(ከአሰግድ ተስፋዬ) የቡርኪና ፋሶ የአማካይ መስመር ተጫዋች ጆናታን ፒትሮይፓ በናይጄሪያ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። በሻምፒዮናው ምርጥ ቡድን ውስጥ አሸናፊዋ ናይጄሪያ አምስት ተጫዋቾችን በማስመረጥ ቀዳሚ ሆናለች።
ለፈረንሳዩ ሬን እግር ኳስ ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው ፒትሮይፓ በሻምፒዮናው ሁለት ግቦች ከማስቆጠሩም በላይ ለአገሩ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ያሳየው ብቃት በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የሻምፒዮናው ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ለመመረጥ አብቅቶታል።
ተጫዋቹ ቡርኪና ፋሶ በሩብ ፍጻሜው ከጋና ጋር ባደረገችው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ይታወሳል። ሆኖም ጨዋታውን የመሩት አርቢትር ስሊም ጄዲዲ በወቅቱ ባቀረቡት ሪፖርት መሳሳታቸውን በማመናቸው የውድድሩ አዘጋጅ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ቅጣቱን በማንሳቱ በእሁዱ የፍጻሜው ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ፒትሮይፓ የሻምፒዮናው ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ቢመረጥም በሻምፒዮናው ምርጥ ቡድን ምርጫ ውስጥ በርካታ ተጫዋቾችን ማስመረጥ የቻለችው እ.ኤ.አ ከ1994 ወዲህ የፍጻሜ ተፋላሚዋን አንድ ለዜሮ በሆነ ጠባብ ውጤት በመርታት ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ያገኘችው ናይጄሪያ ናት።
በፍጻሜው ጨዋታ የአረንጓዴ ንስሮቹ አምበልና ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከተው ቪንሴንት ኤኒየማ ለሻምፒዮናው ምርጥ ቡድን በግብ ጠባቂነት ተመርጧል። ለእስራኤል ክለብ በመጫወት ላይ ከሚገኘው ኤኒየማ በተጨማሪ ተከላካዩ ኤፌ አምብሮስ፣ የአማካይ ስፍራ ተሰላፊዎቹ ጆን ኦቢ ሚኬልና ቪክቶር ሞሰስ እንዲሁም የፊት መስመር ተሰላፊው ኢማኑኤል ኤምኒኬ ለምርጥ ቡድኑ ከናይጄሪያ የተመረጡ ተጫዋቾች ናቸው።
ለእንግሊዙ ቼልሲ እግር ኳስ ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘውና በፍጻሜው ጨዋታ ምርጥ ብቃቱን ያሳየው ቪክቶር ሞሰስ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ሲያገኝ አገሩ ናይጄሪያ ለዋንጫ ሽሚያ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ላይ በጉዳት ያልተሰለፈው ኢማኑኤል ኤምኒኬ በአራት ግቦች የሻምፒዮናው ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ሆኗል። ተጫዋቹ ከጋናው ሙባራክ ዋካሶ ጋር እኩል አራት ግብ ቢኖረውም አገሩ የሻምፒዮናው አሸናፊ በመሆኗ የወርቅ ጫማውን መውሰድ ችሏል።
ተጫዋቹ ለቢቢሲ የስፖርት አምድ ዘጋቢ በሰጠው አስተያየት « ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኘው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ በማጠናቀቄ ደስተኛ ነኝ። ሻምፒዮናው ከመጀመሪያው አንስቶ ለእኔ ጥሩ ነበር። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ለአገሬ ጥሩ ነገር አድርጌ አላውቅም ነበርና » ብሏል።
በሻምፒዮናው ምርጥ ቡድን ውስጥ ማሊ፣ ጋና፣ ኬፕ ቨርዴና ኮትዲቯር አንዳንድ ተጫዋቾችን አስመርጠዋል ። ለጋና ብሔራዊ ቡድን አራት ግቦችን ያስቆጠረው ሙባራክ ዋካሶ በቡድኑ አለመካተቱ አስገራሚ ሆኗል።
በተያያዘ ዜና የዋንጫ ተፋላሚ የነበረችው የቡርኪና ፋሶ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቤልጅየማዊው ፖል ፑት በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋንጫ ፍልሚያ የደረሰው ቡድናቸው ተጫዋቾች በናይጄሪያ አንድ ለዜሮ ከተሸነፉ በኋላ ላሳዩት የመንፈስ ጥንካሬ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለፍጻሜ ባለመድረስ ብቻም ሳይሆን ከሜዳው ውጪ አንድም ጨዋታ አሸንፎ የማያውቀው የቡርኪና ፋሶ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በደቡብ አፍሪካው ሻምፒዮና ተጫዋቾቹ ያሳዩትን ተነሳሽነትም አሰልጣኙ አድንቀዋል። « እስከ ጨዋታ መጠናቀቂያ ድረስ ትግል የሚያደርግ ቡድን አይቻለሁ» ብለዋል አሰልጣኙ።
« በፍጻሜው ጨዋታ ብንሸነፍም ከሌሎች ቡድኖች በተሻለ ለፍጻሜው መቅረብ የነበረብን እኛ ነን » ያሉት ፖል ፑት ፤ « በፍጻሜው ጨዋታ ለናይጄሪያ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ትልቅ ክብር ሳንሰጣት የቀረን አይመስለኝም። በሁለተኛው አጋማሽ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ሞክረናል። በግልጽ ለመናገር እድለኞችም አልነበርንም » ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በምድብ ሦስት ከኢትዮጵያ፣ ዛምቢያና ከሻምፒዮናዋ ናይጄሪያ ጋር የተደለደለችው ቡርኪና ፋሶ ብዙም ግምት ሳይሰጣት ለፍጻሜ ለመድረሷ ዋናው ምክንያት የተጫዋቾቿ ቁርጠኝነት፣ ችሎታና ጽናት ለዋንጫ ተፋላሚነት እንዳበቃት ብዙዎች ይስማማሉ።
አሰልጣኝ ፖል ፑት አክለውም « ተጫዋቾቼ በፍላጎትና በቆራጥነት ተጫውተዋል። የእዚያን ያህል ግን እድለኞች አልነበርንም። ለፍጻሜው የደረስነው በራሳችን ጥንካሬ ነው። ተጫዋቾቼ በፍጻሜው ቢሸነፉም ከሌሎች ቡድኖች ተሽለው የፍጻሜ ተፋላሚ በመሆናቸው ኩራት ሊሰማቸው ይገባል » ብለዋል።
አሰልጣኙ አያይዘውም ከዚህ በኋላ በብራዚል ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከኒጀር ጋር ስላለባቸው የማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በምድብ አምስት የተደለደለችው ቡርኪና ፋሶ ካለምንም ነጥብ የምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
« ጥሩ ስብስብ አለን። ነገር ግን ገና ብዙ መስራት ያለብን ነገሮች እንዳሉ ማመን አለብን። ትልቁ ተግዳሮት ስኬትን ቀጣይ ማድረግ ነው። በእግር ኳስ ዛሬ ተሸንፈህ ለነገ ጨዋታ መዘጋጀት ግድ ይላል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከኒጀር ጋር ላለብን ጨዋታ በተገቢው መልኩ መዘጋጀት ካልቻልን አደጋ ነው » በማለት ነው የገለጹት የ56 ዓመቱ ቤልጅየማዊ አሰልጣኝ ፖል ፑት።