ሲና ዘ ሙሴ
የመንግሥት ህግ አሥከባሪ ወይም ወንጀልን ተከላካዩ ፤ የአቃቢ ህግ መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም ፣ ንፁሐን የአለአንዳች ተጨባጭ የሆነ የህግ መተላለፍ ፤ ያለማሥረጃ ፤ በፖሊስ እየታፈኑ ሲታሰሩ እያየ ፣ “ ይኽ አካሄድ ህግን የጣሰ ነው ።
“ ብሎ ለመሞገት አልቻለም ። የፍትህ ሚኒስትሯም ይኽንን ህገ ወጥ ተግባር በግልፅ ለማውገዝ የሚያሥችል ወኔ አጥተዋል ። ጭራሽ ድምፃቸው ጠፍቷል ። ምናልባትም የአፋኞቹ እጅ ረጅም በመሆኑ ለደህንነታቸው ሰግተው ይሆናል ። ድምፃቸውን ያጠፉት ። ለሠላም ሚኒሥቴር ድኤታው ያልተመለሱ በመንግሥት ውሥጥ መንግሥት የሆኑ ፤ ከህግ በላይ የሆኑ ኃይሎች ፤ ለፍትህ ሚኒሥትሯ እንዴት ሊተኙ ይችላሉ ?
ፖሊሱንም ሆነ አቃቢ ህጉን በቁጥጥራቸው ሥር በማዋል ዳኞችንም በብልፅግና ፓርቲ ሥም በመጠርነፍ ልዩ ጥቅም እንዲያገኙ በማድረግ ፣ ለህሊናቸው ሳይሆን ለጥቅማቸው እንዲዳኙ በውዴታ ለጥቅም ሟች በማድረግ ፣በአገሪቱ ህግ ላይ እንዳሻቸው እየፈነጩበት እንዳለ በአይናችን እያየን አይደለም እንዴ ?! ( የኢትዮጵያ መከላከያ ያላለውን ብሏል ብለው ዋሥትና በማሥፈራርቿ የሚያሥከለክሉ አይደሉም እንዴ ? የተከበረውን መከላከያ መነገጃ ሲያደርጉ ማን ጠየቃቸው ? ) እንዳሻቸው ፍርድን ሲያጣምሙ ። በነፍሰ ግድያ ያልተጠረጠረን ፣ ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር ያልተባበረን ፣ የሽብር ፀር የሆነን ጋዜጠኛ እንደ አሸባሪ እና እንደ ሚሥጥር ሰራተኛ ወይም ሰላይ ሲከሱ እያሥተዋልን አይደለም እንዴ ? በጋዜጠኛ ተመሥገን ደሣለኝ እና በጎምቱው ጋዜጠኛ በአቶ ታዲዎሥ ታንቱ ላይ ፣ ግፍ ና እንግልትን በደመ ቀዝቃዛነት እየፈፀሙ ያሉትሥ “ እኛ ፈላጭ ቆራጭ ነን ። ከህግም በላይ ነን ። “ የሚሉ አምባገነኖች አይደሉም እንዴ ?
ዐቃቤ ሕግ ጋዜጠኛ ተመስገን ” ወታደራዊ ምስጢሮችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ ሐሰተኛ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎችን በማውጣት፣ ለአመጽ ሕዝብን ማነሳሳት ። ” የሚሉ ክሶችን አቅርቦበታል ። ሲጀመር ተመሥገን ደሣለኝ ጋዜጠኛ አንጂ የመከላከያ አባል አይደለም ። የመከላከያ ዓባል አለመሆኑ እየታወቀ ለምን ይኽ ክሥ እንደቀረበበት በራሱ ግራ ያጋባል ። ቅጥረኛ ሰላይ ሆኖ በወታደራዊ አታሼነት ከውጪ አገር ካልተላከ በሥተቀር የአገሩን ወታደራዊ ምሥጢር ለመሠለል እንዴት ይተጋል ? ወይም ለማወቅ ከተጋ ምሥጢሩን በረብጣ ብር ይሸጣል እንጂ እንዴት በይፋ መፅሔት ላይ በማውጣት ለአገሩ ዜጎች በሙሉ ያሣውቃል ? ያም ሆነ ይኽ ፣ ተመሥገን ከቶም ወታደራዊ ምሥጢሮችን የሚያውቅበት መንገድ የለም ። በመፅሔቱ ያወጣቸው ወታደራዊ ጉዳዮችም ፣ የሠራዊቱን ህይወት የሚመለከቱ ፣ በሠራዊቱ ውሥጥ ያለው አንድነት እንዲጠናከር ቀድሞ ከነበረው የወያኔ ወታደራዊ አደረጃጀት ልንወጣ እና በሚሊተሪ ህግ ብቻ ልንመራ ይገባናል የሚሉ ናቸው ። መከላከያውን በብሐር ተዋፆ ሳይሆን በፍላጎታቸው በሚቀጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ልንገነባ ይገባናል ። ኮታ አያሥፈልገንም ። የለኮታ በወጣው የቅጥር መሥፈርት ሁሉም ወጣት በወታደራዊ አካዳሚ ውሥጥ በበቂ ሥልጠና አልፎ ለታላላቅ ማዕረግ መብቃት አለበት ። በጠንካራ ዲሲፕሊን የታነፀ መከላከያ ሠራዊት ሊኖረን ይገባል ። ዛሬ የሚሥተዋለው ግን በመርህ ላይ የተመሠረተ አሠራር አይደለም ። …
የተረኝነት አሠራር ነው ፤ በጉልህ በመከላከያ ከፍተኛ አመራር ውሥጥ የሚታየው ። እንደ ወያኔ ቁልፍ አመራሮችን ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪ የማድረግ ነገር ይታያል ። ይኸው መረጃ ። 123..። በፊደራል ፖሊሥም ሆነ በማረሚያ ቤት ውሥጥ ቁልፍ አመራሮችን ከአንድ ቋንቋ በማድረግ ተመሳሳይ ድርጊት ገዢው የብልፅግና ፓርቲ ፈፅሟል ። መረጃ 123 ። …
ለእውነት የቆመው ጋዜጠኛ ትላንት ወያኔ አሥሮኛል ። ብልፅግና ደግሞ ፀረ _ወያኔ በመሆኑ በጭፍን ላጨብጭብለት አላለም ። የብልፅግናንን ህፀፅ ለማሳየት በፍትህ መፅሔት ረጅም መንገድ ተጉዟል ። ሰው የሆኑትን ሹማምት ግብራቸውን ከሥማቸው ጋር አመሣክሮ ተችቷል ። ሂሰ አቅርቦባቸዋል ። ህዝቡ ከሚያውቀው እውነት ጨልፎ ላላወቀው ህዝብ አሣውቋል ። ይኽቺ አገር የጥቂት ግለሰቦች ሣትሆን የ115 ሚሊዮን ህዝብ እንደሆነች እንዲያውቁ አድርጓል ።
መንግሥት ይመጣል ። መንግሥት ይሄዳል ። አገዛዙ ወይም አሥተዳደሩ ፣ ደግም ይሁን ክፉ ፣ ማለፉ አይቀርም ። ሁሉም ኃላፊ ነው ። በሚያልፈው ህይወታቸው የማያልፍ አኩሪ ታሪክ የሚፅፉ የታደሉ ናቸው ።
ሞት አይቀርም ዛሬ በፖለቲከኞቻችን ድንቁርና አማራ ነኝ ። ትግሬ ነኝ ። ኦሮሞ ነኘ ። ወዘተ ። እያለ የሚገዳደለው ሰው እጅግ አሣዛኝ ነው። አሣፋሪም ነው ። ሰውነትንም የረሳ ነው ። ለጥቅም ባደሩ ፖለቲከኞች ህሊናው ታውኮ በጥድፊያ ለሞት ቢዳረግም ፣ ቢዘገይም ሞት አይቀርለትም ። ህይወት እንደሆነች ለማንም አጭር ሆና ሣለ ፤ በዚች አጭር ህይወት የኢትዮጵያ ሰው እንዳይደሰት፣ ህይወቱን በተቻለ መጠን አጣፍጦ ፣ ህይወትን አጣጥሞ እንዳያልፍ ፣ ዛሬ ወይ ነገ መሞታቸው የተረጋገጠ ፖለቲከኞች ፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በንቃተ ህሊናው እና በሆዱ አየታገዙ በአጭሩ ይቀጩታል። ይኽንን እውነት ተመሥገን ደሣለኝ በፍትህ መፅሔት በተለያየ ጊዜ ደጋግሞ ገልፆታል ።
ዛሬ ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም የተገለፀለት አንድ እውነት አለ ። ይኽም እውነት ሞት በህይወት ላለ ሰው ሁሉ በተራ መድረሱ ነው ። ኦሮሞ ሥለሆነ ፣ ትግሬ ሥለሆነ ፣አማራ ሥለሆነ ፤ ወይም ዶክተር ሥለሆነ ፤ ጠ/ሚ ሥለሆነ ፤ ፕሬዘዳንት ሥለሆነ ፤ ፓትርያርክ ሥለሆነ ወዘተ ። አይፈራውም ። ሞት ለማንም የማይቀር የሰው ሁሉ ዕጣ ፈንታ ነው ። ምት ሰው አይመርጥም ። ከገደለም በኋላ በብሔሩ አይጠራውም ። አማራ ሞተ ። ትግሬ ሞተ ። ኦሮሞ ሞተ ። ወዘተ። ሞተ አይልም ። ለሞት ሁሉም ሟች ፤ “ሬሣ ” ነው ። ሁሉም ሟች ” አሥከሬን ” ነው ። ነገ ሟች መሆኑን የዘነጋ ሰው ሁላ ለቀብር ተሰባስቦ ከሆሥፒታል ወይም ከቤተክርስቲያን የሚመጣውን አሥከሬን ” አሥከሬኑ አልመጣም እንዴ ? ” ብሎ ሲጠይቅ አልሰማህም እንዴ ? ከሞትክ የምትጠራው በአሥከሬን ነው ። ይኽም የወል ሥምህ ነው ። አዳሜ !! ከወዲሁ ይኽንን ተረዳ ። ከመሞትህ በፊትም ከመቃብር በላይ ለሚውለው ሥምህ ተጨነቅ ።