በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪገን ኢዩጂን እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በታምራት ቶላ አማካኝነት አግኝታለች ።
አመሻሹን በተደረገው የወንዶች ማራቶን ውድድር ባለ ድል የሆነው ታምራት ከበርሊኑ ቻምፒዮንሺፕ ወዲህ በኬንያዊው አቤል ኪሩይ ለ13 ዓመታት ያህል ተይዞ የቆየውን የርቀቱን የቻምፒዮንሺፕ ክብረወሰን አሻሽሏል።
ውድድሩ ሊጠናቀቅ 10 ኪሎሜትሮች ገደማ ሲቀረው ጀምሮ ከተፎካካሪዎች ተነጥሎ ወደፊት የገሰገሰው ታምራት ቶላ ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ በድል አጠናቋል።ይህ ሰዓት አቤል ኪሩይ ከገባበት ሰዓት ከ ደቂቃ በላይ የፈጠነ ነው።አቤል በቲዊተር ገጹ በኩል ” ከ13 ዓመታት በኃላ ክብረወሰኔ በዛሬው ዕለት ተሰብሯል !” በማለት ለታምራት የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክቱን አስተላልፏል ።ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሞስነት ገረመው በአንድ ደቂቃ ከስምንት ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። ቤልጂየምን የወከለው ትውልደ-ሶማሊያዊው በሺር አብዲ በበኩሉ 2 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በሆነ ሰዓት 42 ኪሎ ሜትር ማካለል የሚጠይቀውን ውድድር በማጠናቀቅ የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኗኑን አረጋግጧል።
ከዛሬው የወንዶች ማራቶን ድል በፊት ፣ በትናንትናው ዕለት በተደረገው የሴቶች 10ሺ ሜትሮች ውድድር በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እልህ አስጨራሽ ፉክክር ያደረገችው ለተሰንበት ግደይ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስመዝግባለች ።
VOA