ሸኖ፣ አሌልቱ፣ ቤኪ፣ ሰንዳፋና ለገጣፎ – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

ከዚህ በላይ በስም የጠራኋቸው አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች የግልም ሆነ የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ከዎልድያ፣ ከደሴም ሆነ ከሰቆጣ በሸዋ-ሮቢት፣ በደብረ-ሲናና በደብረ-ብርሃን በኩል አድርገው ወደሀገሪቱ ርእሰ-ከተማ፣ አዲስ አበባ መናህሪያዎች ለመግባት በየእለቱ የሚንደረደሩባቸው የኦሮምያ ክልል ከተሞች ናቸው፡፡ሆኖም ይህ የየብስ ትራንስፖርት በለየለት የውንብድና ስራ ላይ በተሰማሩ የኦሮምያ ጸጥታ ሀይሎች ያለአግባብ መስተጓጎልና አልፏልፎም ጭራሹን መቋረጥ ከጀመረ ትንሽ ሰነባብቷል፡፡

ለቁጥር የበዙ የዚያን መስመር መንገደኞች በተለያዩ ጊዜያት ካነጋገሩ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ-ብዙኃን በግርድፉም ቢሆን ለመረዳት እንደተቻለው እየሆነ ያለውና የሚሰማው አስነዋሪ ነገር ሁሉ ፍጹም ለጀሮ ይቀፋል፡፡

ህዝባዊ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው ከፍተኛ እምነት የተጣለባቸው የጸጥታ ሀይሎች ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ከተሞች መነሻ አድርገው በተቋቋሙት የፍተሻ ኬላዎች ተሽከርካሪዎችን በሀይል እያስቆሙ ያሳፈሯቸውን ሠላማዊ ተጓዦች በፍተሻ ስም ያስወርዳሉ፣ የነዋሪነት መታወቂያዎቻቼውን እየጠየቁ ይሰበስባሉ፣ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው ያለሀፍረትና ያለይሉኝታ ወደመጡበት እንዲመለሱ ያስገድዳሉ፣ ይልቁንም አሽከርካሪዎችን ለምን ጫናችኋቸው በማለት ያሸማቅቃሉ፣ ያንገላታሉ የትራፊክ ፖሊስ አባሎቻቸውን በመሳሪያነት እየተጠቀሙ ያለአግባብ በገንዘብ ይቀጣሉ፣ ሲያሻቸውም በአደባባይ ጉቦ እየተቀበሉ አንዳንዶቻቸውን በሙሰኝነት ያሳልፋሉ፡፡

በሂደቱ ተመላላሽ ህሙማን ሀኪም በያዘላቸው ቀጠሮ መሰረት ወደሆስፒታል በወቅቱu እንዳይደርሱ በመከልከላቸው የቁም ሞት ተፈርዶባቸዋል፡፡ የው በረራ የተስተጓጎለባቸው ወገኖችም እንዳሉ ተወስቷል፡፡

ከመካከላቸው ሰብኣዊ ክብርን በሚጋፋ አኳኋን ብሔራዊ ማንነታቸው እየተጠቀሰ ያለአግባብ የሚዘለፉና በድብደባ ምክንያት አካላዊ ጥቃት የሚደርስባቸው እናቶችና ህጻናት እንደሚገኙባቸውም ሮሮዎች በስፋት ተስተጋብተዋል፣ አሁንም ድረስ እየተስተጋቡ ነው፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ ይበልጥ የሚገርመው፣ እንደኮሶ የሚያንገሸግሸውና ክፉኛ የሚያመው ይህ ሁሉ በደል ከሳምንታት ለበለጠ ጊዜ በገሃድና በማናለብኝነት በወገኖቻችን ላይ ሲፈጸም የአውራ ጎዳናው ባለቤት ነኝ ከሚለው ከፌደራሉ መንግሥት አንስቶ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ክልሎች በኩል እየተሰጠ ያለው ምላሽ በጣም ቀዝቃዛና ታዲያ ምን ይጠበስ? የሚል አይነት ሆኖ መታዘባችን ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድርድር ወይስ ማደናገር!

ለምሳሌ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጉዳዩ የሚያገባው እንደሌለ ሁሉ እንዲህ ያለውን ከረር ያለ ስሞታ ቢያዳምጥም ጀሮ ዳባ ልበስ እንዳለ ነው፡፡

የፌደራሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ነኝ ያሉ አንዲት ሴት ደግሞ ስለጉዳዩ የበኩላቸውን ማብራሪያ እንዲሰጡ ያን ሰሞን በአንድ የውጭ ሚዲያ ተጠይቀው ነበር፡፡ የፈረደባቸው ኦ.ነ.ግ ሸኔና ህ.ወ.ሀ.ት ድህረ-ወረራ ያሰማሯቸው አሸባሪዎች በተጭበረበረ የመታወቂያ ወረቀት ወደመዲናዋ ሰርገው ወይም ተሹለክልከው እንዳይገቡ ለመከላከል በታቀደ እርምጃ ጥብቅ ፍተሻ እየተካሄደ እንደሆነ እናውቃለን ሲሉ ኀላፊነት የጎደለው የግብር ይውጣ ምላሽ በመስጠት አድራጎቱን ከመኮነን ይልቅ ያልተገባ ኦፊሴላዊ ሽፋን ሲያላብሱት ተደምጠዋል፡፡

ከንዲህ አይነቱ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚመነጨው ኩርማን እንጀራ ሳይበላ ቢቀር ምን አለበት ጎበዝ?

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የሲቪልና የፀጥታ ባለሥልጣናትማ ስለጉዳዩ አንዳች እውቀት እንደሌላቸው ነበር ደጋግመው የነገሩን፡፡

ለነገሩ ውሉ ጨርሶ ከጠፋባቸው ከኒያ ሴቲዮ እነርሱ ሳይሻሉ አልቀሩም፡፡

ተሳፋሪዎቹ የሚነሱበት የአማራ ክልልም ቢሆን አፍጥጦ ለወጣውና አሁንም ድረስ ሃይ ባይ ሳያገኝ ተጠናክሮ ለቀጠለው ለዚህ ችግር መፍትሄውን በዋነኝነት እየጠበቀ ያለው በበደሉ አድራሽነት ከሚወቀሰው ከኦሮምያ ክልል የስራ ኀላፊዎች በመሆኑ ያው እንደተለመደው የምንትስ ባል ከምንትስ አያስጥልም አስብሎታል፡፡

ይህ የዘፈቀደ እርምጃ ከገዢው የብልጽግና ፓርቲ የኦሮምያ ክንፍ አኳያ ሲታይ ወደአዲስ አበባ ድርሽ እንዳትል  ብንለው አማራ ምን ሊያመጣ ይችላል? እየተባለ ያለ ነው የሚመስለው፡፡

በርግጥ ለጊዜው ምንም ያመጣው የለም ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን ለወደፊቱ ምንም የሚያስከትለው መዘዝ አይኖርም ማለት እንዳልሆነ ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ለመሆኑ ግኡዙና ዳፍንታሙ ሕገ-መንግሥታችን እንዲህ ያለውን አፓርታይድ-መራሽ እርምጃ በተመለከተ ምን ይላል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ መሰረት የለውም!!! - መሰረት

እንደኔ ባሉት ጦማርያን አማካኝነት ለአካዳሚያዊ ፍጆታ ብቻ የሚያገለግል በሚመስል መልኩ አሸብርቆ በዋቢነት ከመጠቀስ ባለፈ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ገቢራዊ ለመደረግ ያልታደለው የኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 32 ንኡስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ስር አይደለም የዜጎችን፣ በሀገሪቱ የግዛት ወሰን በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ባእዳንን የእንቅስቃሴ መብትና የመኖሪያ ስፍራ ምርጫ ነጻነት ያከብራል፣ ለዚህም በሰነድ የተረጋገጠ ዋስትና ይሰጣል፡፡

ዳሩ ይህ ፍሬቢስና አማላይ ቃለ-ሕገ-መንግሥት ብቻውን ምን ይረባናል?

የተጻፈ ሕግ በስማችን ስለተጻፈ ብቻ ህይወት አይኖረውም፡፡ አበው አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም! የሚሉት ለዚህ ነው፡፡

ውድ ወገኖቼ፣ ቁልፉ የሀገራችን ችግር እኮ ለተራዘመ ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየው የተጠያቂነት አለመኖር ባህል ወይም ክፉ ልማድ እንጂ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ እንግዲህ ከነዚህ ቀማኛና ወስላታ የጸጥታ ሀይሎች መካከል አንዳቸውስ እንኳ በሕግ ተይዞ ሥልጣንን አለአግባብ በመገልገል ወንጀል የተጠየቀ ስለመሆኑ ያወቅነው ነገር የለም፡፡

ነገሩ ሚስትህ ወለደች ወይ ቢሉት ማንን ወንድ ብላ እንዳለው አባ-ወራ መሆኑ ነው፡፡

ለመሆኑ መንግሥት ሸኔ እያለ በዳቦ ስም የሚጠራው የዎለጋው አሸባሪ ቡድን ታጣቂዎች በሕግ ማስከበር ጥላ ስር ተከልለው በ1ኛው የአዲስ አበባ መግቢያ በር ላይ ለጥፋት የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ወሮበሎች ከሚፈጽሙት የከፋ ምን በደል አድርሰው ነው የማያቋርጥ የውግዘት ናዳ የሚወርድባቸውና በየደረሱበት የሚሳደዱት?

ለማናቸውም ፈጣሪ በኪነ-ጥበቡ ቶሎ ወደቀልባችን እንድንመለስ ካልረዳን በስተቀር የጀመርነው እርስበርስ የመገፋፋት መጥፎ ልምምድ ፍጹም አደገኛና ዳፋውም ለትውልድ የሚተርፍ በመሆኑ አስተውለን መራመድ ይኖርብናል፡፡ እድሉ ስለተመቻቸልን ብቻ ዛሬ በገፍ የምንወስደው ግዙፍ የመከራ ብድር ለነገ የምንከፍለውን እዳ እንዳያከብደው መጠንቀቅ አለብን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሄንሪ ቀመር በአንፊልድ ሊቨርፑል (ልዩ ትንታኔ)

አስፍተን ካየነው ተረኝነት የኑሮ ሕግ ነው፡፡ የዛሬ አጥቂ የነገ ተጠቂ የመሆን እድል አለው፡፡ ስለሆነም ይህንኑ እውነታ ከወዲሁ ተረድተን በኀላፊነት ከሚያስጠይቁ አስነዋሪ ድርጊቶች ብንታቀብ እላለሁ፡፡

2 Comments

  1. The only people that can stop this drunken OPDO warlords are the Oromo people. Because whatever crimes the OPDO commits in the name of the Oromo people today will be avenged not on OPDO but the poor Oromo as the looting elite will be the first ones to hightail it to Dubay, Turkey or Washington DC with the stolen treasure. The average Oromo citizen should speak up against the Amhara genocide, the ethnic cleansing and the unlawful and inhuman treatment that the OPDO cadres are committing. What the cadres are trying to do is build a rift between people. Once they succeed with that, a civil war will be the inevitable result. Today is the time to oppose the lunacy of OPDO cadres and their crime boss, Abiy Ahmed.

  2. ባለፈው ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ነበሩ ሲናገሩ ሲራመዱ እንደ ፈረንጆች ካት ዎክ እንደሚባለው ሰበር ሰካ እያሉ የሚራመዱ አሁን ደግሞ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዲዛይን ልብስ በቄንጥ አረማመድ በቄንጥ ንግግር እያስደሰቱን ነው ኑሩልን ዘንጡልን እናንተ ባትኖሩ ማን ይዘንጥልን ነበር፡፡ባለፈው ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ነበሩ አሁን የት እንዳሉ የሚያውቅ ይወቅ የእናንተም እንደሳቸው የመደበቂያ ጊዜ መምጣቱ ግን አይቀርም፡፡ ነገ ደግሞ ማን ይመጣ ይሆን ይህ መከረኛ ህዝብ በቃችሁ ማለት ከብዶታል ወይም ገና ነው ጫኑብኝ ብሎ ፈቅዶላችኋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share