራት በይነውበታል። ይህን በሚመለከት ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወጋ ‹‹የእስክንድርን እስር የአንድ ግለሰብ እስር አድርጌ ለመቀበል ይከብደኛል። እስክንድር እኮ የኢትዮጲያ ሪሶርስ ነው። ኢትዮጲያ አንድ ትልቅ ሪሶርስ አታለች። ይህ ሪሶርስ ቃሊቲ መቀመጥ የለበትም። ከቃሊቲ መውጣት አለበት።›› ነበር ያለኝ፡፡ ስለ እስክንድር ይህን ሁላ ብዬ ስለ ጽናቱ ሳላነሳ ባልፍ የእስክንድርን ትልቁንና ዋናውን ጠንካራ ጎን መሳት ይሆናል። እስክንድር ጽናቱ እጅግ ያስደምማል። ጽናቱ የት ድረስ እንደሆነ የሚገልጹ አንድ ሁለት ነገሮችን ላንሳላችሁ።

እስክንድር ፣ ናፍቆት የሚባል ብቸኛ ልጅ አለው። ናፍቆት የተወለደው ምርጫ 97ትን ተከትሎ እሱና ባለቤቱ ለእስር በተዳረጉበት 1998 ዓ.ም ላይ ነው። የናፍቆት የትውልድ ቦታ ደግሞ ቃሊቲ እስር ቤት ነው። ባለቤቱ ሠርካለም ናፍቆትን የተገላገለችው በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ በሚገኝ ክሊኒክ ነው። እስክንድር ከእስር አስኪፈታ ማለትም እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ልጁን አላየውም። ከዚህ በመነሳትም ልጁን ናፍቆት ሲል ሰየመው። እስክንድር እንዲህ የሚወደውን ልጁን ለስምንተኛ ጊዜ ለእስር በበቃበት ማለትም በ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም ላይ በድጋሚ ተለየው። በወቅቱ ናፍቆትን ከትምህርት ቤት በማውጣት ላይ የነበረው እስክንድር ፣ በፖሊሶች ቁጥጥር ስር ሲውል ልጁ ናፍቆት አብሮት ነበረ። ፖሊሶቹ ናፍቆትን ከአባቱ በመለየት አባቱን ይዘውት ሄዱ። ይህን ሲያስተውል የነበረው ናፍቆት ክፉኛ ተረብሾ ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሥለምን ወያኔን ከሥር መንቀል ያስፈልጋል? ሰማዕታት ሲታሰቡ (ከሥርጉተ ሥላሴ)

እስክንድር በእንዲህ መልኩ ከልጁ ከተነጠለ በኋላ ልጁን የሚያገኘው በቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ ነው። ናፍቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ ስነልቦናው በጣም እየተጎዳ ሲመጣ እስክንድርና ባለቤቱ ሠርካለም በአንድ ነገር ላይ መከሩ። ይህም ልጃቸው አዲስ ከባቢ እንደሚያስፈልገው ነው። በዚህ መሠረትም ሠርካለምና ናፍቆት እስክንድርን በመሰናበት ወደ አሜሪካ አቀኑ። ይህ ውሳኔያቸው ምንኛ ከባድ እንደነበር ሠርካለም ለስደት በተዳረጉበት ጊዜ ፤ በአንድ መጽሄት ላይ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያለፈችባቸውን ውጣ ውረዶች ጽፋ ለንባብ ማብቃቷን አስታውሳለሁ። ይህን ጽሁፍ ካነበብኩ በኋላ ቃሊቲ በማምራት

እስክንድርን አገኘሁት። እሱና ሠርካለም ስላሳለፉት ውሳኔ ስጠይቀውም እንዲህ አለኝ፡-
‹‹ለናፍቆት በማሰብ ያደረግነው ነው። እዚህ ሲመጣ የመረበሽ ስሜት አስተውልበት ነበር። ከዛም በተጨማሪ በትምህርት ቤት ውስጥ ከሌሎች ልጆች የመነጠልና የብቸኝነት ስሜት ይታይበት ስለነበር ከባቢ መቀየር የተሻለ ሆኖ ስላገኘነው በጋራ መክረን የደረስንበት ውሳኔ ነው።››
‹‹ባለቤትህንና ልጅህን አንተ እዚህ ሆነህ በስደት መነጠቅህ አይከብድም ወይ?›› አልኩት

እሱም፡-‹‹ባለቤቴንና ልጆቼን በእጅጉ እናፍቃቸዋለሁ። ከእነሱ መነጠሌ ክፉኛ ጎድቶኛል። ግን ይህ መስዋትነት መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ነው። እነ ናፍቆት ዴሞክራሲያዊ ስርአት በተገነባባት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አለባቸው። ለእዚህ ደግሞ መስዋትነቱን መክፈል ያለብኝ እኔ ነኝ።›› ሲል መለሰልኝ፡፡

የተናገረው ንግግሩ የእስክንድር ጽናት ምን ደረጃ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። እንዲህ አይነቱ ጽናት ያላቸው ሰዎች ፣ እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ከእነዛ ጥቂቶች መሀል ደግሞ አንዱ ታላቁ እስክንድር ነው።

የእስክንድርና ጽናት የሚያሳይ አንድ ሌላ ነገር ጨምሬ ጽሁፌን ልቋጭ። በአንድ ወቅት እስክንድርን እየፈራሁና እየተባሁ እንዲህ የሚል ጥያቄ አነሳሁለት። ‹‹እስክንድር ፣ይቅርታ ጠይቀህ የመውጣት ሀሳብ የለህም ወይ?›› (ይህን ጥያቄ ያነሳሁለት የእስክንድር ምላሽ ጠፍቶኝ ሳይሆን የእስክንድር እዛ መሆን ስለሚያበሳጨኝ ነው።)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ 2011 ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዛ ዘመነ ሄሮድስ ደረሰች! - ነፃነት ዘለቀ

እንዲህ በማለት ለጥያቄዬ ምላሹን አስከተለ፡- ‹‹የኢህአዴግን መንግስት አይደለም ይቅርታ ይቅርና አመክሮ አልጠይቀውም። 18 አመት አይደል የፈረደብኝ እሷኑ 18 አመት ጠጥቼያት እወጣለሁ እንጂ እንዲህ አይነት ነገርን በጭራሽ አላስብም።››

ይህ ምላሹ የእስክንድር የአእምሮ ጥንካሬና ጽናት ምን ድረስ እንደሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል። እንዲህ አይነት ጽናት ከየት እንደሚገኝ ግን አላውቅም። እንደ ታላቁ እስክንድር ለመሆን እንዲህ አይነት ጽናትና የአእምሮ ጥንካሬ ግድ ይላል። ኢትዮጵያ ብዙ ታላቁ እስክንድሮችን ትሻለች። እስከዛው ግን በአንዱና ቃሊቲ በሚገኘው ታላቁ እስክንድሯ አንገቷን አትደፋም!

Share