…እኛ ግን እንኳን ለእልፍና ለሁለት እልፍ ሰው፤ የኢጣሊያ አገር ሰው ሁሉ ቢመጣ የኢጣሊያን ጥገኝነት ይቀበላሉ ብለህ አትጠርጥር።…(ዳግማዊ ምኒልክ ነሀሴ 23 ቀን 1887 ዓ/ም ኤሮፓ ለነበረው ለሙሴ ኢልግ የፃፉት የግል ደብዳቤ)
***
…እኔ ሴት ነኝ። ጦርነት አልወድም። ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ… (እቴጌ ጣይቱ፤ ዲሴምበር 23 1890 በሚለው የሳላምቢኒ ማስታወሻ ከሰፈረው)
***
የውጫሌ ውል ከምፅዋ ባህር ገብቷል … ቀደም ባለው ጊዜ የያዝነው የወሰን ጉዳይ በገዛ የጦር መሳሪያችን የነገሠው ምኒልክ በውሉ አልስማማ ብሎ የውጫሌን ውል አፍርሷል።… (የኢጣሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒሰትር ባሮን ብላንክ ለኢጣሊያ ፓርላማ ካደረጉት ንግግር)
***
የጦርነት አዋጅ
አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሄር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰዉን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።
አሁን ግን በእግዚአብሄር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው፤ ከሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፤ ለምሽትህ፤ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ሁዋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።
(አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያ ህዝብ ወራሪዋን ጣሊያን እንዲዋጋ ያቀረቡለት የክተት አዋጅ፤ 1888 ዓ/ም)
አድዋ፤
የተተከለው ድንኩዋን ሲታይ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ ኤሮፓን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል። የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፤ ጠመንጃና ጦር ይዘው፤ ጎራዴ ታጥቀው፤ የነብርና ያንበሳ ቆዳ ለብሰው፤ አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ፤ ቄሶች፤ ልጆች፤ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የኢጣሊያን ጦር አሸበሩር።
ሀያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ። በኔ እምነት መሰረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋ ያለ ጦርነት የለም። በእልቂቱ በኩል 25 ሺህ ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው። ፖለቲካና ታሪክ አበቃ። በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጆች ሃይል መነሳቱ ታወቀ። የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ። ጥቁሩ ዓለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተፀፎላቸዋል። የኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሰያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትና ሀይማኖት የተቀበሉ ናቸው። አሁን የሁሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው።…{2}
***
የኢትዮጵያ ሠራዊት አድዋ ላይ የተቀዳጀው ወታደራዊ ድል፤ በሠላሙ ውል መፈረም ተደምድሟል። ይሀ የሠላም ውል ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የነበራትን ዕቅደ ለመጨረሻው ውድቅ አድርጎታል። ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ዕውቅና አገኘች። በወቅቱ በነበረው የአውሮፓ ፕረስም በኩል በአፍሪካ አንድ አዲስ ሃይል ተወለደ የሚል አመለካከት አስተጋብቷል። ነገር ግን ይበልጥ ትክክል የሚሆነው የአድዋ ድል ከሁሉም ነገር በላይ ኢትዮጵያን ወደ ዓለማቀፋዊ መድረክ ከፍ አድርጓታል፤ አፍሪካ በቅኝ አገዛዝ ቅርምት ስር በወደቀችበት ወቅት ራሷን የቻለች ነፃ መንግሥት ሁና እንድትቀጥል አስችሏታል… {1}
[ ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ በደማቸው ዋጅተው ሀገር፣ ነፃነት፣ ክብርና ታሪክ ለሰጡን የአድዋ አብናቶቻችን ይሁን፤ ዛሬም ዘወትርም እስከ ወዲያኛው – ዓሜን! ]