የሙሶሊኒና የቫቲካኑ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ፋሺሽታዊ ሕብረት ሐቅ የቀድሞ አምባሳደር፤ ዘውዴ ረታ፤ ቫቲካንን ከኃላፊነት ነጻ ለማድረግ ስላደረጉት ሙከራ

/

ኪዳኔ ዓለማየሁ

PDF-   [ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]-

መግቢያ

በቅርቡ፤ አምባሳደር ዘውዴ ረታ የደረሱት፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” መጽሐፍ(1)፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በልዩ ልዩ ከተሞች እየተሸጠ በመሆኑ፤ አንድ ወዳጄ፤ ለኔም ልኮልኝ አንብቤዋለሁ። ይህን መጣጥፍ የማቀርበው ግን፤ ስለ መጽሓፉ በአጠቃላይ ለመተቸት ሳይሆን፤ በተለይ ከገጽ 295 እስከ 314፤ “የቫቲካን አቋም በኢትዮጵያ ጉዳይ” በተሰኘው ምእራፍ፤ የቀድሞ አምባሳደሩ፤ ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው ግፍና የጦር ወንጀል ሁሉ ቫቲካን ተጠያቂ አይደለችም ያሉት፤ ከሐቅ የራቀ፤ የውድ ሐገራችንን፤ የኢትዮጵያን ክብርና ፍትሕ የሚያጓድል በመሆኑ፤ በማስረጃ የተደገፈ እውነት ለማቅረብ ነው። በመጽሐፉ የቀረቡትን ጉድለቶች እራሳቸው በጽሑፍ እንዲያስተካክሉ፤ በኢሜይልና በግልጽ ደብዳቤ ልዩ ልዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ቢቀርቡላቸውም፤ ለማስተካከል ፈቃደኛ ሆነው ስላልተገኙ፤ ይህ ጽሑፍ በይፋ እንዲወጣ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከዚህ በመቀጠል፤ (ሀ) አምባሳደሩ የሰነዘሯቸውን ዋና ዋና ነጥቦች፤ (ለ) ኢጣልያ፤ በቫቲካን ተደግፋ፤ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ፈጸመችው የጦር ወንጀል፤ (ሐ) ስለ የቫቲካኑ ፖፕ ፓየስ 11ኛና የሙሶሊኒ ሕብረትና ሚና፤ (መ) በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው የጦር ወንጀል ሐገራችን ስላጣችው ፍትሐዊ ውጤት፤ (ሠ) ሰሞኑን (August 11, 2012) የቫቲካን ተወካይ በተሳተፉበት፤ ለፋሺሽቱ መሪ፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ አፊሌ በምትሰኝ ከተማ ስለ ተቋቋመው መካነ መቃብርና መናፈሻ፤ (ረ) ኢትዮጵያ ለደረሰባት እልቂትና ውድመት ተገቢ የሆነ መካሻ እንድታገኝ በመታገል ላይ ስላለው፤ “ዓለምአቀፍ ሕብረት ለፍትሕ የኢትዮጵያ ጉዳይ” (Global Alliance f or Justice – The Ethiopian Cause) ስለ ተሰኘው ድርጅት(2) ዓላማና ተግባር ከዚህ በታች አቀርባለሁ። ስለ ድርጅቱ ዝርዝር ግንዛቤ ለማግኘት፤ www.globalallianceforethiopia.org መመልከት ይቻላል።

በአጠቃላይ፤ መጽሐፉ ውስጥ የተካተተው በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ ሐተታ፤ የሚከተሉትን ዋና ዋና ጠንቆች ስለሚያስከትል፤ አንባቢዎች በልዩ ጥንቃቄ ሊመለከቱት ይገባል፤

 

1ኛ/ ናዚ ጀርመኒ እይሑዶችን ስትጨፈጭፍ፤ ዝም በማለቷ ብቻ ቫቲካን፤ አይሑዶችን በመደጋገም ይቅርታ ስትጠይቅ፤ በጳጳሶቿና ካሕናቷ ድጋፍና ቡራኬ፤ ፋሺሽቶች በኢትዮጵያውያን ላይ ለፈጸሙት አሰቃቂ የጦር ወንጀልና ግፍ፤ እስካሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ አለመጠየቋን መጽሓፉ እንደሚደግፍ ግልጽ ነው። በመሆኑም፤ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤ ከላይ በተጠቀሰው ድረገጽ የሚገኘው፤ እስካሁን ከ30 ሐገሮ ች በላይ ነዋሪ የሆኑ 3490 ሰዎች የፈረሙት አቤቱታ ውድቅ እንዲሆን ይሞክራል ማለት ነው።

 

2ኛ/ በተጨማሪ፤ መጽሓፉ ለሽያጭ የወጣው በቅርቡ ቢሆንም፤ ካሁኑ፤ ስለ ፖፕ ፓየስ 11ኛና ስለ ቫቲካን ያቀረበውን እንደ እውነት በመቁጠር፤ አንዳንድ ሰዎች ለመከራከሪያ ማስረጃነት ሊያውሉት ሞክረዋል።

 

3ኛ/ የፖፕ ፓየስ 11ኛና የፋሺሽቱ የሙሶሊኒ ግንኙነት፤ እ.ኤ.አ. ክ1922 ጀምሮ ሆኖ ሳለ፤ መጽሓፉ ያተኮረው በኢጣልያ የኢትዮጵያ ወረራ ዘመን ብቻ በመሆኑ፤ በሁለቱ መሀል ስለ ነበረው የጠበቀ መደጋገፍ፤ ሕብረትና ውል ምንም አይልም(3)። ስለዚህ፤ መጽሐፉ፤ ባልተሟላና በተሳሳተ ቅንጫቤ ለአንባቢ ትክክለኛ ግንዛቤ የሚሰጥ አይደለም።

 

የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ዓላማም፤ ግፈኞቹ የጣልያን ፋሺሽቶች፤ በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ በሚሊያን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ስለ ፈጸሙት ግድያና ሰቆቃ፤ ስላወደሙዋቸው ቤተ ክርስቲያኖችና መኖሪያ ቤቶችና ስለ ዘረፏቸው ንብረቶች ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲገኝና፤ ተነፍጋ የምትገኘውን ፍትሕ ሐገራችን እንደትጎናጸፍ ትግላችንን ለማጠናከር ነው።

 

  • ዘውዴ ረታ፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት”፤ 2012

 

  • ድርጅቱ ከተቋቋመ ከ5 ዓመት በላይ ሲሆነው፤ ለኢትዮጵያ ስለሚያስፈልገው ፍትሕ በመታገል ላይ ይገኛል።

 

