የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር ጉባኤ  ይቋቋም! 

እንደ መግቢያ 

————-  

ከአንጋፋው የታሪክ ሊቅ ከሴኮንቴ-ሮሴኔ ነው፡፡ የተጻፈው በ1952 ዓ፡ም እ፡ኤ፡አ “የኢትዮጵያ ታሪክ” ለተባለው መጽሀፍ እንደ አርዕስት ሆኖ የተቀመጠውም በጥያቄ መልክ ነው፡፡ 

እንዲህ ይላል፤ 

“”—-ከ 2000 ዓመት በላይ ታሪክ፣ አልበገር ባይነት የተጠበቀ ነጻነት፣ ከማንኛውም ነገር እና ከሁሉም ጋር (አጌንስት ኤቨሪቲንግ ኤንድ ኤቭሪ በዲ) ጦርነት፤ እነዚህ በርግጥም ዛሬ ከሰው ለሆነ ፍጡር ቢሸከማቸው ግዙፉ ኃላፊነት ናቸው፡፡ በጨለማው አህጉር የወደፊት ሂደት፣ በነጻነት መቆየት ለቻለው ብቸኛ ህዝብ የእድል እጣ ምን አልሞለት ይሁን? —-” ‘  ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዓለም ጭራ ሆነን፤ ብዕር ሊከትበው፤ እዕምሮ ሊመዝነውና፤ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያልተመዘገበው የጭካኔና የአረመኔነት ተግባር በገንዛ ወገናችን ላይ  እየፈጸምን ያለው፤ ሊቅ ከሴኮንቴ-ሮሴኔ እንዳለው ፤ በርግጥስ ”ምን አልሞልን ይሆን?’——– 

 

ከዚህ በታች  የማሰፈረው ሃሳብ እንደመነሻ ነው። ስለዚህም  በሃስቡ የሚያምን እንዲደግፈው፣ የማያምን  ደግሞ እንዲተችበት ወይም አማራጭ የመፍትሄ ሃሳብ  እንዲሰጥ፤ በአጠቃላይ  ለአገራችን  ኢትዮጵያ በተለይም መፍትሄ  የሚሆንና ገንቢ ሃሳብ ለማሸራሸር  መሆኑ  በቅድሚያ ማስገንዘብ እወዳለሁ።

  በ’ኔ እምነት አሁን  በኢትዮጵያ ምድር መንግሥት የለም።  የአገሪቱ ተቋማትና  መዋቅር ከፊሎቹ ፈርሰዋል፤ ከፊሎቹ ደግሞ እየፈረሱ ነው። የቀረውም በጎሳና በካድሪ ገዥዎች ሥር ወድቆ ከማአከላዊ  ከአዲስ አበባው አገዛዝ  ጋር ግንኙነት ተቋርጧል።
 

የኢትዮጵያ ህዝብ  በታሪኳ ሰምቶትም ሆነ ገጥሞት የማያውቀው  የርስበርስ ጦርነት፣ የጎሳኝነት ፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ  ቀውስ፤  የሠላምና በህይወት የመኖር መብቱ ሁሉ ተገፎ  ቀውስ ውስጥ ወድቋል። ማንንትንና ሃየምኖትን መሰረት ያደረግ የዘር ማጽዳት ወንጀል በገዥዎቻችን መዋቅርና እቅድ ወጥቶለት እየተፈጸመ ነው። መጨው ዘመናችን  ለሁሉም ዜጋ አስፈሪ ነው። 

 የማዕከላዊ መንግሥት የሚባለው አሁን ‘በራሳቸው አጠራር የኦሮሙማ  ቡድን ብቻ ነው።  ከዚህ ላይ ይኽ የኦሮሙማ ቡድን ራሱን እንጅ የኦሮሞን ህዝብ የማይወክልና፤ ነገር ግን በስሙ ከሌላው ወገኑ ጋር ደም እያቃባው ያለ፤  የኦሮሞ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

 አገራችን  አሁን ላለችበት እጅግ ምስቅልቅል፣ ችግርና የጎሳ አገዛዝ ብሎም የዘር ማጽዳት ወንጀል ዋናው ተጠያቂውና ኃላፊነቱ  ሥልጣን ላይ ያለው ራሱን ብልጽግና ብሎ የሚጠራው  የኦሮሙማ አገዛዝና በተቃውሚ ስም ተደራጅተው ሥልጣን የተጋሩት ናቸው።

