በረከት ነው መርገምት? -ጠገናው ጎሹ

/

December 5, 2023

ጠገናው ጎሹ

መርገምት

ጋዜጠኛና ደራሲ አቤ ጎበኛ ከዛሬ ግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት (አኢአ በ1966) ለንባባብ ባበቃት በመጠን ትንሽ በይዘት ግን ግዙፍ እውነት ለያዘችው መጽሐፉ ዋና ገፀ ባህሪ ባደረገውና ሳይፈልግ የአስከፊው የጎዳና ላይ ኑሮ ሰለባ ከነበረችው ምስኪን እናቱ ተወልዶ በማደግ ይሠራበት በነበረው መ/ቤት የሚሠሩ ባልደረቦቹ መብት ተሟጋች በመሆን የባርነትንና የጉስቁልናን ሥርዓት በመቃወሙ ምክንያት በጥይት ተደብድቦ እንዲሞት የተበየነበት አልወለድምን ፦

“ሁሉም ፈስሶ ሲቀር አስተናባሪ አጥቶ ፣

ይህን ሁሉ እያየ የሚጨነቅ ፍጡር

ምን ሰላም ያገኛል? ማረፍ እንጅ ሙቶ።

የምላችሁ ሁሉ ምንም ካልገባችሁ ፣

እግዜር ልባችሁን ስስ አድርጎባችሁ፣

እኔን ውስጤ ገብቶ ያቃጠለኝ ሃዘን ገብቶ በውስጣችሁ፣

እናንተን እንደ እኔ በጣም ያቃጥላችሁ” በሚል የተሰማውን መሪር ሃዘን እንዲግልፅ አድርጎታል።

የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለሩብ ምእተ ዓመት በህወት መራሽነት የመጣንበትንና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኛ ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን የበላይነት እና የወራዳነት ፖለቲካ በማይሰለቻቸው ብአዴኖችተባባሪነት እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ የምንገኝበትን የመከራና የውርደት ዶፍ በግፍ ተገድሎ ከተቀበረበት መቃብር ተነስቶ ቢያይና ቢሰማ ምን ሊሰማው እንደሚችል ለመረዳት የሚቸግር አይመስለኝም። ከገዛ ራችን ግዙፍና መሪር እውነት እየሸሸን የሰብብ ድሪቶ የመደረታችን ክፉ ልክፍት የህሊናችንን ሚዛናዊነት ጨርሶ ካላበላሸብን በስተቀር።

እንደ መግቢያ ይህንን ካልኩ ወደ እኔው ርእሰ ጉዳይ ልለፍ፦

በጎቹ በተኩላ መድረሻ ሲያጡበት፣

የአባት (የእረኛ) ያለህ ብለው ድረስልን ሲሉት ፣

እንኳንስ አለሁ ሊል ሊደርስ ከመቅፅበት፣

አቅም እንኳ ሲያጣ ከምር ለመቆጣት፣

ተኩላዎችን ደፍሮ አቁሙ ለማለት፣

የግድ ካስፈለገም ለመሆን ሰማዕት ፣

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዛሬው ያገራችን ሁኔታ ከዲፕሎማሲ አንጻር ሲታይ - ባይሳ ዋቅ-ወያ

ሰበብ ሲደረድር ሲያመነታ መስማት ፣

የጭንቀት ገፅታ ሲያጠላበት ማየት ፣

በረከት ነው መርገምት?

ያስተሳሰረውን ሰውን በሰውነት፣

በእግዚአብሔር ልጅነት፣

በእርሱም አምሳልነት፣

ፀንቶ ለማስቀጠል ከመቆም በፅዕናት፣

ጥንብ ነው ለሚሉት የዘር ፖለቲካ አሳልፎ መስጠት፣

ለምን? ሲባል ደግሞ “ለሰላም” ነው ማለት፣

የተምታታበትን ይበልጡን ማምታታት፣

ምን እንበለው በእውነት?

በረከት ነው መርገምት?

የተሸከሙትን ሥልጣነ ሃይማኖት፣

መወጣት ሲያቅታቸው በተግባረ ፅዕናት፣

ብሎም በአርአያነት፣

ለመከረኛ ህዝብ ለጠማው ነፃነት፣

እረኞቼ ብሎ ለሚቀበል በእውነት፣

ጉንብስ ቀና እያለ ለሚሰጥ አክብሮት፣

የሰበብ ድሪቶ ሲደራርቱለት ፣

በረከት ነው መርገምት?

ብሎ ቢጠይቅስ ምኑ ላይ ነው ስህተት?

ሰው ሆኖ መሳሳት ፣ ብረት ሆኖ ዝገት ፣

እያልን የምንጠቅሰው ተምሳሌተ ተረት፣

ቢሆንም እንኳ እውነት፣

ልኩን እየሳቱ እረኞች ነን ማለት ፣

በጎችን ረስቶ ከተኩላ ትሽሽት ፣

እስኪ እንነጋገር ስለ እውነት በእውነት፣

በረከት ነው መርገምት?

ወይ በቅድስና ወይ በብፁዕነት ፣

የተሸከሙትን ታላቅ ሃላፊነት፣

በአግባቡ መዝነው ሥራ ካልሠሩበት፣

ቀድሞ እነርሱ ድነው ሰው ካላዳኑትበት፣

አላስድን ያሉትን ደፍረው ለመገሰፅ ካልተጠቀሙበት፣

በግፍ ለተገፋው ጠበቃ ካልሆኑት ፣

ታዲያ ምን እንበለው ይህን መሪር እውነት?

በረከት ነው መርገምት?

ከገዛ ራሳችን ዘመን ጠገብ ውድቀት፣

ሰብረን እንዳንወጣ የሆንበት ምክንያት፣

አለመማር አይደል ከራሱ ከውድቀት?

ታዲያ ይህ አይነቱን የውድቀት አዙሪት ፣

ምን ስም እናውጣለት?

በረከት ነው መርገምት?

እንኳንስ ሊወጡ ከዚያ ከመጡበት፣

የብዙ ዓመታት የሰላም ፀርነት፣

የአገር አፍራሽነት የግፍ ገዳይነት፣

መድረሻ የማሳጣት ሰውን በማንነት፣

የግፉን ደረጃ ከፍ ባደረጉበት፣

በዚህ አስከፊ ወቅት፣

በቃችሁ በማለት፣

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለሃያ ሁለት ማዞሪያ ሰማእታት - አሁንገና ዓለማየሁ

ለሁሉም የሚደርስ ጩኸት ከማሰማት፣

ይበጃል ያሉትን የየራስን ግብአት ወደ ፊት ከማምጣት፣

እንዲያው በደምሳሳው ሰላም ይውረድ ማለት ፣

እየተከተሉ የክስተት ትኩሳት ፣

አውጀናል ማለት ምህላና ፀሎት ፣

ደግሞ እንደ ገዥዎች መግለጫ መደረት፣

እስኪ እንጠያየቅ ስለ እውነት በእውነት፣

በረከት ነው መርገምት?

ይህ ሁሉ ድብልቅል በተባባሰበት፣

የመከራው ብርታት እጅግ በከፋበት፣

የገዦቻችን ግፍ በተንሰራፋበት ፣

የርሃብ ቸነፈር እጅግ በከፋበት፣

የጤንነት ጉዳይ ጭንቅ ውስጥ ባለበት ፣

የባእዳን ምፅዋዕት ብርቅ በሆነበት፣

የቅድሚያ ቅድሚያና የርብርብ ትኩረት ፣

ከዚሁ አኳያ መሆን ሲኖርበት፣

ምንም እንዳልሆነ በሚያስመስል ስብከት፣

እጅግ በሚፈትን የመድረክ ላይ ተውኔት፣

በሳምንታትና በ24 ሰዓታት፣

እያነበነቡ እንቅልፍ አልባ ትርክት፣

ለባህር ማዶው ገዳም ወይ ቤተ እምነት፣

ዶላር አትሰስቱ ቁልፉ ይኸውና የሰማየ ገነት፣

በሚል ዘመቻ ላይ ተጠምዶ መገኘት፣

በረከት ነው መርገምት?

በእውን ለሚያስተውል ወጥቶ ከግልብ ስሜት ፣

በዚህ ዘመቻ ላይ የቀረበን ትርክት፣

ለተከታተለ ከምር በቅንነት፣

በሚዛናዊነት፣

በሃይማኖትና በአገር ወዳድነት፣

ያጣው አይመስለኝም የእኛኑ እኛነት፣

የገባንበትን የውድቀት አዙሪት።

ህሊናቸው ሲያውቀው ያሉበትን እውነት፣

የሃላፊነትና የተልእኮ ክሽፈት፣

ቅድሚያ ግድ ለሚለው ቀድሞ ከመገኘት ፣

ጥቅምን እያሰሉ እረኞች ነን ማለት።

ምን ብለን እንጥራው ታዲያ ይህን ልክፍት?

በረከት ነው መርገምት?

እናም ያ የመጣንበት፣

ለአያሌ ዘመናት፣

የእኩያን አገዛዝ የኢሰባዊነት፣

የእኛም የራሳችን የውድቀት አዙሪት፣

ዛሬም የቀጠለው ጭራሹን ብሶበት፣

ነገ ሳይሆን ዛሬ መገታት ካለበት፣

መርገምት በበረከት መሸነፍ ካለበት፣

የግድ ይላል ወቅቱ እምቢ በቃን ማለት፣

የባለጌንና የጨካኝን ሥርዓት።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share