  • ለበለጠ ዝርዝር፤ ከዚህ በታች ስለ ቫቲካን ሚና የሚቀርበውን ገለጻ ይመልከቱ።

 

የቀድሞ አምባሳደር ዘውዴ ረታ አቋም

 

ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፋቸውና በተጨማሪም፤ እ.ኤ.እ. በ9/26/12 በእጅ ጽሑፍ በመየሉት ደብዳቤ፤ ስላቀረቡዋቸው ዋና ዋና ነጥቦቻቸውና ስለሚመለከታቸውም ትንተና፤ ከዚህ በታች ይቀርባል፤

 

1ኛ/ ደራሲው፤ ስለ የማስረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴያቸው፤ ከዚህ እንደሚከተለው ገልጸዋል፤

 

“የዚህ መጽሐፍ ደራሲ በሮም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አምባሳደር በነበረበት ዘመን ከተከታተለውና ከሚያውቀው ሌላ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ የቫቲካን ትክክለኛ አቋም እንዴት እንደነበረ በጥልቀት ለመረዳት እ.ኤ.አ ከጥቅምት 18 ቀን እስከ ኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ሳምንታት በቫቲካን ሰንብቶ፤ ያገኛቸውን መረጃዎች ለአንባቢዎች እንደሚከተለው ያቀርባል።”(4)

 

ደራሲው እንደ ገለጹት፤ የማስረጃቸው ምንጭ ከቫቲካን ባገኙት ነበረ ማለት ነው። ምንም እንኳ ባንዳንድ አከራካሪ በሆኑ፤ ከዚህ በታች በምናያቸው በጥቂት ሌሎች ምንጮች የተጠቀሙ ቢሆኑም፤ ስለ ቫቲካን ሲጽፉ በአብዛኛው የተጠቀሙበት ከዚያው ከቫቲካን ባገኙት መሆኑ ራሱ ግንዛቤያቸውን አጠያያቂ እንደሚያደርገው ለማንም ቢሆን ግልጽ ነው። ማስረጃው አስተማማኝ እንዲሆን ቢፈለግ ኖሮ፤ ሌሎች ልዩ ልዩ የማስረጃ ምንጮችንም መዳሰስ ይገባ ነበር። በዚህ መሠረት ብቻ፤ የደራሲው ድምዳሜ፤ በመጽሓፉ እንደ ተገለጸው መሆኑ ባያስደንቅም ትክክለኛ አያደርገውም።

 

2ኛ/ ከላይ በተጠቀሰው ደብዳቤያቸው፤ ከዚህ በታች ያለውን ሐተታ አቅርበዋል፤

 

“1ኛ/ የመንበረ ቅዱስ ጴጥሮስ መሪ ፒዮስ 11ኛ ኢትዮጵያ የፋሺሽት ግዛት እንድትሆን ለሙሶሊኒ ድጋፍ መስጠታቸውን የሚገልጽ፤

 

2ኛ/ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን ለመውጋት የፋሽስት ወታደሮችን ሲልክ፤ ፖፑ ራሳቸው መርከብ ጣቢያ በመገኘት ባርከው መሸ(ኘ)ታቸውን የሚያሳይ መረጃ ባደረግኩት ምርምር አለማግኘቴን አስረድቻለሁ……

 

አቶ ኪዳኔ በጻፉት ማስታወሻ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለመዝመት የተላኩትን የፋሽስት ወታደሮች ፒዮስ 11ኛ ራሳቸው ባርከው ባይሸኙም፤ በዚያ በመርከቡ ጣቢያ የተገኙት ካህናት የፈጸሙት፤ በፖፑ ስም ስለሆነ ከተጠያቂነት አያድናቸውም ብለዋል። እኔ እንደሚመስለኝ ይህን የመሰለው መግለጫ፤ “አስተያየት” ሆኖ የሚቆጠር እንጂ “ሰነድ” ወይም “መረጃ” ሆኖ የሚቀርብ አይደለም። በናፖሊ መርከብ ጣቢያ የተገኙት ካህናት ወታደሩን መባረካቸውና ከዚያም ሲመለሱ ከወርቅ የተሠሩ የጣት ቀለበቶቻቸውንና የአንገት ሐብሎቻቸውን እያወለቁ፤ ለፋሽስት ጦር እርዳታ ያበረከቱት በየግላቸው እንጂ በፖፑ ስም ነው የሚል መረጃ አልተገኘም።”(5)

 

ከዚህ በታች፤ ስለ ቫቲካን ሚና በዝርዝር በሚቀርበው ክፍል፤ ስለ ሙሶሊኒና ፖፕ ፓየስ 11ኛ የቅርብ ግንኙነት፤ በተለይም “ላተራን” በተሰኘው ውላቸው እጅና ጓንት ሆነው ይሠሩ አንደ ነበር፤ የፋሺሽቱ ጦርም አዲስ አበባ ሲደርስ፤ የደስታ መግለጫ ካስተላለፉት የዓለም መሪዎች፤ ከመጀመሪያዎቹ መሀል፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ እንደ ነበሩ በግልጽ የሚያስረዱ ማስረጃዎች ለአምባሳደር ዘውዴ ቀርበውላቸው ለመቀበል አልፈለጉም።

 

ስለ ቡራኬው ጉዳይ፤ እኔ ለአምባሳደሩ በላክሁላቸው ግልጽ ደብዳቤ ያቀረብኩላቸው ማስረጃ፤ 1ኛ/ የካቶሊክ ካሕን የፋሺሽቱን ጦር ሲባርክ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፤ 2ኛ/ የፋሺሽቱ ጦር ኢትዮጵያን ሲወር፤ የቱራኖው ጳጳስ፤ ጦርነቱ ቅዱስ መባል እንዳለበትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሐዲ (“infidels and schismatics”) በመሆኑ ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት መለወጥ የሚገባው እንደ ሆነ የገለጹትን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነበር። ዝርዝሩ ስለ ቫቲካን ሚና በሚገልጸው ክፍል ይቀርባል።

 

  • ዘውዴ ረታ፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት”፤ ገጽ 295

 

