የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ትናንት ረፋዱ ላይ ባዋለው ችሎት የዩትዩብ መገናኛ ብዙኀን ዝግጅት አቅራቢዋን መስከረም አበራን ጉዳይ ተመልክቷል። በዕለቱ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዋ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት እና አማራ ክልልን ከፌደራል መንግሥቱ ለመነጠል ገንዘብ ተከፍሏት ትሰራለች ብሎ እንደጠረጠራት ለችሎት አስረድቷል።
የተጠርጣሪዋ ጠበቆች ከመርማሪ ፖሊስ ጋር ክርክር ያደረጉ ሲሆን፣ መርማሪ ፖሊስም 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ይሰጠኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል። መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት የጠየቀው፣ በተጠርጣሪዋ ላይ የሰነድ ማስረጃዎችን እያሰባሰበ እንደሆነ እና ግብረ አበሮቿን ለመያዝ እንደሆነ ለችሎቱ አብራርቷል።
የተጠርጣሪዋ ጠበቆች በበኩላቸው፣ ደንበኛቸው ሥራዋን በግልጽ በመገናኛ ብዙኀን እንደምትሰራ ለችሎት እና የፖሊስ ውንጀላ ከመገናኛ ብዙኀን አዋጁ ጋር የሚጣረስ እንደሆነ በመግለጽ፣ ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዳይሰጠው ጠይቀዋል። ተጠርጣሪዋ የ7 ወር ሕጻን ልጅ ያላት፣ ጡት የምታጠባ እና ቋሚ አድራሻ ያላት መሆኑን በመጥቀስም፣ በውጭ ሆና ጉዳዩዋን እንድትከታተል ጠበቆቿ ጨምረው አቤት ብለዋል።
የሁለቱን ወገኖች ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ፣ መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። ችሎቱ በዛሬው ውሎው የተጠርጣሪዋ ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ፣ ለመርማሪ ፖሊስ የ13 ቀናት የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል። በችሎቱ ውሳኔ መሠረት ቀጣዩ የችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ግንቦት 29 ሆኗል።
መስከረም አዲስ አበባ ላይ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋለችው ቅዳሜ ቀትር ላይ ከባሕርዳር ወደ አዲስ አበባ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመለሰችበት ወቅት ነበር።
በተያያዘ ዓርብ ረፋዱ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የቴሌቪዥን ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢው ሰለሞን ሹምዬ ቅዳሜ ጧት ላይ ከፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቧል። መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪው ሰለሞን ላይ 14 የምርመራ ቀናት የጠየቀ ቢሆንም፣ ችሎቱ ግን ለፖሊስ ዘጠኝ የምርመራ ቀ በመፍቀድ ለግንቦት 22 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
[ዋዜማ ራዲዮ]