ሙሉ.ገ (አዲስ ነገር) የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ-ኢህአዴግ) ፓርቲ ሊቀመንበር እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በመኾን በቅርቡ የተሾሙት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ለሕክምና ወደ ታይላንድ ከሄዱ ሁለት ወራት ቢያልፉም መንግሥት በጨፌ ኦሮሚያ ለሚገኙ የሥራ ባልደረቦቻቸው ለሥልጠና ወደ ቻይና እንዳመሩ አድርጎ እንገለጸላቸው ምንጮች ለአዲስ ነገር አስታወቁ።
አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ለሕክምና ከአገር ከመውጣታቸው በፊት በመንፈስ ጭንቀት እና በድብርት ታውከው ነበር ያሉት ምንጮቻችን ኦህዴድ-ኢሕአዴግ ከየካቲት 12 እስከ የካቲት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ በአዳማ-ናዝሬት ባደረገው ድርጅታዊ ግምገማ ላይ ቀድሞውን የአባዱላን ቡድን በግምገማ የማስመታት ሥራ ከሠሩ በኋላ በተፈጠረ ውጥረት መንግሥት ለሕክምና ሄዱ ከማለት ይልቅ ለሥራ ነው የሄዱት በማለት መደበቅን መርጧል ሲሉ ተናግረዋል።
በግምገማው ላይ አቶ ዓለማየሁ ከምክትላቸው ከአቶ ሙክታር ከድር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የኦህዴድ የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ኩማ ደመቅሳ ጋራ በመኾን ግምገማውን በመሩበት ጊዜ ንቁ ተሳታፊና አሳታፊ ነበሩ። በድርጅቱ ውስጥ እና በክልሉ መንግሥት ውስጥ በሙሰኝነት እና በአስተዳደር በደል የሚወቀሱ አባላትን በተጨባጭ ሂስ በማድረግ፣ ግለሂስ እንዲያደርጉ መድረኩን በማመቻቸት የማይደፈሩ የተባሉ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን እና ግብረ አበሮቻቸውን የሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግራቸውንና በሥልጣን ያካበቱትን ሀብት በይፋ እንዲወጣ አድርገው ከዘጠኝ ያላነሱ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እንዲሁም ከስድሳ በላይ የፓርቲው የአመራር አባላት በብሔራዊ ደኅንነት ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርገዋል። በተጨማሪም የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ ሀብታቸው እንዲታገድም አድርገው ነበር፡፡
ከግምገማው በኋላ በቀድሞው የኦህዴድ ሊቀመንበር እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በነበሩት በአቶ አባዱላ ገመዳ መስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥርስ ውስጥ እንደገቡ የሚነገርላቸው አቶ ዓለማየሁ የአባዱላ ባለሥልጣናትን የአስተዳደር በደል፣ ሙስና እና የአቅም ማነስ እንዲያጋልጡ ከበስተጀርባ ድጋፉ ሲሰጣቸው የነበረው ከአቶ መለስ ዜናዊ ነው ሲሉም ተናግረዋል። መንግሥት ከኹኔታው የሚያገኘውን ትርፍ እና ኪሣራውን አስልቶ ቀስ ብሎ ድጋፉን ነፈጋቸው ያሉን አንድ የኦህዴድ አመራር አባል በዚህ የተነሳ ከጨዋታ ውጭ እየተደረጉ የነበሩት የአቶ አባዱላ ገመዳ መስተዳደር ሰዎች እንደገና በማንሰራራት በአቶ ዓለማየሁ አስተዳደር ላይ እንቅፋት መፍጠር ጀምረዋል ብለዋል፡፡
ይህን ኹኔታ አስቀድመው የተረዱት የአቶ ዓለማየሁ ምክትል አቶ ሙክታር ከድር እና አቶ ኩማ ደመቅሳ ራሳቸውን ከኹኔታው ጋራ ሲያዛምዱ አቶ ዓለማየሁ ግን ብቻቸውን ለመጋፈጥ ያደረጉት ፖለቲካዊ ትግል ከላይም ከታችም ዋጋ ሲያሳጣቸው አሰጥቷቸዋል ብለዋል ምንጮቻችን።
የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መንግሥት ከ2002 ዓ.ም ምርጫ በኋላ በኦሮሚያ የአባ ዱላን መስተዳድር በመለወጥ አቶ ሙክታር ከድርን ወደ ርዕሰ መስተዳደርነት ለማምጣት ውስጣዊ ሥራ ሲሠራ ቢቆይም በወቅቱ አቶ ሙክታር ከኦህዴድ ሰዎች ያገኙታል ተብሎ የታሰበው ድጋፍ እንደታሰበው ኾኖ ባለመገኘቱ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ተመርጠው አቶ ሙክታር ምክትል ኾነው እንዲቀጥሉ መደረጉንም ጨምረው አስረድተዋል። አቶ ዓለማየሁ ለሕክምና ከሄዱ በኋላ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን አስተዳደራዊ እንቅስቃሴ ምክትላቸው አቶ ሙክታር ከድር ተክተው በመሥራት ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።