 በአገራችን ከመሃል እስከ ዳር፤ ከዳር እስከ መሃል በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት ተለኩሷል። ሁሉም በየጎሳውና በየመንደሩ ተቧድኖ  እየተጨራረሰ የሰላማዊ ዜጋ ህይወት በከንቱ እየፈሰሰ ፤ ገዳማትና መስጊዶች እየፈረሱ፣  የሰው ልጅ እንደ አውሬ እየታደንና እየተገደለ፤  በአጠቅላይ ሁላችንም ወደ ማንውጠው የርስ በርስ እልቂት ላይ መሆናችን ብቻ ሳይሆን፤  ለበለጠ መጠፋፋትና አገር አልባ ለማድረግ ቤተ-መንግሥቱን የተቆጣጠሩት ቡድኖች እየተዘጋጁ ነው። 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተወዳጇ ድምጻዊ ከዚህ ዓለም ድካም አረፈች

 
ታዲያ ከቻልን እንደ ሰው፤ ያለያም እንደ ኢትዮጵያዊ  አሁን መልስ የሚያሸው፤ ግዜ ያማይሰጠው፤ የህልውናችን  ጥያቄ  ”እንዴት ከዚህ እንውጣ ?” የሚል ነው።  ያለፈው ደም ማፍሰስ አይበቃም ወይ? ምን ያህልስ ህዝብ ቢፈናቀልና ቢሳደድ ይበቃል?  ሰው በገዛ አገሩ ወዴትስ ይሄድ?  ከእስካ አሁኑ የኢትዮጵያ ውድመትና መራቆትስ ማን አተረፈ?

የብልጽግና አገዛዝ ከማንኛውም  የኢትዮጵያ ህዝብ  ጋር ተለያይቷል ብቻ ሳይሆን ፤ ሁሉም ነገር ከቁጥጥሩ ውጭ ሆኗል ።  የቀረው  ነገር ቢኖር በጥቅምና በጎሳ ገመድ የተሳሰሩት  ገዥዎቻችን፣ ወንጀል የሰሩት ባለሥልጥናት ፣ ካድሪዎቹ ፤ በጎሳ ያደራጃቸው ወታደሮቹና ጥይታቸው ብቻ ነው። ብልጽግና  የሚገዘው አገር አለ ከተባለም የአዲስ አበባን ከተማ ነው። እሷንም በሚሊዮን ህዝብ አፈናቅሎ፣  በንጹሃን ደም እያጠባትና የዜጎች ማጎሪያ አድርጓታል።

ስለዚህም ወደድንም ጠላንም አሁን ያለን  አማራጭና በግሌ መፍትሄ የምለው፤   የብልጽግና መንግሥት በአስቸኳይ በፍቃደኝነት ሥልጣኑን እንዲለቅ፤ ያለያ ግን ማንኛውንም  አሰገዳጅ ኃይል ፈጥሮ  ብልጽግናን ከሥልጣን ማስወገድና ላልተውሰነ ግዜ የሚቆይ ከሁሉም ከአገሪቱ ክፍል የተውጣጣ  የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  በማቋቋም፤ ቅድሚያ አገርንና ህዝብን አግባብቶ - አረጋግቶ ፤ መሳሪያ ላነሱትም ቡድኖች የሰላም ጥሪ አድርጎ; ፓለቲከኞችን ወደ አድነት በማምጣት፤ ለሁሉም የሚያመች የመወያይ መድረክ ማዘጋጀት የሚችል መዋቅር መፍጠር  መቻል ነው።

ታዲያ ይህ የመፍትሄ ሃሳብ ከዚህ በፊት በተዘዋዋሪ  መንገድ ቢሆንም፤ በተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የቀረበና በገዥዎቻችን ዘንድ የተፌዘበት መሆኑን ዘንግቸው አይደልም። ግን አሁን በየተኘውም  የአገሪቱ ክፍል በገዥዎቻችን ተስፋ ቆርጧል፤ እርሙን አውጥቶ ”ምጽአትን” እየጠበቀ ነው። ያለንበት ሁኔታ ከምንግዜውም  የተለይና ለሁላችንም የቀረበልን ጥያቄ የመኖርና ያለምኖር  ከምሆኑም አልፎ፤ ሁልችንም  እንደ ህዝብ ሊያሰባስበንና ከእልቂት ሊታደገን  የሚችለው መንገድ ይኽ  እንደ መነሻ ያነሳሁት ሃሳብ “የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  ማቋቋም!” ነው ብየ አምናለው።

