September 26, 2014
10 mins read

የትዉልድ አተላዎች ከመሆን ይሰዉረን –  ናኦሚን በጋሻው

ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የሟቹ የመለስ ዜናዊ ሰላባ ከሆኑት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች መካከል አንዱ ነበሩ። ከ19 ዘጠኝ አመታት በፊት፣ በኩወቤክ ካናዳ የቀድሞ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስተር ጆን ክሬቲየን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ በስክቶላንድ የአሁኑ የእንግሊዘ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዴቪድ ካሜሮን ፣ የአገራቸውን አንድነት ለማስጠበቅ፣ ክዌቤክና ስኮትላንድ እንዳይገነጠሉ ብዙ የደከሙ፣ የድካማቸውን ፍሬ ያዩ አገራቸዉን እና ህዝባቸውን  የሚወዱ መሪዎች መሆናቸውን ያስመሰከሩ ናቸው።

ሟቹ መለስ ዜናዊ ግን ፣ ከጉዳዩ ባለቤቶች  ከኤርትራዊያን በላይ የኤርትራ መገንጠል ዋና አዝማች ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ፣ ኢትዮጵያን ባህር አልባ ያደረጉ፣ ወንድምን ከወንድም የለያዩ ሰው ነበሩ።

ከዚያም የተነሳ ለጅቡቲ ኢትዮጵያ 700 ሚሊዮን ዶላር በአመት  ለወደቡ መጠቀሚያ እንድትከፍል ተደርጋለች። 700 ሚሊዮን  ዶላር፣  የአዲስ አበባ የመለስተኛ ባቡር እንዲሁም ከሰበታ ሜኤሶን ያለውን የባብሩ መስመር ለመገንባት የሚያሰፈልገው ሙሉ ወጭን ይሸፍን ነበር (ከማንም ብድር ሳንበደር) ። ለጅቡቲ በየአመቱ የሚከፈለው ፣ በስድስት አመት ዉስጥ የአባይን ግድብ ወጭ ሙሉ ለሙሉ ይዘጋ ነበር።

በወቅቱ፣   መለስ ዜናዊ «ስዊዘርላንድም ያለ ወደብ አድጋለች። ሶማሊያ ደግሞ ወደብ ሞልቷት አላደገችም።  ለእድገት ወደብ አያስፈልግም»  እያሉ ሲፎክሩ ፣ ፕሮፌሰር አስራት ፣ በዋናነት ኢትዮጵያ ባህር አልባ መሆን እንደሌለባት፣ የኤርትራ ህዝብ ወንድም ህዝብ እንደሆነ በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲከራከሩና ሲሟገቱ የነበሩ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ። አገራችንንም ለምንወድ  ኢትዮጵያዊ ሁሉ አባት ! (በነገራችን ላይ ያኔ ከመለስ ጎን የነበሩ እንደ አቶ ገብሩ አስራት ያሉ በርካታ የቀድሞ የሕወሃት ባለስልጣናት የፕሮፌሰር አስራትን አቋም ይዘው፣ አሁን ለኢትዮጵያ ወደብ እንደሚያስፈልጋት መከራከራቸው፣ የፕሮፌሰሩ ሐሳብ በሕወሃቶችም ዘንድ እያሸነፈ መምጣቱን አመላካች ነው)

መለስ ዜናዊ በአካል ቢሞቱም ፣ አሁንም ዳግማዊ መለስ ዜናዊው ኅያለማርያም ፣ ሕሊናቸዉን፣  ክብራቸውን፣ ማስትሬት ያገኙበትን እውቀታቸዉን ፣ የክርስትና እምነታቸዉን ጥለው፣ የጥቂት ሕውሃት ማፊያዎች ሮቦት በመሆን፣ የመለስ ጸረ-ኢትዮጵያዊ፣ ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ዲሞክራሲያዊ አሰራሮችና ጎጂ ፖሊሲዎች እያስቀጠሉ ነው።  መለስ ቢሞቱም የመለስ መንፈስ በሃይለማሪያም ዉስጥ አድሮ ሕዝብን እያሸበረ ነው።

ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለአገራቸው ኢትዮጵያ ደማቸውን ያፈሰሱ፣  ሰማእት ሆነው ያለፉ ትልቅና የተከበሩ ሰው ነበሩ። መለስ ዜናዊ አሰቃይተው ነው የገደሏቸው። ፕሮፌሰር አስራት ያኔ እንደሞቱት አሁንም ብዙዎች እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው። ብዙዎች እየታሰሩ ነው። ብዙዎች እየተሰደዱ ነው። ብዙዎች የሚኖሩበት አካባቢ በጥቂት ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ባላቸው  ኢንቨስተሮች ስለተፈለገ ብቻ በጭካኔ ከቅያቸው እየተፈናቀሉ ነው። ሰቆቃና መከራ በዛ። በርግጥ ይህን የመለስን መንፈስ ከመዋጋትና ከመታገል ዉጭ ሌላ አማራጭ ሊኖር አይችልም።

አንዳንዶች በሌላው ላይ የሚደርሰው ግፍ ሳይሰማቸው፣ ከአገዛዙ ትናንሽ ፍርፋሪ ጥቅም ስላገኙ ብቻ፣ ዝምታን የመረጡ ወይንም የአገዛዙ አቀንቃኝ ሆነው የሚሯሯጡ እንዳሉ እናያለን። «የተሰሩ ብዙ የልማት ስራዎች አሉ» ይሉናል። «እንዴት ይሄ ሁሉ ፎቅ፣ ይሄ ሁን መንገድ ተሰርቶ ኢሕአዴግን ትቃወማላችሁ ? » ይሉናል።  «መንገዱን፣ ልማቱን እንደግፋለን። ግን የልማቱ ተጠቃሚ ጥቂቶች ሳይሆኑ ሁሉም ይሁን። በሚሰሩ ፎቆች ደስ ብሎናል፤ ግን የጀነራሎች ፎቅ ብቻ ሳይሆን ሌላውም የሚኖርበት ይሁን» እንላቸዋለን። ስናክልም « ሰው ያለነጻነቱ ምንድን ነው? እንደተባለው፣ መንገድ ተሰርቶ፣ ፎቅ ተገንብቶ፣  የኛ መኖሪያ ወህኒ ከሆነ ፣ ነጻነታችንና ልእልናችን ከተደፈረ፣ ፎቁና ሰገነቱ ለኛ ምናችን ነው ? » ብለን እንጠይቃቸዋለን።

ፕሮፌሰር አስራት ከ22 አመታት በፊት በደብረ ብርሃን  አደባባይ ካደረጉት ንግግር የሚከተለውን ቀንጭብ አድርጌ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፡

«የአባቶቻችንን የሚያኮራ ታሪክ በማስደፈርም ሆነ ባለማስደፈር በውርደትም ሆነ በኩራት ለማስረከብ ባለብን የዜግነት ግዴታ አንፃር በአሁኑ ጊዜ በታሪክ ፊት ተጋልጠን የምንገኝበትን እንደገና ላስታውሳችሁ እገደዳለሁ፡፡ በጠላት ወረራ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ በ3 ተከፍሎ እንደነበር አስታውሱ። አንደኛው ወገን ውርደትን በመጥላት በነፃነቱና ለክብሩ ሲል ቤት ንብረቱን ትቶ ወደ አርበኝነቱ በመግባት፣ የዱር ገደሉን ኑሮ በመጀመር፣ ታሪክ ሠርቶ ያለፈና የኖረ፣ ሁለተኛው አገር ሲረጋ እመለሳለሁ ብሎ ሕይወቱን ለማዳን ሲል የተሰደደ፣ ሦስተኛው ለሆዱ አድሮ የጠላት መሳሪያ በመሆን ወገኑን ከሚጨፈጭፈው የኢጣሊያ ጦር ጋር ያበረ ነበር፡፡
ሆዱን ለመሙላትና የማይቀረውን ሞት ለጊዜው ለማዘግየት ሲል የውርደትን መንገድ የመረጠው በትዝብት ውስጥ ወደቀ እንጂ የኢትዮጵያ አርበኞች ድል አድራጊነት አልቀረም፡፡
ለሀገሩና ለወገኑ ክብርና ደህንነት ደረቱን ለጥይት በመስጠት የቆረጠው አርበኛም ያለቀኑ አልወደቀም፣ አልሞተም እንዲያውም ከተፈጥሮ ሞቱ በኋላም ቢሆን በታሪክ ውሰጥ እየኖረና ኢትዮጵያንም በታሪክ እያኖረ ነው፡፡
ወገኑን የከዳውና ለሆዱ ያደረው ባንዳም ከውርደት በቀር ትረፍ ሕይወትና ትርፍ ኑሮ አልኖረም፡፡ ዛሬም እንደነዚህ ያሉ የሕዝብ ጠላቶች ለማንም የማይበጁ ማንኛውንም የሀገርና የወገን ጉዳይ ለጥቃቅን ጥቅማቸው የሚሸጡ፣ የትውልድ አተላ ስለሆኑ እግዚአብሔር በቸርነቱና በኃይሉ ቀናውን አስተሳሰብ እንዲሰጣቸው እየተመኘን ይህን ከመሰለው የትውልድና የታሪክ አተላነት የሚላቀቁበትን ልብ ለማግኘት በቂ ጊዜ ስላላቸው ማሰብና ደጋግመው ማሰላሰል ከዚያም ስለአቋማቸው መወሰን የኖርባቸዋል፡»

ፕሮፌሰሩ  እንዳሉት ለመብታችን እና ለነጻነታችን የምንቆም ያድርገን። የትዉልድ አተላዎች ከመሆንም ይሰዉረን !

 

 

 

1 Comment

  1. Ene yemigermegn eritrea beyetgnaw zemen new ye ethio akal hona yemtawkew? Ya Tdar begdun? yetornet gize? Ethio gena leraswa and mehon alchalechim be ethiopiayawinetu yemayamn tigre:oromo sumalie yalebt ager endet bihon new yale meretachihu wede semen yemtangatitut.lenegeru yeflegachihut bahr new kfel tetekembet beterefe wendm eht hizb atbelu ewnet ennegager ketebale ethio ertran tmeslalech weys somalian? Ena profesor meta meles hede ye ertra neger be ertrawyan tejemro bertrawyan alkual!

Comments are closed.

Previous Story

የ13 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የመኪና አደጋ የሹፌሩ መሞት ማጣራቱን ያጓትተዋል ተባለ

Next Story

ጋዜጠኛ ውብሸት መንግስት ለተሰደዱ ጋዜጠኞች ዋስትና እሰጣለሁ ማለቱ ማታለያ መሆኑን ተናገረ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop