የሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ሌሊቱ ነግቷል፡፡ ኮሎኔል ወደ ቅርብ ሰዎቹ የድረሱልኝ ስልክ መደወል ጀምሯል፡፡ኮሎኔል እንዳጫወተኝ፣ ጠዋት ከ3-4 ሰዓት ሲሆን ሰሮቃ ለሚገኘው ጓደኛው ለመቶ አለቃ ደጀኔ ማሩ፣ “ታፍኛለሁና ከቻልክ ድረስልኝ” ይለዋል፡፡ ደጀኔም ወሬ ሳያበዛ፣ “ስንት ጥይት አለህ?” ሲል ኮሎኔልን ይጠይቀዋል፡፡ ኮሎኔልም፣ “30 ጥይት አለኝ” ይለዋል፡፡
“በል ለመድረስ እሞክራለሁ፤ ከመድረሴ በፊት አንድ የሆነ ነገር ከተፈጠረ ግን እጅህን እንዳትሰጥ! ለሁሉም አንዲት ጥይት አውጥተህ ከጠረጴዛህ ላይ አስቀምጥ፤ ቁርጥ ከሆነ በመጨረሻ በዝች ጥይት ራስህን አጥፋ” ይለዋል፡፡ በዚህ የደጀኔ ምክር የተበረታታው ኮሎኔል ደመቀ፣ “ችግር የለም፡፡ ሽጉጥም አለኝ … የእኔን፣ ያንተን ወንድም እጅ ማንም ወንበዴ አይዛትም! እንደ አጼ ቴዎድሮስ ጥይቴን ጠጥቼ ነው የምሞት!” በማለት መለሰለት፡፡
ደጀኔ እንደነገረኝ፣ ከኮሎኔል የተደወለ ስልክ ሲያይ፣ የሆነ ነገር ተሰምቶታል፤ የፈራው አልቀረም፤ ድረስልኝ የሚል ድምጽ ነበር፡፡ደጀኔም ጣጣ ሳያበዛ፣ ሰሮቃ ላይ ወደ 13 ያህል የታጠቀ ኃይሉን ይዞ ከቀኑ 5 ሰዓት ሲሆን፣ ጉዞ ወደ ጎንደር አደረገ፡፡ እግረ መንገዱን ለሕዝቡ እየተናገረ ስላለፈ ተከታዩ ቁጥር፣ ወደ 40 ደረሰ፡፡ ይህ ኃይል ጎንደር ከተማ ብልኮ አካባቢ ከመኪና ከወረደ በኋላ፣ በፍጥነት በእግሩ ቀሀ ወንዝን ተከትሎ ወደ ኮሎኔሉ ቤት አመራ፡፡ አሁን ጊዜው ወደ 12 ሰዓት እየተጠጋ ነው፡፡
ለዐይን ወደ መያዝ እያመራ ነው፡፡ ደጀኔና ጦሩ ከኮሎኔል ቤት ሲደርሱ፣ አካባቢው በሠራዊት ተወረርዋል፡፡ መደበኛ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል ሁሉም ተፋጠዋል፡፡ሠራዊቱ ኮሎኔሉን አምጡ ብሎ አስቸግሯል፤ ኮሎኔል ደመቀ ደግሞ፣ “እሞታለሁ እንጂ፣ ለፌደራል ኃይል እጄን አልሰጥም!” የሚል አቋም ወስዷል፡፡
“እጄን የምሰጠው ለፌደራል አሳልፈው የማይሰጡኝ ከሆነ፣ ለክልሉ ልዩ ኃይልና ለጎንደር ከተማ አስተዳደር ብቻ ነው!” ብሏል፡፡ ጊዜ እየሄደ ነው፣ ሀገር ተጨንቋል፡፡ በዚህ መካከል ነበር ደጀኔና ጦሩ የኮሎኔልን ቤት ከቦ አስቸግሮ በነበረው የፌደራል ፖሊስ ላይ የቶክስ እሩምታ የከፈቱበት፡፡
ይህ በደጀኔ ጦር የተከፈተው ማጥቃት ከባድ ስለነበር፣ የመንግሥት የጸጥታ አካለት ጉዳዩን መቋቋም አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ደጀኔና ጦሩ የሚገድለውን ገሎ፣ የሚማረከውን ማርኮ፣ የኮሎኔልን ቤትና አካባቢውን ተቆጣጠረው፡፡ከዚህ በኋላ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲቋጭ ስምነት ተደረሰ፡፡ በዚህም መሠረት ደጀኔ ማሩና ኮማንደር ዋኛው (የልዩ ኃይል አመራር) የተወሰኑ ሽማግሌዎችን (በሪ፣ ዘለቀ አሰማራው … )
በማስከተል፣ ለ2 ቀናት ያህል ከሙሉ ቤተሰቡ ጋር ቤቱን ዘግቶ ሲፋለም ወደ ነበረው ኮሎኔል ደመቀ ቤት፣ “እኛ ሽማግሌዎች ነን! እኔ ደጀኔ ነኝ” እያሉ ድምጻቸውን እያሰሙ ወደ ኮሎኔል ቤት ተጠጉ፡፡ ኮሎኔልም ጦርነቱ እንዲያ ሲበረታ፣ እነ ደጀኔ መጥተው እንደሚሆን ጠርጥሮ ነበርና እኔ “ደጀኔ ነኝ!” እያለ ሲጠጋው አመነ፡፡ ቤቱንም ከፈተላቸው፡፡
ደጀኔና ኮሎኔል ተገናኙ- ሁለቱም የደስታ እንባ አነቡ፡፡ ሽማግሌዎቹና እነ ደጀኔ በፍጥነት በል ተነስ ብለው እጁን ይዘው ከዛች መከረኛ ቤት ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ አወጡት፡፡ሽማግሌዎቹና ደጀኔ፣ የከተማው አስተዳደርና የክልሉ መንግሥት በደረሱበት ስምምነት፣ ኮሎኔል ለፌደራል ተላልፎ አይሠጥም፡፡ ነገር ግን ሕግ አለና ኮሎኔል በክልሉ መንግሥት ኃላፊነት መሠረት፣ በዞኑ ፖሊስ መምሪያ እንዲቆይ ተደረገ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሽማግሌዎቹ፣ ደጀኔና ጦሩ የክልሉን መንግሥት እስጠንቅቀዋል፡፡ ኮሎኔልን ለፌደራል መንግሥት አሳልፋችሁ ከሰጣችሁ ጠባችን ከናንተ ጋር ነው ብለዋል፡፡
ኮሎኔልን ለመንግሥት በአደራ ካስረከበና ሌሎቹን ጣጣዎቹን ከጨረሰ በኋላ፣ ጎንደር ተቀምጦ የኮሎኔልን መጨረሻ ለማየት የሚያስችለው ሁኔታ አልነበረምና ይዞት የመጣውን ጦር ይዞ ወደ ሰሮቃ ተመለሰ፣ ሰሮቃ ሁኖ ነገሮችን መከታተል ጀመረ፡፡ የክልል መንግሥትም ቃሉን መጠበቅ ቻለ፡፡በዚህ ግጭት መንግሥት ባመነው መሠረት፣ 19 ያህል “የጸጥታ አካላት” ተገድለዋል፡፡
በወቅቱ በግጭቱ ከተሳተፉ አካለት እንደተነገረኝ ከሆነ ደግሞ፣ “ከህወሓት-ኢህአዴግ ታጣቂዎች” በኩል የሞተው ሰው ቁጥር ወደ 40 ከፍ የሚል ይመስላል፡፡ ከስቪሉ ሕዝብ ደግሞ 4 ያህል ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ግጭት ወቅት፣ በሁለቱም ወገን የተማረኩ አካላት ነበሩ፡፡
በመሆኑም የግጭቱን መብረድ ተከትሎ፣ የምርኮኛ ልውውጥ እንዲደረግ ስምምነት ተደረሰ፡፡በዚህም መሠረት፣ “በቅድሚያ፣ በጃችን ያለውን ምርኮኛ ቁጥር እናሳውቅ” ተባለ፡፡ ክንደ ነበልባሉ ደጀኔ ማሩ፣ “ቁጥር አላሳውቅም!በናንተ እጅ ያለን የስቪል ምርኮኛ ስታስረክቡኝ እኔም በጄ ያለውን አስረክባለሁ፤ ቁጥር ግን አልናገርም…” ብሎ እምቢ አለ፡፡ የመንግሥት አካላትም ዐማራጭ አልነበራቸውምና 11 ያህል ምርኮኞችን ለደጀኔ ለማስረከብ ይዘው ቀረቡ፡፡ ደጀኔም ከነሙሉ ትጥቃቸው ካልሆነ፣ በጀሊያቸው አልረከብም አለ፡፡ አሁንም አማረጭ ያልነበረው መንግሥት፣ የ11 ሰዎችን ሙሉ ትጥቅ አብሮ አስረከበ፡፡
አሁን ደጀኔ ማሩ የእርሱ ተራ ደርሷልና የማረከውን ምርኮ ለመንግሥት ማስረከብ ነበረበት፡፡የመንግሥት አካላት በርከት ያሉ ምርኮኞችን ይጠብቃሉ፡፡ ደጀኔ ግን፣ “አንድ ምርኮኛ ብቻ ነው ያለኝ …” በማለት፣ ቆስሎ ስለነበር ሲያሳክመው የሰነበተውን አንድ የፌደራል ፖሊስ ብቻ አሰረከበ፡፡ ያኔ በመንግሥት አካለት ዘንድ መደናገጥ ተፈጠረ፤ “ጨረስከን አይደል!?” በማለት ስሜታቸውን ገለጹ፡፡ ደጀኔ ደግሞ፣ “… እንግዲህ የማረኩት ይህን ብቻ ነው!” በማለት መለሰላቸው፡፡
በኮሎኔሉ ተጋድሎ የተደሰተው የጎንደር ሕዝብ፣ ደስታውን ለመግለጽና ኮሎኔሉን ለማየት ወደ ፖሊስ መምሪያ መጉረፍ ጀመረ፤ ፖሊስ ይህን ሕዝብ ለማስተናገድ ተቸገረ፡፡ በመሆኑም ለደኅንነቱም ሲባል ጭምር፣ ኮሎኔል አንገረብ ወንዝ ዳር ወደሚገኘው ጎንደር ወህኒ ቤት እንዲዛወር ተረደገ፡፡ ይሁን እንጂ፣ አሁንም ሕዝቡ በሌሊት አፍነው ሊወስዱት ይችሉ ይሆናል በማለት፣ ውሎና አዳሩን ከኮሎኔሉ ጋር፣ በወህኒ ቤቱ ዙሪያ አደረገ፡፡
በርግጥ መንግሥት ኮሎኔል ወህኒ ቤት ከወረደም በኋላ፣ ተላልፎ እንዲሰጠው፣ የክልሉን መንግሥት በተደጋገሚ ከመጠየቁም በላይ፣ ወህኒ ቤት ውስጥ እንዳለ አፍኖ ለመውሰድ ጭምር በርካታ ሙከራዎችን እንዳደረገ ይታወቃል፡፡ ብቻ ወቅቱ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፤ በተለይም ኮሎኔሉ ወደ ችሎት በቀረበ ቁጥር ሁሌ ውጥረት ሆነ፡፡ ይህን ሁሉ ከከወነ በኋላ ነበር ደጀኔ፣ ኮሎኔልን ለመንግሥት በአደራ አስረክቦ ወደ ቤቱ የተመለሰው፡፡
ምንጭ፦
ቹቹ አለባቸው “ዳገት ያበረታው የአማራው ፍኖት” መጽሐፍ ደራሲ እንደጻፈው!
https://youtu.be/6UAsz50iGw8