July 9, 2022
14 mins read

አማራን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው! አማራን መጨፍጨፍ ይቁም! – በጀርመን ኑረንበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን

290684552 3309915649279615 7045677791337159006 n

በጀርመን ኑረንበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቅዳሜ በ09.07.2022 ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ያስተላለፋት መልዕክት!

መግቢያ : –

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ፓለቲካዊ ቀውስ ፣ አማራ ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዋነኛ ምንጩ ህገመንግስቱ ሲሆን ጥቃቱም መዋቅራዊ እንደሆነ ግልጽ ነው። ብሔርን መሰረት ያደረገው የክልል አወቃቀር እና የግለሰብን መብት የደፈጠጠው ህገመንግስት መሰረታዊ የቀውስ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። ከ 4አመት በፊት የተተካው መንግስትም ይህን መሰረታዊ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ሲጠበቅ : በተቃራኒው ኮትኩቶ በማሳደግ አሁን ላለንበት የከፋ ችግር ዳርጎናል።

በተረኝነት አመለካከት የተለከፈው ኦዴፓ መራሹ የብልፅግና መንግስት ጠባብ አመለካከት ካላቸው ሃይሎች ጋር በመናበብ እና በጋራ በመስራት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ይገኛል። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረት የሆኑ አካላት፣ ተቋማት ፣ እሳቤዋች እና እሴቶቻችን እየተመረጡ የጥቃት ሰለባ መሆናቸው ነው። አማራን ማፅዳትና መጨፍጨፍ፣ ኦርቶዶክሳዊያንን ማሳደድ እና መግደል ፣ ቤተ ክርስቲያናትን ማቃጠልና ይዞታን መቀማት ፣ ቤተ ክህነትን እንዲሁም መጅሊሱን መክፈል አንድነቱን መሸርሸር ፣ ብሓራዊ በዓሎቻችንን እና በሀላዊ እሴቶቻችንን ማጣጣል እና ታሪክን ማዛባት እና አዲስ የሀሰት ትርክት መፍጠር ፤ መዳረሻው ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ጠላቶቻችን በታሪካችን ባላየነው መልኩ እኩይ አላማ ይዘው ፣ የመንግስትን መዋቅር ተቆጣጥረው እና ጭካኔን መሳሪያ አድርገው ሀገራችንን ለማፍረስ ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ።

የአማራ ህዝብ በዚህ ኢትዮጵያን የመናድ ፕሮጀክት ዋነኛው ሰለባ እና ተጠቂ ሆኗል። ይህ መንግስት ኦርቶዶክስን እና አማራን አከርካሪውን መስበር የሚለውን የወያኔን ዓላማ በማስቀጠል ያባቱ ልጅ መሆኑን አስመስክሯል። የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያን በማለቱ ብቻ እየተገፋ እና ያለማቋረጥ እየተገደለ ይገኛል። ባለው ሀገራዊ ስሜት ምክንያት እንደሌሎች በብሔር ተደራጅቶ እራሱን ሊጠብቅ ባለመቻሉ : ህገመንግስቱ ለሕብረ ብሔራዊ አደረጃጀቶች እንቅፋት በመሆኑ የሚጠብቀው እና የሚከላከለው በማጣቱ ግፍ በዝቶበታል : መከራውን ፀንቶበታል። ለምን አማራ እና ኦርቶዶክሳዊያን ላይ መከራው በዛ? መልሱ ግልጽ ነው : ኢትዮጵያን በማለታቸው ለአንድነት በመስራታቸው እና ለጠባቦች ባለመመቸታቸው!!!

የሰኔ 11 ,2014,ዓ፣.ም June 18 2022 ዓ.ም የንፁሃን አማራዋች ጭፍጨፋ በወለጋ

በሰኔ 11ዱ የዘር ማጥፋት ወንጀል በርካታ አማራዎች በማንነታቸው ተለይተው በመንግስት በታገዙ በታጠቁና በተደራጁ የኦነግ ሰራዊት በግፍ ተጨፍጭፈዋል። አሀዙን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም የአማራ ማህበር በአሜሪካ : የአይን እማኞችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ባጠናቀረው መረጃ : የተሰወሩትን እና የቆሰሉትን ሳይጨምር በትንሹ 554 ንፁሃን አማራዎች መገደላቸውን በተጨባጭ መረጃ አረጋግጧል። 455 የሚደርሱትንም ስማቸውን ዘርዝሮ አስቀምጧል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በምዕራብ ወለጋ : በጊምቢ ወረዳ : ቶሌ ቀበሌ በሚገኙ 10 መንደሮች ነው። የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት አብዛኞቹ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እና ተጋላጭ የሆኑ : ሴቶች፣ ህፃናት እና አረጋውያን ናቸው። በዕድሜ ስናየው ትንሹ ኑረዲን የሚባለው የ 15 ዓመት ጨቅላ ሲሆን : ትልቁ ደግሞ 100 ዓመት የሞላቸው አረጋዊ ናቸው። የጥቃቱ ሰለባዋች ሁሉም አማራዋች ናቸው : ለዚህ ነው ድርጊቱን በስሙ ጠርተን አማራን መጨፍጨፍ ይቁም የምንለው። ጭፍጨፋው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 2:30 – 9:30 ለ ሰባት ሰአታት ሳይቋረጥ የቀጠለ ነበር። በአንዳንድ መንደሮች እስከ ቀኑ 11 ሰአት ቀጥሎ ነበር።

አውሬዎቹ ይህን አሰቃቂ ጥቃት የፈፀሙት በአውቶማቲክ መሳሪያ፣ በስለት እንዲሁም በማቃጠል ነው። ዝርዝሩን ለመናገርም ለመስማትም ለሰው ልጅ ስለሚከብድ አፈፃፀሙን እንደው : ፋሺስታዊ ከዛም የከፋ ብሎ መግለፅ ይሻላል። ንፁሃኑ ከተጨፈጨፋ በኃላ በተገደሉበት ቦታ በጅምላ እንዲቀርብ ተደርገዋል። ድርጊቱ ከአይምሮ በላይ ነው : ምናልባት እራሳችንን በተጠቂዎቹ ጫማ ውስጥ ከተን ማየት ከቻልን : ምን ያህል ዘግናኝ መሆኑን በጥቂቱም ቢሆን እንረዳው ይሆናል።

ጥቃቱን ማን ፈፀመው?

ጥቃቱ የተፈፀመው በተደራጀ እና በተናበበ መልኩ በአካባቢው ባለስልጣናት እና አንዳንድ ነዋሪዎች በታገዙ የኦነግ ሰራዊት አባላት ነው። ዛፍ ላይ በመውጣት እና በመደበቅ ህይወቱን የታደገው ታዳጊ እንደተናገረው ድርጊትን የፈፀመው የኦነግ ሰራዊት ውስጥ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሞ ልዩ ሀይል ዩኒፎርም የለበሱ ይገኙበታል። አብዛኛውም የወታደር ጫማ እንዲሁም የፓሊስ ሀይል የሚጠቅመውን ጫማ የተጫሙ እና ዘመናዊ መሳሪያዋች ( መትረየስ፣ ስናይፐር፣ ሞርታል እና አውቶማቲክ መሳሪያዎች) የታጠቁ ናቸው።

 

የመንግስት ቸልተኝነት እና ተባባሪነት:-

ጥቃቱ መንግስት መር (state sponsored) ነው የምንለው ያለምክንያት አይደለም። ማረጋገጫዎች ስላሉ ነው። ጥቃቱ ከመፈፀሙ ጥቂት ቀናት በፊት በአካባቢው የነበሩ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ቦታውን ለቀው እንዲሄዱ በማድረግ : ጥቃቱ እንዲፈፀም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም የተደረገው የጊምቢ ወረዳ አስተዳደር ከኦነግ ሰራዊት የደረሰውን መረጃ ተከትሎ እንደሆነ እማኞች ተናግረዋል። ሌላው በጥቃቱ ቀን የፌደራር መንግስት የሚቆጣጠረው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በአካባቢው እንዲቋረጥ ተደርጎል። በተጨማሪም የመከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሞ ልዩ ሀይል ጭፍጨፋው በሚከናወንበት ግዜ ወደ አካባቢው እንዳይደርሱ ተደርጎ : ድርጊቱ ከተፈፀመ በኃላ ቦታው ላይ በመድረስ የተረፋ ሰዎች ፎቶ እንዳያነሱ ቪዲዮ እንዳይቀርፁ ሲያስፈራሩ እና ሲከላከሉ ነበር። በተጨማሪ ከሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ውጪ : መንግስት ብሔራዊ ሀዘን ለማወጅ፣ ድርጊቱን ለማውገዝ እና ለማስቆም ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ አረጋግጦልናል።

ማጠቃለያ

የመንግስት ዋነኛው ሃላፊነት የዜጎችን መብት ህይወት እና ንብረት ማስጠብቅ : ህግና ፍትህን ማስፈን ሆኖ ሳለ : የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት : በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ኢሰብአዊ ጭፍጨፋ እና ህገወጥ ድርጊት ማስቆም አልቻሉም። ፍላጎትም አላሳዩም። ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስተሩ እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ከስልጣን እንዲወርዱ እና ተጠያቂ እንዲሆኑ ሁላችንም በግል እና በህብረት ግፊት ማድረግ ይኖርብናል። መንግስት ዜጎችን መታደግ ባለመቻሉ : በወለጋ እና በሌሎች ጥቃት ባለባቸው አካባቢዎች የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲገባ መጠየቅ ይኖርብናል። በተጨማሪም ይህን የዘር ጭፍጨፋ የሚመረምር ነፃ እና ገለልተኛ የሆነ አለም አቀፍ ተቋም እንዲገባ ግፊት ማድረግ ይኖርብናል።

በተረፈ እኛ በዚህ የተሰበስበብ እያንዳንዳችን ነፃ ፍቃድ አለን ፤ ከገዳይ ጋር በተባባሪነት ወይም ከተገዳይ ጋር በሀቀኝነት ልንቆም አልያም እሳቱ እቤታችን እስኪገባ በቸልታ ልናልፈው እንችል ይሆናል። ነገር ግን ሁሉም ውጤት አለው : የዛሬ ውሳኔአችን : የነገ ኑሮአችን/ማንነታችን ነው። “ ሀጥኡን እንደ ሊባኖስ ዝግባ ከፍ ከፍ ብሎ አየውት : ስመለስ ግን አጣውት” እውነት ነው ገዳዮች ዛሬ ከፍ ከፍ ብለዋል : ሀይል አግኝተዋል ፤ ነገር ግን በቅርቡ ይጠፋሉ። ሰልፋችን ከሚጠፋት እና ከግፈኞች ጋር እንዳይሆን እንጠንቀቅ ፤ ግፍንም ለማውገዝ አንሸማቀቅ።

ዲያስፓራው ምን ያድርግ?

አስቀድመን ልንነቃ እና የችግሩን ስፋት ከመሰረቱ ልንረዳው ይገባል። ጭፍጨፋውን ለማስቆም ሀቁን በመቀበል እና እውነቱን በመጋፈጥ : ወንጀሉን በስሙ በማውገዝ “ የአማራ ጭፍጨፋ” Amhara Genocide እንዲቆም በግል እና በማህበር ልንታገል ይገባል።

ፍትህን ማስፈን፣ አማራን ማዳን ኦርቶዶክሳዊያንን ማዳን : እና የኢትዮጵያዊነት ሙጫ/ማጣበቂያ የሆኑ ሌሎች አካላትን እና ተቋሞቻችንን ማዳን : ኡትዮጵያን ማዳን እንደሆነ ተረድተን : መንቃት፣ መደራጀት እና መታገል አለብን። ለድምጽ አልባ ወገኖቻችን በግል እና በህብረት ድምጽ በመሆን ግፈኞችን እንቃወም : እናጋልጥ : ለፍትህ መስፈን ያቅማችንን ሁሉ እናድርግ ፣ የሚሰሩትን እንደግፍ እንጂ እንቅፋት አንሁንባቸው።

 

አማራን ማዳን : ኢትዮጵያን ማዳን ነው!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

 

July 09, 2022

Nuremberg, Germany

Solomon Getu

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

blood sucker Abiy
Previous Story

አራምባና ቆቦ…..ሰውየው ምን ያህል ጮርቃ እንደሆነ ያሳያል

Daniel
Next Story

የቀጥታ ስርጭት:- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት (የመጨረሻ ክፍል)

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop