ከታሪክ ማህደር: መምህር ፣አርበኛ፣ ዲፕሎማት እና ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ

/
ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ
ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ

ህዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም

መምህር ፣አርበኛ፣ ዲፕሎማት እና ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ በተወለዱ በዘጠና አራት ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈበት ዕለት ነበር።

ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ከእናታቸዉ ከወ/ሮ ደስታ ዓለሙ እና ከአባታቸዉ ከዓለማየሁ ሰለሞን ጥቅምት 7 ቀንድ 1902 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር እንዶዳም ኪዳነ ምህረት ተወለዱ፡፡እንዶዳም ከደብረ ማርቆስ ከተማ ቅርብ ርቀት፣ ጎዛምን ወረዳ ዉስጥ ትገኛለች፡፡ በሁለቱም ወገን ከካህን ቤተሰብ የሆኑት ሀዲስ፣ እናታቸዉ ወ/ሮ ደስታ ዓለሙ የተወለዱት እንዶዳም ሲሆን አባታቸዉ ዓለማየሁ ሰለሞን ግን ዮፍታሄ ንጉሴና መላኩ በጎሰዉን የመሳሰሉ የብዕር ሰዎችን ያፈራችዉ የደብረ ኤልያስ ሰዉ ነበሩ፡፡

ክቡር ዶ/ር ሀዲስ በህይወት ዘመናቸዉ ብዙ ፍሬያማ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ ሀዲስ የሃገራችንን ትምህርት ከ”ሀሁ” አንስቶ እስከ ጾመ ድጓ ድረስ የዜማ መምህር ከነበሩት እናታቸዉ አባት ዓለሙ ስዩም ዘንድ ረዘም ላለ ጊዜ ተምረዋል፡፡ ከዜማ በኋላ መጀመሪያ ደብረ ኤልያስ ፣ ቀጥሎም ደብረ ወርቅ፣ በመጨረሻም ዲማ ጊዮርጊስ ቅኔ ተምረዉ አጠር ባለ ጊዜ ዉስጥ ተቀኝተዋል፡፡ ሀዲስ ዓለማየሁ የቅኔ መምህራቸዉን ተከትለዉ ወደ አዲስ አበባ ከጓደኞቻቸዉ ጋር ሲጓዙ፣ መምህራቸዉ ሰላሌ ላይ ትተዋቸዉ በሹመት ወደ ደብረ ብርሃን ሄዱ፡፡ ሆኖም ሀዲስና ሌሎች ጓደኞቻቸዉ ጉዟቸዉን ቀጥለዉ አዲስ አበባ ደርሰዉ ለ 7 ዓመታት ያህል ቆይተዋል፡፡

ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ
ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ

አዲስ አበባ በስዊድን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት በኋላም በራስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ለትንሽ ጊዜ በአስተማሪነት ሥራ ተሰማርተው እንዳገለገሉ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተከሰተ።

የኢጣልያ ወረራ ሲከሰት ከልዑል ራስ ዕምሩ ኃይለ ሥላሴ ጦር ጋር በምዕራብ ኢትዮጵያ በአርበኝነት ሲዋጉ ቆይተው በመያዛቸው ጣሊያን ከልዑል ራስ ዕምሩ ጋር በግዞት ለሰባት ዓመታት በፖንዞ ደሴትና በሊፓሪ ደሴት ታስረው ቆይተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እርዝመቱ 2 ሜትር ከ 20 ሳ.ሜ ፣ የክቡር ዘበኛ የማርሽ ባንድ መሪ ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ተወላጁ ሻቃ በልሁ (አባ ቆሮ)፤

ከዚያ የተባባሪ ኃያላት ወታደሮች በ 1935 ዓ.ም ሲያስመልጧቸው በተመለሱበት ጊዜ በትምህርታቸው እንደገና በኦክስፎርድ ከገፉ በኋላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተለይም በትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል።

1936 – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ

1937-1938 – የኢትዮጵያ ቆንሱል በኢየሩሳሌም

1938 – በ International Telecommunications Conference አትላንቲክ ከተማ፣ ኒው ጄርዚ ወኪል

1938-1942 – በተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኒው ዮርክ ሠራተኛ

1942-1948 – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይረክተርና ምክትል

1948-1952 – የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሰደር

1952 – የትምህርት ሚኒስትር

1952-1957 – የኢትዮጵያ አምባሰደር ወደ እንግሊዝና ሆላንድ

1957-1958 – የልማት ሚኒስትር

1960-1966 – ሴናቶር

ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ
ታላቅ ደራሲ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ

ሀዲስ ዓለማየሁ በርካታ የስነጽሑፍ ሥራዋችን አበርክተዋል። ከነዚህም ውስጥ ታላቅ አድናቆትንና እውቅናን ያተረፈው ሥራቸው ፍቅር እስከ መቃብር (1958) በሁለት የተለያዩ መደቦች ውስጥ የሚገኙ የሁለት ሰዎች የፍቅር ታሪክ ላይ ሲያተኩር፤ በጊዜው የነበረውን ወግና ልማድ ይገልጻል። እንዲሁም በ 1970 ወንጀለኛው ዳኛ በ 1980 ደግሞ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮችና ስለ ጣሊያን ውርስ የሚዳስሰውን የልም እዣት የተሰኙትን ልብ ወለድ ታሪኮች ለንባብ አቅርባዋል።

በተጨማሪም:–

የአበሻና የወደኋላ ጋብቻ – ተውኔት ፣ ተረት ተረት የመሰረት ፣ ትዝታ

የተሰኙት ጽሁፎችና የሌሎች በርካታ ሥራዎች ባለቤት ናቸው።

በ 1974 አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ፍቅር እስከ መቃብርን በኢትዮጵያ ራድዮ ግሩም አርጎ ከተረከዉ ወዲህ መጽሐፉ በኢትዮጵያዉያን ልብ ዉስጥ ተቀመጠ ወጋየሁንም ከጫፍ እስቀጫፍ አስተዋወቀ ለዚህ ብዕረኛዉ ሀዲስ አለማየሁ መጽሐፉን እኔ ጻፍኩት እንጂ መጽሐፉ ያንተ ነዉ ብለዉ መጽሐፋቸዉ ላይ ጽፈዉና ፈርመዉ እንደሰጡት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ተናግሮአል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከታሪክ ማህደር: አፄ ዮሐንስ ማን ናቸው ? Abebaw Ayalew With Meaza Birru - ሸገር ካፌ

ደራሲ፣ ዲፕሎማት፣ አርበኛ፣ መምህር የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ከነኀስ የተሠራ ኃውልት የቆመላቸው ጥቅምት 5 ተቀን 1902 ዓ.ም ተወልደው ኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም ላረፉት ለሀዲስ ዓለማየሁ ደብረ ማርቆስ ከተማ ላይ ነው።

ለክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ያዘጋጀው የፖስታ ቴምብር በኢትዮጵያ የፖስታ ድርጅት በ 2002 ዓ.ም ታትሞ ተሠራጭቷል፡፡

ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክቶርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ደራሲው በኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም በ 94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

#ታሪክን_ወደኋላ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share