  • ዘውዴ ረታ፤ “ይድረስ በኢትዮጵያ ጉዳይ፤ “ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ” ድርጅት አባሎች”፤ ገጽ 13 በተጨማሪም፤ ማንም ሊገነዘበው የሚችለው ሓቅ፤ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጳጳሶቿና ካሕኖቿ ሌላ ሐገር ለማጥቃት የሚጓዘውን ጦር ሲባርኩ፤ ያለቫቲካኑ መሪ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ፈቃድ፤ በግል ፍላጎታቸው ነበር ማለት የሚያስገርም ነው። መረጃ ካስፈለገስ፤ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው የፋሺሽት ጦር ወንጀል ጳጳሶቹ ስለገለጹት ይፋዊ ድጋፍና ስለ ካሕናቱ ቡራኬ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ተቃዋሚ ነበሩ የማለት አስተያየት ካለ፤ ይህንኑ የሚያረጋግጥ የውግዘት ወይም የውሳኔ ሰነድ ማቅረብ ያስፈልጋል። አምባሳደሩ፤ የቫቲካንን መዝገቦች ሲያገላብጡ፤ እንደዚህ ያለ ሰነድ ቢያገኙ ኖሮ በዋቢነት ያቀርቡት እንደ ነበረ እይጠረጠርም። በመጽሓፉ፤ በገጽ 307፤ ፖፕ ፓየስ 12ኛ፤ የካርዲናሎቹ “የግል እርምጃ” እንጂ ቫቲካንን የማይመለከት መሆኑን በቃል ገለጹ የተባለው ሐቀኛነት በጣም አጠራጣሪ ነው። ሌላው አስገራሚ የደራሲው ነጥብ፤ ፖፑ ራሳቸው፤ የመርከብ ጣቢያ ሔደው፤ ጦሩን ሲባርኩ የሚያሳይ ማስረጃ መፈለጋቸው ነው!
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ ወደ ሕገ አረሚ ተገለበጠች - ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

 

3ኛ/ ፖፕ ፓየስ 11ኛ፤ ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ ለሰነዘሩት የጦር ወንጀል፤ ለነርሶች ጉባኤ ባከናወኑት ቡራኬ፤ ተቃውሟቸውን የገለጹ መሆናቸውን፤ ደራሲው፤ እንደ ትልቅ ማስረጃ በመቁጠር፤ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበውታል፤

 

“ፒዮስ 11ኛ እነዚህን በብዙ መቶ የሚቆጠሩትን የዓለም ነርሶች ሲቀበሉ፤ የቅዱስነታቸው ረዳቶች ያዘጋጁላቸውን የቡራኬ ቃል ካነበቡ በኋላ፤ ማንም ያልጠበቀውንና ያላሰበውን ጉዳይ በቃላቸው (መስመር የኔ ነው) በመጨመር፤ የሙሶሊኒ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ስለአቀደው ጦርነት አስተያየታቸውን ገለጹ።”(6)

 

ከላይ እንደሚታየው፤ ፖፑ አቀረቡ የተባለው ተቃውሞ በቃል የነበረ ከመሆኑም በላይ፤ በመጽሓፉ፤ በሚቀጥሉት ገጾች፤ በንግግራቸው፤ የኢትዮጵያን ስም ያላነሱ መሆኑንና አነጋገራቸውም፤ በአጠቃላይ፤ “….ለግዛት ማስፋፊያ የሚደረግ ጦርነት ፍትሓዊ ባለመሆኑ የማይደግፉት መሆናቸውን አስታውቀዋል….”(7) ይላል። ያንኑ የፖፑን ገለጻቸውን፤ “ኦብስርባቶሬ ሮማኖ” በተሰኘው ጋዜጣ፤ “….. በቃላቸው ባደረጉት ንግግር፤ የማንም ደጋፊ ወይም የማንም ተቃዋሚ ለመሆን አለማሰባቸውን……” ያስረዳ መሆኑ ተገልጿል። እንግዲህ፤ ይኼ ነው ፖፑ ሙሶሊኒን የተቃወሙ አስመስሎ የቀረበው ማስረጃ! አንባቢ ይፍረድ።

 

4ኛ/ ስዊድናዊው ጋዜጠኛ፤ ኤሪክ ሉንደርም፤ በጊዜው ለቫቲካን በጻፈው ደብዳቤ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ የሙሶሊኒ አጋር እንደ ነበሩ የሚገልጽ ኃይለኛ ደብዳቤ የጻፈላቸው መሆኑ ከነነጥቦቹ ቀርቧል። (8) ነገር ግን፤ የጋዜጠኛውን ጽሑፍ ለማጣጣል፤ “አቡነ እንድርያስ ዣሮሶ” የተባሉት የሰጡትን መልስ፤ ደራሲው እንደሚከተለው አቅርበውታል፤

 

“…..ቅዱስ ፓፓው ከአንድም ሁለት ጊዜ በሰጡት መግለጫ፤ ግዛትን ለማስፋፋት የሚደረግ ጦርነት ሁሉ ፍትሓዊነት የሌለውና መብትም አለመሆኑን ደህና አድርገው በማስረዳት አውግዘዋል።”(9) (መስመር የደራሲው ነው)

 

እውነቱ ግን፤ ፖፑ ክላይ ከተጠቀሰው፤ ለነርሶች በቃል ከተናገሩት ሌላ፤ በይፋ የገለጹበት ወይም ያወገዙበት ምንም ማስረጃ የለም። በተቃራኒው፤ ዝምታን መርጠው የቆዩ መሆኑን የሚያንጸባርቁ፤ ደራሲው ራሳቸው የጠቀሷቸው ሰነዶች ተገኝተዋል።

 

5ኛ/ አጼ ኃይለ ሥላሴ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛን የደገፉ በማስመሰል ደራሲው ያቀረቡት ዘገባም፤ በሌላ በኩል የሚከተለውን፤ የጃንሆይን አስተያየት አክሏል፤

 

“ይህ ሁሉ ግፍ ከክርስትና ዕምነት፤ ከሰብአዊ መንፈስና ከሥልጣኔ ውጭ የተፈጸመ መሆኑን ቅዱስ ፓፓው እየሰሙ እንዴት ዝም አሉ? ብለን እኛም ቅሬታ ተሰምቶን ነበር።” የሚለው ይገኝበታል። (10)

  • ዘውዴ ረታ፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት”፣ 2012፤ ገጽ 296
  • ከላይ ከተጠቀሰው፤ ገጽ 300. (ደራሲው ይህንን ማስረጃ ሲያቀርቡ፤ ምንጩን በተሟላ መንገድ አላቀረቡም።)

 

(8)፤ ገጽ 304
(9)፤ ገጽ 30530
(10)፤ ገጽ 313

 

6ኛ/ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው እጅግ አሰቃቂ ግፍ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ በማውገዝ ፋንታ ዝምታን ስለ መምረጣቸው፤ ደራሲው ከዚህ የሚከተለውን አስተያየት አቅርበዋል፤

 

“….ፒዮስ 11ኛ ፋሽስት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ግፍ በማውገዝ ድምፃቸውን አሰምተው ቢሆን ኖሮ፤ ሙሶሊኒ

 

