October 6, 2022
15 mins read

መስከረም 26 ቀን 1928 ዓ.ም – እንደ ወጣ የቀረው ደራሲ የልደት ቀን ሲታወስ

ከ 88 ዓመት በፊት መስከረም 26 ቀን 1928 ዓ.ም አንጋፋው ደራሲ እና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ከህንዳዊ አባቱ እና ከኢትዮጵያዊ እናቱ በኢሊባቡር ሀገር ሲጴ በምትባል ስፍራ የተወለደው ዕለት ነበር።

⩩ የበዓሉ ወላጆች

Bealuየበአሉ አባት ወላጅ አባት ስም ግርማ ሳይሆን ጂምናዳስ ይባላል፡፡ (ሞልቬር ‘ብላክ ላየንስ’ በሚለው መጽሐፉ ግርማ የእንጀራ አባቱ እንደሆነ ሲገልጽ እንዳለጌታ ደግሞ ‘በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ’ በሚለው መጽሐፉ ግርማ አባቱ ሳይሆን በዓሉ ከሱጴ ተነስቶ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ተቀብሎ ያሳደገው ነው ይላል፡፡)

ጂምናዳስ ፣ የተወለደው ህንድ ውስጥ ጉጅራት በተባለ ከተማ ነው፡፡ በእዚያ ከተማ ውስጥ ዝርያችን ከኢትዮጵያ ይመዘዛል የሚሉና ራሳቸውን “ሀቢሲስ” ወይም “ሲዲስ” ብለው የሚጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ ሀቢሲስ ማለት ከሃበሻ ሃገር የመጣ ህዝብ ማለት ሲሆን ሲዲስ የሚለው ደግሞ ስድስተኞቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች ማለት ነው፡፡ የበአሉ እናት ያደኔ ቲባ የምትባል የሱጴ ቦሩ ተወላጅ ናት፡፡ በጊዜው አባቷ በሚነግዳቸው ንግዶች ስር ትሰራ የነበረ ሲሆን ጂምናዳስ ደጋግሞ በወቀየው ሲያመራ በውበቷ ተማርኮ በወጉ መሰረት ሽማግሌ ልኮ ነበር የተጋቡት፡፡

ህንዳዊ አባቱ ለልጁ ያወጣው ስም “ባሉ” የሚል ሲሆን ትርጓሜውም ከህንድ ቋንቋዎች ባንዱ “እድለኛ” ማለት ነው፡፡ ሰዎች ስያሜው አዲስ ስለሆነባቸው ለአጠራር እንዲቀላቸው በአሉ እያሉ ይጠሩት ጀመር፡፡ ስሙም በዛው ቀጥሎ መደበኛ መጠሪያው ሆነ፡፡ የሚጠራው በወላጅ አባቱ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ነው፡፡ ያደኔ ቲባና ጂምናዳስ በአሉን ብቻ አይደልም የወለዱት፡፡ ከበአሉ ቀጥሎ ሶሎሞን የሚባል ልጅም ወልደው ነበር፡፡ ነገር ግን ሶሎሞን ሁለት አመት ከመንፈቅ እንደሆነው በተነሳው ፈንጣጣ በሽታ ህይወቱ አልፏል፡፡

⩩ የበዓሉ የትምህርት እና የስራ ህይወት

አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በኢሊባቦር፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ከዛም በመቀጠል ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ወደ አሜሪካ በመሄድ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በአሉ ትምህርቱን እንደጨረሰ ፣ ስራ የጀመረው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ነበር፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ሳለም ዜና ያነብ ጋዜጣም ያዘጋጅ ነበር፡፡ የ’መነን’ና ‘አዲስ ሪፖርተር’ መጽሔቶች የ’አዲስ ዘመን’ና ‘ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ’ አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በእነዚህ ጋዜጦች ላይ ከፍ ያለ ለውጥ እንዳመጣም ይነገርለታል፡፡

በአሉ፣ በጋዜጦቹ ከመንግስት አቋም ውጪ የሆኑ ጽሑፎችን ወይም የዘውድ ስርአቱንና የመንግስት ባለስልጣኖችን የሚተች ጽሑፎችን ያስተናግድ ነበር። በእነዚህም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከመሰጠትና ከሥራ እስከመታገድ ደረጃ ደርሷል፡፡ በግሉም ሌሎች ማለትም እንደ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር እና ሰለሞን ደሬሳ አይነት ተጋባዥ ጸሐፊዎችን እያስተባበረ የግል ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ለማቋቋም ቢፈልግም በመንግስት ክልከላ ይታገድበት ነበር፡፡

ከዚህ ባሻገርም፣ ከአብዮቱ በኋላ የዜና አገልግሎት ኃላፊ፣ በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመሆን አገልግሏል። ከአብዮቱ በኋላ በአሉ ከመንግስቱ ሃይለማርያም ጋር ጥብቅ ግንኙነት መስርቶ እንደነበር ይነገራል፡፡ (እራሳቸው ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ለገነት አየለ እንደነገሯት ከሆነ የበአሉ ግርማና የመንግስቱ ትውውቅ ሰባ ደረጃ አካባቢ በሚገኝ አንድ ባር ውስጥ ነው፡፡ በአሉ እዚያ ባር ውስጥ ወዳጁ ከነበረችው ድምጻዊት ብዙነሽ በቀለ ጋር ይመላለስም ነበር፡፡) በአሉ ከመንግስቱ ጋር በነበረው ጥብቅ ግንኙነት የኤርትራውን የቀይ ኮከብ ዘመቻ አጋዥነት ደርሶም ነበር፡፡ ከዚህ ዘመቻ በፊት የእሱ “የቀይ ከከብ ጥሪ” የሚለው መጽሐፍ ወጥቶ ስለነበር ዘመቻው ጥሪም ከዚህ መጽሐፍ ርእስ እንደተቀዳ ይነገራል፡፡ በዚህ ዘመቻም ሊቀመንበሩ በአሉን ወደ ዘመቻው ይዘውት ሄደው ነበር፡፡ የመጨረሻ የሆነው ‘ኦሮማይ’ የተሰኘው ልቦለዱን የፃፈው ያንን በ1 974 ዓ.ም ኤርትራ ክፍለሀገር የተካሄደውን ዘመቻ መሰረት አድርጎ ነው፡፡

⩩ የበዓሉ የፍቅርና የትዳር ህይወት

በአሉ ቆንጆ ሴት አይቶ አድናቆቱን ሳይገልፅ የማያልፍ ነበር፡፡ ከተወዳጇ ድምጻዊት ከብዙነሽ በቀለ ጋርም ፍቅር ውስጥ ገብተው እንደነበረም ይነገራል፡፡ ሆኖም ብዙነሽ በቀለና በአሉ ግርማ በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት ተለያዩ፡፡ ከብዙነሽ የተለያየው በአሉ ብዙም ሳቆይ አሜሪካ ሄዶ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ሲጨርስ አልማዝ ከምትባል የካዛንቺስ አካባቢ ልጅ ተወዳጀ፡፡ አልማዝ ቆንጆና ዳንስ የምትወድ ሴትም ነበረች፡፡ (አልማዝ ከበአሉ ጋር የመሰረተችው ትዳር መጀመሪያዋ አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል ከበደ ሃይሌ (የአርበኛው ሃይሌ አባ መርሳ ልጅ) የሚባል ባል ነበራት፡፡ ከከበደ ሀይሌም ልጆች ወልዳ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የወንድሟን አምደሚካኤልን ጓደኛ በአሉን ያገባችው፡፡ በአሉ በትዳራቸው ውስጥም ይሄ የሴት ሙያ ነው ይሄ የወንድ የሚለው ስራ አልነበረውም፡፡ ሲያሻው ወደማእድቤት ገብቶ ምግብ ያበስልም ነበር፡፡ ከአልማዝ ጋር ተጋብቶ ሶስት ልጆችንም ወልዷል፡፡ ከሶስቱ ውስጥ ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ ዘላለም በዓሉና ቢኒያም በዓሉ ይባላሉ፡፡ ሴቷ መስከረም በአሉ ትባላለች፡፡

⩩ የድርሰት ስራዎቹ

ደራሲ በአሉ ግርማ በአጠቃላይ ስድስት ረጃጅም ልቦለዶች አሉት፡፡ እነሱም ‘ከአድማስ ባሻገር'(1962) “የህሊና ደወል (1966) ” ‘ደራሲው (1972)፣ ‘ሀዲስ’ (1975) እና ኦሮማይን (1975) ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስራዎች ውስጥ ‘የህሊና ደወል’ እና ‘ሀዲስ’ በመቼት እና በተሳሉ ዋና ገፀባርያት ተመሳሳይነት ቢታይባቸውም በጭብጥ ረገድ ግን ልዩነት እንዳላቸው የስነ-ጽሑፍ ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ‘ሀዲስ’ ፤ በ’ህሊና ደወል’ ውስጥ የተነሱ ጉዳዮች ሰፋ ባለ እይታና የተወሰኑ ቅንጭብጭብ ታሪኮች እና ገፀባርያት ታክለውበት የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፡፡ በአሉ ከዚህም በተጨማሪ መጀመርያያ በየካቲት መጽሔት (1975) በኋላ ደግሞ ‘ጭጋግና ጠል’ በሚል ርእስ አንጋፋና ወጣት ደራስያን ስራ ይዛ በ 1990 ዓ.ም በታተመች መድበል ላይ የታተመ “የፍፃሜው መጀመርያ” የሚል አጭር ትረካ አለው፡፡

