ሐምሌ 15 ቀን 2014ዓም(22-07-2022)
በክርስትና እምነት ለፍጥረታት ሁሉ ምንጭና ባለቤት የሆነው ፈጣሪ በሦስት በማይነጣጠሉ መለኮታዊ ባህርያት ማለትም በአብ በወልድና በመንፈስቅዱስ ወይም ሦስቱ ሥላሴዎች በተባሉት ማንነቶች ይገለጻል። ይህንን ተገን አድርገን ወደ ዓለማዊው ህይወት ማለትም ወደ ሰው ልጆች ኑሮና ሃገራዊ አመሠራረት ስንተረጉመው ለአንድ አገር ምሥረታ መንግሥት የተባለ አካል መኖሩ አስፈላጊ ስለሆነ ያንን መንግሥት ለማቋቋም የሚረዱ እንደሦስቱ ሥላሴዎች በስም ቢለያዩም በተግባር የተሳሰሩ ሕግ አውጭ፣ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ የተባሉ ምሰሶዎችን እናገኛለን።ሦስቱን ሥላሴዎች ለአገራዊ ምሥረታና ለመንግሥት መፈጠር ከሚረዱት ተቋማት ጋር ማመሳሰሌ በስም ቢለያዩም አንድ አካል አንድ አምሳል መሆናቸውን ለማሳዬት እንጂ የሃይማኖቱን ትንታኔ በምድራዊው የፖለቲካ ቦታ ላይ ለመደንቀር እንዳልሆነ አንባቢያን እንዲረዱልኝ በቅድሚያ እጠይቃለሁ።እነዚህ ሦስት ተቋማት በአንጻራዊነት ለመመዘን ፣የሚተጋገዙና ፤የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ለማሳዬት ስል በስላሴዎች አምሳያ ልስላቸው መምረጤን ተረዱልኝ እላለሁ። ማነጻጸሪያ የሌለው አካል ሊፈረድበት ወይም ሊፈረድለት ስለማይችል ለመጥፎም ሆነ ለመልካም ተግባር ሚዛንና ማነጻጸሪያ ሊኖረው ይገባል።የሰው ልጅ በአርአያ ስላሴ ተፈጠረ ስንል አገርም በአርአያ የፍትሕ ተቋም መፈጠሩን ማሰብና መቀበል ከብዙ ውዥንብር ያድነናል ፤ የችግር ምንጩ የትና ማን መሆኑንም ለማወቅ ይረዳናል ከሚል እምነት በመነሳት ነው።
ሦስቱ የፍትህ ተቋማት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለአገረ መንግሥት ግንባታና ህልውና ምሰሶዎች ናቸው። ካለእነዚህ ምሰሶዎች አገርና መንግሥት ሊቆም አይችልም።በአገር ደረጃ የሚከሰት ውድቀትም ሆነ እድገት የሚመነጨው ከነዚህ ሦስትም አንድም ከሆኑት ተቋማት ነው።
አንድ መንግሥት ወይም አገር መኖሩ የሚታወቀውና ስያሜውን የሚያገኘው ሕብረተሰቡ የሚተሣሰርበት ሕግና ደንብ ሲኖረው ነው።ያንንም ሕግና ደንብ የሚያወጣ፣የሚተረጉምና የሚያስከብር አካላት ሲኖረው ነው። በታሪክ አጋጣሚ አንድ አገር ሲመሠረት በመሥራቹ ሕዝብ መካከል እኩልነት እንዲሰፍንና አንድነት እንዲዳብር ሲባል ከሁሉም ነዋሪ በምርጫ የተውጣጣ አካል ወይም የሕዝብ ወኪሎች የሚመክሩበት መድረክ ይኖራል።ምንም እንኳን ጥራትና ችሎታው ከጊዜው ጋር እያደገ የሚሄድ ቢሆንም ጽንሰ ሃሳቡ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ሕዝብ የጋራ መብት ማስከበር ነው።