September 14, 2024
36 mins read

ዘንድሮም ማሩኝ!

677898800በላይነህ አባተ([email protected])

 

ዓይኔን ተሚጥሚጣ በተሰራ ድልህ ያጠብኩ ዋሾና አጭበርባሪ ነኝ፡  የዚህን ዘመን ባለስልጣኖች፣ፓስተሮች፣ ሼሆች፣ ጳጳሳትና ፓትርያሪኮች ያህል ባይሆንም ይህቺ ነገ የምታልፈዋ ምድራዊ ዓለም አታላኝ በመሬትና በታሪክ ሲያስረግም የሚኖር በሰማይም የሚያስኮንና ሲኦል የሚዶል ኃጥያትን ፈጥሚያለሁ፡፡ የፈጸምኩትን ኃጥያትና የዋሸሁትን ቅጥፈት በዚህ አዲስ ዓመት እናዘዛለሁ፡፡ ህሊናዬን በብርጭቆ ስባሪ ፈቅፍቄ የዋሸሁና ያጪበረበርኩትን ግጥም አድርጌ እናዘዛለሁ፡፡ “አቡኑ ካባውን ተገላው ደርቦ፣ ጳጳሱ ቆቡን ታናቱ ሰቅሎ፣ ቄሱ መስቀሉን በእጁ ጨብጦ፣ ፓስተሩ የማይገባውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ እያነበነበ፣ ሼሁ ቁርአኑን ከብብቻው ታቅፎ፣“ባለስልጣን” በሕዝብ ወንበር እንደ ቁራ ቁጢጥ ብሎ ቅጥፈት እንደ አቡጀዴ ሲቀድና ሲያጭበረብር በሚውልበት አገር ውሸትና ማታለል ባንተ ቤት ብርቅ ነው እንዴ? ልብ አውልቅ!” ብላችሁ ንባቧን እዚሁ እንዳታቆሙ እማጠናለሁ፡፡

 

“ዋሾ ምክንያት መደርደር አይሰለቸውም” ብላችሁ ከንፈራችሁን አትምጠጡብኝ እንጅ እኔ የዋሸሁት እንደ እነ እንቶኔ ተረግሜ፣ ውሸታም አሳድጎኝ ወይም ውሸታም ማህበረሰብ ኮትኩቶኝ አይደለም፡፡ እንድዋሽ በባእድ ተገዝቼ ወይም ለስልጣንና ለገንዘብ ቋምጬ አይደለም፡፡ እንደ ኤፍሬም ይስሃቅ ሽምግልናን ለማጎሳቆል፤ እንደ ከንቱ ቆብ ደፊዎች ምንኩስናን ለማርከስ፣ እንደ እንድርያስ እሼቴ ምሁርነትን ለማርከስ አለዚያም እንደ አቶ ኦባማ ለዲፕሎማሲ ስልም አይደለም፡፡ እኔ የዋሸሁት እንደ ይህ አድግ ቁንጮዎች በተንኮል፣ በቂም፣ በክፋት፣ በጥላቻ፣ በበታችነት ስሜት ተወጥሬ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ትውልድን ከትውልድ፣ ጎረቤትን ከጎረቢት፣ ጓደኛን ከጓደኛ፣ ልጅን ከወላጅ፣ ሚስትን ከባል፣ ወንድምም ከወንድም፣ እህትን ከእህት፣ እህትን ከወንድም አጋጭቼ አገርን የደም አበላ ለማድረግም አይደለም፡፡ የዋሸሁትና ያጭበረበርኩት በአጋጣሚ ነው፡፡

 

ስንቱን እንደሰፌድ አንጓሎ እሚጥለው ማትሪክ እየተባለ እሚጠራው የ፲፪ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ2.2 የማለፊያ ጠርዝ አስቀምጦኝ ተአፋፍ ላይ ነፋስ እንደ ነዳው ሸክላ ዋጋ ቢስ ወይም ቦዘኔ ከመሆን ዳንኩና በ፲፱የ፸፱ ዓ.ም ለአካባቢ ንጽህና ጥበቃ ሳይንስ (ሙያውን በሚያናንቁት ቋንቋ የፀረ-ውሻ ትምህርት) ተመድቤ ቸቸላ ከሚገኘው የጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ገባሁ፡፡ በዚህ የሳይንስ ኮሌጅ የመጀመሪያው ዓመት ትምህርት (ፍሬሽ ማን ኮርስ) አሰጣጥ የጦር ውሎ ወይም አውድማ ይመስል ነበር፡፡ ባስተማሪና በተማሪ መካከል እሚደረገው ትግል በእስራኤላዊና በፍልስጤማዊ መካከል እንዳለው ትግል መፍትሔ ያጣ ነበር፡፡ አስተማሪው ለመጣል ተማሪውም ላለመውደቅ እግር አምቧትረው የሚፋተጉ እንጅ አስተማሪው እውቀትን ለመመገብ ተማሪውም እውቀትን ለመቅሰም እሚገናኙ አይመስልም ነበር፡፡ ለምሳሌ ምግባሩም ግንባሩም የድንጋይ መፍለጫ መርቴሎ የመሰለው የፍልስፍና መምህር በመጀመሪያው ቀን ትምህርቱን(ኮርሱን) ሲያስተዋውቅ “ኤ” ለእግዚአብሔር፣ “ቢ” ላስተማሩት ለፕሮፌሰር መሳይ፣ “ሲ” ለእርሱ፣ “ዲ” ለጎበዝ ተማሪ “ኤፍ” ለሌሎች ተማሪዎች ይልና ተማሪውን ዘወትር ያስፈራራ ነበር፡፡ የያኔው የኮሌጅ መምህር እንደዛሬው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተማሪ ደፍተር ገልጦ በማያውቅ አራተኛ ክፍል የኮር አባል ሽቅብ ቁልቁል ታይቶ “ኤ”ና “ቢ” እንዲሰጥ አይገደድም ነበር፡፡ የያኔው መምህራን እንኳን እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተማሪዎች ፍቅረኛቸውን ከራሳቸው ሾለው ከኪሳቸው ባበጡ ካድሬዎች ተነጥቀው ይቅርና ከሌሎች ልጃገረዶች ጋር ካዩንም ደም በጎረሰ የዓይን ግልምጫና በማርክ ይቀጡን ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የኛ ተማሩ ተብለን ኮሌጅ የታሰርነው ተማሪዎች ዓይኖች የሚተከሉት ከወረቀት እንጅ ፈቃዳችሁን ፈጥሙ ተብለው እንደ ሾላ ፍሬ ተመሬት እንደተወረወሩት የአዳምና ሔዋን አይኖች ውበት ላይ አልነበረም፡፡

 

አርባ ከመቶውን እሚደመስሰው ‘ፍሬሽ ማን’ በምህረት አለፈኝና ወደ ሁለተኛው ዓመት እንደ አንድ ዓመት ልጅ በመዳህ ተሸጋገርኩ፡፡ በሁለተኛው ዓመት የኮሌጅን ኑሮ ስለምደውና የትምህርቱ ጭነትም ሲቀለኝ እንደ ኢስያስ አፈወርቂ ፊት ተጨማዶ የከረመውን አካሌን አካባቢውን እንዲቃኝ አፍታታሁ፡፡ አስተማሪዎቼ እንደሚሉት አካሌ የተፈጠረው ከወረቀት ለመለጠፍ ብቻ ሳይሆን ዘፍጥረት እንዳለው ከእንስት ገላ እንደ ሙጫ ለመጣበቅም መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ በዚህ ረቂቅ ግንዛቤ የተነሳም አዳም ኃጥያቱ እንደ ባውዛ ያበራለትን አይኑን ከሔዋን ገላ እንደተከለው ሁሉ እኔም ሁለተኛ ዓመት እንደ ቀትር ጀንበር ያበራልኝን አይኔን ከኮሌጁ እንስቶች ቁመና፣ ፀጉር፣ ዓይን፣ ከንፈር፣ ዳሌ፣ መቀመጫና ባት ላይ እንደ ጦር መትከል ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን የበራው ዓይኔ እንደ ጦር የተተከለባቸውን የኮሌጅ እንስቶች የህክምና(ዶክትሬት) ተማሪዎች እንደ ጪልፊት ሲልፏቸው እኔ ፀረ-ውሻ ተማሪው እንደ ጀማሪ ገበጣ ተጫዋች ውራ ቀረሁ፡፡

 

