የአስቆርቱ ይሁዳ እንኳን ህሊና ነበረው! – በላይነህ አባተ

“በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ ሰላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡  እነሱ ግን እኛስ ምን አግብቶን አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ፡፡” ማቴ 27፤3-5

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ሕዝብ እንደሚያውቀው በጲላጦስ ዘመን ተነበረው የከፋ ክህደት በይህ አድግ ቁጥር አንድና ሁለት ዘመን ተፈጽሟል፡፡ ዳሩ ግን የይህ አድጉ ዘመን ይሁዳዎች የጲላጦሱን ዘመን ይሁዳ  ታህል ለጸጸት የምታበቃ እራፊ ህሊና አጥተዋል፡፡

በይህ አድግ ቁጥር-አንድ ዘመን የዘር ማጥፋት ወንጀል በወልቃይት፣ በራያ፣ በሃረርጌ፣ በአሩሲ፣ በባሌ፣ በጋንቤላ፣ በወለጋና ሌሎችም አካባቢዎች ተፈጥሟል፡፡ ስንቱ በወህኒ ቤት ተጠብሷል፣ ተገሏል፡፡ እንደ ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ ያሉ አዛውንቶች በአስተማሪነት፣ በአርበኝናትና በዲፕሎማትነት የገነቧት አገር በዘር ቢላዋ ስትታረድ አይተው አዝነውና ተክዘው አልፈዋል፡፡ እንደ እነ ክቡር ፕሮፌሰር አስራትና ፕሮፌሰር መኮንን ቢሻው ያሉ ባለሙያዎች እድሜ ልክ በምህርነትና በህክምና ባገለገሉባት አገር ታስረውና ሕክምና ተከልክለው ተሰውተዋል፡፡

የብዙ ሺ ወጣቶች ደም ፈሶ ይህ አድግ ቁጠር- ሁለት ሲመጣ ደሞ በይህ አድግ ቁጥር-አንድ ዘመን ተነበረው የከፋ የዘር ፍጅት በመላ አገሪቱ በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ በመፈጸም ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ይሁዳ የአማራ ምሁራን ሕዝባቸውን ክደው ከዘር ፈጅዎች ጋር ተሰልፈዋል፡፡ በተለይ ይህ አድግ ቁጠር ሁለት ሲመጣ “ሙሴና ኢያሱ የሚመሩት ባህር አሻጋሪ መንግስት መጣ” እያሉ በውጪም በውስጥም በሜዳዎችና በአዳራሾች እጃቸው እስቲመለጥ አጨብጭበዋል፤ ወገባቸው እስቲሰበር በዳንስ ተወላግደዋል፣ ጀንዲ እሚያካክል ጠልሰም ጠልስመዋል፡፡ ዳሩ ግን ዳንሳቸው ሶስት ወር ሳይሞላው የማህፀን ጽንስ ያልማረው የአማራ ዘር ፍጅት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ተፈጥሟል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነጻ ምርጫ ባልዋለበት መስከረም 30 - ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ

የይሁዳ የአማራ ምሁራን የጲላጦሱን ዘመን ይሁዳ የምታህል ጭላጭ የጸጸት ህሊና ዛሬም አጥተዋል፡፡ የጲላጦሱ ዘመን ይሁዳ ክርስቶስ እንደተፈረደበት በሰማ ጊዜ ተጸጽቶ “በድያለሁ” ሲል ተናግሯል፡፡ ይሁዳ የአማራ ምሁራን ግን አማራ እንዲጠፋ በተፈረደበት ቀን ብቻ ሳይሆን አማራ ዘሩ እየተፈለገ ሲሰዋ፣ ሲቃጠል፣ ሲፈናቀልና አገር አልባ ሲሆን በአይኗ በብረቷ እያዩም ታራጁ ይህ አድግ ጀርባ መደነሳቸውም ሆነ “ሙሴና እያሱ መጡ!” እያሉ ሕዝብን አዘናግተው ለከፋ የዘር ፍጅት መዳረጋቸውም አላጸጽታቸው ብሏል፡፡

የጲላጦሱ ዘመን ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ለመስጠት የተቀበለውን የመቅቡጥ ገንዘብ ለመመለስ ተማጽኗል፤ የሚቀበለው ሲያጣም ወርውሮታል፡፡ አንዳንድ ይሁዳ የአማራ ምሁራን ግን እንኳን ከዚህ በፊት ሕዝባቸውን ለመክዳት ከዘር አጥፊዎች የተቀበሉትን የስልጣን፣ የገንዘብም ሆነ ሌላ ሌላ መቅቡጥ ሊመልሱ ወደፊትም እየከዱ የክህደት ጉርሻቸውን እንደ ጎረሱ ለመሞት የተዘጋጁ ይመስላል፡፡

የጲላጦሱ ዘመን ይሁዳ የፈጸመው ክህደት ነቀዝ እንደ በላው ባቄላ ክፉኛ ጎድቶት ራሱን በስቅላት ገሏል፡፡ አንዳንድ ይሁዳ የአማራ ምሁራን ግን እንኳን ለሞት የሚያበቃ የጸጸት ህሊና የውሻ ታህልም የይሉኝታ ህሊና አጥተዋል፡፡

የይሁዳ አማራ ምሁራን ጉዳይ ሰፊ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ በሄሮድስና በጲላጦስ ዘመን የከሀዲው ብዛት ከአስራ ሁለት ሐዋርያት ውስጥ አንድ ሲሆን በይህ አድግ- ቁጥር አንድና ሁለት ዘመን ያለው የምሁር ከሀዲ መጠን ግን ከአስራ ሁለት ምሁራን ውስጥ አስራ አንድ ይመስላል፡፡ ሕዝባቸውን የከዱ ይሁዳ የአማራ ምሁራን ክርስቶስን የከዳውን የአስቆርቱን ይሁዳ ታህል የጸጸት ህሊና አጥተዋል፡፡ ያሳዝናል!

 

ግንቦት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share