(DW) በኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ ፤ ኬንያና ሶማልያ ፣ 8 ሚልዮን ያህል ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት፣ በዛሬው ዕለት ፤ ሮማ ላይ አስታወቀ።
በድርቅ፤ እንዲሁም በምግብና ነዳጅ ዋጋ መናር ሳቢያ፣ በአፍሪቃውን ቀንድ አካባቢ ብርቱ የምግብ እጥረት የሚያሠጋቸው ሰዎች ቁጥርም መጨመሩ እንደማይቀር የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት(FAO) መግለጫ ያስረዳል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ገደማ ኢትዮጵያ ውስጥ 11, 4 ሚልዮን ገደማ የሚሆን ህዝብ ፣ እርዳታ እንደሚያስፈልገው FAO ሲገልጥ፤ አገ ሪቱ የውሃ እጥረት እንዳለባትና የግጦሽ ቦታ ይዞታም በጣም መጥፎ ይዞታ ላይ እንደሚገኝ በመገንዘብ ነው።
በሶማልያ 2,5 ሚሊዮን ሶማሌዎች፤ ከየ3ቱ ሶማሊ አንዱ መሆኑ ነው፤ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የተገለጠ ሲሆን በደቡብ ሶማልያ ያለው ውዝግብና በመጪው አዝመራም የሚፈለገው ምርት እንደማይገኝ ከወዲሁ በመታወቁ በዛ ያሉ ሶማሌዎች ከባድ ችግር ላይ መውደቃቸው አይቀሬ ነው ተብሏል።
በኬንያ፤ሰሜናዊና ሰሜን ምሥራቃዊው የአገሪቱ ክፍል፤ ከ 2,4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ
መሠረታዊውን የምግብና የሚጠጣ ውሃ ማሟላት እንደማይችል ተገልጿል።