(ከግርማ ካሣ)
የሕንድ፣ የቻይናና የሳውዲ ኩባንያዎች በአገራችን ኢትዮጵያ ለእርሻ ሥራዎች ሰፊ መሬት በሊዝ እንደወሰዱ በስፋት ተዘግቧል። የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት «ሰዎች የማይኖሩባቸው ቦታዎችን ነው ለልማት ስንል ለውጭ አገር ዜጎች የሰጠነው» ይላሉ።
ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ያለ ውዴታቸው ዜጎች እንደተፈናቀሉ፣ ከመኖሪያቸው እንደማይፈናቃሉ የሚናገሩት እንደሚታሰሩና እንደሚገደሉ፣ የመሬቱም “ሽያጭ” በርካሽ ዋጋ፣ እስከ 99 አመታት ላለ ረጅም ጊዜ እንደሆነ በመግለጽ፣ የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግን እንቅስቃሴ ጸረ-ሕዝብና የአገርን ጥቅም የሸጠ እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ።
አንድ ጊዜ፣ ከአዲስ አበባ የመጣ አፍቃሪ ኢሕአዴግ የሆነን ሰው «መሬት ለ99 አመታት ለውጭ አገር ዜጎች ይሸጣል ይባላል። እውነት ነው ወይ?» ብዬ ጠየኩት። ለ99 አመታት ለውጭ አገር ዜጎች መሬት በሊዝ እንዳልተሰጠ፣ ቢበዛ ለ25 አመታት ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገለጸልኝ። 25 አመት ለምን ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዳኝ «የተሰጠውን ቦታ ኢንቨስተሮች መጀመሪያ ማልማት አለባቸው። መንገዶች ይሰራሉ። ለሰራተኞች የሚሆን በአካባቢው ትምህርት ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶች ይሰራሉ። ይሄ አይነት ቅድመ ትርፍ ሥራዎች ሁሉ፣ ቢያንስ ከአምስት እስከ አሥር አመት ይፈጃሉ። ትርፍ ሊያገኙ የሚችሉት ከአሥር አመት በኋላ ቢሆን ነው። ያን ሁሉ ሰርተው፣ ያን ሁሉ ገንብተው፣ ለእነርሱም ትርፍ የሚያገኙበት ሚዛናዊ የሆነ ተጨማሪ አሥር አሥራ አምስት አመታት መስጠት ያስፈልጋል። አለበለዚያ ኢንቨስት ላድርግ ብሎ የሚመጣ አይኖርም» ነበር ያለኝ። ይህ እንግዲህ የአንድ አፍቃሪ ኢሕአዴግ ቃል ነው። ያለኝን አለኝ እንጂ ውሎች በርግጥ 25 አመታት ብቻ መሆናቸውን፣ የሚያረጋግጥበት አንዳች አይነት መረጃ አላቀረበልኝም።
ከዚህ ከኢሕአዴግ ደጋፊም ሆነ ከሌላ ምንጮች፣ ለውጭ አገር ዜጎች የሚሰጠው መሬት በምን ሂሳብ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ በተጨባጭ በመረጃ የተገለጸበት ቦታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ላገኝ አልቻልኩም ነበር።
ሱልጣን ኢብራሂም አሰብን ለጣሊያኖች እንደ ሸጠ፣ የአገራችን መሬት፣ እኛ በማናውቀው መንገድ ለውጭ አገር ዜጎች እየተቸበቸበ ይሆን? ከአመታት በኋላ ኢትዮጵያ የሕንዶችና የቻይናዎች አገር ትሆን ይሆን? አይናችን እያየ በልማት ስም ብሄራዊ ጥቅማችን እየተሸረሸረ ይሆን? ወይንስ ጥቅም ላይ ያልዋለ መሬቶችን ጥቅም ላይ በማዋል፣ ለዜጎች የሥራ እድል የሚከፍቱ፣ እህል በአገራችን ገበያዎች በብዛት እንዲኖሩ የሚያደርጉ፣ የስንዴም የጤፍ የስኳርን ዋጋ የሚያስቀንሱ፣ ገጠሪቷ ኢትዮጵያን የሚያለሙ፣ ጸረ-ድህነትና አገር ጠቃሚ ተግባራት ነው እየተሰሩ ያሉት?
በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ የሚንቀሳቀስ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ንቅናቄ የሚባል የሲቪክ ማህበር፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለብዙ ጊዜ ማወቅ የምፈልገውን፣ ከላይ ለጠቀስኳቸው ጥያቄዎች አንዳንድ ምላሽ የሚሰጥን መረጃ ይፋ አድርጓል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ንቅናቄ አክቲቪስቶች፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊያውቀው፣ ሊመረምረው፣ መላ ሊፈልግለት የሚገባውን ይህ አይነቱን ቁልፍ መረጃ አቀናብረው፣ ይፋ ማድረጋቸው በጣም ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ትልቅ ተግባር ነው። እጅግ በጣም ትልቅ ሥራ ነው የሰሩት።
ያልሆነውን ሆነ በማለት፣ በስሜት በመነዳት ብቻ መቃወም ሳይሆን፣ ይህ አይነቱን ጥናታዊ፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ማንም ጥሩ አይምሮ አለኝ የሚል ዜጋን አይምሮ የሚቆረቁር መረጃዎችን ማሰባሰብና ለሕዝብ ማሳወቅ፣ ተቃዋሚዎች በዋናነት ሊሰሩት የሚገባ ትልቅ ተግባር ነው። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ይህንኑ ነው ያደረገው።
ሶሊዳሪቲ ይፋ ካደረጋቸው መረጃዎች መካከል፣ ምን ያህል መሬት፣ በየትኛው ክልል በሊዝ እንደተሰጠ፣ ለማን እንደተሰጠ፣ በምን ያህል ዋጋ እንደተሰጠ የሚገልጹ፣ የመንግስት ባለስልጣናት የፈረሙበትና ማህተማቸውን የመቱበት፣ ሊካዱ የማይችሉ፣ የማያከራክሩ የሕግ ሰነዶች ይገኙበታል።
ድህረ ገጹን በሚከተለው ሊንክ ሊያገኙት ይችላሉ፡ ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠው መሬት ስፋት
ለኢትዮጵያውያን በሊዝ የተሰጡትን መሬቶች ለጊዜው ትተናቸው፣ ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጡት መሬቶች ብቻ ብንመለከት፣ ለቻይና ኩባንያ 25000 ሄክታር፣ ለሳውዲ ኩባኒያ 10000 ሄክታር፣ ለሕንድ ስድስት ኩባንያዎች 246,5012 ሄክታር መሬቶች በሊዝ ታድሏል።
ይህንን አሃዝ አብዛኞቻችን በሚገባን መልኩ እንደሚከተለው ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡
1. ወደ አራት ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖሩባት የአዲስ አበባ ከተማ ስፋት 54,000 ሄክታር አካባቢ ነው። በሌላ አባባል የአዲስ አበባን አምስት ጊዜ የሚያህል መሬት ነው ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠው።
2. በሕንድ በርካታ ፌደራል ክልሎች አሉ። ከነዚህ ክልሎች መካከል በደቡብ ምዕራብ የምትገኘው፣ ወደ 34 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት የኬራላ ክልልንና በሰሜን የምትገኛዋ ወደ 26 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት የሃሪያና ክልል ይገኙበታል። ኬራላ ስፋቷ 3,886,300 ሄክታር ስትሆን ሃሪያና 4,421,200 ሄክታር ትሰፋለች።
ለውጭ አገር ኩባንያዎች የተሰጠውን መሬት ስንመለከት፣ የኬራላን ስድስት በመቶ የሃሪያናን ደግሞ 5.4 በመቶ የሚሆንን መሬት ያህላል። በኬራላ የሕዝብ ብዛትን በሄክታር ብናሰላው፣ በአገራችን ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠውን መሬት በሚያክል የኬራላ ክልል ቦታ 2,147,884 ሕዝብ ይኖራል። በሌላ አባባል 2,147,884 ሊያኖር የሚችልን መሬት ነው ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠው።
3. ሉክሳምበርግ በአውሮፓ፣ ፈረንሳይን በሰሜን ምእራብ ሆላንድንና ቤልጅየምን በሰሜን የምታዋስን አገር ናት። ስፋቷ 258,600 ሄክታር መሬት ነው። ለውጭ አገር ዜጎች በኢትዮጵያ የተሰጠው መሬት ሉክሳምበርግን የሚያክል መሬት ነው።
4. በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በከንቱ ያለቁበት የባድመ ይገባኛል ጦርነት ነው። የባድመ ከተማ ከዳር እስከ ዳር ከአንድ ኪሎሜትር አትበልጥም። በመሆኑም ስፋቷ ከ100 ሄክታር ያነሰ ነው ማለት ይቻላል። እንደሚታወሰው ከ100 ሄክታር በታች ለሆነ መሬት ነው፣ ያ ሁሉ የንብረት እልቂት የተከሰተው፣ ያ ሁሉ ደም የፈሰሰው። ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠው 250,012 ሄክታር መሬት በስፋቱ፣ 2,500 ባድማዎች እንደተሰጡ የሚያስቆጥር ነው። ለአንድ ባድማ ያን ያህል መስዋእትነት ሲከፈል ለ2,500 ባድማዎች በቀላሉ መሬቶች ሲሰጡ ማየት እጅግ በጣም የሚያሳዝንና እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ሊያስቆጣ የሚገባ ጉዳይ ነው።
ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠው መሬት ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ
የተሰጠው መሬት ብዛት አሳሳቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለምን ያህል ጊዜ ነው ሊዙ የተፈረመው የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ ከአዲስ አበባ መጥቶ ያነጋገርኩት አፍቃሪ ኢሕአዴግ ከነገረኝ ጋር ፈጽሞ የማይሄድ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ከተሰጡት መሬቶች መካከል 178, 012 (71 በመቶ) ሄክታር መሬት ለአምሳ አመት ነው የተሰጠው። አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለውም ትውልድ መዘዝ የሚፈጠር ስምምነት እንደተፈረመ ነው የምናየው።
እንደዚያም ሆኖ ግን በስምምነቶቹ እንደተቀመጡት የፌዴራል መንግስቱ የተሻለ ሶሲዮ ኢኮኖሚ ጥቅም ከተገኘ የስድስት ወራት ጊዜ ሰጠቶ ሊዙን መሰረዝ የሚችልበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ ከካሩቱሪ የሕንድ ኩባንያ ጋር በተደረገው የስምምነት ውል አንቀጽ 5.4 “The lessor has exclusive right to terminate the land lease agreement subject to at least six months prior notice in written up on the Federal Government’s decision for any better socio-economic benefit” ይላል።
ስለዚህ ውሉን በተፈለገ ጊዜ መሰረዝ እስከተሻለ ድረስ የውሉ ዘመን 25 ሆነ አሥር ሆነ ብዙም ስጋት ውስጥ የሚከት አይመስለኝም።
ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጠው መሬት ዋጋው ምን እንደሆነ
በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ገርጂ በመሳሰሉ ብዙ ቦታዎች ወደ 200 ካሬ ሜትር (0.02 ሄክታር) ስፋት ያለው ቤት ከሁለት ሚሊዮን ብር ያነሳ አይገኝም። አንድ ሄክታር መሬት ወደ 67 ሚሊዮን ብር ነው የሚያወጣው እንደ ማለት ነው። አስቡት … መቶ ሺህ ሄክታር መሬት ስድስት ትሪሊየን፣ ስድስት መቶ ቢሊዮን ብር ይደርሳል።
ሲ.ዔል.ሲ ስፔንቴክስ ለተባለው የሕንድ ኩባንያ 100,000 ሄክታር መሬት ለአምሳ አመት የተሰጠበት ዋጋ ሃያ ብር ( አንድ ዶላር ከሃያ ሳንቲም) ብቻ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ በአንድ ተራ ምግብ ቤት፣ ጥቂት ጉርሻ የሚሆን ስጋ ጣል ጣል የተደረገበት አንድ እንጀራ ወጥ ምግብ ለመመገብ 170 ብር ያወጣል። የአንድ እንጀራ ምግብ ዋጋ 8.5 ሄክታር ይገዛል።