በእሳቸውና በቫቲካን ላይ ከባድ እርምጃ እንደሚወስድ ጥርጥር አልነበረውም ብለው የሚያምኑት እጅግ ብዙዎች ናቸው። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ድርጅታችሁ ሚዛን ያለው ውሳኔ እንዲያደርግ አሳስባለሁ።” (11)

 

እንግዲህ፤ ደራሲው፤ ከዚህ በላይ በገለጹት መሠረት፤ ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸሙት ግፍ፤ የፖፕ ፓየስ 11ኛ ዝምታ፤ በፍርሓት ስለ ነበረ፤ አያስጠይቃቸውም በማለት እየተማጸኑ ነው። ደራሲው ለመመልከት ያልፈለጉት ሐቅ ግን፤ የቫቲካን ድጋፍ በሌለበት፤ ቢኖርም አከራካሪ በሆነው በናዚዎች የአይሑድ ጭፍጨፋ፤ ቫቲካን የአይሑድን ሕዝብ በመደጋገም ይቅርታ ስትጠይቅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ተመሳሳይ ክርስቲያናዊ ተግባር አለማከናወኗን ነው። ለዚህም ማስረጃ፤ በBBC የተዘገበውን፤ በwww.globalallianceforethiopia.org ድረገጽ መ መልከት ይቻላል።

 

በቫቲካን ድጋፍ ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙት ግፍ

 

እ.ኤ.አ በ193541 በፋሺሽት ኢጣልያ ወረራ፤ በኢትዮጵያ ላይ በተፈጸመው ግፍ፤ (12)

 

  • አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈዋል። ከነዚህ ውስጥ፤ በ3 ቀኖች ብቻ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፤ 30፣000 ኢትዮጵያውያን እንደ ተገደሉ የታወቀ ነው። አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል፤ እንዲሁም፤ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ክ300 መነኮሳት በላይ እንደ ተሰዉ በታሪክ የተመዘገበ ሐቅ ነው።

 

(ለ) 2000 ቤተ ክርስቲያኖችና 525000 ቤቶች ተደምስሰዋል።

 

  • 14 ሚሊዮን እንስሶች ከማለቃቸው በላይ በብዙ አይሮፕላኖች በተነሰነሰው የመርዝ ጋዝ፤ እጅግ ሰፊ የአካባቢ ብክለት እንደ ደረሰ የታወቀ ነው።

 

(መ) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፤ በእስርና በልዩ ልዩ እንግልት ሰቆቃ ደርሶባቸዋል።

 

ኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው እልቂትና ግፍ የቫቲካን ሚና

 

1ኛ/ በሙሶሊኒ ዘመን የነበሩት የቫቲካን መሪዎች

 

በደራሲው የተጠቀሱት ዋነኛው የቫቲካን መሪ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ናቸው። ምንም እንኳ እኚህ ፖፕ ያረፉት እ.ኤ.እ በ1939 መሆኑን በመጽሓፉ የተገለጸ ቢሆንም፤ በፖፕ ፓየስ 11ኛ ዘመን የቫቲካን ዋና ጸሓፊ ጭምር በመሆን በከፍተኛ ደረጃ ያገለግሉ የነበሩት ካርዲናል ዩጂኖ ፓቼሊ የተባሉት ሰው፤ ፖፕ ፓየስ 12ኛ በመሰኘት እ.ኤ.እ ከ1939 ጀምሮ፤ ፋሺሽቶች ከኢትዮጵያ እስከ ተወገዱበት፤ እ.ኤ.አ. እስከ 1941 እና ከዚያም በኋላ የቫቲካን መሪነታቸውን ቀጥለው ነበር። ፖፕ ፓየስ 12ኛ ለሙሶሊኒ ብቻ ሳይሆን፤ ለሒትለርም ደጋፊ እንደ ነበሩ የታወቀ ቢሆንም፤ መጽሐፉ ስለዚህኛው ፖፕ ሚና የገለጸው በጣም መጠነኛ ነው።

  • ዘውዴ ረታ፤ “ይድረስ በኢትዮጵያ ጉዳይ “ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ” ድርጅት አባሎች”፤ 26/9/12፣ ገጽ 7

 

  • ጳውሎስ ኞኞ፤ “የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት”፤ 1980 ዓ/ም፤ ገጽ 224 እና 225

 

2ኛ/ የቫቲካን ሚና

 

ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው የጦር ወንጀል፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ እና ፖፕ ፓየስ 12ኛ የቫቲካን መሪዎች እና የፋሺሽቱ መሪ፤ ሙሶሊኒ እጅና ጓንት ሆነው በመተባበር እንደ ነበር ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፤ Avro Manhattan በጻፉት እንደ ዘገቡት፤ (13)

  • እ.ኤ.አ ከ1922 በፊት፤ ቫቲካንና ፋሺሽቶች ተጻራሪዎች ነበሩ። ከዚያ ዓመት ጀምሮ ግን፤ ቫቲካንና ፋሺሽቶች (ፖፕ ፓየስ 11ኛና ሙሶሊኒ) መቀራረብና መወዳጀት ጀመሩ። በዚሁ መሠረት፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ፤ “የካቶሊክ ፓርቲ” የተሰኘውን የፖለቲካ ድርጅታቸውን ደመሰሱ።

 

  • እ.ኤ.እ. በ1926 “Mussolini is the man sent by Providence” (ትርጉም፤ ሙሶሊኒ በፀጋ የተላከ ሰው ነው።) በማለት ሙሉ ድጋፋቸውን በይፋ በመግለጽ የኢጣልያን ሕዝብ የፋሺሽቱን ፓርቲ እንዲደግፍ አመቻቹ።

 

  • እ.ኤ.አ. በ1928፤ ፖፐ ፓየስ 11ኛና ሙሶሊኒ “ላተራን” የተሰኘውን ውል ተዋዋሉ። ውሉ ሲፈረም የሚያሳየውን ፎቶግራፍ በሚቀጥለው ገጽ መመልከት ይቻላል። ስለዚህ ውል በManchester Guardian (14) የሚከተለው ተነቦ ነበር፤

 

“Pope Pius XI is credited with much admiration for Mussolini. That the Italian clergy as a whole are pro-Fascist is easy to understand, seeing that Fascism is a nationalist, authoritarian, anti-liberal, and anti-Socialist force.” (ትርጉም፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ለሙሶሊኒ ስላላቸው ክፍተኛ አድናቆት ይነገርላቸዋል። የፋሺሽት ሥርዓት አምባገነናዊ፤ ብሔርተኛ፤ ፀረ ዲሞክራሲና ፀረሕዝባዊ ኃይል ስለ ሆነ የኢጣልያ ካሕናት በአጠቃላይ የፋሺሽት ደጋፊ መሆናቸውን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።)

  • Manhattan, Avro, “The Vatican in World Politics”, 1949, Chapter 9 (ይህንን ምእራፍ በሙሉ በwww.globalallianceforethiopia.org ድረገጽ ላይ ማንበብ ይቻ ላል።
  • Manchester Guardian, February 12, 1929
ተጨማሪ ያንብቡ:  ታማኝ እና ቴዲ ትላንት ምሽት (ከክንፉ አሰፋ) ጋዜጠኛ

 

በፖፕ ፓየስ 11ኛ ስም ካርዲናል ጋስፓሪና ሙሶሊኒ “ላተራን” የተሰኘውን ውል እ.ኤ.አ. በ1929 ሲፈራረሙ

  • ቫቲካን ከላይ የተጠቀሰውን ውል በመፈረሟ፤ ከፋሺሽቶቹ መጠነሰፊ ገንዘብ ያገኘች ሲሆን በተጨማሪም፤ ሕጋዊ ሉዓላዊነት ተፈቀደላት። አቭሮ ማንሓታን እንደ ጻፈው፤

“It was the alliance of these two men, Pius XI and Mussolini, that influenced so greatly the social and political pattern, not only of Italy, but also of the rest of Europe in the years between the two world wars.” (ትርጉም፤ የነዚህ የሁለት ሰዎች፤ የፖፕ ፓየስ 11ኛና የሙሶሊኒ ሕብረት ነበር በኢጣልያ ብቻ ሳይሆን በቀረው የአውሮፓ ክፍል ላይ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መሀል በነበሩት ዓመቶች የማሕበራዊና የፖለቲካ ይዘት ከፍተኛ አጽንኦት ያሳደረው።)

በዚህ መሠረት፤ በሙሶሊኒ የተመራው የፋሺሽት ፓርቲ፤ በፖፕ ፓየስ 11ኛ ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው የወረራና የጦር ወንጀል ምን ያህል እንደ ጠቀማት መገንዘብ አያዳግትም። አቭሮ ማንሓታን በተጨማሪ እንደ ገለጸው፤ “Thus the Church became the religious weapon of the Fascist State; while the Fascist State became the secular arm of the Church.” (ትርጉም፤ ስለዚህ፤ ቤተ ክርስቲያኗ (የካቶሊክ) የፋሺሽቱ መንግሥት ሃይማኖታዊ መሣሪያ ስትሆን፤ የፋሺሽቱ መንግሥት ደግሞ የቤተ ክርስቲያኗ ዓለማዊ ክንድ ሆነ።)

 

  • ቫቲካን የፋሺሽቱን ጦር መባረኳ የማይጠረጠር ሐቅ ነው። ካቶሊኩ ካሕን ጦሩን ሲባርኩ የሚያሳየውን ፎቶ ከዚህ በታች መመልከት ነው፤

የቫቲካኑ ካሕን የፋሺሽቱን ጦር ሲባርኩ

  • ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ ያከናወኑትን ወረራ፤ የመከላከል ጦርነት መሆኑን ፖፕ ፓየስ 11ኛ ገልጸው ነበር። የፋሺሽቱ ጦር አዲስ አበባ ሲደርስ፤ ከዚህ በታች የተጠቀሰውን የደስታ መግለጫቸውን እ.ኤ.አ. በግንቦት 12 ቀን 1936 በማወጅ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ በዚህ ረገድ ከዓለም መሪዎች ከመጀመሪያዎቹ አንዱ እንደ ነበሩ ተረጋግጧል፤

“The triumphant joy of an entire, great and good people over a place which, it is hoped and intended, will be an effective contribution and

prelude to the true place in Europe and the World.” (15) (ትርጉም፤ ለአውሮፓና ለዓለም፤ መልካም ጅማሮና ሁነኛ ደረጃ ተገቢ አስተዋጽኦ እንዲሆን ለታቀደና ተስፋ ለተጣለበት ቦታ (ኢትዮጵያን ማለት ነው) የታላቅና ግሩም ሕዝብ (ኢጣልያኖችን ማለት ነው) ከፍ ያለ ደስታ።)

የፖፕ ፓየስ 11ኛን መግለጫ የበለጠ ያጠናከሩት ደግሞ የቱራኖ የካቶሊክ ጳጳስ ነበሩ። የሳቸው መግለጫ እንደሚከተለው ነበር፤“The war against Ethiopia should be considered as a holy war, a crusade” (as Italian victory would) “open Ethiopia, a country of infidels and schismatics, to the expansion of the Catholic Faith.” (ትርጉም፤ በከሐዲዎቹ ሐገር፤ በኢትዮጵያ፤ የካቶሊክን ሃይማኖት ለማስፋፋት ስለሚጠቅም፤ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው ጦርነት እንደ ቅዱስ ጦርነት፤ መንፈሳዊ ዘመቻ መቆጠር አለበት።)

  • Quoted by Avro Manhattan from Teelman, “The Pope in Politics”

ሌሎችም የቫቲካን ካርዲናሎች፤ ጦርነቱን ደግፈው እንደ ነበረ በደራሲው መጽሐፍ፤ ገጽ 307

የተገለጸ ሲሆን፤ በፖፕ ፓየስ 12ኛ ገለጻ፤ በግላቸው የተከናወነ አስመስለው መናገራቸውን አክለውበታል። ይህ አባባል ግን፤ እንኳን የበሰለ የታሪክ ምሑርን ይቅርና የኔብጤ ተራ ሰውንም ሊያሞኝ ወይም ሊያዘናጋ አይችልም። ማንም እንደሚያውቀው፤ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፤ በተለይ ካርዲናሎች ከባድ በሆነ የሐገር ጉዳይ ይቅርና በሌላም መርሆን በተመለከተ ነጥብ፤ ከቫቲካን መመሪያ ውጭ በይፋ ሊናገሩ አይችሉም። ዛሬም እንደምናየው፤ እንደዚህ ያለ ተግባር እስከ ውግዘት የሚያደርስ ጣጣ ያስከትላል። በነዚያ ካርዲናሎች ላይ አንዳችም እርምጃ አለመወሰዱ፤ የኢጣልያን ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን ወረራ ቫቲካን መደገፏን ያረጋግጣል።

ፖፕ ፓየስ 11ኛ እ.ኤ.አ በ1939 ካረፉ በኋላ፤ የቅርብ ደጋፊያቸው የነበሩት፤ ካርዲናል ፓቼሊ፤ ፖፕ ፓየስ 12ኛ ተሰኝተው ከነሙሶሊኒ ጋር የነበረውን የቫቲካን ሕብረት ቀጥለዋል።

 

ሌሎች ምሑራን ምን አሉ?

 

1ኛ/ ስለ ቫቲካንና ፋሺሽቶች ሕብረት ያቀረብኩላቸውን ማስረጃዎች ከተመለከቱ በኋላ፤

 

  • ታዋቂው የኢትዮጵያ ታሪክ ምሑር፤ በቅርቡ፤ ስለ አጼ ኃይለ ሥላሴ፤ “The Lion of Judah in the New World”, 2011 የተሰኘ መጽሐፍ የደረሱት፤ ፕሮፌሰር ቲዮዶር ቬስታል፤ ከዚህ በታች የተጠቀሰውን መልእክት ላኩልኝ፤

 

“Your work is most convincing for those with ears to hear and eyes to

 

see.” (ትርጉም፤ ሥራህ መስማት የሚፈልጉ ጆሮዎችና ማየት የሚፈልጉ ዓይኖች ላሏቸው ሰዎች እጅግ በጣም አስተማማኝ ነው።)

 

  • ሌላው ታዋቂ ምሑር፤ እርሳቸውም፤ በቅርቡ፤ “TheS ymphony of My Life” በተሰኘ አርእስት ስለ ሕይወታቸው ታሪክና ስለ ኢጣልያን ወረራ መጽሐፍ የደረሱት፤ ዶር. ሥዩም ገብረ እግዚአብሔር፤ ከላይ በገጽ 7 የተጠቀስወን በፖፕ ፓየስ የተገለጸውን የደስታ መልእክት ካረጋገጡ በኋላ፤ ከዚህ በታች የቀረበውን መልእክት ላኩልኝ፤

 

“From my book you can note, how one of the Catholic priests took the personal responsibility to entice me to be a priest! How we the seminarians marched outside Harar in a heavily Moslem country protected by Fashist military to attend church every week! Picture P 63 . This was a clear policy of the Catholic church in support of Fascism. The establishment of “Collegio Ethiopico” within the vatican compound was to train and indoctrinate Ethiopian seminarians. We were then told that if we become good potential priests, we will be eligible to go to Rome for further education(indoctrination”! There was a definite crusade to propagate Catholicism in Ethiopia with the help

 

of fascism based on Aparthaid policy I had faced on my way to priesthood! (ትርጉም፤ ከመጽሐፌ ማየት እንደምትችለው፤ አንድ የካቶሊክ ካሕን እኔን ወደ ቅስና ለመሳብ የግል ኃላፊነት ይዞ ነበር። ገጽ 63 ላይ ባለው ፎቶግራፍ እንደሚታየው፤ ከሐረር ወጣ ባለ፤ እስላሞች በሚበዙበት (ክፍለ) ሐገር፤ ተማሪዎቹ፤ በፋሺሽት ወታደሮች እየታጀቡ፤ በየሳምንቱ ይሰለፉ ነበር። ይህም፤ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፤ ለፋሺሽዝም ያላትን ድጋፍ በግልጽ የሚያሳይ ፖሊሲ (መርሆ) ነበር። በቫቲካን ግቢ የተቋቋመው “ኮሌጂዮ ኢትዮፒኮ” ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ለማሠልጠንና ለማሳመን ነበር። በዚያን ጊዜ ተነግሮን የነበረው፤ ጥሩ የቅስና አዝማሚያ ካሳየን፤ ወደ ሮም ተልከን፤ ለቀጣይ ትምሕርት (ማሳመን) እጩ እንድንሆን ነበር። ወደ ቅስና በምጓዝበት፤ ባጋጠመኝ፤ በዚያ በዘረኛ (በ”አፓርቴይድ”) መርሆ፤ በፋሺዝም እርዳታ፤ በኢትዮጵያ፤ የካቶሊክ እምነትን ለመስበክ ዘመቻ መካሔዱ የተረጋገጠ ነበር።)(16)

ተጨማሪ ያንብቡ:  መርህ አልባነት ፣ የጭፍን ወይም የጨለማ ጉዞ!

 

በቫቲካን ድጋፍ፤ ፋሺሽቶች ለፈጸሙት ወንጀል ኢትዮጵያ እስካሁን ያገኘችው ውጤት

 

1ኛ/ እ.ኤ.አ. በ1947፤ ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ከፈጸመችው ከፍተኛ ወንጀል ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም፤ 6 ሚሊዮን ስተርሊንግ ፓውንድ ብቻ ካሣ ተከፍሏት፤ የቆቃ ግድብ እንዲሠራበት ተደርጓል፡፤ የሚያስገርመው ጉዳይ ግን፤ ኢጣልያ፤ በቅርቡ ለሊቢያ መንግሥት $5 ቢሊዮን ካሣ እንድትከፍል ተስማምታለች። (17) ይኸውም ክፍያ፤ ኢጣልያ ሊብያም ውስጥ ግፍ በመፈጸሟ ብቻ ሳይሆን፤ 30000 ሊብያውያን ወታደሮች ኢትዮጵያ ላይ በማዝመቷ ነው። (18)

 

2ኛ/ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን የጦር ወንጀል በታሪክ ሰነዱ አላሰፈረውም። በኢትዮጵያ ላይ የጦር ወንጀል ፈጽመው የነበሩት ፋሺሽቶች አብዛኛዎቹ ለፍርድ ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

 

3ኛ/ ቫቲካንም፤ ከላይ እንደ ተጠቀሰው፤ እስካሁን ድረስ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ሳትጠይቅ መቅረቷ ብቻ ሳይሆን፤ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው፤ የሙሶሊኒና የፋሺሽቶቹ ደጋፊ የነበሩትን፤ ፖፕ ፓየስ 12ኛን ወደ “ቅዱስነት” ደረጃ ከፍ ለማድረግ፤ ቫቲካን አንድ ሒደት ጀምራለች። (19)

 

4ኛ/ ቫቲካንና የኢጣልያን መንግሥቶች፤ በጦርነቱ ጊዜ የተዘረፉትን የኢትዮጵያን ንብረቶች እስካሁን አልመለሱም።

 

ለፋሺሽቱ መሪ፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ በኢጣልያ፤ ሰሞኑን ስለ ተቋቋመው መካነመቃብ ርና መናፈሻ

 

እንደሚታወቀው፤ ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን ሐገሪቱን በግፍ ይገዛ የነበረው ማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ ነበር። ያ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፈና ብዙ ውድመት ያደረሰው የጦር ወንጀለኛ፤ 19 ዓመት እሥራት ከተፈረደበት በኋላ፤ ከሁለት ዓመቶች በኋላ ተለቅቆ እ.ኤ.እ. በ1955 ሞቷል።

