አቶ እስክንድር ነጋና  ባልደራስ -ፊልጶስ

ባልደራስ ሲባል ለኔ በዕእምሮየ የሚመጣው አቶ እስክንደር ነጋ ነው። ባልደራስ ሲታወስ “ፊኒፍኔ ኬኛ ልዩ ጥቅም ያስፈልጋታል”  የሚለውና እየተተገበረ ያለው ነው። ባልደራስ ሲነሳ ህገ-ወጡ ከንቲባ ታከለ ኡማና  ታደለች  አበቤ በአዲስ አበቤ ላይ የፈፀሙት ግፍና ተባብሶ የቀጠለው ዲሞግራፊ የመቀየር መንግሥታዊ ፓሊሳቸው ነው።

ባልደራስን ከእስክንድር፤ እስከንደርን ከባልደራስ፣ ባለደራስን “ አዲስ አበባ የማንም ሳትሆን የሁላችን መዲና ነች” ከሚለው ትግል ነጣጥሎ ማየት ይከብዳል። ባልደራስም ያለ እስክንድር ‘’በአየር ላይ እንደተበተነ ዱቄት ማለት ነው።’’ እስክንድር ለባለድራስ ”አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤዎች” በማለት ለተነሳለት ትግል  ከመሰል ጓደቹ ጋር ብዙ መሰዋአትነት ከፍሎበታል። ከአገር ውጭም የሚገኙ ኢትዮጵያኖች፤  ከአሜሪካ እስከ  አውሮፓ፣ ከአውስትራሊያ እስከ ደቡብ አፍሪካ፡  እስክንድር ባለው ጽናትና ባለደራስ የተመሰረተበትን ዓላማ በመገንዘብ፤ ፓለቲካዊና ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን ለመወጣት ሞክረውል።

በወያኔ መቀሌ መግባት ማግሥት ”ፊኒፊኔ ኬኛ ” ተብሎ አገር ሲቀወጥ ፤ ለአዲስ አበባ ብሎም   ለኢትዮጵያ  የሚበጀ መንግሥት ይመሰርርታሉ ሲባል ፤ ”ጽድቅናውስ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ ”  እንደተባለው  ሆነና፤  ብዙዎቹ በየጉሪያቸው ተወሽቀው ለስልጣን ፍርፋሪ ሲያጎነብሱና ለኢትዮጵያ የገቡትን የኢትዮጵያዊነት ቃል ሰልቅጠው ለኦነጋዊ – ብልጽግና  የጎሳ ስብስብ ሲያጨበጭቡ፣ ህዝብን ያለ መሪ -ፓርቲ ሲያስቀሩት፤ እስክንደርና መሰሎቹ ነበሩ ለቆሙለት ዓላማ በጽናት  ተረኞቹን የታገሉትና ያጋለጡት።

ባልደራስ ገና ከጅምሩ  በጠ/ሚ አብይ አህመድ ጦር የተሰብቀበት። ነገር ግን እስክንድርና አጋሮቹ  አንገት የሚደፋ ሆኖ አልተገኘምና  ወደ እስር ቤት ተወርውረው ከአንድ  ዓመት በላይ ከቆዩ በኋላ ፤ የትኛውን የጦር ዕዝ እንደ መቱና የትኛውን ከተማ እንዳቃጥሉ ባናውቅም፤ ከነ አቶ ስበሃትና ጃዋር ጋር  ”ወንጀላቸው”እኩል ተቆጥሮ ” ምህረት ተደረገላቸው” ተብሎ ተፈቱ። ይሁን እንጅ  አንዳንዶቹ የባልደራስ አባላት እንደ  አቶ ስንታየሁ ቼኮል ያሉትም አሁንም በእስር ይማቅቃሉ። ከፊሎቹም በገዥው ኃይል እይተሳደዱ ይገኛሉ። የባልደራስን  ትግል እንቆቅልሽ የሚያደርገው ግን፤ የፓርቲው መስራችና  ሊቀ-መንበር መሰወራቸውን ወይም የት እንዳሉ ራሱ ፓርቲውን እንመራለን ያሉት ”አናውቅም ” ማለታቸውና  ርስ-በርስ  እየተውነጃጀሉ ”በተከፈተ አፍ እንጎል ይታይበታል” እንዲሉ   በየመገናኛ ብዙሃን  እየወጡ መዘላበዳቸው ነው። እስክንደርን ከወያኔ ዘመን እስከ አሁኑ የተረኞቹ አገዛዝ የምናውቀው በሰባአዊ ታጋይንቱ፣ በዓላማ ጽናቱ፣ ለመከራ ያለመበርከኩ ብቻ  ሳይሆን፤ በተለይም በብልጽግና አገዛዝ አሁን ሊመጣ የሚችለውን የህዝብ እልቂትና  የአገር ውድመት ቀድሞ ተረድቶ ፤ ለምንም ለማንማ ሳያጎበድድ  መታገሉና መሰዋአት መክፍሉ ነው። ይህ ደገፍነውም- አልደገፍነው፣ ወደድነውም -ጠላነውም የማንክደው ሃቅ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰለማዊ ትግል ፋይዳ (ከአብርሃ ደስታ)

በ’ርግጥ   እስክንደር ወደ ፓለቲካው ሳይገባና ባልደራስንም ወደ ፓርቲ ሳይቀይር ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንደሆነ፤ በሰባአዊ ታጋይነቱ ቢቀጥል  የግል እምነቴ ነበር።  ነበር ባይሰበር። ይኽን ማለቴ   በሴራና በእኩይነት በተዋቀረና በአጥፍቶ መጥፋት በተካነ  ፓለቲካ፤ ከአገርና ከህዝብ ይልቅ ሆድ አደርነትና መንደርተኝነት በነገሰባታ ኢትዮጵያ፤ እንድ የእሰክንድር  ዓይነት ሰባአዊ ባህሪ ላለው፤ ሰውን በሰውነቱ ለሚያምንና ለሚያከብር  ”በአሁኗ ዘመን በኢትዮጵያ” ቦታ የለውም ከሚል እሳቤ እንጅ፤ ነጻ ውድድርና የሃሳብ ልዕልና ባለበት ቦታ ቢሆንማ  እስክንድርም ባላሰፈለገ ነበር።

ታዲያ በተለይም  እስክንድር ከአሜሪካ ወደ እናት አገሩ  ከተመልሰ በኋላ ”ተሰወረ” መባሉን ስሰማ ናፓሊዮን ቦነፓርታን  አስታወሰኝ።  ናፓሊዮን ወደ   ዋተርሉ – ቤልጀም   ከመዝመቱ  በፊት ጦሩንና   ጀኒራሎቹን ሰብስቦ ”የመጨረሻ” የተባለውን ንግግር እንዳደረገ ይተረካል። ጦሩ በየቦታው ተብትኖ በየግዛቱ የሾማቸው  ገዥዋችና መሪዋች የከዱበት፤ ለጠላቶቹ በባንዳነት ያደሩበት ወቅት ነበር። እናማ  ለዘመቻ ለተጠራው የጦር ሠራዊትና ጀኒራልሎች  ረጅም ንግግግር ያደረገ ሲሆን፤ በመልዕክቱ መጨረሻም ፤ ” በአሁኑ ሰዓት፣ በዚች ግዜ  ሶስት ነገሮችን እፈልጋለሁ ወይም ፈረንሳይ   ትፈልጋለች።” አለ  ወደ ተሰብሳቢ የጦር ሠራዊት እያመለከተ። ናፓሊዮን ንግግሩን ገታ አደረገ። ሠራዊቱና ጀኒራሎቹ ”ምን ይሆን?” በማለት ለማወቅ ያላቸው ጉግት ጨመረ። ናፓሊዮን ” አዎ!  ሶስት ነገሮች እፈልጋለሁ። አንደኛ ታማኝ ሰው፡ ሁለተኛ ፣ ታማኝ ሰው፡ ሶስተኛ፣ ታማኝ ሰው።” በማለት ንግግሩን ቋጨ።

አዎ! በግል  ህሳቤየ እስክንድር ራሱን ከባለደራስ  ከማግለሉ በፊት እንደ ናፓልዮን ሁሉ ”እኔም ሆንኩ ኢትዮጵያ ታማኝ ሰው ያስፈልጋታል።” ብሎ የቃተተና ያጣ ይመስለኛል። የባልደራስ  መሰረትና ዓላማ  የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው። ዛሬ አዲስ አበባ ታጋይ አልባ ሆና ፤ የተረኞች መጫዎቻ ከሆነች ውላ አደራለች። ጭራሽ ምን ታመጣላችሁ ተብሎ ”በአዲስ አበባና በአካባቢያ ያለው ወሰን ተወሰነ።” ተባላ። ‘ርግጥ ነው—- ነገ -ከነገ ውዲያ የከፋው እንደሚመጣ ነብይ መሆን አይጠበቅም። ታዲያ ዛሬ ባልደራስ ነኝ የሚል አካል  ካለ የታሰሩትን የፓርቲው አባላትን ለማሰፈታት መታገልና  የኦነጋዊ ብልጽግና  በመዲናችን ላይ የሚፈጽመውን ህግ-ወጥ ሥራና የህልውና ጥያቄ ህዝብን አስተባብሮ በተገኘው የትግል መሳሪያ ሁሉ በመታገል ፋንታ፤ ርስ-በርስ በመወነጃጀል ፤ እስክንድር የደከመለትን ፓርቲ በዜሮ ማባዛት ልብ ያደማል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ ያላወቂ ሳሚ …….. ይለቀልቃል”

እኛ ኢትዮጵያዊያኖች እንደ አለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያዊ ተቋም መመስረት አልቻልንም። ተቋም መስርተን ቢሆን ኖሮ አንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ በግለሰቦች መውጣትና መግባት   ባልፈረሰ   ወይም   አባላቶቹ ባልተበተኑና ትግሉ ሁሉ ‘ከ ሀ” ባልተጀመረ ነበር። ባልደራስም የደርሰበት ዕጣ ይኽው  ነው። በአገር ደረጃ እንኳን ተቋም መመስረት ባለመቻልችን ገዥዎቻችን እንደፈለጉ ጥባጥቢ ይጫወቱብናል።  በእስክንድር መሰወርና ጻፋት በተባለችው መልዕክት ዙሪያ ብዙ  መላ ምቶችን መስጠት ይቻላል።  ሃቁን የምናውቀ  ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከራሱ ከእስክንድር ነጋ ብቻ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን ስለ እስክንድርም ሆነ ስለ ባልደራስ  ”ዝም” ብንል መልካም ነው። አሁን አገራችን ያልችበትን ሁኔታ ተገንዝበን ለጋራ  ህልውናችንና ለኢትዮጵያችን የድርሻችን ሁሉ እንወጣ። ምክንያቱም ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከፓለቲካና  ከሥልጣን ሁሉ በላይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ከጎሳ፣ ከዝና፣ በአጠቃላይ በዚች ምድር ላይ ካለ ጥቅማጥቅም፣  መጓተትና መቆራቆስ፣ ማግኘትና ማጣት ሁሉ የበላይ ሰው የመሆን ነው። ኢትዮጵያዊነት  የመላው  የኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ህብር-ማንነት መገለጫ የከፍታዎች ሁሉ ማማ ነው። ኢትዮጵያዊነት ትላንት የነበረ ዛሬም ያለና ለነገው ትውልድ ለማስረከብ ብዙዎች እንደ ጥንቱ በውስጥም በውጭም የህይወት መሰዋአትነት እየከፈሉለት ያለ የክብር ሞት የሚሞቱለትና ከጸረ ኢትዮጵያዊያንና ከጎሰኞች ጋር ጉረሮ-ለጉሮሮ የሚተናነቁለት  ነውና።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

—————/———–ፊልጶስ

መስከረም 2015

e-mail: philiposmw@gmail.com

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share