የሲ.ኤል.ሲ የሕንድ ኩባንያ ለአምሳ አመታት መሬቱን ከተጠቀመ በኋላ የሚከፍለው ጠቅላላ ዋጋ ወደ 2 ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ ይህም በአዲስ አበባ 0.02 ካሬ ሜት ለሚያወጣ መሬት የሚከፈል ዋጋ ነው። ሌላው ከዋጋው ነገር በተገናኘ ለማንሳት የምፈልገው ሌላ ነጥብ አለ።በመሬቱ «ሽያጭ» ስምምነቶች እንደምናየው ኩባንያዎቹ የሚከፍሉት በውጭ ምንዛሪ በዶላር ወይንም ዩሮ ሳይሆን በኢትዮጵያ ብር ነው። የብር ዋጋ ካሽቆለቆለ እነርሱም የሚከፍሉት ክፍያ የዚያኑ ያህል ያሽቆለቁላል። ለምሳሌ አገሬን ለቅቄ ስደት ስጀምር፣ አንድ የአሜሪካን ዶላር በ2.07 ብር ነበር የሚመነዘረው። አሁን አንድ ዶላር በ17.5 ብር ይመነዘራል። በአሥራ ዘጠኝ አመት ውስጥ 800% ጨምሯል። የዶላር ዋጋ ወደፊት መጨመሩ አይቀርም። እንበል በጥቂት አመታት ውስጥ አንድ ዶላር ሃያ አምስት ብር ቢመነዘር፣ ለአንድ ሄክታር መሬት፣ 1.2 ዶላር የሚከፈለው ዋጋ ያኔም በሃይ ብር ስለሚታሰብ፣ የዶላር ዋጋው ሰማኒያ ሳንቲም ብቻ ነው የሚሆነው።
ለኢትዮጵያውያን ውሉ በብር መሆኑ አያስደንቅም። ነገር ግን ለውጭ አገር ዜጎች ውሉ በዶላር ከመሆኑ ይልቅ በብር መሆኑ ከማስገረም አልፎ አሳዛኝ ነው። በርግጥ ስምምነቱን የፈረሙ ባለስልጣናት ምን ያህል የኢትዮጵያን ጥቅም እንዳላስቀደሙ ያሳያል።
የስምምነቶቹ ሰነዶች እንደሚገልጹት የፌደራል መንግስቱ የሊዙን ዋጋ እንደገና ማሻሻል እንደሚችል በግልጽ ያስቀምጣሉ። በመሆኑን የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ይሄን ውል እንደገና ማሻሻል አለባቸው እላለሁ።
ለውጭ አገር ዜጎች ከተሰጠው መሬት የሚመረተው ምርት ሕዝባችንን አያበላም
ለውጭ ዜጎች ከተሰጡት 250,012 ካሬ ሜትር ከሚሆነው መካከል 120,000 ሄክታር መሬት (ግማሹ) ማለት ይቻላል ለሩዝ ምርት የተመደበ ነው።
እንደሚታወቀው ሕንዶችና ቻይናዎች ዋናው ምግባቸው (ጤፋቸው) ሩዝ ነው። የኢትዮጵያን መሬት ወስደው የሚያመርቱት ምርት በአገራችን ወዳሉ ጉሊቶችና መርካቶዎች እንዲሄድ ታስቦ አይደለም። ነገር ግን ምርቱ በቀጥታ፣ ኢትዮጵያውያን አንዷን ጥሬ አፋቸው ሳያደርጉ፣ ወደ ሻንሃይና ቦምቤይ ነው የሚያመራው። ኢትዮጵያውያን ካለባቸው የምግብ እጥሮት፣ በላያቸው ላይ ከተጫነው የኑሮ ውድነት ቀንበር የሚያላቅቅ አይደለም።
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵጵያ ውስጥ አንድ ኪሎ ምስር አምሳ ብር ነው የሚሸጠው። 1 ኪሎ የሸኖ ቂቤ 300 ብር ነው። አንድ እንቁላል 2 ብር ነው። ዘይት በአገሩ የለም። ኢሕአዴግ በዚህ ምክንያት በየቀበሌው ማደል እንደጀመረም ይነገራል። ሕዝባችን ግራ ገብቶታል። ህዝባችን በችጋር ውስጥ ውስጡን እያለቀ ነው። የኑሮ ውድነት እጅግ በጣም አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ትላልቅ እርሻና የአባይ ውሃ
ለውጭ አገር ዜጎች በብዛት መሬት የተሰጠው በቤኔሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎች ነው። ኢሕአዴግ ሊገነባው ያሰበውና አብዛኞቻችን በመርህ ደረጃ የምንደግፈው የአባይ ግድብ፣ በቤኔሻንጉል እንዲገነባ ነው፣ በማይታወቅ ሁኔታ የተወሰነው። በቤኔሻንጉልና በጋምቤላ ለውጭ አገር ዜጎች የተሰጡትን ሰፋፊ መሬቶችን (በተለይም ሩዝ የሚመረትበት) በመስኖ ለማልማት ውሃ ያስፈልጋል። «በእነዚህ ትላልቅ እርሻዎች ምክንያት የአባይን ውሃ በመስኖ ሊጠቀሙ ይችላሉ፣ የምናገኘውም የውሃ መጠን ሊቀነስ ይችላል» የሚል ትልቅ ስጋት ግብጾች እንዳላቸው እየሰማን ነው።
ኢትዮጵያ ሕዝቧን ለመመገብ፣ ሕዝቧን ለማሳደግ የአባይን ውሃ ለኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫና ለመስኖ ስራ የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት የተረጋገጠ ነው። የአለም አቀፍ ሕግ አይከለክላትም። ነገር ግን ከአባይ ወንዝ፣ ውቂያኖስ አልፈው የሚገኙ እንደ ሕንድና እንደቻይና ያሉ አገሮች ግን የአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ሽፋን ለብሰው፣ የአባይን ውሃ የመጠቀም ምንም መብት የላቸውም። ሕንድንና ቻያናን በተዘዋዋሪ መንገድ ለመጥቀም ሲባል ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ግብግብ የምትፈጥረበት ምንም ምክንያት የለም።