 

ለተፈጸመው እጅግ አሰቃቂ የፋሺሽት ግፍ ደንታ የሌለው፤ የኢጣልያ መንግሥት፤ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 11 ቀን 2012፤ የቫቲካን ተወካይ በነበሩበት፤ ለግራዚያኒ፤ አንድ መካነመቃብርና የመናፈሻ መታሰቢያ ከሮም ከተማ ወደ ደቡብ በምትገኝ፤ አፊሌ በምትሰኝ ሥፍራ ተከፍቶለታል። ይህ ድርጊት፤ የኢትዮጵያንና የሊቢያን ክብር የሚነካ፤ እጅግ አሳዛኝ ድፍረት በመሆኑ፤ በአፊሌና በለንደን ትእይንተ ሕዝቦች ተከናውነዋል። ስለዚህ ከባድ ጉዳይ፤ “ዓለምአቀፍ ሕብረት ለፍትሕ የኢትዮጵያ ጉዳይ” (www.globalallianceforethiopia.org) የተሰኘው ድርጅታችን ያቀደውና ያከናወነው ከዚህ በታች ይቀርባል።

 

  • Syoum Gebregziabher, “The Symphony of My Life”, 2012
  • Kidane Alemayehu, “Italy’s Excellent News for Ethiopia”; posted on www.globalallianceforethiopia.org)
  • Theodore Vestal, “Libyan Soldiers in Ethiopia”; (posted onglobalallianceforethiopia.org)
  • Kidane Alemayehu, “Why is the Vatican Adding Insult to Injury on Ethiopia?”

 

የ“ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ የኢትዮጵያ ጉዳይ” ድርጅት (Global Allaince for Justice – The Ethiopian Cause) www.globalallianceforethiopia.org ዓላማና ተግባሮች፤(20)

 

ባጭሩ፤ የዚህ ድርጅት ዓላማዎች፤

  • ቫቲካን ከፋሺሽቶች ጋር ተባብራ በሐገራችን ላይ ለደረሰው የጦር ወንጀል፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤
  • የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን የጦር ወንጀል በሰነዱ እንዲመዘግብ፤

 

(ሐ) በቫቲካንና በኢጣልያ የተዘረፉት ንብረቶች ለኢትዮጵያ እንዲመለሱ፤

  • በፋሺሽቶች አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው እልቂትና ውድመት፤ የኢጣልያ መንግሥት ተገቢውን ካሣ እንድትከፍል፤
  • በቅርቡ፤ ለፋሺሽቱ የጦር ወንጀለኛ፤ ለማርሻል ግራዚያኒ፤ የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት የኢጣልያን መንግሥት በቅርቡ የከፈተው መካነመቃብርና መናፈሻ ሥፍራ እንዲፈርስ ለማድረግ ነው ።

ድርጅቱ እስካሁን ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባሮች ውስጥ፤ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፤

1ኛ/ ቫቲካን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤ የሚያመለክት ደብዳቤ ላሁኑ ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ከማቅረቡ በላይ፤ ስለዚሁ ጉዳይ፤ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች፤ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፕሬዚዳንትና ለእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ድጋፍ የማስገኚያ ደብዳቤዎች ጽፏል። እንዲሁም፤ ከላይ በተጠቀሰው የድርጅቱ ድረገ ጽ፤ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ የሚያሳስብ አንድ ዓለምአቀፍ አቤቱታ እየተፈረመ ነው። እስካ ሁን ድረስ፤ ከ30 ሐገሮች በላይ የሚኖሩ 3490 ዜጎች፤ አቤቱታውን ፈርመውታል። ከፈራሚዎቹ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች ሐገሮች ምሑራንም ይገኙበታል። በተለይ ሊጠቀስ የሚገባው፤ ጆን ፖሊፍሮኒዮ (John Polifronio) የተባለ፤ የኢጣልያ ትውልድ የሆነ ሰው፤ በፊርማው ዝርዝር ቁጥር 60 ላይ ከዚህ የሚከተለውን አስተያየቱን አስፍሯል፤

“I’m an Italian, born during this atrocity, and wish to express my profoundest horror that this was done by members of the government,who were from the country of my origins……” (ትርጉም፤ እኔ በዚህ ሰቆቃ ጊዜ የተወለድኩ ኢጣልያዊ ስለ ሆንኩ፤ የትውልድ ሐገሬ መንግሥት ስለ ፈጸመው የሚሰማኝን እጅግ ጥልቅ ሰቀቀን ለመግለጽ እወዳለሁ።..)

2ኛ/ ከኢትዮጵያ የተዘረፉ አንዳንድ ንብረቶች፤ በተለይ፤ በቫቲካን እጅ የሚገኙት ከ500 በላይ የሆኑ ሰነዶች፤ እንዲሁም በኢጣልያ አየር ኃይል ሚዩዚየም የምትገኘው፤ “ፀሀይ” የተሰኘች አይሮፕላን፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመለሱ በጽሑፍ ተጠይቋል።

(20)ይህ ጽሑፍ የቀረበው፤ በደራሲው የግል ኃላፊነት ቢሆንም፤ “ዓለምአቀፍ ሕብረ ት ለፍትሕ የኢትዮጵያ ጉዳይ” (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) (www.globalallianceforethiopia.org) የተሰኘው ድርጅት አመራር አባል መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው።

3ኛ/ ከኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር ጋር በሕብረት ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው።

 

4ኛ/ በቅርቡ፤ የቫቲካን መንግሥት ተወካይ በተገኙበት፤ “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” በመባል ለሚታወቀው፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ በኢጣልያ፤ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 11 ቀን 2012 የተመረቀው መካነ መቃብርና መናፈሻ እንዲፈርስ በማሳሰብ ለኢጣልያን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ደብዳቤ ከመጻፉ በላይ፤ የድርጅቱን አቋም የሚገልጹ ልዩ ልዩ መግለጫዎች አውጥቷል።

 

  • በለንደን ከተማና በአፊሌ የተከናወኑትን ትእይንተሕዝቦች ደግፏል። በቅርቡ ም፤ በዋሺንግተን፤ ዲ.ሲ. ተመሳሳይ ትእይንተ ሕዝብ እንዲከናወን ታቅዷል።

 

5ኛ/ እ.ኤ.አ በ1947፤ ካሣ ተብሎ፤ የቆቃ ግድብ የተሠራበት፤ 6 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ፤ ከተፈጸመው ግፍ ጋር ሲመዛዘን፤ በምንም መስፈርት በቂ ስላልሆነ፤ ተገቢው ካሣ ለኢትዮጵያ እንዲከፈል ጥረቱ ይቀጥላል። በዚህ አጋጣሚ፤ በመደጋገም መገለጽ የሚገባው፤ ኢጣልያ በሊቢያ ላይ ለፈጸመችው ግፍ 5 ቢሊዮን ዶላር ካሣ ለመክፈል በቅርቡ የተስማማች በመሆኑ፤ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ለተጨፈጨፈባት ለኢትዮጵያ መከፈል ያለበት ካሣ ከዚያም የላቀ መሆኑን ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ ነው።

 

6ኛ/ የዓለም መንግሥታት ድርጅት፤ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን የጦር ወንጀል እንዲመዘግበው ጥረት ይደረጋል።

 

7ኛ/ ለወደፊቱም፤ ድርጅቱ ለቆመባቸው ዓላማዎች፤ ዓለምአቀፍ ድጋፍ እንዲያገኝ፤ ሰፊ ጥረቱን ይቀጥላል።

 

ድምዳሜ፤

1ኛ/ ከላይ በቀረበው ዝርዝር ማስረጃ መሠረት፤ ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው እጅግ የከፋ ግፍ፤ ሊከናወን የቻለው፤ በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ገጽ 8 ላይ የተጠቀሱት፤ ፕሮፌሰር ቲዮዶር ቬስታል፤ እቅጩን እንዳስቀመጡት፤ እውነቱን ለመስማትና ለማየት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አያጣውም።

 

2ኛ/ ኢትዮጵያ ሐገራችን ለደረሰባት እጅግ ከፍ ያለ ጥፋትና በደል ሁሉ ተገቢውን ፍትሕ ያላገኘች በመሆኑ፤ እኛ ዜጎቿና ለሰብአዊ መብት የቆሙ ሰዎችና ድርጅቶች ሁሉ፤ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤ የኢጣልያ መንግሥት፤ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍልና የግራዚያንንም መካነ መቃብርና መናፈሻ እንዲያፈርስ፤ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታትም በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን የጦር ወንጀል፤ በታሪክ ሰነዱ እንዲያውል ያላሰለሰ ጥረት ማድረገ ይገባናል። አሁን በነጻነት የምንኖረው፤ በብዙ መስዋእት መሆኑን በማሰብ፤ “እሳት አመድ ይወልዳል” እንዳንባል መጠንቀቅ ይኖርብናል።

 

ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ፤ ጥረታችንን ባርኮ ለቁምነገር ያብቃን።

 

https://zehabesha.com/wp-content/uploads/2023/02/RODOLFO-GRAZIANI2.pdf

https://zehabesha.com/rodolfo-graziani-war-criminal-who-escaped-justice/

 

 

https://zehabesha.com/africa-ready-for-continental-synod-meeting-in-ethiopia/?ct=t(RSS_EMAIL_CAMPAIGN)&mc_cid=2c355e3442&mc_eid=37d69347d6

1 Comment

  1. ክቡር ኪዳኔ አለማየሁ ኢትዮጵያዊ ሰላምታዬ ካለህበት ይድረስህ መቼም ለሃገርህ በትጋት የምታደርገውን ጥረት በግል ሳላመሰግን ባልፍ ህሊናዬ ጋር ትግልና ሙግት እገጥማለሁ፡፡ ባለፈው ለፋሺስቱ የመታሰቢያ አደባባይ እንዳይገነባለት በገዛ ሃገሩ ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀህ ማስቀረትህ በዘመናችን ዘርአይ ደረስ ከሰራው ስራ የተናነሰ አይሆንምና እድሜና ጤና ይስጥልን፡፡
    ስለ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ጉዳይ ስንመለስ እንዳንተው ሁሉ ለሃገራቸው የደከሙ በመሆናቸው ይህ በምዘና ስህተት ታሪክን ለቀነሱበት ባንተ በኩል እርምት መወሰዱ ደስ የሚል ነው፡፡ በማስረጃ የተሰራውን የታሪክ ስህተት እርምት በመስጠትህ ሲጠቅስ የሚኖረው ያንተው ነው፡፡ አንድ ሰሞንም እንደ ዘመኑ ፓስተሮች ካቶሊክን አትንኩብን የሚል ገመድ ጉተታ መጥቶ ነበር መቼም የችግራችን ምንጩ ተቀድቶ አያልቅም፡፡ አምባሳደር እንኳን ኮቶሊክ ይሁኑ አይሁኑ አላውቅም ቢሆኑም ታሪክ እንዳለ መቅረብ ነበረበት፡፡
    ጌታዬ ዛሬ ከጥልያን በላይ ግፉ የበዛብን የጥልያን ልጆች (ትግሬዎች እነዛ እንኳን ተገንጥለዋል) ጡጦ እያጠቡ ያሳደጓቸው የራሳቸው የሆነ እሳቤ የሌላቸው ከላይ የተጫኑብን ጉግ ማንጉጎች ናቸው፡፡ ከታሪክ እንደምናነበው ጣሊያን ጥሩ አርበኛም ሲሞት በሰልፍና በክብር እንደሚቀብረው ነው የዛሬዎች የዲያብሎስ ዝርያዎች በማይካድራ የ10፣000 ዜጋ አንገት ቀንጥሰው ተቀነጠስን ብለው የሚያወሩ ለመዋሸት ወደ ኋላ የማይሉ ምሁራኖቻቸውም ከተራው ዜጋ የማይሻሉ ክፉ ፍጥረቶች ሲሆኑ ኦነግ የተባለው የነሱ ውላጅ ደግሞ ለሰው ህይወት ቁብ የማይሰጠው እርጉዝና ሴት ሳይለዩ በር ዘግተው የሚያቃጥሉ የሚገድሉ የሚያርዱ ሰው ሁነው ሰው ያልሆኑ ጭራቆች ገጥመውናል፡፡ 1፣500 አማራ ሲገደል ጠ/ሚኒስተሩ ምንም እንዳልሆነ ሁሉ መደበኛ ስራውን ተረጋግቶ ይሰራል አሁን አሁንማ 85 ሰው ሞተ የሚባለውን ተለማምደነው ማዘንን አቁመናል፡፡
    እንግዲህ ጌታዬ አባቶቻችን ላይ በደረሰው በደል አንተ ልጃቸው ዛሬ በቁጭት እርምት ማድረገህ የሚያስመስግን ሁኖ ዛሬ የአዳምን ፍጥረት ቁም ስቅል የሚያሳዩትን ክፉዎችም ጨምረህ የተቻለህን ብታደርግ መልካም ይመስለኛል፡፡ ረጅም እድሜ መልካም ጤና

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share