ያ ትውልድና የብሄረሰቦች ጥያቄን አስመልክቶ አጭር አስተያየት – አበጋዝ ወንድሙ

ያ ትውልድ ተብሎ የሚታወቀውና በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ 1960ዎቹና በ 1970ዎቹ፣ በተማሪውና በግራ ዘመም ድርጅቶች ተካፋይ የነበረው ትውልድ፣ በዘመነኞች ብዙ የሚወቀስባቸው ነገሮች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።  በጥቅሉ ሲታይ ኩነኔው የሚጠነክረው ግን ‘የ ብሄረሰቦች ጥያቄ በሚል የሌለ ነገር ፈብርኮ’ ወይንም ትንሽ ‘ቸር’ በሆኑት ወገኞች ደግሞ፣ የሌሎች ሀገሮችን ልምድ ከሀገራችን ሁኔታ ሳያገናዝብ እንዳለ ኮርጆ በማምጣት አሁን ሀገራችን ለገባችበት ችግር ዳረገን የሚል ይገኝበታል።

በሌላ ወገን ደግሞ፣ ራሳቸውን የተወሰነ ብሄረሰብ ብቸኛ ጠበቆች አድርገው በሚወስዱ ጠባብ ብሄርተኛ ወገኖች ደግሞ፣ ዋለልኝ የጻፋት ባለ አምስት ገጽ ጽሁፍ ላይ ተቸክለው፣ ትውልዱ የብሄር ጥያቄን አስመልክቶ የነበረውንና፣ በሂደትም፣ በጥልቀት ያዳበረውን አመለካከት ሳይሆን፣ ዋለልኝ ጽሁፍ ላይ ‘ቁንጽል ቃል ወይንም ሃሳብ ወስዳችሁ ግነትን አስወግዱ’ ያለውን ምክር ዘንግተው የሚያካሂዱት የተዛባ እንቅስቃሴ፣ ትውልዱ ላይ ለሚደርስበት የሀሰት ውንጀላ የራሱ ድርሻ አለው።

ዋለልኝ ‘የብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ ያቀረበው ባለ አምስት ገጽ ጽሁፍ፣ እሱ ራሱ እንዳለው  ‘የጅምላ እሳቤና የደካማ ትንታኔ ‘ (suffers from generalizations and inadequate analysis) ችግር ቢኖርበትም፣ ለጀማሪ ጽሁፍ ግን ‘ተራ ወይንም እዚህ ግባ  የማይባል’ (  mediocre) እንዳልሆነ ይገልጻል ። ጽሁፉ የዋለልኝን ስም ይዞ ይውጣ እንጂ  በጽሁፉ እንደገለጸው የተወሰኑ ሰዎች በህቡዕ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ያካሂዱበት የነበረ ስለነበር ፣ ጽሁፉ የቡድኑን አመለካከት ያንጸባርቃል የሚል ግምት መውሰድ ይቻላል።

በወቅቱ በቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ የነበሩ የተማሪው ትግል አቀጣጣይ መሪዎች ፣ በአጠቃላይ በዓለም ላይ የበላይነት ይዞ የነበረው የሶሻሊስት አመለካከት ‘ምርኮኛ’ የነበሩ በመሆኑ ፣ የህብረተሰብ ችግር ትንታኔያቸው በዚያው አውድ ውስጥ እንደነበር ይታወቃል።

ሆኖም የህብረተሰብ ችግርን ተንትነው የሚረዱበት መንገድ፣ ሶሻሊስት አመለካከት ላይ ባላቸው ወይንም በነበራቸው በቂ ያልሆነ ወይንም የዕውቀት ውሱንነት ላይ የሚመሰረት በመሆኑ፣ የዋለልኝንም ጽሁፍ ማየትና መረዳትም ያለብን ከዛ አንጻር ሊሆን ይገባ ነበር ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለአማራ ህዝብ ታሪካዊ ጉዞ ጥናታዊ ፅሁፍ መነሻና መንደርደሪያ የሚሆን ግንዛቤ፣

ለዚህም ነው፣ የዋለልኝ ጽሁፍ በኢትዮጵያ የ ብሄረሰቦች ጥያቄ ላይ ያለው ፈር ቀዳጅነት እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ግርድፍና ያልተሟሸ ስለነበር ፣ የተማሪው ንቅናቄም ሆነ በወቅቱ የነበሩት የሶሻሊስት ርአዮተ ዓለም ተከታይ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሂደት ጥያቄውን በቅጡ ተወያይተው፣ አበልጽገውና አዳብረው በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችን  በማቅረብ በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ ነው ብለው የሚያስቡትን  አቋም ለመውሰድ የበቁት።

በወቅቱ ይመሩበት ከነበረው የሶሻሊስት ርአዮተ ዓለም በመነሳትም ፣ የብሄረሰቦች ጥያቄ በህብረተሰብ ውስጥ ካሉት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች አንዱና ምላሽ የሚያስፈለገው ቢሆንም፣ በዋናነት ግን የህብረተሰቡ ችግር የሚፈታው የሁሉም ብሄረሰብ አባላት የተጨቆኑ መደቦች በአንድነት ፣በአንድ የሰራተኞች ፓርቲ መሪነት ተደራጅተው በሚያደርጉት የህብረት ትግልና ይዞት በሚመጣው ሶሻሊስታዊ ስርዓት እንደነበር በሙሉ ልብ  ያምኑም ነበር።

በወቅቱ የ የካቲትን አብዮት ተከትሎ በሀገርቤት የነበሩት ሁለት ዋና ዋና የግራ ድርጅቶች፣ማለትም ኢህአፓም ሆነ መኢሶንና እንዲሁም ሌሎች ህብረብሄራዊ ድርጅቶች ፣ አደረጃጀታቸው፣ የአባላት ምልመላቸውና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ህብረብሄራዊ የነበረ ከመሆኑም በላይ፣ በኢትዮጵያ የብሄረሰቦችን ጥያቄ አፈታት አስመልክቶ የነበራቸው መሰረታዊ አቋም ከላይ በተጠቀሰው የሶሻሊስት ርአዮተ ዓለም የተቃኘ ነበር። (ትናንት የህብረብሄራዊ ትግል አቀንቃኝና መሪ የነበሩትን እኔ ሃይሌ ፊዳን ‘ቀይ ጎበናዎች’ እያለ ሲያወግዝ የከረመ የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኛ ዛሬ ላይ ‘ሃቀኛ የኦሮሞ ታጋዮች’ በሚል ማንቆለጳጰስና ወደ ጠባብ ብሄርተኛ ታጋይ ጉያ ለመክተት ሲውተረተር ማየቱ ገራሚ ቢሆንም!)

ሁለቱም ድርጅቶች የብሄረሰቦች ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ የሚያገኘው ከመደብ ትግሉ ስኬት ጋር እንደሆነ ቢቀበሉም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የ የካቲትን አብዮት ተከትሎ የፈሉ ድርጅቶችን ፣ በየብሄረሰቡ ያሉ የገዥ መደብ አባላት ‘የኛ’ የሚሉትን፣ ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍል  ነጥሎ ለመበዝበዝ እንዲያመቻቸው ስሜት ኮርኳሪ ቅስቀሳ በማካሄድ የጭቁኖችን አንድነት ሊያላሉ ስለሚችሉ ፣ ይሄንን ለመግታትና ትግሉን ፈር ለማስያዝ ፣ በብሄር ለተደራጁትም ትግሎች ውሱን  ድጋፋቸውን አልነፈጉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጲያ ገዳማት እና የግብፅ ሴራ የመነኮሳቱ ገድል እንዳይረሳ!

የብሄሮች ጥያቄን ዴሞክራሲያዊ ገጽታ ተቀብለው ድጋፋቸውን ቢሰጡም ግን በዋናነት የተንቀሳቀሱት ፣ ህብረብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበት እንደነበር በወቅቱ የሚያወጧቸው ጽሑፎችም ሆነ ውድ ህይወታቸውንም የገበሩበት የትግል ታሪካቸው ህያው ምስክር ነው ።

በወቅቱ የነበሩት ድርጅቶችም ሆነ አባላቱ ሊወቀሱ የሚገባቸው ነገር ቢኖር ጠባብ ብሄረተኝነትና፣ በዛም ላይ ተመስርቶ የተደራጁ ድርጅቶች የሚያደርጉት ስሜታዊ ቅስቀሳዎች ምን ያህል  ህዝብን በቀላሉ የማማለል ሃይል እንዳላቸው ባለመገንዘብ ፣ ከድርጅቶቹ ጋር ማድረግ የነበረባቸውን ፣ አስፈላጊና ጠንካራ ርዕዮተ ዓለማዊ ትግል አለማድረግና፣ ይብሱኑ  ያሳዩት ቸልተኝነት፣ደርግ ካደረገባቸው ገደብ የለሽ ጭፍጨፋና፣ ድርጅቶቹን ለማጥፋት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ጋር ተዳምሮ ፣ በሂደት ህብረብሄራዊ ትግሉን ሸርሽሮና አዳክሞ ጠባብነት የበላይነት እንዲጎናጸፍ ማስቻሉ ላይ ነው።

በወቅቱ በዚህ ጥያቄ ላይ የተሰራው ስህተት ለብሄርተኛ ድርጅቶች ጎልቶ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ያገኙትን ጥንካሬ በመጠቀም ከደርጉ በትር ተርፈው ለማንሰራራት የሚሞክሩትን ህብረብሄራዊ ድርጅቶች በተቀናጀ መልክ ጦር መዘው እስከ መበተንና ራሳቸውንም እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል ።

የዚህ መዘዝም ሀገራችን ከ1983 ዓ.ም. የህወሃት ስልጣን ላይ መውጣት ጀምሮ እስካሁን የሀገሪቱን ፖለቲካ የሚንጥ፣ የሀገራችንን የዴሞክራሲና የእድገት ጎዳና በማጨናገፍ ላይ ያለ መሰረታዊ ችግር ሆኖ ዘልቋል።

ህወሃት፣ ኢህአዴግ የሚል ጭምብል አጥልቆ አራት ኪሎን ቢቆጣጠርም፣ በጠባብ ብሄርተኝነት የተቃኘው መሰረታዊው ስትራቴጂው፣ ሃገራዊ አንድነትን በማላላትና በብሄረሰቦች መሃከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ በማደፍረስና ልዩነትን በማራገብ፣ የበላይነቱን ለዘለቄታው የሚያስቀጥል መስሎት ስለነበር፣ ለ 27 አመታት ሲተገብረው ከርሞ፣ በስተመጨረሻ አገዛዙ ባንገሽገሻቸው አካላት የተባበረ ህዝባዊ ትግል ለውድቀት ተዳርጓል ።

እኩልነትና ፍትሃዊ አገዛዝ በናፈቀው ህዝብ ትግል የሀወሃትን የበላይነት ተክቶ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት የጨበጠው የኦሮሞ ብልጽግና ክንፍ፣ በመጀመሪያው ዓመት በመሪው አማካኝነት ካለፈው ስህተት ተምሬ ከልዩነት ይልቅ ሃገራዊ አንድነት ላይ አበክሬ እሰራለሁ ብሎ ምሎ ቢገዘትም ፣ በሂደት ግን ከህወሃት ውድቀት ምንም ያልተማረ እንዲያውም የከፋ ጠባብ ብሄርተኛ አንጃ በውስጡ አቅፎ ፣ ሀገሪቷን ከባድ አደጋ ላይ ጥሏት ይገኛል፤ በወቅቱ ካልታረመም በታኝ የመሆን ወይንም ሀገራችንን ለማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት የመዳረግ አቅም ሊኖረው    ስለሚችል፣ ዛሬም እንደትላንቱ ጠባብ ብሄርተኝነት ለሀገር እድገትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንቅፋት ስለሆነ በጽኑ ልንታገለው ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከታሪክ ማህደር: እውቁ የታሪክ ዘካሪ ፀሐፊ ደራሲ አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ

ያለፉት 31 ዓመታት በተግባር የታየው የጠባብ ብሄርተኞች አገዛዝ ለሀገር የማይበጅ፣ እንወክለዋለን በሚል በስሙ የሚነግዱበት ብሄረሰብንም ከርሃብ፣ከድህነትና ከቸነፈር ፈቅ ያላደረገ፣ ፍትህን የነፈገ ፣ በተቃራኒው ለአገዛዙ ቁንጮዎችና ባለሟሎቻቸው ስልጣንና ንብረት ዘረፋ የተመቻቸ እንደነበር ያየነውና በማየት ላይ ያለነው እውነታ ነው።

ጠባብ ብሄርተኛ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአንድ ህብረብሄራዊ ሀገር፣ የኛ ከሚል እሳቤ ይልቅ ሁልጊዜ የኔ ለሚለው ወገን ብቻ ተቆርቋሪ መስሎ ራሱን ለበላይነት የሚያጭን ኃይል ይመለከታል። አንዳንድ የጨነቀረ አስተሳሰብ የሚያራምዱ አካላት ከህዝብ ቁጥር ጋር በማያያዝ ፣ ጠባብነት በቁጥር ትንሽ ለሆኑ የብሄረሰብ ክፍሎች ብቻ የተሰጠ የሚመስላቸው፣ በቁጥር ትንሽ ሆኖ ሀገራችንን 27 ዓመት ያመሰውን ህወሃትና አሁን ደግሞ በተራው እያመሰን ያለውን የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን አካሄድ ማጤን ትምህርት ይሆናቸዋል።

ከላይ የቀረበውን ዕውነታ በቅጡ ካገናዘብን ፣ የስልሳዎቹ ታጋዮች ስለ ጠባብ ብሄርተኞች መሰረታዊ ድክመት የነበራቸውን እይታ ትክክለኛነት የሚያሳይ መሆኑን፣ ጠባብ ብሄርተኞች በትግል ስም ለሰፊው ሕዝብ ሳይሆን፣ ለራሳቸው ለልሂቃኑ የዘረፋ መንገድ ለማመቻቸት የተቧደኑ ሰፍሳፋዎች መሆናቸውን ተገንዝቦ፣ ለዴሞክራሲ ለፍትህና ለሀገራዊ እድገት ህብረብሄራዊ ትግል ብችኛው አማራጭ ነዉ ብሎ መታገሉ ሊያስመሰግነው የሚገባ እንጂ የሚያስወቅሰው መሆን አልነበረበትም።

 

 

4 Comments

  1. The reality is that the entire Stalinist ideology was imported to serve as a tool to weaken the Ethiopian government. When the much older Eritrean secessionist movement adopted and introduced the radical movements into the Ethiopian student body, the goal was not to fight for a new era of democracy, rather to help weaken the Ethiopian state from within.
    Communism, with its track record for demolishing a monarchy from within and its anti-Christian, atheist values was brought in and slogans such as “land to the tiller” introduced against the very interests of the northern Ethiopia communities from which the students hailed.
    From the perspective of the duped generation, what was attempted was to fit the leg into the shoe and not the shoe onto the leg. As a result Ethiopian polity as well as valued were chopped to pieces.

  2. ባጭር አባባል ነገሮችን ቁጭ ቁልጭ አርጎ ለአንባቢ ለማሳየት የተፈጥሮ ስጦታ ይጠይቃል፡፡ መማር ብቻውን አያጣፍጠውም፡፡ ከላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በ Ahoon የጻፈው ባጭሩ ገመናና መከራችን አሳምሮ ያሳያል፡፡ ልክ ነው በልዪ ልዪ ብሄር ውስጥ በንጉሱም ሆነ በደርግ መንግስት ውስጥ በስልጣን ላይ የነበሩ ሁሉ ሃገሪቱን ለማፍረስ ብዙ ሴራ ፈጽመዋል። ለውድ ሃገራቸው ሌት ተቀን የሚያስቡ ተማሪዎች፤ የሰራተኛ መሪዎች፤ ወታደራዊ መኮንኖች፤ የህብረተሰብ ተሰሚነት የነበራቸው ሁሉ በየሰበባ ሰበቡ እንዲታሰሩ፤ እንዲገደሉ ታላቅ የህቡዕ አስተዋጾ አድርገዋል። ከበረሃ ተጽፎ የተላከ በማስመሰል በሰዎች ኪስ፤ መ/ቤት ወይም መኖሪያ ቤት ውስጥ ወረቀቶችን በማስቀመጥ የተቃዋሚና አድሃሪ ድርጅት ወረቀት ተገኘባቸው እየተባለ ስንቶች በተቀነባበረ ሴራ ለሞት ተዳርገዋል። በስንቶች ላይ የውሸት ምስክር ቆሟል? ቤቱ ይቁጠረው! ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የግፈኞች ሃገር ናት የምለው። ዛሬ ያን ትውልድ በዚህም በዚያም የሚያጣጥሉ የቁም ሙቶች ሰው የሚመዘነው በኖረበት ዘመንና ጊዜ መሆኑ ለእነርሱ አይገባቸውም። ጥያቄው ዛሬ እነዚህ የዘር ፓለቲካ ድውያኖች አሁን ላይ ቆመው ምን እያደረጉ ይገኛሉ? በውኑ ካለፈው መጠላለፍና መገዳደል የዛሬው የተሻለ ነውን? በጭራሽ፤ ባሰበት እንጂ! እንደ እንቁራሪት አንድ ሲጮህ ሌላው ተከትሎ የሚንጋጋበት እንደ አሽን አንዴ ወሮ እንደ አሸን አንዴ የሚረግፍባት ምድር ካለፈው ስህተት የተማረው የቱ ላይ ነው? ያለፈን ነገር ጭቃ እየቀቡ ራሳቸው አረንቋ ውስጥ ሲንከባለሉ ማየትና መስማት ምንኛ የሰውን ጅልነት ያሳያል።
    በየዘመናቱ አፋቸው ማር ድርጊታቸው ድርቡሽ የሆኑ ባለስልጣኖች በምድሪቱ ላይ ብቅ እያሉ ከክፋት ወደ ክፋት ሲያሸጋግሩን ሰው ለምን ደነዘዘ? መልሱ አንድ ነው የራሱን ቤት እሳት እስኪለበልበው ድረስ ስለ ጎረቤቱ ቤት አመድ መሆን ምንም የማይገደው የተሳከረ የፓለቲካ እይታ ላይ ስለሆነ ነው። የመኖር ተስፈኝነቱና የጊዜው የፓለቲካ ትኩሳት ተሰላፊነቱ በራስ ማሰቡን ስለቀማው የፓለቲካ ፍርፋሬ እየለቀሙ መኖር ብልሃት ነው ብለው ይዘውታል። በየትኛውም የኢትዮጵያ የፓለቲካ ታሪክ ውስጥ ሰውን ለክትባት ተሰብሰቡ ብሎ መትረጌስ ያርከፈከፈና በጅምላ አንድ ዘርን መርጦ የፈጀ የፓለቲካ ያየነው? ይህ ግን በኦሮሞ ጭፍን ፓለቲከኞች አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው በኦነግ ሸኔ በኩል የሚያስፈጽሙት ተግባር እንደሆነ እልፍ መረጃዎች አሉ። ሰው የሆነ ያለምንም ግጭት አርሶ አደር ገበሬን የሚረሽን፤ ቤቱን የሚያቃጥል፤ የጤናና የንግድ ተቋሞችን የሚዘርፍና የሚያቃጥል ድርጅት እንዴት ባለ ሂሳብ ስለ ኦሮሞ ነጻነት ይገደዋል ብሎ የሰው ልጅ ያምናል? በቅርቡ 27% የኢትዮጵያ ህዝብ የአዕምሮ በሽታ ተጠቂ ነው የሚለውን ስመለከት አልተገረምኩም። ታማሚው ከጥቃትና ከዘረፋ የተረፈው ብቻ ሳይሆን የሰውን ደም እንደ ውሃ ያፈሰሰው የዘር ፓለቲካ አራማጅ የቁም ሙትም ቁማርተኛም ጭምር ነውና ቁጥሩ ከፍ ማለት ነበረበት ባይ ነኝ። ሰው ቆሞ ስለሄደ ጠነኛ ነው ማለት አይቻልም። በፈጠሩት በራሳቸው ዓለም እየኖሩ የሚስቁ ስንቶ ናቸው?
    ንጉሱን ሌባ ሌባ እያለ ያስወረደው ያ ትውልድ ሌላ ሌባና ሌላ የሃገርና የወገን ጠንቅ ነው ያመጣው። ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም ያለው የወታደር ስብስብም የ17 ዓመቱ መከራው ሲገታ ሰራዊቱን በትኖ፤ ሃገርን ለብሄርተኞች አስረክቦ ነው የፈረጠጠው። ወያኔና ሻቢያ ደግሞ የከተማ አለቆች ከሆኑ በህዋላ የተፈጠረው ሽርክናና ፉክቻ የሩቅ ጊዜ ታሪክ ስላልሆነ እዚህ ላይ መድገም አላስፈላጊ ነው። ዛሬም የቆምንበትንና የምንራመድበትን የከፋ የድህነት ፓለቲካ እያየን ነው። ባጭሩ ትላንት የሚያለቅሱ አይኖች ዛሬም ያለቅሳሉ። ትላንት የተራቡ ዛሬም ይራባሉ፤ ይሰደዳሉ። ችግራችን ብዙ ነው። ግን የሚበልጠው ችግር እኛው ራሳችን በራሳችን ላይ የምናዘንበው የመከራ ዝናብ ነው። የተከመረ ክምር አቃጥሎ ተራብኩ የሚል የጅል መንጋ። አሁን ደግሞ ይባስ ተብሎ ከሱማሊያ የተገነጠለችው ጎረቤታችን ሱማሊላንድ በዚህም በዚያም እየተጋጩ ወደ 80ሺህ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገቡ ይለናል የቀኑ ወሬ። ነገስ ምን እንሰማ ይሆን? በቃኝ!

  3. ወንድማችን አበጋዝ የሰጠህን ሚዛናዊና ወቅታዊ ትንታኔ በወቅቱ ለጋ ወጣት ብሆንም ማን ይመስከር የነበረ ነውና እውነታውን ከወቅቱ የፖለቲካ ሂደት ጋር ለማስማማት በሚችል መልኩ የቀረብ ድንቅ ጽሁፍ ነው አመሰግናለሁ::
    የተማሪው ትግል በሃገር ቤትም በውጭም ግምባር ቀደም ሆኖ ሲንቀሳቀስ ለማስተባበር የተሰለፉት ከንጉሳዊ በተሰብ በጋብቻ የተገኘው ጥላሁን ግዛው የከበርቴ ልጅ የነበረው ዋለልኝ መኮን ን ሃገረገዥ የነበሩት የጄነራል መብራቱ ልጅ ማርታ መብራቱና ሌሎቹም የተገፋው ህዝባችን ጉዳይ ግድ ብሏቸው ክቡር ህይወታቸውን የሰጡትን ድሮም ዛሬም የሚነቅፉ የሚያሳዝኑ ሰዎች ናቸው:: አበጋዝ እንዳልከው በዚያን ወቅት የቀረቡ ትንታኔዎች በተለይ ከዘሩ በላይ ኢትዮጲያን የሚያስቀድመው አማራን ከሁሉም ዘረ የግፈኛው ነፍጠኛው ስርአት የተሳተፉበትን በተናጠል አማራውን ዛሬ ተመርጦ እንዲታረድ እንዲፈናቀልና እንዲሰደብ ያደረገው ከስህተቶ ቹ አንዱ ቢሆንም ሀሉም የኢትዮጲያ ህዝቦች በተለይ ገባር ተብለው የተለየ ጭቆና በነበሩት ገዥዎች የደረሰባቸውን አማራ ጨቆነ የሚለው የሳተ አካሄድ ሲሆን እነዚህ ህዝቦች የመሬታቸው ባለቤትነት እንዲረጋገጥ መሬት ላራሹ የሚለውን ድንቅ መርህ ያራመዱ እኩለነትን ያወጁ ታሪካቸው ዘላለም ሊወሳ የሚገባ ነው:: የደቡብ አፍሪካ /አዛኒያ/ ህዝቦች ትግል በነማንዴላ የተጠቀመበት የማርክሲዝም ፍልስፍና በወቅቱ ተገቢ የነበረ ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ያንን ድርጊት ማውገዝ ተገቢ አይደለም:: የነበረውን ግፍ ለተማሪው ትግል ቀስቃሽ የነበሩ የታላቁ ደራሲ ሃዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር የአቤ ጉበኛ አልወለድምን በጥሞና የሚያነብ የዚያ ትውልድን ተገቢ የትግል ሂደት ይረዳል::
    ዛሬ ሊደረግ የሚገባው የትጋረጠብን በዘረኝነት የተሞላ ክፉ ፕለቲካና መስተዳድር ህዝባችን ን በመከባበር በመፈቃቀድ እንዴት በሰላም ወደተሻለ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት እንሻገር ያሉትን ልዩነቶች በነጻ መድረክ በመወያየት መፍታት እንዴት ይለመድ የሚለው ወቅታዊ ወሳኝ ጉዳይ ነው ::ፓስተር ዲጎኔ ሞረቴው

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share