April 26, 2014
20 mins read

ሰልፍና ሰደፍ፤ ዘመቻ ነቀምትና ዘመቻ ኢትዮጵያ – ከተክለሚካኤል አበበ

(ተክለሚካኤል አበበ)
ሰልፍና ሰደፍ፤ ዘመቻ ነቀምትና ዘመቻ ኢትዮጵያ - ከተክለሚካኤል አበበ 1
፩- የሲያትሉ ባተሌ ወዳጄ ደውሎ፤ “አንድነት የአዲስ አበባውን ሰልፍ ፈቃድ ተከልክሏል፡፡ ስለዚህ ምን ርምጃ ይውሰድ” በሚል ጥያቄ ሲያደርቀኝ ነበር፡፡ ሳንግባባ ተለያየን፡፡ ከሞላ ጎደል እሱ የሚለው፤ “ቢከለከሉም ገፍተው ይውጡ፡፡ ምክንያቱም፤ በተከለከሉ ቁጥር እሺ ብለው የሚገቡ ከሆነ፤ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣሉ፡፡ ገፍተው ከወጡ ግን፤ መንግስትም ጨክኖ ርምጃ አይወስድም፤ ቢወስድም ግን፤ ትግሉን ያበረታል፤ ሌሎችንን ይቀሰቅሳሉ” ነው፡፡ ኢፍትሀዊ ህግን መጋፈጥ ፍትሀዊነት ነው የሚለውን ይትበሀል ይዞ መሰለኝ የሞገተኝ፡፡ እኔ ደግሞ “የለም ሁሉንም ሰብስቦ ያስራቸዋል፤ ካሰራቸው ደግሞ ሌሎች ሰልፈኞች መውለድ አመታት ይፈጃል፡፡ ስለዚህ ይታገሱ፤ ሲሆን ሲሆን ወደፍርድቤት ይሂዱ፤ ወይም ሌላ ጥበብ ፈጥረው ሂደቱን ያጡዙት፡፡ እንጂ፤ አሁን ገፍተው ሰልፍ ቢወጡ ትግሉን ማጨናገፍ፤ ማስወረድ ነው” ብዬ ሞገትኩ፡፡ አልተስማማንም፡፡ የዚህ ጽሁፍ አብይ ዓላማም ማስታወቂያና ማስታወሻ ቢሆንም፤ የኛ የወጤዎቹ (ዳያስፖራ) ሚና የት ድረስ ነው? ድርጅቶቻችንስ ከመፈክር የዘለለ አመራር ለመስጠት ምን ሸበባቸው? በማለት፤ ከቅዳሜ ኤፕሪል 26ቱ የቶሮንቶ-ነቀምት ዝግጅት ማስታወሻ ጎን ለጎን፤ ሌሎች ጉዳዮችን በስሱ ያሻሻል፡፡ ከዚያ በፊት ግን፤

፪- ዘወትር ጽሁፍ ልጽፍ ኮምፒውተር በከፈትኩ ቁጥር፤ የሚያሸማቅቁኝና በዘዴ የማልፋቸው ሁለት ነገሮችን ላንሳ፡፡ አንደኛው “ትግሉ/ትግላችን” የሚለው ቃል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ “አንተ/እናንተ እዚህ ቁጭ ብለህ/ብላችሁ ሰው ልታስጨርስ/ልታስጨርሱ” የሚለው ትችት፡፡ መቼም የተሳካለትን ጠላት ማድነቅ አለመደብንም እንጂ፤ የራሳቸውን የሕወሀትን ትግል ላስተዋለ፤ በኛ፤ በተለይ በወጤዎቹ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ቋንቋ ውስጥ፤ ትግል፤ትግላችን የሚለው ቃል ሰቆቃ ተፈጽሞበታል፡፡ የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ፊትለፊት የሚደረግ ሰልፍ ትግል ይባላል፡፡ የፓልቶክ ውሎ ራሱ ትግል ተደርጎ ሲቆጠር ኖረናል፡፡ እኔ ራሴ፤ ለምሳሌ፤ እንደድሮው ቢሆን፤ የኤፕሪል 26ቱን የነቀምት ሰልፍ በገንዘብ የመርዳት ዝግጅት እንደትግል ነበር የማየው፡፡ አገራችንን እዚህ ያደረሰ ትግል ካልረሳን በስተቀር ይሄ ትግል አይደለም፡፡ ነገሩ፤ እንደው በረከት ይድረሰን፤ አይቅርብን አይነት ነገር ነው፡፡ ይሄ የኔ አቋም ነው፡፡

፫- እዚያ ቁጭ ብላችሁ ሰው ታስጨርሳላችሁ የሚለውም ሀሳብ እንደዚያው፡፡ በርግጥም እዚህ ቁጭ ብለን፤ እዚህ ጋር ተሰለፉ፤ አደባባይ ውጡ፤ እርካቡን ብትረገጡት፤ ፈረሱን ወዲያ ብትስቡት፤ ፈቃድ ባይሰጡም ውጡ፤ ፍርድቤት ሂዱ፤ ተጎንበሱ፤ ተነስነሱ ማለት አግባብ አይደለም፡፡ ስንጠየቅ፤ አንዳንዴ ባንጠየቅም፤ አገር ቤት ያሉትን ታጋዮች በማያስገድድ መልኩ፤ የመሰለንን ሀሳብ እንሰነዝራለን፡፡ በምንም መልኩ ግን የኛ በዚህ በውጭ የምንኖር ሰዎች ሚና፤ የአጋዥነት እንጂ የወሳኝነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድነትን በ15 ወይም በ25 ከተሞች ሰልፍ ውጣ ብለን አንቀሰቅስም፡፡ አንድነት ግን ዓላማውን ለማሳካት ሲል ሰልፍ እወጣለሁ ካለ፤ ከሆነልን ስንቅና ትጥቅ እናቀብላለን፡፡ ትንሽ የሚያሸማቅቀው፤ የምናቀብለው ስንቅና ትጥቅ፤ ፍርክስ ፍርክስ የሚል ወይም የማይጨበጥ፤ ኢምንት ሆነብን እንጂ፡፡ እኔ በበኩሌ በዚህ አስተሳሰብ ነው ወደዚህ የቶሮንቶ-ነቀምት ግንባር ውስጥ የገባሁት፡፡

፬- ባለፈው ሳምንት እንደቀሰቀስኩት፤ አንድነት ቶሮንቶ፤ ለነቀምቱ ሰልፍ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ቅዳሜ ኤፕሪል 26 ቀን፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከ3pm ሰኣት ጀምሮ፤ 2050 ዳንፎርዝ ጎዳና ላይ በሚገኘው ሂሩት ካፌ፤ የአብረን እንዋል መርሀግብር አዘጋጅቷል፡፡ አገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ ራሳቸውን አንዳንዴ ለሰደፍ፤ ከገፉም ለሰይፍ አጋልጠው ለሰልፍ ከተነሱ፤ ሰልፋቸው በገንዘብ እጦት ምክንያት እንዳይሰናከል የማድረግ ግዴታ አለብን፤ በሚል ስሌት የተዘጋጀው ዝግጅት፤ እንዲሳካ ደፋ ቀና እያልን ነው፡፡ ትንሽ ያልተመቸኝ፤ የአንድ ሰው አማካይ የወር ደመወዝ የማይሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ የምናልፍበት ሂደት፤ ለነቀምት ሰልፍ ሳይሆን ለኢትዮጵያ አብዮት የመዘጋጀት ያህል ማድከሙ ነው፡፡ ያም የሚከተለውን ትችት ለኮሰብኝ፡፡

፭- ከምርጫ 97 በኋላ ያለፍንባቸው ጥቂት አመታት እንደሚያሳዩት ከሆነ፤ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ፤ ፖለቲካዊ ስንፍናው እያየለ መጥቷል፡፡ አብዛኛው ሰው አንድም ተጠርጥሯል፤ አንድም ሸሽቷል፡፡ ባለፈው አመት የ40-60 ኮንዶሚኒየም ግንባታ መርሀግብር ሲወጣ፤ በኤምባሲው አቋርጦ ያለፈ ሰዉ የሰዉን ሰለፍ ብዛት በነገረኝ ግዜ፤ እኔም ነሽጦኝ ነበር፡፡ በርግጥም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ፖለቲካ ነክ ዝግጅቶች ላይ የሚታደሙትንና ያላቸውን የሚወረውሩ ቸሮች፤ ተመሳሳይና የተወሰኑ ሰዎች ናቸው፡፡ አብዛኛው ሸሽቷል፡፡ ካልሸሸውም ለአገራዊ ዝግጅት የሚወጣው ሰው ቁጥር አናሳ ነው፡፡ የምናጠቃው ከአቅም በታች ነው፡፡ የዚህ ከአቅም በታች የመንቀሳቀስ ምክንያት ምንድር ነው የሚለው ራሱን የቻለ ምርምር ያስፈልገዋል፡፡ አመራር/መሪ እጦት አንዱ ነው፡፡

፮- በርግጥ፤ ከምርጫ 97 በኋላ የተስተዋለው ስንፍና፤ የተከታይ ብቻ ሳይሆን የአመራርም ነው፡፡ በኢትዮጵያዊን ድርጅቶች ስራ ውስጥ ጣልቃ መግባት ወይም ምክንያታዊ ያልሆነ ተጽእኖ መፍጠር አግባብ አይደለም የሚለው እምነቴ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አንዳንድ የተመለከትኳቸውን የአመራር ድክመቶች እተቻለሁ፡፡ ለምሳሌ በደሴውም ይሁን በባህርዳሩ ሰልፍ መሳካት፤ እንዲሁም ለሰልፎቹ መሳካት የድርጅት መሪዎቹ ደረጉትን ጥረት የማድነቄን ያህል፤ በተለይ ከደሴው ሰልፍ በኋላ፤ በተጠናቀረው የ13 ደቂቃ የምስልና ድምጽ መረጃ ላይ፤ ተደጋግመው ከሚሰሙ መፈክሮች ውጪ፤ የተለየ የፖሊሲና የራእይ እንዲሁም አቅጣጫ ጠቋሚ ንግግር አለመመልከቴ አበሳጭቶኛል፡፡ ተቃውሞና መፈክር፤ የዚህን ስርአትም ህጸጽ ማሳየት እንድ ነገር ነው፡፡ ይህቺን አገር ከኢህአዴግ ተቀብለን ምን እንደምናስመስላት መሳልና ማሳየት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ ማሰርና ማስፈራራት፤ ማፈንና ማሰደድ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ የአምስት አመት የአስር አመት፤ የምእተአመት መርሀግብር እያለ ብዥታ መፍጠር ላይም የተሻለ ነው፡፡ እኛ አልቻልንም፡፡

፯- አንድነትም ይሁን ሌሎች፤ በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም ያሉ ድርጅቶች ከኢህአዴግ ነጥቀው ስለሚፈጥሯት ኢትዮጵያ ግልጽ የሆነ ምስል የላቸውም፡፡ ካላቸውም ደግመው ደጋግመው አያሳዩንም፡፡ በቋሚው ምስል ላይ ሳይሆን በእለታዊው ወይም ወቅታዊው ጉዳይ ይዋጣሉ፡፡ በተለይ አንድነት፤ የጸረሽብር ህጉ ይሰረዝ፤ እስረኞች ይፈቱ ከሚሉለው መፈክር የዘለለ ቋሚና ዘላቂ ፖሊሲ የሚያሳይ ንግግር ወይም መልእክት ሲያስተላልፍ መመልከት ብርቅ እየሆነብኝ ነው፡፡ ከአንድነት ጋር በተያያዘ ድርጅቱም ችግሩን የተረዳው ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፤ አቶ ግርማ ሰይፉ ባለፈው ሰሞን በጻፈው ጽሁፍ ላይ፤ አንድነት የኢህአዴግን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መርሀግብር በሰፊው እንደገመገመና እንደተወያየበት ጠቅሶ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የዕቅዱን ግምገማ ውጤት ለህዝብ ለማድረስ እንዳልተቻለ ጽፏል፡፡ አቶ ግርማ በራሱ ስም በየወቅቱ የሚጽፋቸው በመረጃ የተሞሉ ጽሁፎች ግሩም ናቸው፡፡ የአቶ ግርማ መረጃዎችና ጽሁፎች ህዝብ ዘንድ መድረስ ከቻሉ፤ የአንድነት ድርጅታዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊ፤ ዲፕሎማሲያዊና፤ ሕግ-ነክ ትንታኔዎችና ሰነዶች ህዝብ ዘንድ የማይደርሱበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ አንድ ነገር ያሳስበኛል፡፡ መፈክርና ዜና ቢደጋገሙም እውቀት አይሆኑም፡፡ ከዚያ በዘለለ፤ አቶ ግርማም ይሁን ሌሎች አመራር አባላት በጽሁፉ ያነሷቸው ጉዳዮች ድርጅታዊ ቅርጽ ይዘው መውጣትና፤ ይህ ህዝብ አንድነትን ለምን ማመን እንዳለበት ማሳየት አለባቸው፡፡

፰- ከዚህ በኋላ የአንዱዓለም እስር ዜና አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ሰልፍ መከልከሉም ዜና አይደለም፡፡ የጸረ-ሽበር ሕጉም ዜና አይደለም፡፡ ከመኢአድም ይሁን ከአረና ጋር ስለሚደረጉ ውህደቶች ማተት፤ በደብረታቦርም ይሁን በእምድብር ስለሚደረጉ ሰልፎች መናገር ብቻውን ዜናም ፖሊሲም አይደሉም፡፡ አንድነት ከነዚህ እውቀትም ብልሀትም ከማይፈጥሩ ዜና መሰል ጉዳዮች ወጥቶ፤ አንዳንድ በህዝብ ዘንድ ውይይትና መነቃቃትን፤ የሚፈጥሩ፤ በርግጥም ተለዋጭ መንግስት የሚያስመስሉ ተግባራትን መስራት መጀመር አለበት፡፡ አንዱ ትልቁ የተቃዋሚዎች ድክመት እንደተለዋጭ መንግስት ማሰብ አለመቻላቸው ነው፡፡ ሰልፍና ትችት ብቻውን አገር ለመምራት አያበቃም፡፡ አንዳንድ ግዜ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ያለው የሚቀበለው ተለዋጭ መሪ አጥቶ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ተለዋጭ እንዳይኖር ማድረጉ ራሱ የኢህአዴግ ስራ ውጤት ቢሆንም፡፡ እነዚህም ለሌላ ጽሁፍ ጥሩ ርእሶች ናቸውና አሁን አልገፋባቸውም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ኢህአዴግን እንደሰበብም ይሁን እንደተጠያቂ ልንጠቅስ የምንችልባቸው ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በኛ ብቃት ወይም እውቀት ማነስ የሰነፍንባቸው ነገሮች መተራረም እንዳለብን እናገራለሁ፡፡ ይሄ እንደተለዋጭ መንግስት ሆኖ አለማሰብ በራሳችን ካለመተማመን የመነጨ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ረገድ ግንቦት ሰባት ከውጭ፤ አንድነት ከውስጥ ያቃጥሉኛል፡፡

፱- ለምሳሌ፤ መጪው “ምርጫ?” ፊታችን ተደቅኗል፡፡ አንድነት በቀጣዮቹ ወራት ህዝቡንና ትኩረቱን ወደነሱ ለመሳብ ቢያነሳቸው ብዬ ከማስባቸው አንገብጋቢ ርእሶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ቡናውና ደኑ፤ የተፈጥሮ ሀብቱ፤ ደቡብና ደቡብ ምእራብ ሆኖ ሳለ፤ ጎንደርና ጎጃምን ዘሎ፤ መቀሌ የባቡር መስመር ለመስራት ማስቀደምን ምን አመጣው፡፡ ይሄ አይነቱ እቅድ፤ ኢህአዴግ ያኔ ስልጣን እንደያዘ ሰሞን ከተጠናወተው የስግብግብነትና የብቀላ ስሌት እንዳልወጣ ያሳያል፡፡ እንጂ፤ በምን የኢኮኖሚ ስሌት ነው ከጅቡቲ፤አዋሽ መቀሌ ባቡር የሚዘረጋው፡፡ ይሄን ይተዉት፤ በእሳት መጫወት ሊሆን ይችላል፡፡ የባህር በር ጉዳይን መጋፈጥ ይችላል አንድነት፡፡ አንድነት ለኤርትራ መንግስትና ህዝብ ግልጽ ደብዳቤ ሊጽፍ ይችላል፤ የሁለቱን አገሮች ታሪካዊ ትስስር በማሰብ፤ ድንበሩም ባህሩም አንድ ነገር እንዲበጅለት፡፡ የመሬት ጉዳንም አንድነት ፈራተባ እያለ ነው የያዘው፡፡ በአጠቃላይ፤ አንድነት፤ በርግጥም አገር ለመምራት ከተዘጋጀ፤ አገር መምራት እንደሚችል ፓርቲ ማጥቃት አለበት፡፡ ለያንዳንዱ የኢህአዴግ ሚኒስቴር ሰው መድቦ የኢህአዴግን ፖሊሲና ወሬን እግር በእግር እየተከታተል መበለት፤ የራሱንም ተለዋጭ ፖሊሲ መገንባትና ማሳወቅ አለበት፡፡

፲- ጎዶሎም ይሁን ሰንካላ፤ የማያጠግብም ይሁን ካንጀት ጠብ የማይል፤ የአንድነትን ስራ እናደንቃለን፡፡ እንዳልኳችሁ እንደትግል እንዳይቆጠርብን እንጂ፤ ቅዳሜ፤ ኤፕሪል 26 ተሰብስበን ለነቀምት ሰልፍ የሚረዳ ገንዘብ እንሰበስባለን፡፡ ስለዚህ፤ በቶሮንቶና አካባቢው ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ወደሂሩት ካፌ ብቅ በሉ፡፡ ለተጨማሪ የአንድነት ዝርዝር አገልግሎቶችና መረጃዎች በኢሜል፤ [email protected] ፤ ወይም በ http://andnettoronto.blogspot.ca/፤ ወይም በጽህፈት ቤቱ B2- 2017 Danforth Avenue, Toronto, ዳንፎርዝ ጎዳና ላይ ይግኙት፡፡ በኤፕሪል 26፤ በተለያየ ምክንያት በአካል መገኘትና የአንድነትን በረከት መቋደስ ያልቻለ፤ የገንዘብ ልገሳውን በሰው መላክ እንደሚችል ወይንም በአንድነት ባንክ ሂሳብ Unity for Human Rights and Democracy: TD Trust; የባንክ ሂሳብ ቁጥር፡ 12682 0041 0883 5209213፡ መክተት እንደአማራጭ እንደተቀመጠ፤ አንድነት ቶሮንቶ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡ ባንድነት ዝግጅት ሶስተኛው ሳምንት ደግሞ፤ እሁድ ሜይ 18፤ የኢሳት ቀን በቶሮንቶ ይከበራል፡፡ ኢሳታችን አራት አመት ሞላው፡፡ ከ97 ወዲህ እስከመቼ እንደሚዘልቅ እንጃ እንጂ፤ የመሰረትነው ስኬታማ ተቋም ኢሳት ነው፡፡ ለኢሳት ቀን በቶሮንቶ፤ ወዳጄ መሳይ ወደቶሮንቶ እንደሚዘልቅ በወሬ በወሬ ሰማን፡፡ ከዝግጅቱ አስቀድሜ፤ ስለኢሳት ትዝታዬና፤ መቼም አስተዳደሩ ምክር አይሰማም፤ ይታረሙ ዘንድ፤ ስለኢሳት ድክመቶች አንዳንድ አስተያየቶችን እለግሳለሁ፡፡ እስከዚያው፤
እኔ(ኛ)ው ልጅ ተክሌ ነኝ፤ ቶሮንቶ፤ ሚያዚያ፤ 2006/2014

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

Go toTop