በታኅሣሥ አጋማሽ 1954 ዓ.ም በግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ ጥሪ ተደረገለትና በጥር መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ገባ። ይህ ሰው በሦስት ወራት ከአንድ ሳምንት (በ98 ቀናት) ቆይታው ወቅት እጅግ የተጣበበ መርሐ ግብር እንደነበረበት ያስታውቃል።
በጥር 8/1954 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ በተከፈተውና ለአሥር ቀናት ያህል በቆየው፣ “የአፍሪካ ኤኮኖሚና ሶሻል ዕድገት ጉባኤ” ላይ ተካፍሏል። ከተካፋይነትም አልፎ፣ ስሜታዊ የሆነ ንግግር አድርጓል። ብዙዎቹ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ስለሀገሩና ስለሕዝቡ ሰቆቃ ባለማወቃቸውም አዝኗል። (አዲስ ዘመን፣ ጥር 9 ቀን 1954፣ ገጽ 1) ከዚያም በመቀጠል ከጥር 6 እስከ ጥር 14 ቀን 1954 ዓ.ም የተደረጉትን የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያዎች በዛሬው የአዲስ አበባ ስታዲዮም ተገኝቶ ተከታትሏል። ሀገሩ፣ ለምን በዚህ የአፍሪካ ዋንጫም እንዳልተካፈለች የኢትዮጵያን እግር ኳስ ባለስልጣኖች ጠይቆ ተረድቷል። እንዲህ አሉት፤ “በወርኃ የካቲት 1950 ዓ.ም ጨዋታው ሊጀመር ሦስት ቀናት ሲቀረው፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት የደቡብ አፍሪካ ቡድን አስመልክቶ የውሳኔ ሃሳብ/ሞሽን/ አቀረቡ።
“የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መንግሥት በጥቁር አፍሪካውያን ላይ የሚያራምደውን የዘር መድሎ አገዛዝ ካላቆመ በስተቀር፣ የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ አይገባውም” የሚል አቋም ያዙ። እርግጡን ለመናገር፣ ወደ ካርቱም መጥቶ የነበረው የደቡብ አፍሪካ ቡድን አንድም የአፍሪካነር/ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ/ አላሣተፈም ነበር። በመስራች አገሮቹ የጋራ ስብሰባ ላይ፣ ሐሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ከዋንጫው በእግድ ተሠናበተች።” ሲሉ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ነገሩት። ውሳኔውም ትክክለኛ ነው ሲል ድጋፉን ሰጠ።
\
በጥር 10 ቀን 1954 ዓ.ም በዋለው የከተራ በዓልም ላይ ተገኝቶ “ግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ” በጃን ሜዳ ተገኝተው በዓሉን ከሕዝቡ ጋር ሲያከብሩት ባይኑ አይቷል። የአልጋ ወራሹንና የአቡኑንም ንግግሮች በቱርጁማን አዳምጣቸዋል። ሁሉም ነገር ገርሞታል። በሕዝቡና በከሕናቱ፣ በሕዝቡና በመኳንንቱና በመሳፍንቱ መካከል ያለው ልዩነት የፕሮቶኮል ብቻ እንደሆነ ተሰማው። በጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም (በዕለተ እሑድ ሃምሳ ሺህ ሕዝብ በተሰበሰበበት የቀ.ኃ.ሥ ስታዲየም ተገኝቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን 4 ለ 2 ሲያሸንፍ አይቶ፣ ልቡ በድሉ ሰበብ ደስፈቅ ብሏል። ንጉሠ ነገሥቱም ለብሔራዊ ቡድኑ አባላት ዋንጫ ሲሰጡ የነበረውን ሥነ ስርዓት ተመልክቷል።
ንጉሠ ነገሥቱ ከሕዝቡ ጋር ናቸው፤ ገረመው። ደነቀው። በሕዝቡና በንጉሠ ነገሥቱ እንዲሁም በሹማምንቱ መካከል ያለው ልዩነት የኃላፊነትና የተዋረድ እንደሆነ ገመተ። እራሱንም፣ የዚህ ሕዝብ አካል አድርጎ ለመቁጠር ከጀለ። ማን ያውቃል? ዜግነቱን የሚገልጽ የመታወቂያ ወረቀት (I.D Card/Passport) ያገኝ ይሆናል። ያኔ ታዲያ፣ ዜግነቱ ተረጋገጠለት ማለት አይደለ? ሆኖም፣ በዘር መድሎና በጭቆና ሥር ያለውን የራሱን ሕዝብ ለራሱ ምቾትና ድሎት ሲል ሊሰደድ ፈለገ። “በአፓርታይድ እስር ቤት ከመታጎር መሰደድ ይሻላል፤” ሲል አወጣ አወረደ። በታኅሣሥ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጥሪ አድርጎለት ወደ አዲስ አበባ ከመመጣቱ ሁለት ወራት በፊት፣ የፓርታይድ መንግሥት የእስር ማዘዣ አውጥቶበት ነበር። ለጥቂት ነው፣ አምልጦ የወጣው። “ከስደት መታሰር!” ወይስ “ከመታሰር መሰደድ!” ይሻል ይሆን? እያለ ማመንታቱ አልቀረም።
ከብዙ ማመንታትና ማውጠንጠን በኋላ፣ “እንዴት አድርጎ ሕዝቡን ነፃ ሊያወጣ እንደሚችል ጭላንጭል ስለታየው፣ ቀሪ መርኀ ግብሩን መተግበሩን ቀጠለ። በጣም የተጣበበው የሰውዬው መርሐ ግብር እንደቀጠለ ሲሆን፣ ወቅታዊ ዘገባዎችንና ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባወችን መከታተሉን አላስታጎለም። በጥር 20/1954 ዓ.ም፣ ወዳጁ-የታንዛኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚ/ር ጁሊዬስ ኔሬሬ ሥራውን/ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅም አዲስ አበባ ሆኖ ዜናውን ተከታትሎታል። (በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን የለቀቀ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጠቅላይ ሚ/ር ጁሊዬስ ኔሬሬ ነው።) በጥር 25/1954 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ላይ በአፍሪካ አዳራሽ በንጉሠ ነገሥቱ የመክፈቻ ንግግር በይፋ በተከፈተው፣ “የማዕከላዊና የምሥራቅ አፍሪካ የነጻነት ንቅናቄ ድርጅት ጉባኤም” ላይ፣ የፓርቲው የANC (African National Congress)ን በመወከል፣ የልዑካን ቡድኑ አባል ሆኖ በጉባኤው ላይ ተካፍሏል።
ስፍራዎች አፍሪካውያኖች እንዲሰደዱ ተገደዱ።” እያለ ይቀጥላል (መጋቢት 10 ቀን 1954፤ ገጽ 3 እና 4)። ሰውዬው የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናቱን ቀልብ ከመሳቡም በላይ፣ ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሄዶ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰደውን አቋም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም እንዲደግመው ጠየቀ። ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ የነጮች ልዑክ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፍ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የጃፓኑን ኦሎምፒክ አልሳተፍም እንድትል ጠየቀ። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዋና ፕሬዚዳንት አቶ ይድነቃቸውም “ጉዳዬ ፓለቲካዊ ስለሆነ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ገና ተነጋግሬበት ነው፤” ስላሉት ተበሳጭቶ ንጉሡን እንደዘለፈ ፓልራምፓን Bare Foot Runner ባለው የአበበ ቢቂላ ዘካሪ መጽሐፍ ላይ አስፍሮታል። (ገጽ 165-6)። የሰውዬው ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ባለሥልጣነት ዘንድ ተገቢውን ክብር አግኝቶ ኖሮ፣ ከስድስት ዓመታት በኋላ በሜሰኮው ኦሎምፒክ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካን ተሳትፎ በማውገዟና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችንም በማስተባበሯ፣ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ የኦሎምፒክ ቡድን እንዳይሳተፍ ማዕቀብ ተጣለበት።
ለሦስት ወራት ያህል ያለማሰለስ ስለ ANC /African National Congress) እና ስለ ደቡብ አፍሪካ የነጮች ዘረኛ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ሲሰራ ከቆየ በኋላ፣ በሚያዝያ 5/1954 ዓ.ም የፈጥኖ ደራሽ ዋና አዛዡ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ መረቁት። አንድ ቡልጋሪያ ሠራሽ የሆነ ሽጉጥ ከ 200 ጥይቶች ጋር ሰጡት፤ ከዚያም ወደሀገሩ ለመመለስ ተዘጋጀ። እንደሄደ እንደሚታሰር የጠረጠሩት የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም ለሰውዬው የኢትዮጵያዊ ፓስፖርት ሰጡት። ስሙም “ዱዋል ሰዋዬ” የሚል ሆነ። ትውልዱ በችዋን ላንድ ሲሆን፣ የትውልድ ዘመኑም 1910 ዓ.ም (እ.አ.አ 18/7/1918) ነው። ሥራውም ጋዜጠኛ የሚል ሆነ። የሚስቱ ፎቶ አልተለጠፈበትም። Long Walk to Freedom ባለው መጽሐፍ በ 47ኛ ምዕራፍ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ፣ ያረፈውም ራስ ሆቴል ነበር። ረፍት የለሽና ተናግሮ የመደመጥ ፀጋ ያለው ይህ ሰውዬ፣ በሚያዝያ አጋማሽ ላይ ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ ሰሞን ሊሌስሊፍ በተባለ ቦታ ሽጉጡንና 200ዎቹን ጥይቶች ራቅ አድርጎ ቀበራቸው። እነዚህ የኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ተቋም ሥጦታዎች እስከዛሬም ድረስ ደብዛቸው አልተገኘም። (በቅርቡ “Mandela’s Gun” በሚል ርእስ አንድ ጆን ኢርቪን የተባለ እንግሊዛዊ የፊልም ዳይሬክት ለፊልሙ ጥናት አዲስ አበባ መጥቶ ነበር።)
➳ ማጠቃለያ
ከ 28 ዓመት ከ2 ወራት ገደማ በኋላ፣ በሐምሌ 3/1982 ዓ.ም፣ የ 27 ዓመታት እስሩን ጨርሶ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመገኘት ወደአዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ የተለየች ሆነችበት፤ ለወራት አይደለም ለቀናትም እንደማይቆይባት ሳይታወቀው አልቀረም። ቦሌ አለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሄደው፣ ፕ/ቱ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ጓድ ብርሃኑ ባይህ ነበሩ። በ 26ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤም ላይ ተገኝቶ ንግግር አደረገ። “አፓርታይድ ከምድረ-ደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ ከመላው ዓለም እስኪወገድ ድረስ፣ ማዕቀቡ ተጠናክሮ እዲቀጥል አሳሰበ፤” (አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 3/1982፣ ገጽ-7)። ሰውዬው፣ በ 1982 ዓ.ም በመጣ ጊዜ አዲስ አበባ የቆየው ለ 24 ሰዓታት ብቻ ነበር። ለምን ከዚያ በላይ ለቆየት እንዳልፈቀደ መጠርጠር ካልሆነ በስተቀር፣ ትክክለኛውን ምክንያት ማወቅ ያስቸግራል። በ 43 ዓመቱ ለ 98 ቀናት ያህል የተንፈላሰሰባት አዲስ አበባ፣ ከ 28 ዓመታት በኋላ በ 24ኛው ሰዓት ጥሏት ነጎደ። ከዚያን በኋላም አልመጣም። በሐምሌ 19/1995 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሊሠጠው ቢጋብዘው ዝር ሳይል ቀረ። እግረ መንገዱንም እነ ፕ/ር አንድሪያስ ያሰሩትን መስታወታማ ሕንፃ ይመርቃል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
በወቅቱ አንዳንድ የግል ፕሬስ ውጤቶች፣ “ማንዴላ አልመጣም ያለው፣ ከዘረኞች እጅ ምንም አይነት ሽልማትም ሆነ ዲግሪ አልቀበልም በሎ ነው” ማለታቸውን አስታውሳለሁ (ጦቢያ፣ ልሳነ ሕዝብና አስኳል የሚጠቀሱ ናቸው።) ያም ሆነ ይህ፣ ማንዴላና ኢትዮጵያ ልብ ለልብ እንደተነፋፈቁ ይቀጥላሉ። ዛሬ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ማንዴላ የርቀት ት/ት ኮሌጅ ተከፍቷል። ከላይ እንዳወሳሁት፣ የማንዴላ ሕንፃ በአዲስ አበባ ዩቢቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ ተሰይሟል። አርባ ምንጭ ከተማም ውስጥ “ማንዴላ” የሚባል ት/ት ቤት ተክቷል።