አድዋ ተናገር !! ( አሥራደው ከፈረንሳይ )

እምቢኝ ለማተቤ – እምቢኝ ላገር ብሎ ፤
ሚስትና ልጆቹን – እርግፍ አርጎ ጥሎ፤
እርሻው አይታረስ! – አረም ይብላው ብሎ፤
አረም እንዳይበቅል – ባድዋ ተራራ፤
በጎራዴው አርሶ – ጥይቱን የዘራ፤
ጭንቅላት የቀላው – በጩቤ በካራ፤
ድሉን ያደመቀው – በጀግና ፉከራ፤
አልነበረም እንዴ – መላው ድፍን ሃገር?
አድዋ ተናገር!!
በማተብህ ጽና_ ለህሊናህ እደር፡፡

ከሰሜን ከደቡብ – ርቀት ሳይገድበው፤
ከምዕራብ ከምስራቅ – ጠሃዩ ሳይገታው፤
ሆ! ብሎ የወጣው – ላንተ የሞተልህ፤
ሞቱን ባንተ ሽሮ – ድል ያጎናፀፈህ፤
አልነበረም እንዴ መላው ድፍን አገር ?!
አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ ማ’ተብ አትበጥስ፤
በደም የተጣፈ ታሪክ አትከልስ፡፡

አድዋ ተናገር! – ማነው የሞተልህ?
ማንስ አስደፍሮ – ማንስ ዘብ ቆመልህ?
ስጋውን አጥንቱን – ማን ከሰከሰልህ?
ሞቱን ባንተ ሽሮ ድል አጎናፀፈህ?!
አድዋ ተናገር – ምንድነው ዝምታው?
ድንበር ያስከበረው – ደሙን ያፈሰሰው?
አንድ ጎሣ ነበር – ላንተ ሲል የሞተው?
ወይስ መላው ሃገር?!
ሲዳሞና_ ሐረር፤
ወለጋና_ ጎንደር፤
ሸዋና_ ወሎየው፤
አሩሲው_ ጎጃሜው፤
ኢሉባቦር_ ከፋው፤
ባሌ_ ጋሞጎፋው
ኤርትራና_ ትግሬው፤
አልነበረም እንዴ – ላንተ ሲል የሞተው?!
በዘር ሳይታጠር – ሃይማኖት ሳይፈታው፣
ጥቅም ሳይደልለው- ድህነት ሳይረታው፡፡

አሁን ዘመን ከፍቶ – አገር ተበትኖ፤
በዘር በሃይማኖት – ጎሣ ተሸንሽኖ፤
አገር እበት ወልዳ – ትል ደሟን ሲጠባ፤
በባንዳ ታጅቦ – ጠላት ቤት ሲገባ፤
አድዋ የኛ ነው! – ላንተ ምንህም ነው!
ይሉን ጀምረዋል – ጥንቱን እያወቅነው፤
አድዋ ያለ እናቱ፤
አድዋ ያለ ኢትዮጵያ የሙት ልጅ ባንዳ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቅን ልቦና ካለ (ዘ-ጌርሣም)

አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ – ማ’ተብ አትበጥስ፤
በደም የተጣፈ – ታሪክ አትከልስ፤
ኧረ ለመሆኑ – ማነው የሞተልህ?!!
ማነው የቆሰለው – ማነው የደማልህ?
አጥንቱን ከስክሶ – ድል ያጎናፀፈህ?!

ቼ!! ብሎ በመትመም – ነጋሪት የመታው፤
አንቢልታውን ነፍቶ – ፎክሮ የወጣው፤
ጎራዴውን መዞ – ጦሩን የሰበቀው፤
አንተ እንዳትደፈር – ቃል ኪዳን የገባው፤
ላንተ የሞተልህ – ላንተ የተሰዋው፣
መላው ኢትዮጵያዊ – ድፍን ሃገሩ ነው?
ወይስ አንድ ጎሣ – ብቻውን ትግሬ ነው??

አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ – ማ’ተብ አትበጥስ፤
በደም የተጣፈ – ታሪክ አትከልስ፤
ኧረ ለመሆኑ – ማነው የሞተልህ?!!
ማነው የቆሰለው – ማነው የደማልህ?
አጥንቱን ከስክሶ – ድል ያጎናፀፈህ?!

በህይወቴ እያለሁ – ጠላት አይደፍርህም፤
ጣሊያን ባንተ ጉያ – አይውልም አያድርም፤
ፋሺስት ባንተ መንደር – አይምነሸነሽም፤
ብሎ የተመመው – ላንተ ሊሞትልህ፤
ላንተ የቆሰለው – ላንተ የደማልህ፤
አርነት ያወጀው – ድል ያጎናጸፈህ፤
ኧረ ለመሆኑ – አንድ ጎሣ ነበር ?!
ወይንስ ጦብያ መላው ድፍን አገር ::

አድዋ ተናገር!
በቃል ኪዳና ጽና – ለማ’ተብህ እደር፤
በደም የተጣፈ – ታሪክ አትሸርሽር፤
እንዲህ እንደዛሬው !
ጥላቻን አንግቦ – በዘር ሳይታጠር፤
ላንተ የሞተልህ – መላው ጦቢያ ነበር::

አንድ ቀን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share