በርግጥ የኔ ምኞቴ ብቻ ሳይሆን ምን አልባትም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ምኞት፤  እግዚአብሔር  ለገዥዎቻችን ቅን ልቦና እና ቅንነቱን ፈጥሮባቸው፤   አንዱን የበታች፣ ሌላውን የበላይ አድርጎ የዘር ማጥፋት ወንጅል እየፈጸሙ የሚጸና አገዛዝ  እንደሌለና ከኢትዮጵያ ህዝብ እልቂት   የሚያተርፍ ማንማ እንደሌለ ተገንዝበውና ከታሪክ ተምረው ፤  የበለጠ ደም ሳይስ   ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው ሥልጣናቸን ቢያስረክቡ  ሁላችንም እንተርፍ ነበር። ግን በጥላቻና በድንቁርና የደነደኑ ስለሆነ ካልተገደዱ በቀር  እያደርጉትም። 

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ይቅርታችን ሁልጊዜ ጅምር ነው" - ቃለ ምልልስ ከዘማሪ፣ ደራሲና ሰዓሊ ይልማ ኃይሉ ጋር

አሁን ግራም ነፈሰ -ቀኝ ፤ ብልጽግናዎች በፍቃደኝነት ሥልጥናቸውን ለቀቁም-አለቀቁም፤   የኢትዮጵያ ህዝብ  በአንድነት ለማይቀረው ትግልም ራሱን ማዘጋጀትና የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመጽ በመቀላቀል ፤ ገዥዎቻችን ሲወገዱ  የሚፈጠረውን የአስተዳደር  ክፍተት ለመሙላት ከአሁኑ  የየባለአደራ  ግዚያዊ የአገር ጉባኤ  መቋቋም  አለበት በየ በጽኑ  ።

ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚነት ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሰው ልጅ መብት ቁመናል የምትሉ ሁሉ፤ በአብሮነት በመታገል፤ የባለአደራ ግዚያዊ  አስተዳደር ጉባኤ  ለመቋቋም ሁላችንም፤ እንሰባሰብና የድርሻችን እንወጣ ።

ምክንያቱም ከአሁን በኋላ  ከብልጽግና አገዛዝ ህዝብ የሚቀርበት ነገር ቢኖር፤  እንደ በግ እየተጎተተና እንደ አውሬ እየታደነ መገደል ፤ ብሎም አገር አልባ መሆን ነው።

ስለዚህም ከመግቢያ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ ይኽ እንደ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል   የመፍትሄ ሃሳብ  እጅግ ከባድና እንዴት ሊመሰረትና ሊሳካስ ይችላል፤  የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። በ’ኔ እምነት  ከተለመደው የሴራ ፓለቲካ ወጥተን  ለራሳችንና ለአገራችን ህልውና ስንል በቅንንተ ከተደራጀን፤ ብሎም በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የምንገኝ ግለሰቦችና ተቋማት ከተሰተፍበትና  ዓለማቀፋዊ ካደረግነው፤  ይኽ ሃሳብ እንደ መነሻ ሆኖ  ሊያገለግልና ሊያሰባስብን ይችላል ብየ አምንለሁ።  

 

በአገር ውስጥ የሚቋቋመው ይኽ የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ    ባህር ማዶ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊን ጋር ተባብሮ በመስራት ፤  ብልጽግና በፈቃደኝነትም ሆነ በህዝባዊ አመጽ ተገዶ ሥልጣኑን ሲለቅ  

በመላው አገሪቱ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅና የሚፈጠረውን የሥልጣንና የአስተዳደር ክፍተት የሚሸፍን  መሆን አለበት ። 

 

 

  ”የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  ጉባኤ ” ምን ዓይነት መርሆዎችና ተግባሮች ይኑሩት? ለሚለው፤  ከውቅያኖስ መሃል ጠብ እንደምትል የውሃ ጠብታ፤ እኔም ለመንሻ የሚሆን የሃሳብ ጠብታየን ከዚህ በታች አስቀምጣለሁ፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የምትትግሉና ፤ የወላድ መካን ለሆነችው አገራችንና  ወገናችን እንድረስለት የምትሉ ደግሞ ”ውቅያኖሱን ሙሉት”።
 

”የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  ”  እንደ መነሻ ፤ ምን ዓይነት  መርሆዎችና ተግባሮች እንዲኖሩት ሆኖ ይቋቋም? 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአጼ ሚኒሊክ ሀውልት ሊነሳ ነው |የብርሃኑ ጁላ ጦር መሣርያዉን በዚህ መልኩ ጥሎ ፈርጥጧል| ዳንኤል ክብረት የአብይ ዋና አማካሪ ተዋረደ! | ፕሬዝዳንቷ የገቡበት አጣብቂኝ | ጎንደር ድሉ ቀጥሏል ሚኒስቴሩ ጠፍቷል

1/ በመላው የአገሪቱ ከምሁራን (አውነተኛ ምሁር)፣  ከተከበሩ የአገር  ሽማግሊዋችና ለስጋቸው ሳይሆን ለነፍሳቸው ካደሩ  የሃይማኖት አባቶች፤ ተሰባስበው  በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ በመመወያየት፤ሁሉንም የአገሪቱን ዜጋ ያማከለ  ”የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  ”  ያቋቁሙ ።(”የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  ”   የሚለው ስያሜ  በተሰብሳቢዎቹ የሚወሰን ይሆንል)።  

2/ የዚህ የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ አባላት ከማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲና የጎሳ ቡድን የሌሉበት፤ እስከ አሁንም ያልተሳተፋ፣ ወደፊትም የማይሳተፋ መሆን አለባቸው።

3/ ይህ የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ   የብልጽግናን  የከፍተኛ መንግሥት  አምራር አባላቶችንና ተተኪ የሚኒስተሮቹን በተዋረድ  ከህዝብ በሚያገኘው ድምጽና ጥቆማ በግልጽና በይፋ ይመርጣል። ተተኪ ተመራጮች ከዚህ በፊትም ሆነ ወደፊት በማንኛውም የፓለቲካም ሆነ የጎሳ ቡደን ያልተሰተፍና የማይሳተፋ መሆን አለባቸው።ግን ለቦታው የሚመጥን ሙያና ብቃት ያላቸው መሆናቸው  በይፋ መታውቅ አለበት።

4/ ለብልጽግና ተተኪዎች ከተመረጡ በኋላ፤ ኃላፊነታቸ ከብልጽጋና ይረከባሉ። ለብልጽግናዎችም በግለሰብ ደረጃ እስከ አልሆነ ድረስ  በባለአደራው  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  ከህግ – ተጠያቂነት ነጻ መሆናቸን ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል። ይኽም በብዙ አገሮች ከስልጣን በፍቃደኝነት ለመልቀቅ  ፍቃደኛ የማይሆኑት፤  በስልጣን ዘመናቸው የፈጸሙት ወንጅል  እንደሚያስጠይቃቸው ስለሚያውቁ ነው።

8/ ብልጽግናን የተኩት ኃላፊዎች ቀጥታ ተጠሪነታቸው ለባለአደራው ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ ሲሆን፣  ከፍተኛው የስልጣን  አስተዳደር ሆኖ ያገለግላል። ብልጽግናን የተኩና ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጣቸው  በወደፊት ከሚደረግ ፓለቲካዊ  ስልጣን የታገዱ ይሆናሉ። 

7/  የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ  የሥራ ዘመን   በራሱ በአባላቱና ከዓላማው ግብ  ጋር በሚፈጽማቸው ተግባራት  የሚወሰን ቢሆነም የግዜ ገድብ ግን ማስቀመጥ አለበት። 

 

8/ የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ ዘላቂነት ያለው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ የሚያስችሉትን  ነጻ የዲሞክራሲ ተቋማትንን ማህበራዊ እንቅስቃሴውችን  ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት ይገነባል።

9/ የባለአደራ  ግዚያዊ የአገር  ጉባኤ   የኢትዮጵያን ለዋአላዊነትና የህዝቧን አንድነት፤ እንዲሁም  የዜጋን  መሰረታዊ መብት በማይነካ መንገድ ፤ ግልጽና ለህዝብ ይፋ የሆነ ውይይት በማካሄድ ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ህግ–መንግሥት  በህዝብ እንዲረቀቅና  እንዲጽደቅ ያስደርጋል።

10/  በመጨረሻም በአዲሱ በህዝብ በረቀቀውና በጸደቀው  ህገ -መንግሥት አማካኝነት አገራዊ ምርጫ አካሄዶ፣ ለተመራጮች ወይም ለአሸናፊ ፓርቲዎች ኃላፊነቱን ያስረክባል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች! 

 

———//—— ፊልጶስ 

ግንቦት/ 2015 

 

@ ሃሳብ ለመለዋወጥና ለመወያየት የሚከተለውን የኢሜል አድራሻ ይጠቀሙ።  philiposmw@hotmail.com

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share