በአሉ መጨረሻ መጽሐፉን ‘ኦሮማይ’ን ከጻፈ በኋላ ከስራ ታገደ፡፡ የመታገዱ ምክንያትም በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ በሥራ አጋጣሚ እጁ የገቡትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ስም ሳይቀር የሚያጎድፍ ስራ ሰርተሃል የሚል ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት ሹመቱ የታገደው በ1975 ዓ.ም በነሃሴ ወር ነበር፡፡

⩩ የበዓሉ ሞት

እስከ የካቲት 8: 1976 ዓ.ም ያለስራ የቆየው በዓሉ አንድ ዕለት እንደወጣ ቀረ። ከዛ ምሽት በኋላ በአሉ ወደ ስራ አልተመለሰም፡፡ በአሉ ከጠፋ ከአንድ ሳምንት በኋላ ደብረዘይት መንገድ ቃሊቲ አካባቢ መኪናው ቆማ የተገኘች ቢሆንም በአሉን የበላ ጅብ ግን ወዲህ ነኝ አላለም ነበር፡፡ መንግስትም በአሉ የኛ ወገን ነበር፤ አሁን ግን ከድቶን ስለጠፋ ያያችሁት አሳውቁኝ የሚል ማስታወቂያ ቢያስነግርም እራሱ መንግስት እንደገደለው ይጠቆማል። እርግጠኛውን የሚጠቁሙ አይደሉም፡፡

በአሉ ከቤት ከወጣባት ጊዜ ጀምሮ ግን እዚህ ቦታ ታይቷል የሚል ሰው ባይገኝም የደራሲ እንዳለጌታ መጽሐፍ በዓሉ በደርግ ደህንነቶች ተይዞ ቤርሙዳ ተብሎ ይጠራ የነበረ ቦታ ታስሮ በመጨረሻም መገደሉን ያትታል፡፡ ሆኖም ሞተ መባሉ ተሰማ እንጂ አስክሬኑ ግን እስከዛሬ አልተገኘም፡፡ እናም ሃገሩን በጋዜጠኝነትም በደራሲነትም ያገለገለው በአሉ ግርማ የቆመለት ሃውልት የለውም፡፡ ስለ በአሉ ግርማ በሃገራችን ብዙ ፀሃፍያን በጋዜጣም በመፅሄትም ብዙ ፅፈዋል፡፡ በራዲዮና በቴሌቪዥን ያልተነሳበት አመትና ወርም የለም (ማለት ይቻላል)፡፡ የደራስያንን ታሪክ የያዙ መጻሕፍት በአሉን በቀጥታም በተዘዋዋሪም አያልፉትም፡፡ የደርግ ባለስልጣኖች በተለያየ ስፍራ ሆነው በሚፅፉት መጽሃፍም በዓሉን ያነሳሱታል፡፡ እንዳለጌታ ከበደ ግን በ 2008 ዓ.ም ያሳተመው “በአሉ ግርማ ህይወቱና ስራዎቹ” የሚለው ባለ440 ገፅ መጽሐፍ ከሁሉም የተለየና የደራሲውን ህይወትና ስራዎች” በዝርዝር የተመለከተ ነው፡፡ በዚህም መጽሐፉን “ሃውልት ላልቆመለት ደራሲ የቆመ የመጽሐፍ ሃውልት” የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡

#ታሪክን_ወደኋላ

[ ማስታወሻ ከዚህ ገፅ አቅራቢ፣ የተለያዩ የዚህ ገፅ ታዳሚያን በታላቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ የውልደት ዘመን ላይ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። ስለ በዓሉ ከፃፉት ደራሲያን መካከል የውልደት ዘመኑን 1938 ወይም 1939 (እአአ) ነው በማለት የፃፉ አሉ። በጉግል ዊኪፒዲያ ላይም የሚገኘው ይኸው ነው። ሆኖም ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ‘በዓሉ ግርማ ህይወቱና ሥራዎቹ’ በተሰኘውና የበዓሉ ግርማ የህይወት ጉዞ ላይ በሚያጠነጥነው መፅሀፉ ‘በዓሉ ግርማ በአንድ ወቅት በ1965 ዓ.ም ትምህርቱን፣ የአገልግሎት ዘመኑንና ዕድሜውን አስመልክቶ የሞላው ቅፅ ላይ አገኘሁ፤ ወላጅ እናቱም ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ የወረረን ሰሞን ነው የወለድኩት አሉ’ ያለውን እንደመነሻ አድርጎ እንደፃፈው የበዓሉ የትውልድ ዘመን 1928 ዓ.ም ነው። ለአንባቢ ግንዛቤ ወይም ተጨማሪ ይሆን ዘንድ አቀረብኩት። መማተ )

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop