ሰዎች አንዳንዴ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ እና ፖለቲከኞች ማሽን ይመስሏቸዋል። ሰዎች ወደ አደባባይ ትግል የሚገቡት ብዙ ጊዜ ወደው እና መርጠውት አይደለም፤ የሕሊና ዕዳ ሆኖባቸው ነው። የአፈ እንግሊዞች “ignorance is bliss” (‘አለማወቅ መታደል ነው’ እንደማለት) እውነትነት አለው። በተለይም በኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካ ውስጥ እያወቁ ዝም ሲሉ ቁጭቱ፣ ሲናገሩ መፋጀቱ በሁለት አቅጣጫ ስለት ያለው ቢላዋ እንደመጠቀም ነው።
ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች እና ተሟጋቾች የገዛ ንቃታቸው ሰለባ ናቸው። ለሩቅ ተመልካች ግን ቀላል የሕይወት ምርጫ ይመስላል። ይሁን እንጂ እንደሰው ዘለፋው፣ የሥም ማጉደፍ ዘመቻው፣ እስሩ እና እንግልቱ፣ እጦቱ፣ የቤተሰብ እንክርቱ ሕሊናቸውን እንደ ብዙኃኑ የሚጎዳቸው፣ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚያምራቸው፣ ቤተሰብ መሥርቶ፣ ሀብት ንብረት አፍርቶ መኖር የሚያጓጓቸው ሁለገብ ሰው ናቸው። እንደ ብዙኃኑ የመጣውን አሜን፣ የሔደውን go-hell ብለው ብቻ መቀመጥ የማይሆንላቸው። “ለምን?” ብለው የሚጠይቁ ጥቂቶች በዚህም በዚያም ወገን አሉ። ከነዚያ ጥቂቶች አንዱ ተመስገን ደሳለኝ ነው። ተመስገንን እንደ አደባባይ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ወዳጅም በቅርብ አውቀዋለሁና በዘወትር አጠራሬ ተሜ እያልኩ መጻፌን እቀጥላለሁ።
ተሜ አራት ኪሎ ተወልዶ አድጎ፣ እስከዛሬም አራት ኪሎን ሳይረግጥ ማደር የማይሆንለት፣ የአራት ኪሎ ተቀማጮችን በሐሳብ አለንጋው የሚሸነቁጥ የአደባባይ ሰው ነው። ብዙ ጊዜ ቁርስ የሚበላው አራት ኪሎ አትክልት ቤት ነው። በአራት ኪሎ ያለፈ ያገደመ ሁሉ ተሜን ሳያየው አይቀርም።
ከውጭ ሲያዩት የፖለቲካ ማሽን የሚመስለው ተሜ፣ በቀረቡት ቁጥር ጫወታ አድማቂ እና የልብ ወዳጅ መሆኑን ማስተዋል አይሳነውም። ቀልዱ አይጠገብም። በዚያ ላይ አላፊ አግዳሚው ሁሉ ሰላምተኛው እና ወዳጁ ነው። አንዳንዴ አብሬው ቁርስ እበላለሁ። ቁርስ በልተን ወደ ፒያሳ ወክ የምናደርግባቸው ጊዜያትም አሉ። ታዲያ የሰላምተኛው ብዛት በየመንገዱ ያዘገየናል። በዚህ ጊዜ “ከንቲባው” እለዋለሁ።
ተሜ በአገራችን የታተሙ የፖለቲካ እና የታሪክ መጽሐፎች በሙሉ እያነፈነፈ ያነባቸዋል፤ ከሚያነቡ ጥቂት ጋዜጠኞች ውስጥ የሚመደበው ለዚህ ነው።
ከመጽሐፍት ቀጥሎ ቤቱን የሞሉት የነገሥታቱ ምሥሎች ናቸው፤ በአንድ በኩል ቤተ መጽሐፍት፣ በሌላ በኩል ሙዚየም ይመስላል። ቤቱ መሐል ላይ የተገሸረችው ጠረንጴዛው የተዝረከረኩ ወረቀቶች፣ የተከፈቱ መጽሐፍቶች እና ብርጭቆ አይጠፋትም። የቢሮው ጠረጴዛም እንደዛው የወረቀት ተራራ ነው። ከወረቀት ትርምሱ ጀርባ ተሜ ከአንገቱ ዙሪያ የማትነጠለውን ስካርፍ ለብሶ ይሰየማል። ያነባል፣ ይጽፋል፤ ይደውላል፣ ይጽፋል፤ ይሰርዛል፣ ይደልዛል። ተሜ አንባቢዎቹን የሚያከበር፣ ይዞላቸው የሚወጣውን ጽሑፍ እሴት ለመጨመር የሚፍጨረጨር ግዙፍ የሚዲያ ሰው ነው።
ተሜ ባጭሩ የኅትመት ሚዲያው ንጉሥ ነው። ንግሥናው የተገኘው በብዙ የፈተና ዓመታት ተሞክሮ ነው። መድረኩ ላይ ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ኖሮበታል። ብዙ አይቶበታል።
በተሜ የፖለቲካ ትንታኔ የማይስማሙ ሰዎችም ቢሆኑ ጽሑፉን እያነፈነፉ ያነቡታል። ምክንያቱም እርሱ ከጻፈ ወረቀቱ አዲስ ነገር አይጠፋውም። በመሠረቱ ሚዲያው ከዚህ ያነሰ ሚና እንዲጫወት የሚጠብቅ የዴሞክራሲ ተስፈኛም ይኖራል ብዬ አልገምትም። ተሜ በሚዲያው የሚያንሸራሽራቸው ሐሳቦች ለሐሳብ ገበያው ምርጥ ግብዓት ናቸው። የጎረበጠው ሰው መድረክ ፈጥሮ መሞገት ይችላል። በተለይም ደግሞ መንግሥት ስንት መድረክ ይዞ፣ ስንት ሀብት እያንቀሳቀሰ በአንድ መጽሔት ከተንቀጠቀጠ መጠየቅ ያለበት የገዛ ተወዳዳሪነት አቅሙን እንጂ ሐሳብ አቅራቢዎችን መሆን የለበትም።
ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እንደሌሎች ነጻነቶች በሙሉ ሲባል ተቀባይነት ያለው ገደብ ይጣልበታል። በበኩሌ በየትኛውም ሕጋዊ ቅቡልነት ያለው አግባብ፥ የተሜ ጽሑፎች እና ትንታኔዎች ገደቡን አያልፉም ብዬ እከራከራለሁ። ይህንን የምለው በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ እንደ ነጻ የመቆጠር መብቱን ተጠቅሜ አይደለም፤ ስለ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትም፣ ስለ ተሜ ጽሑፎችም በሚገባ ስለማውቅ ነው።
ተሜ ነጻ ሰው ነው! እስሩም ፖለቲካዊ ነው!
በፍቃዱ ዘኃይሉ