September 19, 2022
ጠገናው ጎሹ
በመሠረቱ እንኳንስ በዘመን መለጫ አይነት ትልልቅ በዓላት በየትኞቹም በጎ እሴት ባላቸው በዓላት እና በሌሎችም አጋጣሚዎች የእንኳን አደረሰንና የመልካም ምኞት መልእክቶችን የመለዋወጥ አስፈላጊነት አጠያያቄ አይደለም። በዓላት ስለሚያከብራቸው ማህበረሰብ የሚናገሩት ወይም የሚገልፁት የእየራሳቸው ሃይማኖታዊ ወይም ዓለማዊ ወይም የሁለቱም የሆነ ትርጉምና እሴት አላቸውና ከአዘቦት (ከዘወትር) ቀናት በተለየ ተከብረው ወይም ታስበው መዋላቸው ተገቢ ነው።
ዘመን መለወጫም ተፈጥሯዊ ህግን ተከትሎ በራሱ የጊዜ ምህዋር ላይ በሚፈራረቅ ሂደት ውስጥ በአጠቃላይ የሰው ልጅን ወይም የተወሰነ ማህበረሰብ ሁለንተናዊ መስተጋብርና የእድገት ግስጋሴ አወንታዊ ወይም አሉታዊ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ከሚነግሩን ዓመታዊ በዓላት አንዱ ነው። ሁሉም ነገር የሚከናወነው በጊዜ ሂደት ውስጥ ነውና ።
እድሜ ቁጥር ብቻ መቁጠር ሲሆን ብዙም ትርጉም እንደሌለው ሁሉ የዘመን መለወጫም በቁጥር ብቻ ተቀምሮ የሚቆጠርና የሚከብር ከሆነ ትርጉም አይኖረውም። ቆጠርነውም አልቆጠርነው የተፈጥሮ ህግ ምህዋሩን ጠብቆ ይጎዛልና ። የዘንድሮው የዘመን መለወጫ ከብዙ ዓመታት በፊትና በተለይም አምስተኛ ዓመቱን በያዘው የእነ አብይ አህመድ አገዛዝ ሥር ሆነን ከሳለፍናቸው የመከራና የውርደት የዘመን መለወጫ ዓመታት ሲሆን የተሻለ ካልሆነም ይበልጥ ያልባሰ እንዳይሆን ለማድረግ ሳንችል የመቅረታችን ውድቀት በእጅጉ ያማል። በዚህ እጅግ መሪር ሁኔታ ውስጥ እጓየጎጥንም ( በመኖርና ባለመኖር አረንቋ ውስጥ እየዳከርንም) እጅግ አብዛኛዎቹ የዘመን መለወጫ መልእክቶቻችን ከተለመደው የእንኳን አደረሰንና ድርጊት አልባ ምኞት መግለጫነት አላለፉም ። ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን ይህ ውድቀት የሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የፖለቲካ ቁማርተኞችና ግብረ በላዎቻቸው ሥርዓተ ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፍፃሜ የሚያገኝበትን የነፃነትና የፍትህ መንገድ በመሳታችን ምክንያት የተፈጠረ ነው። ለዚህም ነው የዘንድሮው የዘመን መለወጫ የእንኳን አደረሰንና የመልካም ምኞት መልእክቶቻችን ብዙም ስሜትን የማይስቡ የሆኑብን።
አዎ! አብዛኛዎቹ መልክቶቻችን ከብዙ ዓመታት ውድቀት ተምሮ ፣ የዛሬን መሪር ሃቅ በግልፅና በቀጥታ ተጋፍጦ መጭውን ጊዜ በባዶ ተስፋና ምኞት ሳይሆን በተግባራዊ አቋምና ቁመና እውነተኛ የለውጥ ዘመን አድርጎ ለመቀበል የሚያስችል የጋራ ተጋድሎ አስፈላጊነትን በግልፅ የሚያመለክት ይዘት የላቸውም። ከዚህ ይልቅ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች (የኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን) የፖለቲካ ሥርዓት ባስከተለው መከራና ውርደት ምክንያት የቀን ተቀን ህይወቱ የተመሰቃቀለበት አገሬ ሰው የዘወትር ጥያቄና ምኞት የሆኑትን ሰላምን፣ እርቅን ፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን ፣ እምነትን፣ በጎ ራዕይን ፣ ተስፋን ፣ መከባበርን፣ አንድነትን፣ ደግነትን፣ ወዘተ መላልሰው የሚሰብኩ ሆነው ነው ያገኘኋቸው ። ፈተናው ያለው ቃልና ተግባርን በማዋሃድ እውነተኛ ፍስሃ የሚገለፅበትን ሥርዓትና ዘመን እውን ከማድረጉ ላይ እንጅ ከባዶ ስብከትና ዲስኩር እንዳልሆነና እንደማይሆን አልቃሽና ዘፋኝ ሆነን የዘለቅንባቸው ሦስት ዓሥርተ ዓመታት ትምህርት በተገባ ነበር። አለመሆኑ ያሳዝናል።
መቼም የጊዜ መፈራረቅ ከተፈጥሮ ህግጋት አንዱ ነውና ከክርስቶስ ልደት ጀምሮ ዓመተ ምህራት በሚል የምንጠራውን የዘመን አቆጣጠር ሁለት ሽ አሥራ አራተኛውን አልፈን ወደ ሁለት ሽ አሥራ አምስተኛው (እ.ኢ የዘመን አቆጣጠር ቀመር) ከገባን አንድ ሳምንት ሆነን።
ይህንኑ ዘመን መለወጫ አስመልክቶ (ከ2014 ወደ 2015) ከገዥዎች ፣ ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሌሎች ወገኖችም የተላለፉትን መልእክቶች በጥሞና አንብቢያለሁ ፣ አድምጫለሁም ።
የመከራና የውርደት አገዛዛቸውን እንደ ምድራዊ የሰላምና የእድገት ጎዳና እና የፅድቅ መንገድ አድርገው ለዘመናት ሲያደነቁሩን ስለ ኖሩትና አሁንም እያደነቆሩን ለመቀጠል ስለ ወሰኑት እኩያን ገዥ ቡድኖች ከቃላት ይልቅ ተግባራቸው ስለሚናገር ብዙ ማለት አያስፈልገኝምና ለማሳያነት ያህል ብቻ የሚከተለውን ልበል።
ከጳጉሜን መግቢያ ጀምሮ በለየለት ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ቁማር ዘመቻ ሲታጀብ የነበረውና “ ከድል ዓመት ወደ በለጠ የድል ዓመት በመሸጋገራችን እንኳን አደረሳችሁ እያልን የላቀ ድል ለማስመዝገብ እየመጣችሁ ተንድትደመሩ ጥሪያችን ይድረሳችሁ ” በሚል አይነት እጅግ ርካሽና ጨካኝ የፖለቲካ ስላቅ የተሞላውን የገዥው ቡድን የዘመን መለወጫ መልእክት የተከታተልኩት እጅግ ፈታኝ በሆነ ስሜት ነበር። የህወሃቱን ኢህአዴግ በኦህዴዱ ኢህአዴግ (ብልፅግና) ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ የተኩት ገዥ ቡድኖች ለአራት ዓመታት የፈፀሙትንና እየፈፀሙት ያሉትን ዘግናኝ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከምር ለሚከታተል ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ከላይ የጠቀስኩት አይነት የቤተ መንግሥት ፖለቲከኞች ስላቃዊ የ”እንኳን አደረሰን” መልእክት ስሜቱን (ህሊናውን) ቢያቆስለው ከቶ የሚገርም አይደለም።
ለዘመናት ባሰለጠኑት ሸፍጠኛ አንደበታቸው መከረኛውን ህዝብ በማታለልና የግልብ ስሜት ፖለቲካ ሰለባ በማድረግ የቤተ መንግሥቱን ሥልጣነ መንበር በተረኝነት ከተቆጣጠሩ ብዙም ሳይቆዩ የግፍ ግድያ ሰለባ ለሆኑ ብዙ ሽዎች እና የቁም ሰቆቃ ሰላባ ላደረጓቸው ብዙ ሚሊዮኖች እንኳንስ ብሔራዊ ሃዘን ሊያውጁ አገር እመራለሁ እንደሚል ፖለቲከኛ እናዝናለን ለማለት የሞራል አቅም የሌላቸው ገዥ ቡድኖች “እንኳን ከድል ጋር አደረሰን” ሲሉን ጨርሶ ህሊናቸውን አልጎረበጣቸውም። ለነገሩ ህሊናውን የሚጎረብጠው ሰው የሚያሰኝ ህሊና ያለው ሰውና የሚገርም አይደለም።
“የምናስረውና ከእሥር የምንፈታው የማንንም ትእዛዝ ሳይሆን የፈጣሪን ትእዛዝ እየተቀበልን ነው” በሚል ፈጣሪን ሳይቀር የግፍና የሸፍጥ ፖለቲካቸው ተባባሪ የሚያደርጉ የቤተ መንግሥት ፖለቲከኞች በየትኛው የሞራል ልዕልና የድል ዘመን አብሳሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንኳን ለመቀበል ለመገመትም ያስቸግራል።
በዘመን መለወጫ ስም በተዘጋጀው የቤተ መንግሥት “የእራት ግብዣ” ላይ ተገኝተው ለርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መልእክት ማስተላለፊያነት በተዘጋጀው ካሜራ ፊት እየተቀባበሉ ውዳሴ አብይ (ውዳሴ ብልፅግና) ያቀረቡትን አረጋዊያን ከምር ለታዘበ እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ህሊናውን በእጅጉ ሳያሳቅቀው (ሳያቆስለው) የሚቀር አይመስለኝም። አዎ! “የእኔ አረጋዊ አባት ወይም እናት የእንደዚህ አይነት እጅግ እኩይና ርካሽ የሆነ የፖለቲካ ኦርኬስትሬሽን ሰለባ ቢሆንስ/ብትሆንስ”? ብሎ ከምር ለሚያስብ የአገሬ ሰው የገዥዎቻችንና የግብረ በላዎቻቸውን ልክ የለሽ የፖለቲካ ሸፍጥና ጭካኔ ለመረዳት አይቸገርም።
እያልኩ ያለሁት ጉዳይ አረጋዊያኑ ለምን ተጋበዙ ከሚል ደምሳሳ ወይም ጭፍን አስተሳሰብ የሚነሳ አይደለም። እያልኩ ያለሁት ሂሳዊ አስተያየት ሀ) አረጋዊያንን ለዘመናትና በተለይ ደግሞ በአራት ዓመቱ ኦህዴድ መራሽ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት ርካሽ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ከማድረግ አንፃር ሲታይ ለ) ይህ አይነት በእጅጉ ተራ የሆነና ጭካኔ የተሞላበት የፖለቲካ ተዋናይነት አራት ዓመት ሙሉ የታዘብነው የአብይ አህመድ የፖለቲካ ሰብዕና ከመሆኑ አንፃር ሲገመገም ሐ) የግፍ ግድያው የቀጠለ ከመሆኑ፣ አስከፊው የቁም ሰቆቃው የቀን ተቀን ዜና ከመሆኑ ፣ አሰቃቂው የእሥርና የአፈና ዘመቻ ከመቀጠሉ መሪር እውነት አንፃር ሲታይ መ) ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው አራት ዓመታት ሙሉ ለተፈፀመውና አሁንም ለቀጠለው እጅግ አሰቃቂ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ቢያንስ ይህንን የዘመን መለወጫ ምክንያት በማድረግ ለሆነው ሁሉ በጣም አዝናለሁ ለማለት ፈፅሞ ካለመፈለጉ አኳያ ስናጤነው ሠ) በሌለው ችሎታና ክህሎት ለዘመናት የህዝብን ደም በመምጠት የኖረው የኢህአዴግ/የብልፅግና ታማኝ የካድሬ ሠራዊት ዴሞክራሲ እውን ከሆነ ጉሮሮዬ ይዘጋል በሚል የጭካኔ ዘመቻውን አጠናክሮ የቀጠለበት ከመሆኑ መሪር እውነታ አንፃር ስናየው ረ) ይህንን እጅግ እኩይ የፖለቲካ ኦርኬስትሬሽን ከምር በታሰበበት፣ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ሊገዳደር የሚችል የፖለቲካ ሃይል ወይም ድርጅት ካለመኖሩ አንፃር ስንመለከተው በእጅጉ አሳሳቢና አስፈሪ ነው ከሚል መሪር ሃቅ የሚነሳ ነው።
የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ቁማርተኞች ለዘመናት የመጣንበትንና አሁንም በአዛኝ ሁኔታ ተዘፍቀን የምንገኝበትን መሪር እውነታ ወደ ታች ዘቅዝቀው እያስነበቡ ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ከነውርነትም አልፎ ወንጀል ነውና በቃችሁ እስካልተባሉ ድረስ ከዚህም የከፉ የሸፍጥና የስላቅ “እንኳን አደረሳችሁ” ዓመታትን ሊያስቆጥሩን እንደሚችሉ የሚያጠራጥር አይደለም ።
የዘመን መለወጫ መልእክቶችን ያነበብኳቸውና ያደመጥኳቸው እጅግ በተደባለቀ ስሜት ነው። ከአራት ዓመታት በፊት ሩብ ምእተ ዓመት የዘለቀውን አስከፊ ህወሃት መራሽ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት በበሰለ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና በተደራጀና በተቀናጀ የነፃነትና የፍትህ ትግል ማስወገድ የምንችልበትን ወርቃማ እድል እጅግ ግልብና አሳፋሪ በሆነ ከክስተቶች ጋር በስሜት የመጋለብ ክፉ ልማድ ምክንያት እንዲጨነግፍ የማድረጋችን መሪር ተሞክሮ ጨርሶ ትምህርት የሆነን አይመስልም ።
የመከራውና የውርደቱ ዋነኛ መንስኤ በሆነው መሪር ሃቅ ዙሪያ እየተሽከረከርን ያስተላለፍናቸውን የዚህ ዓመት የዘመን መለወጫ መልእክቶች ልፍስፍስነት ከምር ለታዘበ ባለ ሚዛናዊ ህሊና የአገሬ ሰው በውድቀት ውስጥ ካሳለፍናቸው አያሌ የዘመን መለወጫ ዓመታት ገና በቅጡ አለመማራችንን ለመረዳት አይቸገርም።
በአንድ በኩል ትልቅ ትርጉም ያላቸው እንደ የዘመን መለወጫ አይነት በዓላት የሚፈጥሩት መልካም ስሜት እና በሌላ በኩል ግን እንደዚህ አይነት በዓላትን ለጥቂት ዓመታት ሳይሆን ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ ባስቆጠረና በእጅጉ አስከፊ እየሆነ በመሄድ ላይ በሚገኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች ሥርዓት ሥር ሆኖ እንኳን አደረሰን ከሚል የተለመደ መልእክት ባላለፈ ሁኔታ ማሳለፋችን በእጅጉ የተደባለቀ ስሜትን ቢፈጥር የሚገርም አይሆንም።
የዘመን መለወጫ መልእክቶቻችን ከባዱ ፈተና አጠቃላይ እውነትን (general truth) ለዘመናት ወደ መጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ወደ ምንገኝበት መሪር እውነታ አውርዶ ለማየትና እውነተኛ ሰላም፣ ፍትህ፣ ፍቅር ፣መተሳሰብ እና የጋራ እድገት የሚረጋገጥበትን ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል የሚመጡ ካለመሆናቸው ላይ ነው።
የእንዲህ አይነት የዘመን መለወጫ መልእቶች የይዘትና የጥልቀት ጉድለት የታየው በፖለቲካው አውድ ብቻ ሳይሆን በሃይመኖት ተቋማት ጭመር ነው ።
መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን በቁንፅሉ በመውሰድ ሃይማኖት በፖለቲካ ምን አገባውና ነው? የሚል ጥያቄ ሊያነሱ የሚችሉ ወገኖች እንዳሉ እረዳለሁ። ይህ መርህ ግን አንደኛው በአንደኛው የአሠራርና የሃላፊነት ጉዳይ ውስጥ ቀጥታ ጣልቃ መግባት የለበትም ለማለት እንጅ ሁለቱም ጨርሶ የሚያገናኛው የለም ወይም ከሁለቱ አንደኛው የአገርን ደህንነትና የህዝብን መሠረታዊ መብቶች ሲጨፈልቅ ወይም የሁከትና የግጭት ምክንያት ሆኖ ማህበረሰባዊ ቀውስ ሲፈጥር እዳር ቆሞና ዝም ጭጭ ብሎ ማየት አለበት ማለት ፈፅሞ አይደለም። በእኛ አገር ለዘመናት የሆነውና አሁንም ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ እየሆነ ያለው ግን መንግሥት የሚባለው አካል የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች የመጨፍለቅ ብቻ ሳይሆን በማንነታቸው ምክንያት እና በእርስ በርስ ጦርነት የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሰለባዎች እንዲሆኑ የማድረጉን መሪር እውነታ ነው። የእኛ የሃይማኖት ተቋማት ጥንካሬና ድክመትም የሚለካው በዚሁ የዓለማዊውንና የሰማያዊውን የጋራ ተልእኮና ሃላፊነት በሚጠይቅ ፈታኝ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ነው።
ባህላችን የሃይማኖት መሪዎችንና አስተማሪዎችን ለማሄስ (ለመተቸት) ጨርሶ ትእግሥት የሌለው መሆኑን እገነዘባለሁ። እውተኛው ፈጣሪ ግን እንዲህ አይኑቱን የማይጠቅም የአስተሳሰብ ባህል ተቀብሎ በትችት ሰንዛሪዎች ላይ ይፈርዳል የሚል እምነት የለኝም። ኋጢአት ወይም ስህተት የሚሆነው የትችት መነሻችን ሊስተካከል ይገባዋል የምንለውን የአስተሳሰብና የድርጊት ስሀተት በተገቢው መንገድ ሳይሆን በግል ህይወት አኗኗር፣ በግል ህይወት አስተሳሰብና በሚጠሩበት የመሪነት ማእረግ ላይ ሲያተኩር ነው ። ማህበረሰብን ወይም አገርን በተመለከተ በተፈጠረና ሊፈጠር በሚችል ጉዳይ ዙሪያ እስካተኮርን ድረስ እና ይህንኑ በአግባቡ ለማቅረብ እስከቻልን ድረስ ሌላው መመዘኛ ብዙም ሚዛን የሚደፋ አይሆንም። አስተያየቴም በዚሁ መሠረታዊ መርህ ላይ የተመሠረተ ነው ።
በሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች በጥንቃቄ ተፅፈው ያነበብኳቸው፣ ሲነበቡ ያደመጥኳቸውና በየሶሻል ሚዲያው የሰመኋቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቶች ፍሬ ሃሳብ ሲጠቃለል ከእኛ አልፎ ዓለም የሚያውቀውን የመከራና የውርደት ገመናችንን መልሶና መላልሶ ከመንገር እና የትኛውም ባለ ጤናማ አእምሮ የአገሬ ሰው ከማንም በላይ የሚያውቀውን የእርቅ ፣ የሰላም ፣ የፍቅርና የአንድነት አስፈላጊነት መላልሶ ከማሳሰብ አያልፉም።
የሰላም ፣የእርቅ ፣የይቅርታ፣ የዘላቂ መረጋጋትና የአንድነት እጦታችን ምክንያት ምንድነው? ምክንያቶቹስ እነማንስ ናቸው? እኛስ ከሃላፊነት አመልጣለሁ/እናመልጣለን ወይ? ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ የዘለቀው የህዝብ መከራና ስቃይ ፍፃሜ አግኝቶ ዘወትር የምንሰብክለት ሰላም፣ እርቅ ፣ ፍቅር፣ ይቅርታና የጋራ እድገት እውን ይሆን ዘንድ ምን አይነትና ምን ያህል ጥረት አድርገናል? አሁንስ ሌሎችን ከመስበክ ባለፈ ተልእኳችን ለመወጣት ምን ያህል ጥረት እያደረግን ነው? ለመሆኑ የመከራውና የውርደቱ ዶፍ ዋነኛ ተጠያቂዎች እነማን ናቸው? ከፈጣሪ በአደራ የተሰጠኝን/የተሰጠንን ህዝብ ክብር እንዳለው ሰብአዊ ፍጡር ለመኖር የሚያስችለውን ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ለማድረግ እንዲችል ምን ያህል ድርሻችን ተወጥተናል? ለህዝብ ክብርና ደህንነት ፣ ለፍትህና ነፃነት መስፈን ሲሉ መስዋእትነት የከፈሉትን ወንጌላዊያንና ሌሎች ሰማእታትን ታሪክ ስንተርክ የእኛ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበትና እንዴትስ ወደ ተግባር መተርጎም እንዳለበት ከምር እናስበዋለን ወይ ? የሚሉና መሰል ፈታኝ ጥያቄዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ (ዒላማ ያላደርገ) የዘመን መለወጫ መልእክት በእጅጉ ጎደሎ ነው።
በተለይ እርቅን፣ ይቅርታንና ሰላምን ሁሉን አቀፍ ከሆነ የሽግግር ጊዜ ፍትህ ውጭ በማድረግ በጎሳ ማንነት የግፍ ግድያ እና በሥልጣን ሽኩቻ ጦርነት ምክንያት በፈሰሰው የንፁሃን ደምእ ጆቻቸው የተዘፈቁ ሁለት የአንደ ሥርዓት አንጃዎች (የህወሃትና የብልፅግና) ጉዳይ ብቻ አድርጎ የመውሰድ እስተሳሰብና አካሄድ በእጅጉ የተንሸዋረረና አደገኛ በመሆኑ በፍጥነት ሊታረም (ሊስተካከል) ይገበዋል።
ለሰማያዊውም ሆነ ለገሃዱ ዓለም ህይወት ይበጃሉ በሚል ጠቅለል ተደርገው የተፃፉ መፃህፍትንና የተነገሩ ትርክቶችን በማጣቀሻነት እየጠቀሱ እና ከእራስ ድክመት (ውድቀት) ለመሸሽ በሚያስችል አተረጓጎም እየተረጎሙ “ያለፈው እልፏል ፣ የሞተውም ሞቷልና የሃላፊነትንና የተጠያቂነትን ጥያቄ እርግፍ አድርገን በመተው ወደ ፊት በሰላምና በፍቅር መራመድ ነው ያለብን “ የሚል አይነት እጅግ ደምሳሳና አሳሳች የዘመን መለወጫ መልእክት ለዘመናት የመጣንበትንና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ተዘፍቀን የምንገኝበትን መሪር እውነት ጨርሶ አይመጥንም።
በግፈኛና ዘራፊ ገዥዎች በእጅጉ የበሰበሰውንና የከረፋውን የፖለቲካ ሥርዓት የግለሰቦችን ወይም የተወሰኑ ቡድኖችን አለመግባባት ለመፍታት በምንሞክርበት እጅግ የተድበሰበሰ የአንተም ተው የአንተም ተው ባህላዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር ውጤቱ በነበሩበት ብቻ ሳይሆን እጅግ በባሰ የቀውስ አዙሪት ውስጥ ተመልሶ መዘፈቅ ነው የሚሆነው።
እየሰማናቸው ያሉ አብዛኛዎቹ መልእከቶች ወደ ፊት መንጎዱን የማያቋርጠውን ተፈጥሮዋዊ የጊዜ አቆጣጠር ህግ ከመቁጠር አልፈው ወደ መሬት በመውረድ ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳብን የመውለድና አበልፅጎ ሥራ ላይ የማዋል ይዘትና አቅም የላቸውም።
የራዕይ ግልፅነት ፣ የፅዕኑ ዓላማና መርህ ባለቤትነት ፣ የአስተሰሰብ ብስለት ፣ የአደረጃጀት ጥንካሬ ፣ የፖሊሲና ፕሮግራም ጥራት ፣ የአፈፃፀም ስልት ጥራት እና የተቀናጀ አሠራር መኖር ፈታኝ ሁኔታዎችን (challenges) ወደ መልካም አጋጣሚነት ለመለወጥ ያስችላሉ። እነዚህ ሁኔታዎች የሌሉበት ሁለተኛው እጣ ፈንታ በፈታኝ ሁኔታዎች የበለጠ ደካማ ከመሆን አልፎ የውድቀት አዙሪት ሰለባ መሆንን ያስከትላል። እስካሁን በአገራችን እየሆነ ያለው ሁለተኛው እጣ ፈንታ ነው ። ለዚህ ነው ለዘመናት የዘለቁትን ፈታኝ ሁኔታዎች ወደ መልካም እድልነት ለመለወጥ የሚያስችል አመርቂ ሥራ ባልሠራንበት መሪር እውነታ ውስጥ ሆነን አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “ኢትዮጵያ ብዙጊዜ ተፈትና ፈተናውን ተወጥታለችና አሁንም ትወጠዋለች“ የሚለው መፈክር አሁን ላለንበት እጅግ አስከፊ ሁኔታ አልሠራም ያለን።
እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!