በአገር ሽማግሌና በሕዝብ እንደራሴ መካከል የስም እና ድርጅታዊ መልክ ይለይ እንደሁ እንጂ በዓላማና ተግባር አንድ ናቸው።በዚህ የሕዝቡ ተወካዮች የሚሰበሰቡበት የዘመናችን ምክር ቤት የሚሰዬሙት አባላት ለሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮና መብት የሚያረጋግጡትን ደንቦችንና ሕጎችን ያወጣሉ፤ከእያንዳንዱም ዜጋ ላይ የሚጠበቅበትን ግዳጆች ያስቀምጣሉ።የአንድ አገር ሕዝብ ወይም ህብረተሰብ የተለያዩ ሃሳቦችንና ዓላማዎችን የሚያንጸባርቁ ሰዎች ጥምር ስለሆነ የሁሉም አይነት ሃሳቦች አስተናጋጆች ሊወከሉበት ግድ ይላል።የሕዝቡን ሰላምና መብት ያረጋግጣሉ ያሏቸውን ሃሳቦች በማቅረብ በውይይትና በክርክር አሸናፊ የሆነውና የብዙሃኑን ድጋፍ ያገኘው ሃሳብ ሕግ ሆኖ ይወጣል።የወጡት ሕጎችና ደንቦች እንዳይጣሱ የሚጠብቅ ሕግ አስከባሪ አካል ይቋቋማል፣ከሕግ አስከባሪው ጎን ለጎንም ሕግ አስፈጻሚ ይኖራል።በዚህ የአሠራር ሰንሰለትና የሥራ ድርሻ የሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ፣ወይም አገራዊ ተቋማት ካሉ ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን ብቻ ሳይሆን ለአገራዊ እድገትና ልዑላዊነት ዋስትናና ማረጋገጫዎች ናቸው።ካለነዚህ ተቋማት መንግሥትና አገር አይታሰብም።
በሕግ አውጭው ፓርላማ፣ በፍትሕ ተቋም፣በፍርድ ቤትና በፖሊስ የሥራ እርከን በሚመደቡት መካከል የሚኖረው ግንኙነት የተሳሰረና አንዱ ከሌላው ጋር የተስማማ ፣ግልጽነት ያለው አሠራር የሚከተል መሆን ይኖርበታል። እነዚህ ሦስት የፍትሕ ተቋማት ለመረጣቸው ሕዝብ የማገልገል ግዴታ አለባቸው።ከነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ ቢደክም ወይም ሸብረክ ቢልና ግዳጁን ባይወጣ ለሌሎቹ መዳከም ብሎም መውደቅ ምክንያት ይሆናል።የአንዱ መለከፍ ለሌላው ይተርፋል።ካለሦስቱ ጤነኛ ፣አብሮነትና ጥንካሬ መንግሥትም ሆነ አገር ጸንቶ አይቆምም፤እንደ እምቧይ ካብ ወይም ፒራሚድ ተደራርቦ ይወድቃል፣ይገረሰሳል።
ለተቋማቱ መድከምና መክሰም ዋና ምክንያቱ ከሕዝባዊ ቁጥጥር ተላቀው በነጠላ ቡድን ቁጥጥር ስር ከዋሉ ሲሆን፣ የሚጠበቅባቸውን አገራዊና ሕዝባዊ ግዳጅ ሊወጡ በማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲገኙ ነው።በተጠቀሱት ተቋማት ውስጥ የሚቆጣጠራቸው ቡድን በሚመድባቸው ሰዎች ይሞላና ህጉም ቢወጣ፣ቢተረጎምና ቢፈጸም ከሚቆጣጠረው ቡድን ፍላጎት ውጭ አይሆንም።በዚህ አይነቱ አሠራር የሚመሩ ተቋማት የዴሞክራሲ ጸርና የአምባገነኖች ስርዓት አገልጋይ ይሆናሉ እንጂ እውነተኛ የሕዝብ ምክርቤት፣ሕግ አውጭና ተርጓሚ ብሎም አስፈጻሚ አይሆኑም።በየሚያወጡት ሕግና ትርጉም የሚጠቀመው በጥቅምና በፍርሃት ተብትቦ የያዛቸው ቡድን ይሆናል።ይህ አይነቱ ፓርላማ፣ አቃቤሕግ፣ፍርድቤትና ፖሊስ የሕዝብ ፍላጎትና መብት የሚያስከብር ሳይሆን ለሕዝቡ መብት የሚከራከሩትን የሚያሳድዱበት፣ የሥልጣኑ ባለቤት ለሆኑት አምባ ገነኖች የቅጣት በትር ሆነው የሚያገለግሉበት ይሆናል። የዚህ አይነቱ በአሸዋ ላይ የተመሰረተ ተቋም የማታ ማታም ለእርስበርስ እልቂትና ለአገር መፈራረስ ምክንያት ይሆናል።
ከዚህ ስንነሳ የአገራችንን የፍትህ ተቋማት፣ከሕግ አውጭው ጀምሮ እስከአስፈጻሚው ድረስ ያሉትን ስንፈትሽ ላለፉት ዘመናት የሰፈነው የፍትህ አሠራር ከላይ ከገለጽነው ጸረ ፍትህ አሰራር የተለዬ አይደለም።በዘውዳዊው ስርዓትም ሆነ በወታደራዊው አምባገነን መንግሥት ከዚያም ወዲህ በሰፈነው የጎሰኞች ስርዓት ዘመን የሕዝብ ምክር ቤት፣የሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው አካል በስም እንጂ በተግባር ለተሻለ ሥርዓት ያላበቃ፣ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ያላገለገለ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።ተቋማቱን በሥልጣን ላይ ያለቡድን ወይም ግለሰብ የሚቆጣጠራቸው ስለነበሩና አሁንም ድረስ ስለሆኑ ሕግ አውጭና አስከባሪነታቸው ይቀርና ሕገወጥ ተግባሮችን በአንቀጽ አጽድቀው ተፈጻሚ ያደርጋሉ።ሕዝቡን ከመከራ ሊያወጡ ሲገባቸው ሕዝብ የአምባገነኖች ባሪያና አገልጋይ እንዲሆን ይሠራሉ።በአንቀጽ የተደገፈ ሕግ በሚል ሽፋን ጸረ ፍትሕ ፣ጸረ ሕዝብና ጸረ አንድነት የሆነ አሠራር የሚመነጨው በነዚህ አይነቶቹ ደካማ ሰዎች በሚሰገሰጉበትና በሚመሩት ተቋማት ምክንያት ነው።በተለይም ካለፉት 31 ዓመቶች ወዲህ በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የሚታዬው የተቋማቱ ጉዞ መንግሥት አለ ባይባልም አገር የመፈራረሱን ሂደት የሚያፋጥን ሆኗል።ጸረ ኢትዮጵያ በሆኑ ቡድኖች መዳፍ ሥር የዋለው ፣ የአገር ምሰሶ መሆን የሚገባው በፍትሕ ስም የሚጠራው ተቋም ለአገር አፋራሾች መሣሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።
በሕዝብ ምክርቤት የሚወጣው ሕግ ለሕዝብ ጥቅምና ለአገር ህልውና ብሎም ልዑላዊነት መሆን ሲገባው በተግባር የሚታዬው የዚያ ተጻራሪ ሆኗል።ምክር ቤት በተባለው በረት ውስጥ የተሰገሰጉት በቅድሚያ ለራሳቸው ጥቅም የሚፋተጉበት መድረክ እንጂ ለመረጣቸው ሕዝብ የሚታገሉ ቁም ነገረኞች የሚውሉበት የሰላማዊ ትግል ሜዳ አልሆነም።አብዛኛዎቹ የፓርላማ ተብዬውን መድረክ ስልጣን ላይ ያለውን ቡድንና መሪ በማሞገሱና ታማኝነታቸውን በመግለጽ እንጀራቸውን የሚጋግሩበት ምጣድ አድርገውታል። አልፎ አልፎ ስለሕዝቡ የሚናገሩ ቢኖሩ በጣም ጥቂቶች ናቸው።እነሱም ቢሆኑ በያዙት አቋም ላይ ጸንቶ ያለመቆዬት ችግር ይታይባቸዋል።በዛቻ ወይም በጥቅም ጭጭ እንዲሉ ይደረጋሉ። ይህ አይነቱ የአድርባዮች መሰባሰቢያ ቦታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመባል ብቃት የለውም።በዚያም ስም መጥራት ያሳፍራል።በዚህ አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ሕዝብና ኢትዮጵያ እውነተኛ ሕዝባዊ ምክር ቤት ኖሯቸው አያውቅም ማለት ከእውነት ጋር መጣላት አይሆንም ።
ሕግ አስከባሪውና አስፈጻሚው አካል እርስ በራሱ እዬተቃረነ ፍትሕን ትርጉመቢስ አድርጎታል።የፍትህ ተቋሙ የባለጊዜዎች ፍላጎት መወጫ፣የሥልጣንና የጉልበት ማሳያ ሆኗል።ይህ የሥርዓቱን መበስበስና አይወድቁ አወዳደቅ ማሳያ ነው።ሕግ ያልተከበረበት አገር ዕድሜው አጭር ነው።አገር ከማለትም የሽፍቶች ዋሻ ብሎ መጥራቱ ተገቢ ይሆናል። መንግሥት የተባለ በሕዝቡ ውሳኔና ምርጫ ሃላፊነት መቀበል ያለበት አካል በጠመንጃ አፈሙዝ የሚመጣ ከሆነ ሕዝባዊነትና ዴሞክራሲነት አይኖረውም። ላለፉት ብዙ ዓመታት በመንግሥትነት ስም ሥልጣኑን የያዙት በሙሉ በዚህ መንገድ የመጡ ናቸው።ከተማውም ጉልበተኞች ያሻቸውን የሚያደርጉበት ፣ከሆነ በከተማ ውስጥ የሰፈረ የጫካ ስርዓተአልበኛ ወይም ሽፍታ የሚቆጣጠረውና የሚምነሸነሽበት ባለቤት የሌለው ከባቢ እንጂ በስርዓተ መንግሥት የሚተዳደር አገር መናገሻ አይሆንም። የሕግ ተቋሙ በጠመንጃ የሚታዘዝ ከሆነ ፣የታጠቀ ያሻውን የሚያደርግበት፣የሚያስር የሚፈታ የሚገል የሚያፈናቅልበት ዕድል ከተፈጠረ ስርዓተመንግሥትና አገር ትርጉሙን ያጣል። ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታና ደረጃ ከዚህ የተለዬ አይደለም።
ባለፉት ዓመታት የተደረጉትን ትተን በቅርቡ በጋዜጠኞች በተለይም ተመስገን ደሳለኝ ላይ የታዬው የፍርድ ጥሰት የፍትሕ ተቋሙን አልባነት ያረጋገጠ ነው።የተመስገንን በዋስ የመፈታቱን ውሳኔ ተከትሎ የመከላከያ አዛዥ የሆነው የብርሃኑ ጁላ የማን አለብኝነት ዛቻና እብሪት ተግባር የዚህ ማረጋገጫ ነው።ፍርድ ቤት የፈታውን ፖሊስ አለቅም ሲል ከዛም አልፎ ተርፎ የሚለቀቀውን እገለዋለሁ የሚል የመከላከያ አዛዥ በይፋ ሲደነፋና ሲዝት፣የፍትሕ ቢሮው መደፈሩ ብቻ ሳይሆን የደፋሪውን ድንፋታ ሲያስተጋባ መስማቱ የፍትሕን አልባነት ያረጋግጣል።በሌሎቹም ጋዜጠኞች ላይ የደረሰው ሕገወጥ አያያዝ ተመሳሳይ ነው።ፍርድ ቤት ተብዬው የገነዘብ ዋስትና አስከፍሎ ፖሊስ በማንአለብኝነት ካለቀቃቸው የህሊና እስረኞች ውስጥ የ83ቱዓመቱ አዛውንት ጋዜጠኛ የሆኑት አቶ ታዲዎስ ታንቱ ይገኙበታል።ነገ ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል ባይታወቅም በቤተሰቦቻቸው ላይ ትልቅ ጭንቀትና ስጋትን አሳድሯል።ለበሽታም የተዳረጉ የተመስገን ደሳለኝ አዛውንት እናት መኖራቸውን የማህበራዊ ገጾች ባቀረቡት ማስረጃ ታይቷል።የልጅ ዕዳ ለወላጆች፣ወይም የወላጆች ዕዳ ለልጆች የሚተርፍበት አገር ምን አገር እንደሚባል ግራ ከማጋባቱ በላይ በዚህ መልኩ ፍትሕ የሚጣስበት አገር ደግሞ ቀጣይነቱ ያጠራጥራል።ፍትሕ ቢኖር እንደዚህ አይነቱን ደፋር የመከላከያ አዛዥ መግባት በማይኖርበት ውስጥ ጣልቃ እዬገባ ሕዝብና ዜጋ ሲያሸብር ማዕረጉን ገፎ በቀጣው ነበር።አገሩን ከውጭ ጠላት ያላዳነ የመከላከያ ተቋምና አዛዥ አገር ወዳዱን ተቃዋሚ በማሳደዱ ላይ ሲሰማራ ማዬት ኢትዮጵያ ያላት መከላከያ የሚባል ተቋም ሳይሆን በሕዝብና በአገር ሃብት የሚተዳደር አሸባሪ ሃይል መኖሩን ነው።መከላከያ ቢኖርማ ኖሮ ሱዳን ድንበር ተሻግራ በብዙ ኪሎሜትር መሬት ላይ ተስፋፍታ አትቀመጥም ነበር። በመከላከያ ስም ያለው የባለተረኞቹ ጎሰኛ ቡድኖች የሥልጣን ክብር ዘበኛ ለመሆኑ ከዚህ የበለጠ ማረጋገጫ አይኖርም።
ከዚህ አገራዊ ቀውስና የመፈራረስ አደጋ ብሎም ከእርስ በርስ እልቂት ለመውጣት ሕዝቡ በአንድነት ቆሞ ያለውን ሥርዓትና የሚጠቀምባቸውን ተቋማትና የሚመራበትን የጥፋት መመሪያ (ሕገመንግሥት) ማሶገድ ይኖርበታል።እስከአሁን ድረስ ካሳለፈውና ከሌሎቹ አገሮች ተመክሮ በመውሰድ በፍርሃትና በዝምታ እየሞተ ከመኖር በህይወት ለመኖር የሚችልበትን መንገድ መርጦ ሊከተል ይገባዋል።በእብሪት የሚደነፉትንና የአገሪቱን ሃብት የሚጫወቱበትን ጉልበተኞች ካላሶገደ ቀኑ በጨመረ ልክ ፣የሟቹ ቁጥር እዬጨመረ፣የአገር መፈራረሱ አደጋ ፍጥነቱና ደረጃው እያደገ ይሄዳል።
ለመጨረሻው ሰዓት የቀረው የጥቂት ደቂቃዎች ዕድሜ መሆኑን ተረድቶ ከጊዜውና ከስርዓቱ ጋር ግብግብ ገጥሞ ማሸነፍ ካልተቻለ ነገ በአንድ አገር ዜግነት ካስማ ላይ ቆሞ የመኖሩ ዕድል የመነመነ ይሆናል።ሁሉም አገረቢስ ሆኖ ይበተናል። የግፉ ሰለባ የሆነው ሕዝብ በዝምታው ከቀጠለበት ጠላቶቹ ባዘጋጁለት እርስ በርሱ እዬተባላ የሚጠፋበትን መንገድ እንደመረጠ ይቆጠራል።
ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይደርስም ነውና እምቢ ብሎ ድምጹን ካላሰማ የሚረዳው አያገኝም።ለህልውናው መቆም ከመረጠ ፣ ሁሉም በጋራ ለመታገል የድርሻውን ለማበርከት ከተነሳ የሌሎቹን እርዳታ ሊያገኝ ከመቻሉም በላይ ጠላቶቹን በቀላሉ ሊያሶግድ ይችላል።በጋራ ከተነሳ ዝም ብሎ ከሚገብረው የህይወት ዋጋ የበለጠ አይከፍልም።ያነሰ መስዋእትነት ከፍሎ የመብቱና የአገሩ ባለቤት ሊሆን ይችላል።በጊዜያዊ ጥቅምና ፍርሃት ተሸብቦ መቀመጥ ሞትን በጸጋ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ነው።ይህ ብሔራዊ ግዳጅ ለጥቂቶች ብቻ አሳልፈው የሚሰጡት አይደለም።እንደ ዜጋ ተከብሮ የአገር ባለቤት ሆኖ ለመኖር የሚሻ ሁሉ በአገር ማዳኑ ትግል ላይ መሳተፍ ይኖርበታል።አገር ማዳን ሲባልም ድንጋይና አፈሩን ሳይሆን እራሱንና ቀጣይ ትውልዱን ማዳን ማለት ነው።
በተለይም የሁሉም ደባና ሴራ የሚጎነጎንባት ከተማ፣የጎሰኞቹ መናኸሪያ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው የግፍና መከራው ገፈት ቀማሽ የሆነው ሕዝብ የሥርዓቱን መሠረት በማንኮታኮቱ በኩል ትልቅ ሚና ይኖረዋል፤ስለሆነም ከፍርሃትና ከተስፈኝነት ድባብ ወጥቶ ለመብቱ ከሚታገሉለት ጥቂት ደፋሮች ጎን ተሰልፎ እራሱንና አገሩን በማዳን የታሪክ ድርሻውን መወጣት ያለበት ጊዜው አሁን ነው።የአዲስ አበባን ሕዝብ ተከትሎ ሌላው ለመነሳት ጊዜ አይወስድበትም።ስለሆነም ግንባር ቀደሙን ሕዝባዊ ትግል የመምራት ሃላፊነቱ በአዲስ አበባ ሕዝብ ጫንቃ ላይ አርፏል። የአዲስ አበባ ሕዝብ ሆይ ይህንን ታሪካዊ ግዳጅህን ነገ ዛሬ ሳትል ተወጣ!
አማራውን ለተለያዩ ጥቃቶች፣ለጭፍጨፋና መፈናቀል ያጋለጠው ምክንያት ቢኖር ለጎሰኞች ባለመመቸቱና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር በመሆኑ ነው። አማራው ካለ የአገር አጥፊዎቹ ዓላማ ሊተገበር ባለመቻሉ ነው።እንደ አማራው አገርህን ኢትዮጵያን የምትወድ የሌላው ማህበረሰብ ተወላጅ ጨርቄን ማቄን ሳትል፣በጎሰኞቹ ትርክት ሳትታለልና ሳትዘናጋ ከአማራው ወገንህ ጎን ተሰልፈህ የጋራ አገርህን ህልውና አስከብር።ከጸረ ኢትዮጵያ ከሆኑት የውጭና የውስጥ ቡድኖች ጋር ተፋልመህ ታሪካው አደራህን ተወጣ።ለተተኪው ትውልድህ የተመቸች አገር አስረክብ።አንድነትህን በተለያዩ ዘዴዎች ሊበጥሱ ሲሞክሩ እምቢ በል።በደካማ ጎንህ ሲገቡ አሻፈረኝ በል።ለጊዜያዊ ችግር ብለህ እጅህን አትስጥ።ሰይጣናዊ ተግባር በሚሰሩት ሃይማኖት አትጠመቅ።በራስህ እምነትና በፈጣሪህ ተመካ።በስምህ የሥርዓቱ አካል በሆኑትና በሚጠቀሙት ላይ ተነሳ።ከጫንቃህ ላይ አውርደህ ጣላቸው።
ፍትሕ ይንገሥ ፤ሁሉም ለጋራ መብቱ ይነሳ!
ጸረ ፍትሕ፣ጸረ አንድነትና ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ ጎሰኞች ከነስርዓታቸውና አስተሳሰባቸው ይወገዱ!!
ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም!!!
አገሬ አዲስ