ስለደፈራ፤ ደፈር ብለን ስናወራ (በእውቀቱ ስዩም)

ኣስገደዶ መድፈር በእንስሳት በኣሶች እንዲሁም በነፍሳት ኣለም ውስጥም ይስተዋላል፡፡ይልቁንም ለሰው እሩብ ጉዳይ በሆኑ ዝንጀሮዎች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ተፈጥሮ በደፋሪነት ያጨቻቸው ባብዛኛው ወንዶችን ቢሆንም ሞገደኛ እንስቶችም ኣልጠፉም፡፡ለምሳሌ ወንዱ ንብ ከሴቷ ጋር ሲሳረር ሴቲቱ በዚያ ነገር ቆልፋ ትይዝበታለች፡፡በጦዘ ስሜት ውስጥ ሆና ኣልመዝምዛ ትቆርጥበታለች፡፡ወይም በጅንኖች ኣባቶቻችን ኣነጋገር ትሰልበዋለች፡፡ኮርማው ንብ በጀንደረባነት የመቀጠል እድል የለውም፡፡ በደረሰበት ጥቃት ያልጋ ቁራኛ ማለቴ የቀፎ ቁራኛ ሆኖ ይሞታል፡፡ሰራተኛ ንቦች ኣስከሬኑን ከቀፎው ጠርገው ወደ ውጭ ይጥሉታል፡፡

ኣብሬሽ ኣድሬ ሲነጋ ልሙት
ላፈር ኣይደለም ወይ የተፈጠርኩት

የሚለው የሙሉቀን መለሰ ዘፈን የኮርማ ንቦችን ህይወት በደንብ ይገልጣል፡፡ ኣስገደዶ መድፈር ባገራችን ትልቅ ጣጣ ሆኖ ይቆያል፡፡ምክንያቱም ወደ ጣጣው የሚያደርሱ ብዙ መንገዶች ኣሉ፡፡ ሲጀምር መናጢ ደሃ ነን። ሀብትና ስልጣኔ ባላቸው ሃገሮች የሴት ልጅን ዳሌ ላመል ያክል ነካ ካደረግህ ኣዳርህ ዘብጥያ ነው፡፡ኣገራችን ኢትዮጵያ ግን ቺስታ ናት ፡፡ያንድን ልጃገረድ መቀመጫ የሚጠብቅ የፖሊስ ግብረሃይል ማሰማራት የሚያስችል ሃቅም የላትም፡፡ሃቅም እንኳ ቢኖራት ባህሉ የላትም፡፡ የቤተመንግስቱን በር እንጂ ያንድን ሴት ገላ መጠበቅን እንደ ብሄራዊ ግዴታ የሚቆጥር ፖሊስ የለም፡፡

ባገራችን በዋናነት የሃብት ምንጭ ጉልበትና ህገወጥነት ነው፡፡ይባስ ብሎ፡ ባገሪቱ ውስጥ ያለው ሀብት ባብዛኛው በገልቱ ወንዶች እጅ ነው፡፡እኒህ ዲታ ወንዶች ድሃ ሴቶች ላይ ያሻቸውን ለማድረግ ኣቅም ኣላቸው፡፡ከሳሾችን ጸጥ የማሰኘት ጉልበት ኣላቸው፡፡የሀና ገዳዮች የተጋለጡት ወንጀላቸውን የሚሸሽጉበት ሃቅም ስለሌላቸው እንጅ እመቤት ፍትህ ፈጥኖ ደራሽ ስለሆነች ኣይደለም፡፡ተጠቅተው ያለ ኣለኝታ የቀሩትን ምኝታ ቤት ይቁጠራቸው፡፡

ሲቀጥል፤የትምርት ስርኣታችን ወንድ ኣንግስ ነው፡፡ሴት ልጅ የራሷ ነጻ ፍቃድ ያላት ፍጡር መሆኗን እያስረዳ የሚያንጽ የትምርት ስርአት የለንም፡፡ውጤቱ በእለት ተእለት ኣስተሳሰባችን ውስጥ ይታያል፡፡ብዙዎቻችን ሴቶችን” ሚስት እናት ገረድ” ከተባሉት መደቦች ባሻገር አናስባቸውም፡፡ኣዲስ ኣበባ ውስጥ ሴቶች ለሚይዟቸው መኪናዎች የሚሰጡ ስሞችን ኣስታውስ፡፡ኣንዷ መኪና” በእምሴ” ትባላለች፡፡ሴት በላቧ፤ጥራ ቆጥባ እቁብ ጥላ መኪና ልትገዛ ኣትችልም ከሚል ኣስተሳሰብ የመነጨ ስያሜን ነው፡፡
ኣንድ እውንተኛ ታሪክ እዚህ ላይ ላንሳ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በየቀኑ ከመሞት አንዴ መሞት አይሻልም ? ? (ከሎሚ ተራ፤)

ባገራችን መሚገኙ ከተሞች ባንዱ ውስጥ(ካርበኞች ጋር ኣላስፈላጊ ሙግት ውስጥ ላለመግባት የቦታውን ስም ዘልየዋለሁ)ኣንዲት ልጃገረድ በሰባት ጎረምሶች በፈረቃ ተደፈረች፡፡ይግረማችሁና ተኣምር በሚያሰኝ መንገድ ተረፈች፡፡ከህመሟ ኣገግማ መንቀሳቀስ ስትጀምር ግን ነዋሪዉ ኣለኝታነቱን ነፈጋት፡ኣንድ ቀን ከተማሪ ቤት ስትመለስ” ሰባት ጎራሽ” የሚል ስም ተወረወረባት፡፡ኣዲሱ ስሟ ከደፋሪዎች ይልቅ ተደፋሪዋን ባለጌ ኣድርጎ የሚያሳይ ነበር፡፡ቀስ በቀስ” ሰባት ጎራሽ” የሚለው ስም እንደ ተስቦ ተዛመተ፡፡ልጂቱ የሰባቱን ወንዶች ደፈራ መቋቋም ችላ ነበር፡፡ህብረተሰብ ተረባርቦ ሲደፍራት ግን ብርክ ያዛት፡፡ከእለታት ባንዱቀን ኣገር ለቅቃ ተሰደደች፡፡

አስገድዶ መድፈር ዋና መንስኤ የብልግና ፊልሞች መስፋፋት መሆኑን ገልጸው በፊልሞች ስርጭት ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚሰብኩ ኣሉ፡፡ይህን ምክር መቀበል አለመቀበል ስለሰው ተፈጥሮ ባለን አመለካከት ላይ የተመሰረተ ይመስለኛል፡፡ ሲመስለኝ፤ሰው ምናብ የሚባል ነገር ይዞ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ የብልግና ስእል ይፈጥራል፡፡የሆሊውድ ጠረን ከማይደርስበት እልም ያለ ገጠር ውስጥ ልጆች እንካስላንትያ ሲጫወቱ የሚያወጡት ብልግና እግዚኦ የሚያሰኝ ነው፡፡እኔና ኣብሮ ኣደጎቼ በልጅነታችን ሁለት ብልት ስላለው የቆሎ ተማሪ የሰማነው ተረት ከ ፕሌይ ቦይ መጽሄት የተቀዳ ኣልነበረም፡፡

በጥንታዊ የውትድርና ስርኣት ውስጥ ከመደበኛው ወታደር የተለየ፡ ሳይታዘዝ የሚዘምት የሰራዊት ዘርፍ ነበር፡፡ፋኖ ይባላል፡፡ዲሲፒሊን የማያውቅ ሀላፊነት የማይሰማው ከየት መጀመርና የት ላይ ማቆም እንዳለበት የማያውቅ ስድ ነው፡፡የሰው ኣእምሮም እንዲሁ ፋኖ ሀሳብ ያዘምታል፡፡ፋንታሲ ይሉታል ሳይኮሊጂስቶች፡፡ የብልግና ፊልሞችን ድርሰቶች የፋኖ ሀሳባችን ነጸብራቅ ናቸው፡፡ወደድንም ጠላንም ሰው የሚባለው ጣጠኛ ፍጡር እስካለ ድረስ ይኖራሉ፡፡ስለዚህ ሰዎች የሚያስቡትን ሁሉ ለማደረግ እንዳይሞክሩ ማሰልጠን እንጂ ሀሳባቸውን እንድያስወግዱ ማድረግ የሚቻል ኣይመስለኝም፡፡

ባንድ ወቅት በኣምስተርዳም ከማስረሻ ማሞ ጋር ስዞር የሰው ሰራሽ- ብልት መሸጫ ሱቅ ተመለከትሁ፡፡የመጀመርያው ስሜቴ ጉደኛው እግሬ ምን ኣይነት ቅሌታም ኣገር ላይ ጣለኝ የሚል ነበር፡፡ እየቆየሁ ሳስበው ሃሳቤን ለወጥሁ፡፡ባንድ ኣገር ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ የሩካቤ ስሜት ኣላቸው፡፡ግን ሁሉም ወንድ ሴት የመጥበስ እድል የለውም፡፡ሁሏም ሴት በወንድ ደረት ላይ የመተኛት እድል ላይገጥማት ይችላል፡፡ዋናው እስኪገኝ ድረስ ባምሳሉ ከማዝገም ውጭ ምን ኣማራጭ ኣለ፡፡የተጠሙ ሰዎች እምቢባዮችን ኣስገደደው ለመርካት እንዳይነሳሱ ማገጃ ዘዴ ይሆን?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትግራይ ህዝብ የወያኔ ስርአት ተጠቃሚነው! (አንዷለም አስራት )

ባገራችን ብቸኛው የስነምግባር ምንጭ ሃይማኖት ነው፡፡የእምነትን በጎ ገጽ ግለሰቦችን ለመግራት ኣስፈላጊ ነው፡፡ያም ሆኖ ለእምነት ሃይሎች ያለን የተጋነነ ኣመኔታ የማታ የማታ ዋጋ የሚያስከፍለን ይመስለኛል፡፡ለምን? ምክንያቱ ግልጥ ነው፡፡የሃይማኖት ኣባቶች የመኖራቸውን ያክል የሃይማኖት እበቶችም በየቦታው ኣሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ኣንድ ሁለት ተምሳሌቶችን ጠቅሼ ዞር ልበል፡፡

የመከራ ቀንበሩን ያቅልለትና ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ቆይታዎቹ ባንዱ ከሁለት ሽሜ እስረኞች ጋር ተገጣጥሞ ነበር፣ የመጀመርያው ስድስት ኣመት ህጻን የደፈሩ ሼህ ሲሆኑ፡ ሁለተኛው ብልታቸውን ማር በመቀባት ህጻናትን ሲያጠቡ የተገኙ መርጌታ ናቸው፡፡የመርጌታን ስልት የፈረንሳዩ ወፈፌ ማርኬስ ደ ሳድ እንኳ የደረሰበት አልመሰለኝም፡፡
ኣዲስ ጉዳይ መጽሄት ባንድ ወቅት በወንጀል ኣምዱ ኣንድ ታሪክ ኣስነብቦ ነበር፡፡ታሪኩን ኣሳጥሬ ስተርከው የሚከተለውን ይመስላል፡፡ሰውየው ፓሰተር ነኝ ብሎ ካንድ ቤተሰብ ጋር ይተዋወቃል፡፡ጥቂት ሳይቆይ ከመላው ቤተሰብ መካከል ልጃገረዶቹን መርጦ ጸለየላቸው፡፡ ከዚያም ሶፍት ዌር ይመስል እጄን ካልጫንኩባችሁ ኣላቸው፡፡ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ የሰራ ኣከላቱን ጫነባቸው፡፡ፖሊስ ጫኝና ኣውራጁን ፓስተር በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ከተደፈሩት ሴቶች መካከል ኣንዷ ራሷን ሰቅላ ነበር፡፡

በመጨረሻም

በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ምክር የማያለዝባቸው፣ ትምርት የማይቀይራቸው ጉዶች ይኖራሉ፡፡የተሻለው መንገድ ልጆቻችንን የኒህ ጉዶች ሙርጥ የማይደርስበት ቦታ ላይ መቀመጣቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ወላጅ የማያንቀላፋ የልጆቹ እረኛ መሆን ግዴታው ነው፡፡

8 Comments

  1. Beweketu seyuem.if you have the gut write about weyane who rape displace and kill thousands.

  2. በ እውቀቱ በጣም ከማከብርህና የማደንቅህ የዘመኑ ጸሀፊ ! በጽሁፎቸህና በግጥሞችህ ግዝፈት አንጻር ሲለካ ይህ ጽሁፍ እጅግ የወረደ ነው !! ብዙ ህዝብ የሚብሰለሰልበትና የሚሰቀጥጠውን ይህ ድርጊት በዚህ ጽሁፍህ የተሳልቅህበት ይመስላል ። ኮስተር ብታደርገው ነበር የሚሻለው ።በ አንዳንድ ቃላቶችህማ ያን ቅሌታም ስብሀትን ነው መሰልከኝ በጣም ብዙ ብዙ አክባሪና አድማጭ እንዳለህ አትዘንጋ ! አድናቂህ ነኝና! ለትችት አይደለም

    • መጽሐፉ “ቁላው የተቀጠቀጠ፣ብልቱ የተቆረጠ፣ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ” ይላል።ምነው ወዳጄ እግዚአብሔር ከአፈር ጪቃ በእጁ አጨማልቆ የሰራውን የሰውን ሰውነት አካል በስሙ ብንጣራው ምንድነው ጥፋቱ?የእውቀቱ ስዩም ጽሁፍ እጅግ የወረደ ነው ስትል ማስረጃ ብተሰጠን መልካም ይሆን ነበር።ዓይን ጨፍኖ ቦክስ ቢሰነዝሩት የሚመቱትን አያውቁትምና መልሶ እራስንም መጉዳት አለ።ከእውቀትና ከማስተዋል የሸሸ ትችት ማደሪያው አደንቋሪ ባሕል በረት ሆኖ ከአዛባው ጋር መሰንበት ነው።
      “ብዙ ሕዝብ የሚብሰለሰልበታና የሚሰቀጥጠውን” ስትል ይህ ሕዝብ የት ነው ቆጥረህ ጥናት ያደረክበት? ብዙ ስንት ሚሊዮን? ምናልባትም ብልግናነው እንዲህ አይባልም፣መባል ያለበት እንዲህ ነው፣የምትሉን ደረጃ መዳቢዎቻችን፣ኪሳራችሁን አላስተዋላችሁም።በኢትዮጵያችን የሴት ዳሌ ገበያ በአደባባይ በደራበት አገር፣በእዚህም ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በኤይድ በሺታ በአለቁበት አገር፣የብልግናው መስፈርት ምንድነው ነው? በተግባር አገር የጨረሰ ወሲብ፣እውቀቱ በጻፈው እጅግ የወረደ ነው ምን አምጣው?ኮስተር ብታደርገው ብሎ ነገር የእውቀቱን ጽሑፍ አርመው ካላሳዩን አንደበቶን ቢሸበሽቡ መልካም ነው።ይህን ተናገሩ፣ይህን አትናገሩ፣እንዲህ ይባላል፣እንዲህ አይባልም፣ሌላው የነፃነት ማነቆ ይሆን?

  3. I agree with most of the point u have raised, but yet, still I can see how ur Ethist sub councious is also struggling to over flow , to try to defy the role of Religion. Etc . I know where ur courage if Criticising religion come from rather than the act three “Ebetoch” . In the first instance, You are over inflated by the public moral support and became the fun of the fascist books like the Davinchi code. That is the driving engine behind ur article.if you are the a responsible Author you will write about thousands of TPLF cadres who murdered and rape across Ethiopia including Ogadean.rapist like Serawit Fikrea, ante limatawi Tsehafi neh. ” Bezuwochu bafnakotina bechibcheba yitefalu. Yihin yetenefegut gin le wuteat yibekalu ” endetebalew.

  4. ምጽሐፉ እንዲህ ይላል “ድንግል ስለመሆኗ የሚያስረዳ ነገር ባይኖር፣ወደ አባቷ ቤት ደጃፍ ይውሰዷት፣በዚያም እርስዋ የምትኖርበት ከተማ ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሏት”” ይህ ጥንት፣ድሮ ነበር።ዛሬ ስሙ ተሻሽሎ አስገድዶ መድፈር ተብሏል።አረመኔነቱ ግን አልተለወጠም።የመጽሐፉም ቃል አልተፋቀም።ሰባኪዎቹም በገደምዳማ ወንጀሉን ቢሰብኩት የእንጀራ ነገር ሆኖ ነው።እውነትማ ከጌታ ጋር እንደተሰቀለ አልወረደም።

    በ፩፱፰፰ የኒዉ ዮርክ ታይም ጋዜጣ መዘገበው እንዳሉት ጋንጋ የምትባል አንዲት የሒንዱ ሴት በአምስት ዓመት ባሏ ክፉኛ በመደብደቧ ከትዳሯ ትኮበልላለች።ይህ በሆነ ማግስት አምስት መቶ የሚሆን ሕዝብ በወ/ሮ ጋንጋ መንደር ሜዳ ላይ ተሰብስቦ ከባልዮም፣ከዘመዶቹም፣ ከእሷም እሰጥ አገባ ያዳምጡ ጀመር።ከሳሿ ጋንጋ ክሷን ስትጀምር የባሏ አባትና አጎት አስገድደው ሊደፍሯት እንደሞከሩ ስትገልጥ አንባጓሮ ተጀመረ።በስድብ የተቀጣጠለው ነገር፣ወደ ዱላ፣ያም ወደ መፈነካከት፣ሰፈሩም ወደ መለስተኛ ጦርነት ተለውጦ ብዙዎች እራሳችውን ስተው ወደቁ። በከፍተኛ የፖሊስ ኃይል ጣልቃ ገብነት ለጊዜው ሁኔታ ጋብ ቢልም፣የችግሩ መንስኤ ግን ሴት የጫረችው እሳት ተብሎ ተደመደመ።
    ይህ መሰሉ በእህቶቻችን ላይ የሚፈጸመው ወንጀል በእኛ ምኞት ብቻ ብን ብሎ የሚጠፋ አይደለም።ስር ከሰደደ ድህነት፣ቅጥ ካጣ የአስተዳደር ስርዓት፣ አገር ከሙሁር አልባነት፣ከሚፈጠሩ ችግሮች አካል ነው።ሥርነቀል የፖለቲካ፣የኤኮኖሚ፣የአስተሳሰብ ለውጥ ካልመጣ “ምን አለ ሴቶች ቢበዱበት” የሚለው ጅል ቢበዛ አይገርምም።

Comments are closed.

Share