በፀጋው መላኩ
የሳዑዲው ንጉስ አብደላ ቢን አብድልአዚዝ ባለፉት ሳምንታት በመላ ሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ሲካሄድ የነበረው ህገወጥ ነዋሪዎችን የማሰስና የማደን ሥራ እንዲቆም አዘዙ። ትዕዛዙ ያለፈቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያለፈቃድ ነዋሪዎችን ጭምር የሚመለከት ሲሆን ንጉሱ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያቤቶች ባስተላለፉት ትዕዛዝ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ነዋሪዎች የእፎይታ ጊዜ ተጠቅመው ከመኖሪያና ከስራ ፈቃድ ጋር የተያያዘ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ አስታውቀዋል። የንጉሱ መግለጫ የምህረት ጊዜውን ተጠቅመው ተገቢውን ማስተካከያ የማያደርጉ ፈቃድ አልባ ነዋሪዎች ህጋዊ እርምጃ የሚወስድባቸው መሆኑን ዜናውን ያሰራጨው አረብ ኒውስ አስታውቋል።
ለተወሰኑ ቀናት በተከታታይ በሀገር ውስጥ ጉዳይና በሰራተኞች ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች የጋራ ትብብር አማካኝነት በህገወጥ ነዋሪዎች ላይ አሰሳ ሲደረግ የቆየ ሲሆን በርካታ ቀጣሪዎችም ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስባቸው የቆየ መሆኑ ተመለክቷል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ባደረገው ማጣራት በርካታ ህገወጥ ነዋሪዎች ፎርጅድ መኖሪያ ይዘው ተገኝተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ 34 የወንጀል አይነቶችንም የተለዩ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስታውቋል። ከህገወጥ ነዋሪዎች የተለያዩ የህጋዊ ሽፋን መረጃዎች ጋር በተያያዘ 1ሺ እስከ 5ሺ ሪያል ቅጣት የሚጥል መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጨምሮ ገልጿል። ከፎርጅድ መኖሪያ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ለህገወጥ ነዋሪዎች እገዛ የሚያደርጉ የራሷ የሳዑዲ ዜጐች ስማቸው በመገናኛ ብዙኃን እንዲገለፅ የሚደረግ ሲሆን እስከ 30ሺ የሚደርስ ሪያል ቅጣት እንዲከፍሉ ይደረጋል ተብሏል።n (ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ)