November 16, 2023
3 mins read

ቆሜ ነው እምሞተው ( አሥራደው ከካናዳ )

ለነፃነት፤ ለእኩልነትና ለወንድማማችነት፤ ለሚታገሉ የለሕሊና እስረኞችና ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ለሚዋደቁ የፋኖ ጀግኖች መታሰቢያ ትሁንልኝ ::
ለነፃነት፤ ለእኩልነትና ለወንድማማችነት፤ ለሚታገሉ የለሕሊና እስረኞችና ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ለሚዋደቁ የፋኖ ጀግኖች መታሰቢያ ትሁንልኝ ::

አልጠብቅም ሞትን – ተኝቼ ባልጋዬ ፤
እኔው እሄዳልለሁ – ፈረሴን ቼ ! ብዬ ፤
አልፈልግም ዋሻ – የምደበቅበት ፤
አልፈልግም ጢሻ – የምሸሸግበት ፤
አልሰብርም አንገቴን – አላዞርም ፊቴን ፤
አይዝልም ጉልበቴ – አላጥፈውም ክንዴን ፤
እጠብቀዋለሁ – ደረቴን ነፍቼ ፤
በኩራት በድፍረት – አንገቴን አቅንቼ ፤
አልንበረከክም – ቆሜነው እምሞተው ፤
የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!
በ’ንባ አልታጠብም – ቁጭብዬ አላለቅስም ፤
ጉልበቴን አጥፌ – አልንበረከክም ፤
አልጠብቅም እሱን – ወደኔ እስቲመጣ ፤
እኔው እሄዳለሁ – ወደሱ እንዳይመጣ ፤
ኩራቴን ይረዳው – ድፍረቴን ይወቀው ፤
ተጋድሜ አልሞትም – ቆሜነው እምሞተው !!

አልጠብቅም ሞትን – ማታ በጨለማ ፤
እንዲወስደኝ ብዬ – ሰው ሳያይ ሳይሰማ ፤
አለምንም ከቶ – ዛሬን እንዲተወኝ ፤
ዘግይቶ እንዲመጣ – ዕድሜ እንዲለግሰኝ ፤
ወይ እንደ ባለጌ – እያሞላቀቀ ፤
ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ እያጨማለቀ ::
ጭራሽ !
እጠብቀዋለሁ – በጠራራ ፀሐይ ፤
መሃላዬ ይሁን – ቃል ለምድር ለሰማይ ፤
ዳግም ድል አድርጌ – እስክነሳ ድረስ ፤
ቆሜነው እምሞተው እንደ ክርስቶስ ::
አገኛለሁ ብዬ – ትርፍራፊ እድሜ ፤
አልጠብቅም ከቶ – እኔ ተጋድሜ ፤
ወደሱ እሄዳለሁ – ወደ’ኔ እንዳይመጣ ፤
ግንባሬን አላጥፍም – የመጣው ቢመጣ ፤
ተኝቼ አልጠብቅም – ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ ፤
እኔው እሄዳለሁ – በቁሜ እንዲያገኘኝ ::
ለመኖር ጓጉቼ – አልንበረከክም ፤
ዛሬን ተወኝ ብዬ – አልለማመጥም ፤
አልንበረከክም – ቆሜነው እምሞተው ፤
የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!

ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ( November 17. 11. 2023 )

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop