“… አላውቅም ! የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን … ? ” ባዮቹ ፤ ቃየንአዊያን እና ባቢሎናዊያን አኛ  አይደለንምን? – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

  ፈጣሪ ፊቱን ወደ ሰው ይመለስ ዘንድ ፤ ሰው ሁሉ  ፤ በነገር ሁሉ ፣ እግዛብሔርን ማስቀደም አለበት ።  ይሁን እንጂ ሰው ሁሉ በነገር ሁሉ የሥጋውን  ጥቅም እንጂ የፈጣሪን ፍላጎት  እንደማያሥቀድም የታወቀ ነው ።  የሥጋ ጥቅም ሰውን በሽንገላ ኗሪ ያደርገዋል   ። የዓለም ተፈጥሮ ፣ የተፈጥሮ ውበት ቀልቡን ይገዛዋል ። እናም ተፈላሳፊው ሰው ልጅ  ፣ “ ሣቢ ፣ ጨምዳጅ ፣ አደዛዥ ና  አፍዛዥ የሴት ውበት   ፈጥሮ ሲያበቃ ፣ እግዜሩ ለምን አታመንዘር አለ ? “ በማለት ጥያቄም ይጠይቃል  ።

ሰው ልጅ ፣ አሁን እና ዛሬ   የሚያገኘውን ለህይወቱ ቅመም የሚሆነውን ሁሌም ይፈልጋል ።እጅግ ስልቹ ስለሆነ ሁሌም ማጣፈጫ ነገር ይፈልጋል ። ሴት ሆነ ወንዱ በህይወቱ መደሠትን አጥብቆ ይሻል ። “ በዚህ ዓለም ከምግብ ፣ ከመጠለያ እና ከሠላም ቀጥሎ  የሚያሥፈልገው ሌላ ደሥታን ይፈልጋል ። የተቃራኒ ፆታ ግንኙነትንም እዚህ ደሥታ ውሥጥ የሚደመረው ለዚህ ነው ።

አማኙ ሰው ሁላ ፣ እግዛብሔርን አሥቀድማለሁ ” በአፉ  ይላል እንጂ ፤ የሚያሥቀድመው የየግል ደስታውን ነው ። በዓለም በህይወት ያለ ፣ የበዛው ሰው   በአፉ ብቻ ነው በነገር ሁሉ ፈጣሪውን የሚያሥቀድመው  ፡፡ በተግባር ሲፈተሽ ግን  ፤  ማሥቀደም ይቅርና በሐጢያት መፀፀት የማይነካካው ነፍ ነው ።    እውነቱ ይህ በመሆኑም  ሰው ማለት ያለበት ፦” አቤቱ የምሠራውን አላውቅም ና  ይቅር በለኝ እንጂ ፤ ነው ። እንሆ ዛሬ ንሣሐ ገብቻለሁ ፡፡  ተመልሼም ለሥጋዬ ብዬ አልሸቅጥም ።  “ ።  ይበቃል ፡፡ …

” በነገር ሁሉ እግዛብሔርን አሥቀድሙ” ቅዱሳን መፀሐፍት ቢሉንም እኛ ዓለማዊ  ሰዎች  ግን  እግዛብሔርን በነገራችን ሁሉ አላስቀደምንም ። በማሥተዋል ካያችሁት ከፈጣሪ ቃል መራቃችን  እውነት ነው ። የበዛው የእግዜር ፍጥረት የሆነው  ሰው ፥  እግዚአብሔርን አስቀድሞ አያውቅም ፡፡  ዓለማዊ ፣ ምድራዊ ሰዎች ሁላችን ፣ እግዚአብሔርን እያሥቀደምን አያደለም ። በምድር  ላይ ፈጣሪያቸውን  የሚያሥቀድሙ ሰዎች አይኖሩም ማለቴ እንዳልሆነ አሥምሩልኝ ። በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም ለፅድቅ የሚበቃ ተግባር እየፈፀሙ ያሉ ጥቂት ብፁአን እንዳሉ ይታወቃል ። መንግሥተ ሠማይ የእነሱ ናት ይላል መፀሐፍ ቅዱስ በሐዲስ ኪዳን  ።

ብዙዎቻችን ግን በአመዛኙ ዛሬ ና አሁን የምናሥቀድመው ገንዘብን እንደሆነ እሙን ነው ። ያለ ገንዘብ በዚህ ዓለም በህይወት ለመሠንበት ያሥቸግራልና ። ገንዘብን ተከትሎ ደግሞ ጥቅም የሚሉት ይመጣል ። ሰው ሁሉ ጥቅምን ሥለሚወድ ከሚጠቅመው ጋር ይጣበቃል ። በገንዘብም ፈቃድ ይኖራል ። በአቋራጭ መበልፀግ የሚመጣው በገንዘብ መጠቃቀምን ተከትሎ ነው ።…የሥጋ ደስታን ፍለጋ ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ፋሽዝም ተወገዘ፤ አድዋም ታወሰ" - በሳንሆዜ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን

ለሥጋ ደሥታ በእጅጉ በማሰብ ፣ በልተህ ታበላለህ ። ሌላውም እንዲሁ በተዋረድ  በልቶ ያበላል ። አንዳንዴም ለመብላት  ሲል ሊያስበላህ ሁሉ ይችላል  ። አፈር ። ( ከዛም ደቼ ብላ ! ይልሃል ። አፈር …) ለዚህ ነው በልቶ ሢተርፈው ፣ ሚጢጢ ከሚያጎርሰን አጠገብ ጭራችን ሥንቆላ አይወድቁ አወዳደቅ ሥንወድቅ የምንታየው ። አብልቶ ፣ አብልቶ ድንገት ጥግብ ሥንል  ” ደቼ ”  የሚያሥበላን  ።

በነገራችን ላይ ግለሰብ ብቻ አይደለም ደቼ የሚያሥበላው ። ህዝብም ፣ ከመሥመር የወጡ ፖለቲከኞችን እና ባለሥልጣናትን  ደቼ ያሥበላል ። ጥቂት የማንባለው ፖለቲከኞች ፣ ፈጣሪያችንን ማሥቀደም ይቅርና ፈጣሪን ሥለማናውቀው ፣ በውሸት ከራስ ፀጉራችን እስከ እግር ጥፍራችን ሥለተሞላን  የኋላ ፣ ኋላ በትዝብት እያየን ያለው ህዝብ ደቼ እንደሚያሥበላን ከወዲሁ እንረዳ  ።   ለጊዜው ነው ፣ሆድ ሲያውቅ   ፣ በቀጣፊ አንደበት ተሞልተን ፣ ባልጀራችንን ከሥልጣኑ ለማውረድ ሥንል ብቻ ፣  ” መና ከሠማይ አወርድላቸዋለሁ ። ” እያልን የሚታዘበንን ህዝብ የምንሸነግለው  ።    ፣  ይኽ በቅጥፈት የተሞላ ድርጊታችንም        በኑሯችን ሁሉ እግዛብሄርን እንደማናስቀድም ይመሰክራል ፡፡…

ይኽ  ሁሉ ቅጥፈት ፣ ሥጋችን ከሌላው ሰው ሥጋ ይልቅ ደልቶት እንዲኖር በመፈለግ የሚከናወን ነው ።    በተለይም የአፍሪካ ፖለቲካ በመርህ ዓልባ ፣ ጀርባ ማከክና ማሳከክ የተቆላለፈ ነው ።  በአፍሪካ ያለ ፖለታከኛ እኮ ነው በአመዛኙ ፣ በጠራራ ፀሐይ እየዋሸ ፣ ከፈጣሪ ይልቅ ለሤጣን ሲያዠረግድ የሚስተዋለው ። ሰው መሆኑንን ፈፅሞ ዘንግቶ ራሱን እንደ አምላክ በመቁጠር ሰማይን በርግጫ የሚለው  ።

ፖለቲከኛው ፖለታካ ሥላልገባው ፣ ከፖለቲካል ሣይንሥ ውጪ ሆኖ ፣ የራሱን የፖለቲካ ወንጌል ፈጥሮ በመሥበክ እያጭበረበረ ቢኖር ባይገርምም ፣ ከፖለቲካው ዋና መድረክ የሌለነው እንዴት ነው ጥቂት እንኳን በነገራችን ላይ ሁሉ ፣ ፈጣሪያችንን ማሥቀደም ያቃተን ?  ከምር ሥንቶቻችን ነን የፈጠረንን አምላክ በውል የምናቅ ? ሥንቶቻችን ነን እግዚአብሔርን እረሥተን ከሌላው ልቀን ለመታየት ፣ ለመግዘፍ ፣ ” ምናልባትም አምላክ ለመሆን ” እየጣርን ያለነው ? … በገንዘብና በጠመንጃ ቡድን ፈጥረን የምንገዳደለው ሥንቶቻችን ነን ? ። በሤራ ተቧድነን የጓዳችንን ውድቀት ማፋጠን የዘወትር ድርጊታችን አይደለም እንዴ ? ። አብዘኞቻችን ተምረናል ፣ አውቀናል ። የምንል ሰዎች ። ለሥልጣን የሚታገሉትሥ “  ጓድ “  መንግሥቱ ኃይለማርያም  እንዳሉት “ አንድ በሆነችሁ የመሪነት ወንበር ላይ ፊጥ ለማለት “ ሎቢ ( ደላላ በብዛት ) መቅጠርና በደላላ አገሩን በሐሰት ወሬ ማዳረስን  ቢያያዙት ና በነገራቸው ሁሉ ሤጣንን ቢያሥቀድሙ አይገርምም ። የሚገርመው ፣  በጥቂት ምሁራን   የሐሰት  ወሬ  ፣ ተገፋፍተን ፣  የእኛ  በመንጋነት አገር ማተራመሥ  ነው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢት-ኢኮኖሚ /ET- ECONOMY የኦህዴድ ብልጽግና አንድ ቢሊዮን ዶላር ጦር መሣሪያ ሸምቷል!!! አንድ ትሪሊዮን ብር የቤተመንግሥት ግንባታ!!! የጦርነት ኢኮኖሚና የነፍስ ገበያ በኢትዮጵያ!!

ሌላው   አሥገራማ እና ግራ የሚያጋባው ነገራችን ፣ አንዱን ጎሣ አግዝፎ አንደኛውን ማኮሰስ የዘወትር ሹክሹክታችን መሆኑ ነው ። አንዱን  ጎሣ ባለምጡቅ ጭንቅላት እና መሪ ለመሆን  የተፈጠረ አድርጎ ፤ ሌላውን ጎሣ መምራት የማይችል ጠባብና መሐይም አድርጎ መሣልና ጥላቻ መፍጠርን ደግሞ የየዕለት ሙያ ያደረግን ጥቂት አንባልም   ። ይኽ የሚመሠክረው በነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ያለማሥቀደማችንን  ነው ። ሰው መሆናችንን ክደን ፤ አምሳያችንን ለመግደል ቢላ መሣላችንን ነው የሚያሳብቀው ።

እንሆ ዛሬም በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እንጎሥማለን ። የዘመናት መገዳደላችን ቀጥሏል ። ዛሬም    አንዳንድ ጎሣ ለመግደል የተፈጠረ ሀኖ በህለና ቢሥ ፖለቲከኞች ያለ ሐፍረት ይፎከርባበታል ።   ይኽ ድንቁርና አይደለም እንዴ ? በእልህና በቁጭት ፣ በበቀል ሥሜት ፣” በለው ጣለው ! ውገረው ! ልኩን አሣየው ! እሠረው ! አሰቃየው ! አሩ እንዲጠማው አድርገው ! ከዛም ለሞት አሣልፈህ ሥጠው ! ወዘተ ። ” ማለትን  ? ። ባህል አደረግነው እኮ !

አናም ዛሬ ምሁር ሲታሰር ፤ ” ይኼ ጥጋበኛ ደብተራ ! ዋጋውን አገኘ ። ” የምንለው እኩይ ምግባርን ባህላችን አድርገን አይደለም እንዴ ??? አይደለም  ? ታዲያ ምኑ ላይ ነው   ” በነገር ሁሉ እግዛብሔርን ወይም ፈጣሪያችንን አስቀድመናል ” የምንለው  ? ( ኃይማኖተኛነታችንሥ መገለጫው ምንድ ነው ? “ መግደል ነው ? ማመንዘር ነው ? በሐሰት መመሥከር ነው ? ጓደኛቻችን መጥላት ነው ? ዘወትር መሳደብ ነው ? በሥኬታማ ሰዎች እርር ድብን ብሎ መጨሥ ነው ? እግዛብሔርን ትቶ ለጣዖት መሥገድ ነው ? መሥረቅ ነው ?…”

ምንድነው የዛሬ ና የአሁን መልሣችን ? ማነው እኔ አልዋሽም ባይ ከመሐላችን ? ያለ ውሸትሥ ከሰው ጋር እንዴት ይኖራል ? ሰውን የማይጎዳ “ በነጭ ውሸት “ የሚፈረጅ ውሸት እኮ አብሮ ለመሰንበት እጅግ አሥፈላጊ ነው ። ማነውሥ በነጭ ውሸት ፣ የሰውን ገንዘብ ፣ በብልጣ ብልጥነት አልወሥድም ባዩ ? “ ንግድ በኢትዮጵያ የተፈቀደ ሌብነት ነው ። “ ያለው ማነው ? ረሳሁት ።

ሰዎች ሆይ ! ከነጋ እንኳ ሥንት ና ሥንት ጊዜ ሰውን የማይጎዳ ውሸት ዋሽተናል ።  ደሞምም በወሬያችን ጣልቃ ጥቂት ሰዎችን   አምተናል ። ሐሜት አውርተናል ።  …

የሚከፈው እና ትልቅ ጉዳት የሚያሥከትለው ፣ በምንም ሁኔታ ያልደረሰብንን ሰው ፣ በቋንቋውና በጎሣው ከእኛ ያለመመሣሠል ብቻ ጥርስ በመንከስ የምንፈፅመው ደባ ነው ። …

ደሞሥ ፣ በዕውቀቱ ፣ በችሎታው እንዲሁም አንዳንዱ በሀብቱ ከእኛ በመብለጡ ቀንተን ፣ እርሱን ለማጥፋት ወደ ባለውቃቢ ፣ ጠንቆይ ፣ ደብተራ ና መፅሐፍ ገላጭ ቤት ተደብቀን ና በግላጭ ፣ የምንመላለሰውሥ ሥንቶቻችን ነን ? ለመልካም እና ለበጎ ፣ ሰውን ለማሥተማር የሚተቹ፣ እንከንን የሚያሳዩ ፣ ደፋር የሆኑ ፣ ፊት ፣ ለፊት እውነትን የሚናገሩትን የምንጠላም ጥቂቶች አይደለንም ። ነውራችን  በህየወት ሣለን እንዳይገለጥብን በብርቱ የምንጠር ብዙዎች አይደለንም እንዴ ? …

እርግጥ ነው ፣ ሰው ፣ በተፈጥሮው ጠንካራ ጎኑን እንጂ ደካማ ጎኑን በአደባባይ እንዲነሳ ያለመፈለጉ እሙን ነው ። ይኽ ግብዝነት እና የራሥን አሥጠሊታ ገፅታ ለማወቅ ያለመሻት ፣ የተጀመረው  ከአቤልና ቃየን መፈጠር ጀምሮ ነው ።( የአዳም ልጆች ። )    ቃየን አቤልን በቅናት ተነሳስቶ ከሰዋራ ሥፍራ ሸንግሎ ወስዶት ሲያበቃ ገደለው ።  ከገደለው በኋላ ፈጣሪያችን ድርጊቱን አይቶ ነበርና ፣ የቃየንን   ምላሹን እያወቀ  ሲጠይቀው ፣ ያለው ምን ነበር  ? እጠቅሳለሁ ፣ ” እግዚአብሔር  ቃየንን አለው ” ወንድምኽ አቤል ወዴት ነው ? እርሱም አለ ፣ ” አላውቅም ፤ የወድሜ ጠባቂው  እኔ ነኝን ? ” ዘፍጥረት መዕራፍ 4 ቁጥር 9 ፡፡   ? …ዛሬም እኛም የእኩዩ ቅናት ዛር ሲሰፍርብን እንደ ቃየን እያደረግን አይደለም እንዴ ? …

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጦርነቱ አለቀ የሚባለው መቼና የት ላይ ሲደርስ ነው? - ነፃነት ዘለቀ

እውር በነበርነበት ሰዓት የዓለምን መንገድ ፣ ከፈጣሪ በተሰጣቸው ፀጋ  በመምራት ፣ ወደ ብርሃን ያወጡንን እንደ ጠላት የቆጠርን ፤ ፈራሽ ሥጋችንን የምናሞላቅቅ በብልህ ሰዎች ምርኩዝም ሀብታም የሆንን  በየቀበሌው የለንም እንዴ ? … በዚህ እጅግ ጠርዝ በረገጠ እራሥ ወዳድነት መንገድ ተጉዘንስ እንዴት ነው ፣ ሁለት ሆነን ብዙ የሆንበትን ፣ ቤተሰብ በመልካም ሰብዕና የምንገነባው ? …

ከቤተሰብ ፣ ማህበረ ሰብ ፣ ከዛም ህብረተሰብ ፣ የማህበረሰቡ ሥብሥብ ደግሞ ህዝብ ይባላል ። ከዛም ይኽ ህዝብ መንግሥት ይመሠርታል ። ታዲያ ራሱን በመልካም ዲሢፕሊን ያላነፀ ፣ ሰው መሆኑንን እንዲረሣ ፣ እግዛብሔርንም በቅጡ እንዳያውቅ የተደረገ ፤  ትውልድ ፣ እንዴት ነው ፣ አገርን በማበልፀግ ና መጪውን ትውልድ ለማኩራት የሚችለው ? …

እንደ ህዝብ ፣በዚህ ዓይነት ከፈጣሪ በራቀ “  በጠልፎ መጣል “ መንገድ ተጉዘን  ና በጥላቻ ተሞልተን የምናልፍ ከሆነ እኮ ፣ ተተኪ ትውልድ ብሎ ነገር አይኖረንም ። የማን ዘር ጎመን ዘር ። የዘሬን ብተው ይዘርዝረኝ ይሆናል ነገራችን ። …” ድመት መንኩሳ ዓመሏን አትረሣም ” እንዲሉም ማንኛውም ሰው ፣ ያደገበት ቤተሰብ ና ማህበረሰብ ግልባጭ በመሆኑ ከጥፋት አዙሪት ከቶም ለመውጣት አንችልም ፡፡

ሰው ውጥ የሆነ ቀና አመለካከቱም ሆነ እኩይ የሆነ መሰሪ ተግባሩ የሚመነጨው ካደገበትና ከኖረበት ማህበረሰብ ነው ፡፡ ….  ይኽንን እውነት በአንክሮ እናጢነው ። ለአፍታ በጭፍን መጓዛችንን አቁመን ራሳችንን ፣ ሰውነታችንን በብርሃን አእምሮ እንጠይቅ ፡፡ ሁላችንም ሰው ነንና ! እናም ይኽንን ሰውነታችንን ከተገነዘብን ፤ ዛሬ ላይ ሆነን ” አቤቱ ! የምንሠራውን አናውቅም እና ይቅር በለን ። ” በማለት በንሥሐ ወደ ቀልባችን እንመለስ ።   ወደ ቀልባችን ሥንመለሥ ነው ፣   በነገሬ ሁሉ  ፈጣሪዬን አሥቀድማለሁ ። “ በማለት አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችለው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share