ውራ መቅረቴ እንደ እሳት አንገበገበኝና እንደ ሌሎች ፀረ-ውሻ ተማሪ ጓደኞቼ ከፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መረቤን እንደ አሳ አጥማጅ መጣል ጀመርኩ፡፡ ብዙዎቹ አጥማጆች ሲቀናቸው እኔ ግን አሁንም ውራ ቀረሁ፡፡ ውራ የቀረሁት በቁመናዬ፣ በአለባበሴ ወይም በአነጋገሬ ነው እንዳልል በእነዚህ መስፈርቶች ከእኔ እጅግ የሚያንሱት ቀንበጥ ቀንበጦችን እያስከተሉ ሲሄዱ አያለሁ፡፡ መረቤ የማይጠልፍበትን ምክንያት ለማወቅ ጓደኞቼን ስጠይቅ “የጎንደር ኮበሌዎች እንደ ነርሶች ከዶክትሬት ተማሪዎች ጋር መታዬት ስለሚወዱ የዶክትሬት ተማሪ መስለህ መቅረብ አለብህ!” ብለው መከሩኝ፡፡ በሰጡኝ ምክር መላ ጨመርኩና አርብ የካቲት ፲፭ ቀን ፲፱የ፹ ዓ.ም በተማሪ መውጫ ሰዓት ከትምህርት ቤቱ በር ተንቀሳቃሽ ስልክ ታገር እንዳጠፋው ስልክ እንጨት ተገትሬ የሚያልፉትን ኮረዳዎች መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡

 

ኮረዶች ግን አስተማሪዎቻቸው በማርክ ስለገዟቸው ልጃገረዶችና ከአስተማሪዎች ጋር አሊበርጎ ስለሚታዩት ኮበሌዎች እያዋሩ ሳያዩኝ አለፉ፡  “ያጠፋሁትን ሳላውቅ እግዚአብሔርም እንደ አስተማሪዎቼ ጉልበቴን እንደ ልጅ ታቅፌ እንድከርም ፈርዶብኛል!” ብዬ ወደ ዶርሜ ልመለስ ስከጅል ስታጠና ቆይታ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ ሳብ-ረገድ ሳብ-ረገድ እያለች የምትሄድ ጠንበለል አየሁ፡፡ እንደ እንቁጣጣሽ ቄጠማ ከትከሻዋ የተነጠፈውን ጸጉሯን ስመለከት ልቤ እንደ ጠገበ የሰላሌ ፈረስ መጋለብ ጀመረ፡፡ ከፀጉሯ በታች እንደ ላስቲክ እሚታጠፉ እሚዘረጉ ሽንጦቿን፣ ቀጥሎም ሽንጦቿ እንዳይቀነጠሱ አጥብቀው የያዟቸውን ደንዳና ዳሌዎቿንና ዳሌዎቿን እንደ ጋሊሊዮ ፔንዱለም ውዣውዤ የሚያጫውቱትን እግሮቿን ስመለከት ደረቴ እንደ ግርማ ወልደ ጊዮጊስ ሱሪ ዚፕ ባንዴ ተተረተረ፡፡ በተተረተረው ደረቴ ከበለል አይኖቿ፣ ኢትዮጵያዊው ደም ግባቷ፣ ሰንደቅ አፍንጫዋና እምቡጥ ከንፈቿ ሲገቡ ልቤ እንደ ስንደዶ ከመቅፅበት ተሰነጠቀ፡፡ በተተረተረው ደረቴና በተሰነጠቀው ልቤ ገብታ ስትጨርስ የልቤ ሳንቃ ጠብደል እንደገፋው የብረት መዝጊያ “ግው” ብሎ ተዘጋ፡፡ ጠንበለል ጠልፋ ሳንቃዋን የዘጋችው ልቤ ዶላር እንደ ታዬው የአስር ሺ ሜትር ሩጫ ተወዳዳሪ ፍጥነቷን ጨመረች፡፡ ነገር ግን እግሮቼ እንደተቀየደው ደመቀ መኮነን ወርቾች ተሽመደመዱ፤ የስሜት ህዋሳቶቼም እንደ ወጥ አመላላሹ ሀይለማርያም ደሳለኝ ደነዘዙ፡፡ በደነዘዙ የስሜት ህዋሳቶቼና በተሽመደመዱት እግሮቼ መካከል ያሉት ሳምባዎቼ እንደ አንጣሪ ወናፍ በፍጠነት ሲነፉና ሲኮማተሩ ሁለት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ያሽመደመደችኝና ያደነዘዘችኝ ጠንበለል ኮቴዎችም እንደ ገነት መግቢያ እየራቁኝ ሄዱ፡፡

 

የደነዘዙት የስሜት ህዋሳቶቼ ሲነቁና የተሳሰሩት እግሮቼም ሲፍታቱ ጓደኞቼ የመከሩኝንና እኔም የወጠንኩትን መላ ለመፈጸም በፍጥነት ተራመድኩና እንዳላየ አለፍኳት፡  እልፍ እንዳልኩም ጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ እሚለውን መታወቂያዬን ከአስፋልቱ ጣልኩና መውደቁን ያልተገነዘበ ባተሌ መስዬ መጓዙን ቀጠልኩ፡፡ “መታወቂያህ! መታወቂያህን ጣልክ!” አለችና ልትሰጠኝ ብድግ አደረገችው፡፡ “በጣም አመስግናለሁ” አልኩ ያልበላኝን ራሴን እንደ ዋለልኝ መኮነን እያከኩ፡፡ በፍርሃት ተውጬ መሬት- መሬት እያየሁ ልቀበል ስርበተበትና ስደናበር መታወቂያው እንደገና ከመሬት ወደቀ፡፡ በመታወቂያው ፋንታ እጇን ጨበጥኩና እንደ ተፈራ ዋልዋ ድርቅ ብዬ ቀረሁ፡፡ እጇን አጥብቄ ጨብጬ ድርቅ በማለቴ ግራ የተጋባቸው ጠንበለልም “ሰላምታ ነው ወይስ ነጠቃ!” አለችና በሳቅ ፈነዳች፡፡ ደስ እሚለው ሳቋ እንደ ቁልፍ የንግግርን በር ከፈተልኝ፤ እንደ ግብጦ ካቲካላም በፍርሃት የራደውን አካሌን አዝናናልኝ፡፡

 

“የጨበጥኩሽ ለሰላምታ ነው የኔ እመቤት! ኤድስ ለሚባለው አዲስ በሽታ መፈወሻ መድሐኒት ለመፍጠር ጥልቅ ምርምር ላይ ነኝ፡  ይህ ምርምር ስጓዝም፣ ስቆምም፣ ስቀመጥም፣ ስተኛም በአእምሮዬ ስለሚመጣ እቃ እጥላለሁ” አልኩ እንኳን የጻፍኩት የምርምር ጦማር እንደ ተስፋዬ ሐቢሶ ከእነሆሄ ግድፈቱ የኮረጅኩት ወረቀትም ሳይኖረኝ፡፡ ተመራማሪነቴን ተጠራጠረችና “በዚህ ወጣት እድሜህ እንዴት እዚህ ደረጃ ደረስክ?” ስትል ጠየቀችኝ፡፡ “አባቴ የተባበሩት መንግስታት ፕሬዘዳንት የጤና አማካሪ ስለሆነ የተማርኩት ከእንግሊዞች ትምህርት ቤት ነው፡፡ ልዩ ችሎታ ስለነበረኝም ለብቻዬ ኮርስ እየተሰጠኝ አስራ ሁለተኛ ክፍልን በአስራ ሁለት ዓመቴ አጠናከኩ፡፡ ከአስራ ሁለት ዓመቴ ጀምሬ ምርምር ላይ ነኝ” አልኳት ህሊናዬን ግጥጥ አድርጌ እንደ ሽመልስ ከማል ፍቄ፡፡ “የእንግሊዘኛ አስተማሪያችንም አንድ አሜሪካዊ በአስራ ሁለት ዓመቱ የዶክትሬት ዲግሪ እንደጫነ ነግሮን ነበር! አንተም እንደዚያ ልጅ ምጡቅ ነህ ማለት ነው!” አለችና የዋሂቷ ቆንጆ ችሎታዬን አደነቀች፡፡ ቀጥላም “እኔም ባቅሜ የማትሪክ ጥናት ቀልቤን ወስዶብኝ እቃ መጣል ስለማበዛ እናቴ ትጨነቃለች” አለችኝ፡፡ በልቤ “ቀልብሽን የወሰደውን ማትሪክ አሁኑኑ ባደረገኝ” አልኩና “መታወቂያ ከአስፋልት ጥለሽ ግን አታውቂም?” ብዬ ስቀልድ እንደ ጎርፍ ጠራርጎ እሚወስደውን ባህር ፈገግታዋን ለገሰችኝ፡፡ ዛሬ ሳይመጣ ትናንት ኢትዮጵያዊን ኢትዮጵያዊ ተልቡ ያምነው ስለነበር አመነችኝ፡፡ ስላመነችኝም ደስ አለኝ፡፡

 

“ከማትሪክ በኋላ ምን መማር ትፈልጊያለሽ?” ብዬ ስጠይቅ “እግዜር ከረዳኝ ሐኪም መሆን እመኛለሁ!” አለች፡፡ “እግዜርም ይረዳሻል፤ እኛም እንረዳለን” ስላት “እግዚአብሔር ይስጥልኝ!” ብላ ደጋግማ መረቀችኝ። ስለሕክምና ትምህርት እየመከርኳት ስንጓዝ ወደ ፒያሳ የሚሄድ ጋሪ መጣ፡፡ ጋሪውን አስቁሜ እንድትወጣ ስጋብዛት ተጋሪው አልሳፈርም ብላ ለደቂቃዎች ተግደረደረች፡፡ በልቤ “መግደርደር የኢትዮጵያውያን ወግ ነው” አልኩና ወገቤ ቅልጥም እስቲል ደጋግሜ ለምኛት በጋሪው ተጉዘን ሻይ ልንጠጣ ኢትዮጵያ ሆቴል ገባን፡፡ “የምርምር ጊዜህን እንዳላባክንብህ ብንሄድ አይሻልም?” አለች እየተሽኮረመመች ሰላሳ ደቂቃቆች አብረን እንደቆየን፡፡ የተማረ ለመምሰል እንግሊዘኛ ተሽሮ እንደሚጣል ቋንጣ ጣል ጣል እንደሚያደርግ ማንኛውም ድስኩራም ኢትዮጵያዊ ምሁር እንግሊዘኛ ቀላቀልኩና “ምርምሩ ‘ኦልሞስት’ አልቋል! ብዙን ጊዚዬን እማሳልፈው በአሜሪካና በአውሮጳ ተመሳሳይ ምርምር የሚያደርጉትን ሳይንቲስቶች በማማከር ነው” አልኳት፡፡ “እነዚህን ነጫጭባዎችንስ አትመናቸው! ግኝትህን ይሰርቁብሃል!” ብላ አስጠነቀቀችኝ፡፡ “አይ አበሻ ጠርጣራው!” ብዬ ፈገግ አልኩ፡፡ እርሷም ፈገግ አለችና “ወደን አደለም! መሰሪ ስለሆኑ ነው! አጼ ቴዎድሮስ መድፍ መስራት የሚያስተምር ሰው ሲጠይቅ ሰላይ ላኩለት፡፡ ለምን ሰላይ ላካችሁ ብሎ ሲቆጣ ወረው ራሱን እንዲሰዋ አደረጉት፡፡ ይዘውት የመጡትን ጦር ለካሳ ምርጫ አስታጥቀውና ጡት አጥብተው አስነገሱና የጎንደርን፣ የጎጃምንና የወሎን ሕዝብ እንዲያሰቃይ አበቁት፡፡ አሁንም አስተማሪዎቻችን “ነጫጭባዎች አገራችን ለመከፋፈል እገንጣይ አስገንጣዮችን እየረዱ ለቀውብናል!’ ሲሉ እሰማለሁ ” አለች በቁጪት፡፡ “አይዞሽ አትስጊ የእኔን ግኝት ፈረንጅና ኢምፔሪያሊዝምን እሚጠላውና በደም የተሞላ ጠርሙስ አስመስሎ በንቀት እሚወረውረው መንግስት እየጠበቀው ነው!” አልኳት፡፡ “ኢትዮጵያ እንዳንተ ዓይነት እሚያኮራ ሰው ማፍራቷ ደስ የሚል ነው” አለችና ወደ ቤቷ ለመሄድ ሰዓቷን አየች፡፡ አንድ ሰዓት ከአስራ አምስት ደቂቃ ተጨዋውተን ስንለያይ” ስምሽን ማን ልበል?” ስል ጠየኩ፡፡ “ኢትዮጵያ እባላለሁ” አለች፡፡ “ደሰ የሚልና ክብር ያለው ስም!” አልኩና “ይህ ሆቴል ያንቺ ከሆነማ ሂሳብ መክፈል የለብኝም!” ስል ቀልድኩ፡፡ “ይህ ሆቴል የኔ ቢሆንማ ምርምሩን እዚህ ታረገው ነበር! እኔም ረዳትህ እሆን ነበር” አለችና ሳቀች፡፡ “ዳዊት እባላለሁ!” አልኩና የዲፓርትመንታችንን ስልክ ቁጥር ሰጠኋት፡፡ ቀጥየም “እኔ አብዛኛውን ጊዜ ላቦራቶሪ ወይም ከውጪ ሳይቲስቶች ጋር ስብሰባ ላይ ስለምሆን ለጸሐፊዬ መልእክት መተው ትችያለሽ፡፡” አልኳትና ተለያየን፡፡

 

ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኘን በነጋታው ከአዲስ አበባ ስጦታ እያመጣሁ ለተግባባኋት የዲፓርትመንታችን ጸሐፊ ምስጢሬን እንደ ፈርስ ዘከዘኩና ኢትዮጵያ የምትባል ልጅ ስትደውል “ሳይንቲስት፣ ፕሮፌሰር ዳዊት ከአሜሪካና ከአውሮጳ ከመጡ ተመራማሪዎች ጋር ስለፈጠረው የኤድስ መድሐኒት በመዋያየት ላይ ናቸው ካልሽ በኋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ደውይ በያት!” አልኳት፡፡ ጸሐፊዋ “ይህንን አላምንም በሚል ስሜት” ራሷን በእጆቿ ይዛ በጉረሮዋ ቧንቧ ጨጓራዋ እስከሚታይ አፏን እንደ ዓባይ ሸለቆ ከፈተችና “እኔ ሴቲቱ በሌላ በተለይም ኢትዮጵያ በምትባል ሴት ላይ እንደዚህ አይነቱ ማጭበርበር እንዲፈጸም አልፈቅድም!” አለች፡፡ ልብ በሉ! ይህንን ማጭበርበር የፈጸምኩት እንኳን እውነተኛ ዲፕሎማ ጊዜ እንደሙጃ እንዳፋፋቸው ቆስጠንጢኖስ በርሄና እንደ አባዱላ ገመዳ በሙስና እንደማሽላ የተሸመተ ዲግሪም ሳይኖረኝ ነው፡፡ የተሸመተ ዲግሪ እንኳ እንደሌለኝ የምታውቀዋ ጸሐፊ የሚያምር ሐብል አንገቷ ላይ ካጠለኩላት በኋላ የጠየኳትን ቃል በቃል ፈጸመችልኝ፡፡ ኢትዮጵያም በዘጠኝ ሰዓት ደወለች፡፡ በአስራ ሁለት ሰዓት ተራራ ሆቴል ልንገናኝ ተቀጣጠርን፡፡

 

በቀጠሮው ሰዓት ተራራ ሆቴል ተጨዋውተን ተለያዬን፡፡ በሳምቱም ትግሬ መጮሂያ አካባቢ ከሚገኘው ጎሀ ሆቴል ተዝናንተን ተመለስን፡  ግንኙነታችን እንደ ሮኬት ፈጠነና ተፋቅረን ማንኛውም ፍቅረኛ የሚያደርገውን አደረግን፡፡ ጀርመን ይኖሩ የነበሩት እህቶቼ ገንዘብ ስለሚልኩልኝ በየቦታው እየወሰድኩ ስለማዝናናትና የኪስ ገንዘብም ስለምሰጣት የደግ መጨረሻ አድርጋ ቆጠረችኝ፡፡ አንድ ቀን ፎገራ ሆቴል ስንዝናና “ለእናቴም ይለፍልሽ ሲላት ገብርኤል አንተን ጣለለኝ!” አለችኝ፡፡ “እናትሽ ችግር አለባቸው?” ብዬ ስጠይቃት “እናቴ ያሳደገችኝ ጠላ እየሸጠች ነው!” አለችና እንባዋ እንደ በረዶ ዱብ ዱብ ማለት ጀመረ፡፡ “ታድያ ለምን ታለቅሻለሽ” ብዬ ስጠይቃትም “አባቴ ትዝ ብሎኝ!” አለች፡፡ “አባትሽ ባገር የሉም? ብዬ ስጠይቅ “አባቴ በሚሊሻነት የሶማሊያን ወራሪ ተዋግቶ ወዲያው እንደተመለሰ ሰሜን ግንባር ዘመተ፡፡ እንዳለመታደል ናቅፋን ሲያስለቅቁ የተጠመደ ቦንብ ፈንድቶ ህይወቱ አለፈ” አለችና አባቷ እሽኮኮ ተሽክመዋት የተነሱትን የህፃንነቷን ፎቶ ከቦርሳዋ አውጥታ እያየች ያኔ እንደተረዳች ሁሉ ጧ ብላ አለቀሰች፡፡ ሳግ እየተናነቃትም “ለአባቴም ለእናቴም ብቸኛዋ ልጅ ነኝ፤ አባቴ በረሃ ለበረሃ ሲኳትን ከቤት የተቀመጠበት ጊዜ ስላልነበረ ሌላ ወልደው ለማሳደግ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡ አባቴ ለእኔ ያለው ፍቅር ልዩ ነበረ” አለችና አሁንም እንባዋ ግድብ እንደጣሰ ውኃ መፍሰስ ጀመረ፡፡ ጨነቀኝና “አይዞሽ! አሁንማ እኔ አለሁልሽ፤ እንደ አባትም፣ እንደወንድምም፣ እንደፍቅረኛም እሆንሻለሁ!” አልኩና ሳጽናናት “እሱስ ጓደኞቼም አንቺማ ታድለሽ ፕሮፌሰር ዳዊት አሜሪካ ወይም አውሮጳ ልኮ ያስተምርሻል ይሉኛል” አለች፡፡ “ችግር የለም ማድረግ የሚቻለው ይደረጋል” አልኳትና ከሐዘኗ ወጥታ እንደበፊቱ በጨዋታና በሳቅ ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ተለያየን፡፡

 

ፍቅር በጀመርን በሶስተኛው ወር ሚያዚያ ፲፭ ቀን ደወለችና መጀመሪያ ስንተዋወቅ ሻይ ከተጣንበት ኢትዮጵያ ሆቴል ከቀኑ አስር ሰዓት እንገናኝ አለችኝ፡፡ “ኢቶጵ ለሶስት ወር ‘አንቨርሰሪ’ መሆኑን ነው!” ብዬ ቀለድኩና እሽ እመጣለሁ አልኳት፡  በተቀጣጠርነው ሰዓት ኢትዮጵያ ሆቴል ስገባ አለወትሮዋ ፊቷ በኮባ እንደተጋገረው የእማማ ይመኙሻል ቡሔ ዳቦ ተነፋፍቶና ጸጉሯ እንደ ቡቱ ቡትቶ ተንጨባሮ ከውሻ የተጣላ አነር ድመት መስላ አገኘኋት፡፡ “ምነው ኢትዮጵያ? ምን ሆነሻል?” ብዬ ስጠይቅ ብድግ አለችና በእኒያ አለንጋ ጣቶቿ ግራ ፊቴን “ጩዋ! ጩዋ!!” የሚል ድምጥ እስከሚያሰማ ደጋግማ ጠፈጠፈችኝ፡፡ “ጠፈጠፈችው አንተ” ስትል አንድ ውበታም ኮረዳ “ፊቱ ስንበር በስንበር ሆነ” አለ አብሯት የተቀመጠው ለጊዜው የታደለ በኋላ ግን የኔ እጣ ሊደርሰው የሚችል በመጀንጀን ላይ ያለ ጎረምሳ፡፡ “አንደኛውን ጉንጭህን ሲመታህ ሁለተኛውን ስጠው!” የሚለውን የሉቃስ ወንጌል ተከትዬ ሳይሆን በድንጋጤ ግራየን ስትጠፈጥፈኝ ቀኝ ፊቴን ሰጠሁ፡፡ ከግራ በመጠፍጠፉ ወደ ቀኝ የተጣመመውን ፊቴን በቀኝ ስትደግመው ወደ መሐል መጣና የድሮ ቦታውን ያዘ፡፡ ከዚያም “አንተ ውሻ ገዳይ! አንተ ብሎ ፕሮፎሰር! አንተ ብሎ ሳይንቲስት! አንተ ብሎ የኢትዮጵያ አለኝታ! ሞላጫ ሌባ” አለችና ሆዴን በእርግጫ ስታፈነዳው እንደ ተቆረጠ ዛፍ ከመሬት የእንግላል ተዘረርኩ፡፡ “ኢቲ.. ኢቲ. ኢትዮጵያ የሰው ወሬ ሰምተሽ አትጨክኝብኝ!” ብዬ ሳልጨርስ “የውሻ ገዳይ ተማሪ መለዮህን ለብሰህ ከመስክ ስትመለስ ባይኔ በብረቷ አይቼሃላሁ!” አለችና ሽሼን ሶስት ጊዜ ጌታዋንም ኮርቻዋንም ተመሬት እንዳነጠፈች በቅሎ ረገጠችኝ፡፡ ፍሬዎቼን ግን እግዚአብሔር እንደ እንቁላል ፉሽርክ ብለው ከመፍረጥ አዳነልኝ፡፡ ከወደኩበት አንስተው ሽማግሎች ሲገላግሉን እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ እየተሳደበች መዳረሻዋን ሳታውቅ ከቋራ ሆቴል ወደ ፋሲል ግንብ የሚያስኬደውን ሰፊ መንገድ ማቋረጥ ጀመረች፡፡

 

ያቆሰለችውን ሆዴን በግራ እጄ ደግፌ እየተከተልኩ “ኢት.. ኢትዮጵያ! አንዴ ስሚኝ! አንዴ አዳምጭኝ የኔ ቆንጆ!” እያልኩ ስጣራ “ሰይጣን ይጥራህና አትጥራኝ!” ብላ ከመንገዱ መሐል ወደኔ ስትዞር በፍጥነት እሚሽከረከር ፍሬን አልባ መኪና ከአስፋልቱ አነጠፈና ደፈጠጣት፡፡ ህይወቷ እንደ ሳሙኤል አወቀ በአጭሩ ተቀጨ፡፡ አንገቷ ተቀንጥሶ፣ እግሮቿና እጆቿ ተገነጣጥለው አየሁ፡፡ በድንጋጤ ህይወቴን ሳትኩና ከመንገዱ ዳር ወደኩ፡፡ ከድንጋጤዬ ስንቃ በጭነት መኪና ባህርዳር ገብቼ አደርኩ፤ በነጋታውም አዲስ አበባ ተሳፈርኩ፡፡ ባለቤታቸውን በአገር አድን ጦርነት፣ አንድ ልጃቸውን በመኪና ያጡት ጠላ ሻጯ የኢትዮጵያ እናትም ሞቷን ሲሰሙ ራሳቸውን አጥፍተው ተዚህ ዓለም እንደተለዩ ተረዳሁ፡፡ በራሴ ጥፋት ከተማውንም ስለጠላሁ የጎንደርን ምድር ዳግም ሳልረግጥ እስከዛሬ አለሁ፡፡

 

ዛሬ ግን ልዩ ሰው ሆኛለሁ፤ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ዳዊት ንስሀ ገብቻለሁ፡፡ በውሸትና በማጭበርበር ኢትዮጵያን በመግደሌ ተፀፅቻለሁ፡  ኢትዮጵያ እጇን ዘርግታ ወዳንተ መጥታለችና ተቀበላት እያልኩም በዋሽንት እዘምራሁ፡፡ እድሜ፣ መከራና ፀፀት ከህሊናዬም ከእግዚአብሔርም እንዳስታረቁኝ አምናለሁ፡፡ “ሞኝህን ፈልግ በወንጌል ማጭበርበርን በታምራት አይተነዋል!” እንደምትሉ እገምታለሁ፡፡ እንደ ታምራት ፍርድንና ቅጣትን ለማምለጥ በደም በተንከረ እጄ ወንጌል እንዳልጨበጥኩ አውቃለሁ፡፡ ፍርዴንና ቅጣቴን ተቀብዬ ከህሊና ቁስል፣ ከታሪክ እርግማንና ከገሐነብ እሳት ለመዳን ወደ ህሊናዬ፣ ወደ እውነት፣ ወደ ክርስቶስ፣ ወደ ጭንቅ አማላጅቱ ተመልሻለሁ፡፡ የመዋሸትንና የማጭበርበርን ፀረ-ሰውነት ተረድቻለሁ፡፡ በጊዚያዊ ስሜት ተወጥሬ አንድ ጉብል አጭበርብሬ ለእናትና ልጅ ሞት ምክንያት ተሆንኩ በቤተክርስትያን መንበር፣ በመስጊድ አመራርና በሕዝብ አስተዳደር ወንበር ራሳቸውን ኮፍሰውና በጊዚያዊ ጥቅም ሰክረው አገርና ዓለምን እያጪበረበሩ ያሉት ስንቱን ሕዝብና ትውልድ እንደሚገሉት እያሰላሁ በሐዘን ውስጥ እገኛለሁ፡፡

 

ይህንን አሳዛኝ ታሪክ ስትሰሙ “ምነው የእንሽርት ውኋ ሆነህ በቀረህ! ምነው ድፍት ባልክ!” እያላችሁ እንደምትረግሙኝ እረዳለሁ፡፡ እርግማናችሁን ብረዳም በአዲስ ዓመት ከልቡ ንስሀ ለገባ ምህረት ደንብ ነውና ምህረትን እለምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ለጊዜአዊ ጥቅም በውሸትና በማጭበር እምነቷን፣ አላማዋን፣ ወኔዋና ተስፋዋን ጎድቼ ተገነጣጥላ እንድትሞት በማድረጌ ማሩኝ እላለሁ፡፡ “እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ፣ ኢትዮጵያን መለኮት እንደ ወላዲት አምላክ ያንሳት!” እንድትሉኝ እጠይቃለሁ፡፡ ከጫማችሁ ተደፍቼ ማሩኝ እላለሁ! ድንጋዩን እንድታነሱልኝ እማጸናለሁ፡፡ ከህሊና ቁስልና ከታሪክ እርግማን እንድንን ! ማሩኝ! ማሩኝ! ማሩኝ! እያልኩ ይኸንን ንስሀ ከዳዊት መዝሙር እዘምራለሁ፡፡

 

አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፣

እንደ ምህረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።

ከበደሌ ፍጽሞ እጠበኝ፣

ከኃጢአቴም አንጻኝ፣

እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፣

ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና፣

አንተን ብቻ በደልሁ፣

በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፣

በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹህ ትሆን ዘንድ፣

ማረኝ እላለሁ፡፡

 

መስከረም ሁለት ሺ ስምንት ዓ.ም.

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop