የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል! – አገሬ አዲስ

ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓም(10-09-2022)

የሰው ልጅ የሚመዘነው በጭንቅና ክፉ ወቅት ነው። በደህናው ቀንማ ሁሉም ደግ፣ሁሉም አዛኝ ይሆናል፣ውስጣዊ ማንነቱ አይታወቅም።።በክፉ ቀን ክፉ ሰሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ጉርብትናና ግንኙነት በዝምድናም ሰንሰለት ሳይቀር አብረው የኖሩ ሰዎች ይከፋሉ፤አንዱ በሌላው ላይ ይጨክናል።በስቃይና መከራው ሊጠቀምበት ይሻል።ሌላውን አሳልፎ በመስጠት አንደኛው ሊሾም ሊሸለምበት ይሽቀዳደማል። ይህንን ያመጣሁት እንደው የለለና ያልሆነ ነገር ፈጥሬ አይደለም ።ከታሪክ በመነሳት ማስረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ነው።ክፋትና ጭካኔ ዘርና ቦታን፣ጾታንና ዕድሜን አይለይም።በሁሉም ዘንድ የሚንጸባርቅ ድክመት ነው።

ይህንን ድክመት ሁለንተናዊ ለማድረግ ከዓለም ጦርነቶቹ በአንዱ በናዚዎች ጊዜ የሆነውን መነሻ ባደርግ ዘርና ቦታን አይለይም በሚለው አባባሌ ወደ አገራችን በምመለስበት ጊዜ ትስስሩን ግልጽ ያደርገዋል።የናዚዎችን አነሳሁ እንጂ በሌሎቹም ወቅቶች በተከሰቱ ጦርነቶችና ጉዳቶች ጊዜ የሰው ልጆች ክፋት ገንፍሎ የወጣባቸውን ሁሉ ላንሳ ብል ቦታና ጊዜ አይበቃኝም።

በናዚ ጀርመኒ ጊዜ የአውሮፓ አገራት ሁሉም በሚባል ደረጃ በጦርነት እሳት ተለብልበዋል ብቻም ሳይሆን አመድ ሆነዋል።ቀድሞ እጁን ያልሰጠና ለናዚዎች ያልተንበረከከ ከናዚዎች የክፋት እርምጃ አላመለጠም።በተለይም በዋናነት ጠላቶቼ ናቸው ብሎ የሚያሳድዳቸው የይሁዲ ተወላጆች የሚኖሩባቸው አገሮች የጥቃቱ ዒላማ ነበሩ።በዚህ ጥቃት ከያገሩ እዬተለቀሙ በቦታው ከተገደሉት ይበልጡን ወደ ጀርመን ተወስደው በማቃጠያ ምድጃ አመድ የሆኑት ከ6 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ መሆናቸውን ታሪክ መዝግቦታል።

የናዚዎችን ክፋትና ጭካኔ ተቀብሎ አጋር የሆነ የዬአገራቱ ተወላጅ ቁጥሩ ቀላል አልነበረም።የራሱን ወገን አሳልፎ እዬሰጠና ለናዚዎቹ እዬሰለለ ባገርና በወገኑ ላይ በደል የፈጸመ ባንዳው ከናዚዎቹ የበለጠ ናዚ ነበር ቢባል ስህተት አይደለም።ለቁራሽ ዳቦ ሲል ዘመዱን፣ጎረቤቱንና ጓደኛውን አሳልፎ የሰጠው ቁጥሩ ቀላል አልነበረም።ከዚህም ጎን ለጎን እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለተቸገሩት መደበቂያ ፣ጥላ ከለላ የሰጡም ደጋጎች ነበሩ።እነሱም በከሃዲዎች ከተጋለጡ ተመሳሳይ እርምጃ ይወሰድባቸው ነበር።ያንን ቢያወቁም  ግን መልካም ነገር ከመሥራት አላፈገፈጉም።በዚህም የብዙ ሰው ሕይወት አድነዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማራና ኦሮሞ አንድ ታላቅ ጦርነት ተዘጋጅቶላቸዋል! - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ሌላው በጦርነት ጊዜ ሁሉም ነገር መጥፋቱ የተለመደ ነው።በመጥፋቱም የዋጋ ጭማሪ ይኖራል።ይህንንም ተቋቁመው ያላቸውን ከሌላው ጋር ተካፍለው ክፉ ቀኑን ያሳለፉ ደጋጎችም ነበሩ።አንዳንዶቹ ጨካኞች ችግርን መሣሪያ አድርገው ባልጠፋ ነገር ላይ ከፍተኛ ዋጋ እዬጨመሩ በሚሰቃዬው ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ስቃይ ያደርሱበት እንደነበር በሁኔታው ያለፉ ሰዎች ይመሰክራሉ።በደህናው ቀን አንድ ቁምጣ ድንች ስሙኒ የነበረውን በጦርነቱ ጊዜ በወርቅ የአንገት ሃብልና ቀለበት የሸጡ አረመኔ ገበሬዎች እንደነበሩ፣እርሃብ የተፈታተናቸው ሰዎች ካለፈ በዃላ እምባቸው እያቀረረ ሲናገሩ መስማት አንጀት ይበላል። ክፉ ቀን አልፎ ሰላም ሲሰፍን ደጎችም ክፉዎችም እንደዬሥራቸው ማህበረሰቡ በታሪክ መድቦ አስቀምጧቸዋል።ክፉ የሠሩት በመልካም ጊዜ የነበሩበትን ቦታ ቀይረው ወደ ማይታወቁበት ቦታ የሸሹም አልጠፉም።ግን ቦታ ቢቀይሩም ጊዜው ቢረዝምም ታድነው ቅጣታቸውን አግኝተዋል።ያልተያዙት ጥቂቶቹ አብሯቸው የሚጓዘው ህሊናቸው የሚቆረቁር ቁስል ፈጥሮባቸው ግማሾቹ በጸጸት እራሳቸውን ሲገሉ አብዛኞቹም ከሰው ተነጥለው በባዶ ቤት ሞተው ለመገኘት በቅተዋል።ቢሞቱም ግን ልጅና የልጅ ልጆቻቸው የዛ ከሃዲና ጨካኝ ልጆች እዬተባሉ ለመሸማቀቅ መዳረጋቸው አልቀረላቸውም።የአባት ዕዳ ለልጅ፣የፊት እድፍ ለእጅ እንዲሉ!

በሌሎቹ አገሮች የሆነውን ካዬን በዃላ ወደ አገራችን ስንመለስ ቦታውና ጊዜው ቢለያይም ተመሳሳይ ድርጊቶ መካሄዳቸውን ካለፉት ታሪኮቻችንና አሁንም ከምናዬውና  ከምንሰማው ለማውቅ እንችላለን።በጣልያን ወረራ ጊዜ ባንዳ የተባሉት ከሃዲዎች ብዙ አርበኞችንና ንጹሃንን በግል በቀልና ጥላቻ ለጣሊያን ፋሽሽቶች አሳልፈው በመስጠት የብዙ ወገኖቻችን ህይወት እንደጠፋ አይካድም። ከጣልያኖች በዃላም በነበሩት  በዘውድና በወታደር አምባገነኑ  አገዛዞች ስርዓቱን ይቃወሙ የነበሩ አገር ወዳዶችን ጎረቤትና ጓደኛ ከዚያም ባለፈ ቤተዘመድ አሳልፎ በመስጠት እንጀራውን እንደጋገረባቸው የድርጊቱ ሰለባ የሆኑትና ከሞት የተረፉት ይመሰክራሉ።

በዚህ  ወገንን ወይም አንዱን የሰው ልጅ ሸጦ የመኖር ወይም በመከራው የመነገድና የመጠቀም ልክፍት አሁንም በኛ ጊዜ በስፋት ሲካሄድ ይታያል።ላለፉት 32 ዓመታት ለሰፈነው የጎሰኞች ሥርዓት ሰላይና አገልጋይ  በመሆን ለራሱ ነጻነትና መብት፣ለአገሩም አንድነት የሚከራከሩና የሚታገሉትን፣ስለ እውነት የሚመሰክሩና የቆሙ ደጋግና ደፋር ዜጎች አሳልፎ የሚሰጠው ጨካኝ ቁጥሩ ቀላል አይደለም።ክህደትና ጭካኔ የመተዳደሪያ ሙያ ሆኖል ማለት ይቻላል። ካለእነዚህ ክፉዎች ክፉ መንግሥታት አቅምና ዕድሜ አይኖራቸውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሁለት መነጽሮች ወግ - አስቻለው ከበደ አበበ ሜትሮ ቫንኩቨር ካናዳ

በወታደራዊው አምባገነን አገዛዝ ወጣቶችን እዬጠቆመ ያስጨረሰው አብሮ አደግና የሚያውቅ ጎረቤትና  የቅርብ ዘመድ ነበር።በአሁኖቹም ተከታታይ የጎሰኞች ስርዓት በወያኔና በኦነግ ኦሕዴድ ብልጽግና ዘመን ተቃዋሚዎችን የሚያሳርደው ያው ጎረቤት፣ጓደኛና ቤተዘመድ ነው። ጠላት ከሩቅ አይመጣም የሚባለውም ለዚያው ነው።

ሌላው የሕዝቡን ስቃይና መከራ መጠቀሚያ የሚያደርጉት ደግሞ በንግድና ባገልግሎት መስኩ የተሰማሩት ናቸው።በደህናው ቀን ብዙ መልካም ነገር ተካፍሎ አብሯቸው የኖረውን ሕዝብ በክፉ ቀን ለመጉዳት ሲሯሯጡ ማዬትን የመሰለ የሚያም ህመም የለም።

ክፉን ቀን ተሳስቦ ከመኖር ይልቅ በክፉ ቀን ስቦ ገደል መክተት ትልቅ እውቀትና ችሎታ ሆኗል።በገበያው ላይ የሚታዬው ክፋትና ስግብግብነት ከሰው ደረጃ አውጥቶ ከአውሬ ደረጃ የሚያሰልፍ ሆኗል። አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ዳቦ ከሁለት ብር ስድስት ብር ገባ ሲባል እንዴት ያልን ሰዎች፣ይኸው ዳቦ በደሴ ከተማ 30 ብር መሸጡን ስሰማ  እኔ የማቃት ደሴ ፣እኔ በአምስት ሳንቲም አንድ ፍርኖ ዳቦ በበላሁባት ደሴ የሆነ አልመስልህ አለችኝ፤ወይስ ሌላ ፕላኔት ላይ ስላለች  ደሴ ነው የምሰማው ብዬ ግራ ገባኝ።በዚችው የደጋጎች ከተማ በነበረችው ደሴ የሚካሄደውን ጭካኔና ራስ ወዳድነት ስሰማ ጭራሽ ማመን አቃተኝ።ወያኔ አዋክቦት ከመኖሪያ ቀዬው ያባረረው ወደ ቤቱ ወይም ህይወቱን ለማትረፍ ከደሴ ወልድያ፣ወይም ከወልድያ ደሴ ልሂድ ቢል ከ2500-3000 ብር ለነጠላ ጉዞ መጠዬቁን ስሰማ ይህ ክፉ ቀን አልፎ ደህና ቀን ሲመጣ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች በኩራት በደሴ ከተማ፣በፒያሳ አስፋልት ላይ  ዳግም መኪናቸውን ያሽከረክሩ ይሆን ብዬ እራሴን ስጠይቅ በእግራቸውም ለመራመድ መቻላቸውን ተጠራጠርኩ።ለሚመጣው ጊዜ ፈራሁላቸው። ሌላ ሌላውማ አይነሳ ይቅር ማለቱ ይሻላል።እንዲህ ጭካኔና ክፋት በዋጣት የደሴ ከተማ ከወለጋና ከሌላው ክልል ከሞት ተርፈው ተፈናቅለው የመጡት ዜጎች የሚገፉትን ኑሮ ሲያስቡት ይዘገንናል። መንግሥት ለነዚህ ሰዎች የሚፈልጉትን ከማሟላት ይልቅ በችግኝ ተከላ ጊዜውንና ገንዘቡን ያባክናል።ዱሮስ ቢሆን ከጎሰኞች መንግሥት ምን ይጠበቃል? አስጨፍጫፊውና አፈናቃዩ ማን ሆነና?ይኸው መከረኛ ሕዝብ መንግሥት ባለበት ከተማ  ሕግ ይኖራል ብሎ ወደ አገሩ ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ልግባ ቢልም እንደባዕድ ወራሪ ተቆጥሮ እንዳይገባ በፖሊስ ሃይል ይከለከላል።ታድያ ዬት ይግባ?ምን ይሁን?ዬት ይድረስ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከዛሬ ጀመሮ የዞን ዘጠኝ ኩሩ አባል መሆኔን አረጋግጣለሁ - ግርማ ካሳ

ግፍ መሥራት የማይታክትህ አምባ ገነን መንግሥት ሆይ!

በወገኖችህ መከራና ችግር ሃብት የምትሰበስብ ጨካኝ ነጋዴ ሆይ!

ለትንሽ ጥቅም ብለህ ሌላውን ሃቀኛና ለእውነት የቆመ፣አገር ወዳድ አሳልፈህ የምትሰጥ ከሃዲና አድርባይ ሆይ!

የሌሎቹ ስቃይና መከራ ባንተላይ ቢደርስ ምን ይሰማህ ይሆን?ሌላው ቢቀር ለምን ለልጅ ልጆችህና ለታሪክህ አታስብም?

የዛሬውን ቦታህን ዘለዓለማዊ አድርገህ ካሰብክ ተሳስተሃል።ከአንተ በፊት አንተ አሁን በተቀመጥክበት ቦታ ላይ ተቀምጠው እንዳንተ በሕዝብ ላይ ግፍ የሠሩ መናጢዎች የት እንዳሉና ምን እንደደረሰባቸው አስተውል።ፍትህ ከሰጣቸው ቅጣት ይበልጥ በሕብረተሰቡ የተሰጣቸው መለያ ሞተውም ቢሆን ከመቃብራቸው በላይ እንደሚኖር ተገንዘብ።የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል የምልህም ለዚያ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!ሌላው ቢቀር በሃይማኖትህ የምትሰማውን ደግ ነገር ሁሉ ለማድረግ ቢሳንህ እንኳን፣እንደ ሰው ለሌላው ወገንህ ብትራራለት በክፋት ከምታገኘው ጥቅም የበለጠ ልባዊ ደስታ ታገኛለህ።ቤት አከራይ ስለሆንክ በተከራዬው ላይ አትጨክን፣ቤትህ ጊዜያዊ እንጂ ዘለዓለማዊ አይደለም፤ሊፈርስ፣በእሳት ሊወድም ወይም፤ልትቀማ ትችላለህ።በርካሽ የገዛኸውን ከሚያስፈልገው ትርፍ በላይ ጠይቀህ ብትሸጠው የገዢው ልባዊ ሃዘን እንደሚጎዳህ አስብ! በደህና ቀን ቋሚ ደንበኛህን እንዳታጣ በክፉ ቀን ተንከባክበህ ያዘው።እዘንለት፣አስብለት!ከገንዘብ ትርፍ በላይ የሰው ፍቅርና ክብር ታተርፋለህ። የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል የምልህም ለዚያ ነው።

የመከራ ቀን ጥሩ መስተዋት፣

ደግና ክፉ የሚታይበት፤የሚለይበት።

አገሬ አዲስ

 

1 Comment

  1. ከዘመናት በፊት እውቁ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንዲህ ብሎን ነበር ። “ህይወት አንድነት ነው። አንድነት ህይወት ነው። ሃይል አንድነት፤ አንድነት ሃይል ነው። … የሃገር ማተቧ ከተበጠሰ፤ የህዝብ እምነቱ ከጎደለ ሃገሪቱም ህዝቡም አወዳደቃቸው አያምርም”። አሁን ባለንበት ዘመን በሃበሻው ምድር እየሆነ ያለው ይኼው ነው። የታጣቂ መንጋ የሚራወጥባት ኢትዮጵያ ለዘመናት የሰዎች ሰቆቃ የሚዘንብባት ምድር ሆናለች። ችግሩ በየጊዜው በመሳሪያ አፈ ሙዝ እየታገዙ አለያም ዘርና ቋንቋን ተገን በማድረግ በስልጣን ላይ ቁጢጥ ያሉት ሃይሎች ብቻ አይደሉም። ችግሩ ራሱ ህዝቡ ነው። በወለጋ ያ ሁሉ የደም ጎርፍ እየፈሰሰ ከንፈሩን ከመምጠጥ ወይም ይበላቸው ከማለት ያለፈ በቁርጠኝነት ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት መንግስት ግድያና ዘረፋውን እንዲያስቆም የጠየቀ የለም። ባንጻሩ በአፋርና በአማራ ክልል የቤት ቆርቆሮ ሳይቀር እየነቀለ ወደ መቀሌ ያጋጋዘውን የወያኔ የሙታን መንጋ ለምን እንዴት ብሎ በህብረት የጠየቀ የለም። ይግረማችሁ ብሎ ወያኔ አይኑን በጨው ታጥቦና በፊት የዘረፈውን አጣጥሞ ለ 3ኛ ዙር ዘመቻ ያለ የሌለ ሃይሉን አደራጅቶ እንሆ ሰውን በማሸበር ላይ ይገኛል።
    በሃሰት ፕሮፓጋንዳ የተካነው ወያኔ ሳይገድል ገደልኩ፤ ሳይማርክ ማረኩ በማለት ከሰው ልጅ ስብዕና ውጭ የሆነ ሬሳን ውሃ ላይ በማንሳፈፍና የአሜሪካውን CNN በማታለል እንሆ በእኛ ላይ የተፈጸመው እንደ ረዋንዳ ነው በማለት ላፍታም ቢሆን የአለምን አይን መሳብ ችሏል። ግን አንድ ያልተረዳነው ነገር ቢኖር ወሬው በነጭ ስለተቀናበረ ጉዳዪን እውነተኛ ሊያደርገው አይችልም። የነጮች ዋና አላማቸው የእኛ እርስ በርስ መገዳደል እንጂ ሰላምና ደስታ እንዲኖረን አንድም ቀን ተመኝተው አያውቁም። የሚያነብ የሚሰማ ጀሮ ያለው ያለፈ ታሪክን አሁን ካለው የፓለቲካ ሸፍጥ ጋር በማገናዘብ እውነትን መረዳት በቻለ ነበር። ግን ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ለውጭ ሃይሎች የሚታዘዝ እንደ ወያኔ ያለ የሌቦች ጥርቅም ለጊዜአዊ ጥቅም እንጂ ለዘለቄታ የሚሆን ነገር አይታሰበውም። ሽብር የወያኔ ዋና መሳሪያ ነው። በቅርቡ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተናገረውን ለሰማ ወያኔ ጽፎ አንብብ ብሎ የሰጠው እንጂ ከስቴት ዲፓርትመንት የመነጨ ቃል አይመስልም። ይህ የሚያሳየው ወያኔና አሜሪካ ተናበው እንደሚሰሩ ነው። ግን ወያኔ የማይረዳው አሜሪካን ያመነ ውሃ የዘገነ መሆኑን ነው። አሁን የኢትዮጵያ ሰራዊት መቀሌ ገብቶ የጌታቸውና የሌሎችንም እጅ በሰንሰለት ቢያስገባ ተገልብጠው ተው ብለን ነበር እንዳሻችሁ እንደሚሉ የታወቀ ነው። አሜሪካ ደስ የሚላት እኛ ስንገዳደል ብቻ ነው። ለዚህ ዋና ማሳያው ለ 30 ዓመት ከሻቢያ ጋር የተደረገው ፍትጊያ ነው። ይህን ጉዳይ የኤርትራው መሪ ጠንቅቀው ይረዳሉ። ለዚህም ነው ብቸኛው አፍሪቃዊ መሪ በመሆን አሜሪካን አክ እንትፍ ያሏት። ግን የቀረነው መቼ ይሆን የምንነቃው? መቼ ነው የዓለም ባንክ፤ ተመድና ሌሎችም ተቋማት የአሜሪካ የፓለቲካ ስልት ማስፈጸሚያ መሆናቸው የሚገባን? ስለሆነም ችግራችን የሚመነጨው ይበልጡ ከራሳችን ነው። የመንግስት ፓሊሲና የህዝብ የመኖር ናፍቆት ከውጭ ሃይሎች ተንኳሽ ሃሳብ ጋር ተገምዶ ይኸው ለዝንተ ዓለም ስም እየቀየረ ሲያፋጀን ይኖራል። የክፋታችን ጥግ ሰማይ ጠቀስ ነው። የድሮዎቹን እያወገዝን ዛሬ እኛ ዳሪዎስ ሆነናል። የነቃ የበቃ ለሃገር አንድነትና ክብር ለህዝቦች እኩልነትና ብልጽግና ዘር ጎሳ ሃይማኖት ሳይለይ ይታገላል እንጂ በራፉ ላይ ቆሞ የአለም መጀመሪያና መጨረሻ ክልሌ ነው አይልም። ጉድ ማለቂያ የለው እንዲሉ ይኸው ዛሬም ትላንትን እየመሰለ ነው። ማክተሚያ ይኖረው ይሆን? አላውቅም። ግን አንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ሆነን ተወልደናል እና እንበርታ (አልወለድም – አቤ ጉበኛ)። “ሞትና ህይወት ድንቁርናና እውቀት” (አደፍርስ – ዳኛቸው ወርቁ)። ይህ የዝብርቅ ዓለም ደሃ አደጎችን፤ ደካሞችን፤ ሰርተው ለማደር የሚፍጨረጨሩትንና መከታ የሌላቸውን ማስለቀሱንና መዝረፉን የሚያቆምበት ዘመን ይመጣ ይሆን? ደራሲው ከላይ ” የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል” ጥሩ የአባባል ዘዴ ነው። ግን ጂኒ የያዘው ሰው በስሙ ቢጠሩትም አቤት አይልም። እየሆነ ያለው ይኸው ነው። ሁሉም የራሱን ከበሮ እየመታ መትመም። በአደፍርስ ግጥም መሳይ ነገር ልዝጋ
    የት ትሄዳለህ የት ትሄዳለህ
    ዋይ ዋይ የት ትሄዳለህ
    እናት አባትህን ታሳዝናለሁ
    ዋይ ዋይ……
    ወዳጅ ዘመድክን ታስለቅሳለህ
    ዋይ ዋይ ….. በማለት ይቀጥላል። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share