አሳየ ደርቤ
ከቀናት በፊት ጋዜጠኛ ሰሎሞን ሹምዬን ሊያፍኑ ወደ ቤቱ ያመሩ ኃይሎች እሱን ማግኘት በተሳናቸው ጊዜ እኅቱን አፍነው ወሰዱ፡፡ ይሄንንም አሳፋሪ ድርጊት የሰማው ጋዜጠኛ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ‹‹ሰሎሞን እስኪመጣ ፥ ሰላማዊት ትቀጣ የሚል ሕግ መኖሩን አላውቅም ነበር›› በሚል ስላቅ እኅቱን አስፈትቶ ታፋኙን ማሕበረሰብ ተቀላቀለ፡፡
ይሄንንም ምርጥ ተሞክሮ ወደ ክልሉ የወሰደው ብአዴን መቶ አለቃ አበበን ለመቆጣጠር ወደ ቤቱ ሲያመራ በተፈላጊው ግለሰብ ፈንታ ጡጦ የሚጠባ ሕጻን ልጅ አገኘ፡፡
እናም ‹‹ይሄን ሕጻን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብንወስደው ተፈላጊው ሰውዬ ልጁን ፈልጎ መምጣቱ አይቀርም›› በሚል ውዳቂ አስተሳሰብ አፉን ያልፈታውን ብላቴና አፍኖ በመውሰድ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ያልሰፈረ አዲስ ገድል ፈጸመ፡፡
ይሄውም አስነዋሪ ድርጊቱ ይፋ የወጣበት ነውረኛ ቡድን አመሻሽ ላይ በቴሌቪዥን ቀርቦ ‹‹የክልሉ መንግሥት የፋኖ ልጆችን አግቶ የሚወስደው ከረሜላና ብስኩት ለመግዛት እንጂ ወደ አስር ቤት ለማስገባት አይደለም›› ከሚል ማስተባባያ ጋር ሕጻኑን በአንቀልባ አዝሎ ወደ ቤቱ ሲያደርስ እንመለከት ይሆናል፡፡