ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ቦዳ ተብላ በምትታውቅ አምቦ ከተማ በምትገኝ ተራራማ አካባቢ በወርሃ ነሐሴ 11ቀን 1928 ዓ.ም ተወለዱ። በአምቦ ማዕረገ ሕይወት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ከዚያም ጄኔራል ዊንጌትና በአዲስ አበባ የንግድ ትምህርት ቤት በአገር ውስጥ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፤ በግዕዝ፣ በአማርኛና በኦሮምኛ እየተማሩ ያደጉት ጸጋዬ፣ የኋላ ኋላ ዓለም ያደነቃቸው ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔትና ባለቅኔ ሆኑ፡፡ ከዚያም በቺካጎ ብላክስቶን በሕግ ትምህርት ተመርቀዋል፤ በ 1952 ዓ.ም በለንደን ከተማ የቴአትር ትምህርታቸውን ደግሞ በሮያል ኮርት ቴአትርና በፓሪስ ኮሜዲ ፍራንሴዝ ተከታትለዋል።
ያኔ በውጭ አገር ተምሮ ወደ አገር ቤት መመለስ ኩራት ነበርና እሳቸውም ወደ አገራቸው ተመልሰው ከ 1954 እስከ 1964 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር በአርቲስቲክ ዳይሬክተርነት አገለግለዋል። ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍልን አቋቁመዋል። በ 1960ዎቹ ደርግ አብዛኛውን የቴአትር ሥራዎቻቸውን ያገደባቸው ሎሬት ፀጋዬ፣ እሳቸውንም አስሯቸው ነበር።
ሎሬት ፀጋዬ በርካታ ግጥሞችን፥ የቴአትር ሥራዎችን የተለያዩ መጣጥፎችንና ዘፈኖችን አበርክተዋል። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ 2002 የብላቴን ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ‹‹አፍሪካዊ በመሆኔ እኮራለሁ›› (“Proud to be African”) በሚል የጻፉት ግጥም በአዲስ በተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሕዝብ መዝሙርነት ከብዙ ተፎካካሪዎች ልቆ ተመርጧል።
በትምህርት እየጎለመሱ ሲሄድም ደራሲነቱን ገጣሚነቱን እንዲያ ሲልም ፀሐፊ-ተውኔትነቱን በዋነኛነት፣ በጎልማሳነት ዘመኑ ደግሞ ማኅበረሰባዊ ሃያሲነት እና የአፍሪካ የሰው ዘር፣ ቋንቋ እና ባህል ጠቢብነትን አክለውበት እስከ ዕለተ ሞታቸው ዘልቀዋል።
ከሐምሌ 14 — 18 ቀን 1989 ዓ.ም በእንግሊዝ፣ ባኪንግሀምሻየር ክፍለ ግዛት፣ ሀይ ዋይኮምብ ከተማ ውስጥ በተካሄደው አሥራ አምስተኛው የዓለም ባለ ቅኔዎች ጉባኤ ላይ፤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን “ኤዞፕ” የተሰኘውን ቅኔያቸውን ከማሰማታቸውም ሌላ ስነ ግጥም ጨለማን ድል አደረገ፤ በዚህም ዓለም ዳነች›› “Poetry Conquered Darkness and the World was Saved” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል።
የዓለም ባለ ቅኔዎች አሥራ አምስተኛ ጉባኤ፤ ፀጋዬ ገብረ መድኅን በአገሩ ቋንቋና በእንግሊዝኛም ጭምር ያበረከቷቸውን ግጥሞች፣ ቅኔዎች እና ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን በመመርመር፤ ሥራዎቻቸውም የሰው ልጅን እኩልነት፣ ነፃነት፣ ወንድማማችነትና ፍቅር አበክረው የገለጡ መሆናቸውን ተረድቶ ባለ ቅኔ ሎሬት የሚያገኘውንና የተከበረውን ባለ ወይራ ዘለላ የወርቅ አክሊል ሸልሟቸዋል።
የሎሬት ፀጋዬ ግጥም መልዕክት ጠቅለል አርገን ስንመለከተው ሁላችንም አንድ እንሁን ለነጻነታችን የተከፈለውን ዋጋ እና ድል እንዘከር የሚል መልዕክት አለው። አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና እና አንድነታቸውን ለመጠበቅ አብረው እንዲሠሩም ያስገነዝባል።
አፍሪካውያን እጣ ፈንታችንን የቀረጹትን፣ ያስተሳሰሩንን ገመዶች እንጠብቅ ይላል። በምድር ላይ ጽኑ ሰላም እና ፍትህ ይሰፍን ዘንድ የአፍሪካ ወንድ እና ሴት ልጆች አብረው መሥራት እንዳለባቸውም ያስገነዝባል። አንድ ሆነን የምንችለውን ሁሉ ለአፍሪካችን ለእስትንፋሳችን እናድርግ ይለናል።
ይህ መዝሙር በመጀመሪያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት በመዝሙርነት የጻፈው ሲሆን፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተካው የአፍሪካ ኅብረት ሲመጣ ደግሞ መዝሙሩን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎታል። መዝሙሩ በተመረጠበት ዓመትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለእዚህ ሥራው ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መዝሙር ሽልማት በሚል ሽልማት አበርክቶለታል።
ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የተለየና ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ከጥበባዊ እውቀታቸው ባሻገር፣ ሰሚ አላገኙም እንጂ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደተሻለ ደረጃ ሊያራምዱ የሚችሉ ሃሳቦችንም በተደጋጋሚ ሰንዝረው ነበር፡፡ በርካታ አንጋፋ የሀገር ውስጥና የውጭ ጸሐፍትና ባለሙያዎች በብዕሮቻቸው ያሞገሷቸውና የመሰከሩላቸው ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ ከፍተኛውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስነ-ጽሑፍ ሽልማትን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡
ባለቅኔው ሎሬት ጋሽ ፀጋዬ ገብረ መድህን ከተለያዩ ግጥሞች በተጨማሪ ከ 35 ተውኔት በላይ ደርሰዋል ከነዚሀም መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፦
- እሳት ወይ አበባ (ግጥምና ቅኔ)
- የዳኒሲዩስ ዳኝነት
#ታሪክን_ወደኋላ
ዳንኤል እንግዳ