እምቢ በል! ብያለሁ እምቢ በል! – አገሬ አዲስ

ይህ ግጥም በአገራችን የመንግሥቱን ሥልጣን በጉልበት የያዘው ህወሃት/ኢሕአዴግ ቡድን ያደረገውንናበማድረግ ላይ ያለውን በታታኝና አገር ከፋፋይ ድርጊት የሚያሳይና የሚቃወም ሲሆን በኢሳት ቴሌቪዥን፣በስዕላዊ ቅንብር በአገር ቤት ሳይቀር በተደጋጋሚ የቀረበ ነው።በቋሚነትም በዩቱብ ሰፍሮ ይገኛል። Hagere Addis embi bel ብላችሁ ብትጠይቁ ታገኙታላችሁ።

የታወቀው ሰዓሊና ፈላስፋ ሊዮናርዶ ዳቪንቺ (1452-1519) እንዲህ ብሎ ነበር

“ከመጨረሻ ይልቅ መጀመሪያ ላይ መከላከል ይቀላል”

ማጉኤል ደ ሴርቫንቴስ (1547-1616)የስፔን ደራሲና ገጣሚ ስለመዘግየት እንዲህ ብሎ ነበር “መዘግየት ሁሌ አደጋን ይፈለፍላል”

እኔም ዝም ብሎ ከማየትና ከመዘግየት

እምቢ በል! ብያለሁ

እምቢ በል!

እምቢ በል ሰሜን እምቢ በል ትግራይ፣

ለዚህ ከፋፋይ ለዚህ አጋዳይ፣

አትሁን መሣሪያ አትሁን አገልጋይ፣

የኔነው ብለህ አትሁን ወላዋይ፣

ብቻህን ቀርተህ መከራ እንዳታይ፣

ላገርህ ክብር በኢትዮጵያዊነት፣

ለዜግነትህ ታገል ባንድነት።

ከችግር ኑሮ ላልወጣህበት፣

በስም፣ በትግልህ፣

በልጆችህ ደም ጥቂት ጨካኞች ተጠቀሙበት፣

ሥልጣኑን ይዘው በለጸጉበት።

ሕንጻ ገነቡ ቪላ ሠሩበት፣

በውጭ አገር ባንክ አከማቹበት፣

ድርሻ እዬገዙ ንብረት ያዙበት፣

ልጆቻቸውን አስተማሩበት፣

ለመተካካት አዘጋጁበት፣

ያንተ ግን ሆኗል ኑሮህ አቀበት፣ ገቢህ ቁልቁለት።

ክልል ከሚሉት ጠባብ እስር ቤት፣የጎሳ በረት፣

ለመውጣት ታገል በኢትዮጵያዊነት

የትም ለመኖር  በትልቅ አገር ባለቤትነት።

በእጅ አዙር ቅኝ አገር ሲወረር፣

በዘር ሸንሽነው ሲያሳዩህ አሳር፣

ይብቃህ ይምረርህ ተሰዶ መኖር፣

እምቢበል ጀግና እምቢ በል ደፋር።

በዘር በሽታ አገር ሲበከል፣

ኢትዮጵያዊነት ስትከለከል፣

እምቢ በል አፋር እምቢ በል ደንከል።

እምቢ በል ጎጃም እምቢ በል ጎንደር፣

እምቢ በል ወሎ፣እምቢ በል ሸዋ፣ እምቢ በል ሀረር፣

ሲሸጥ ሲለወጥ ያገርህ መሬት ያገርህ አፈር።

እምቢ በል ባሌ እምቢ በል ከፋ፣

እምቢ በል አርሲ እምቢ በል ጎፋ፣

አገር ሲዘረፍ አገር ሲጠፋ።

ባንዳ ቀበሮ የበግ ለምድ ለብሶ፣

ያገር አንድነት ቦርቡሮ አፍርሶ፣

በዘር በክልል ሕዝብ አተራምሶ፣

እንዴት ዝም ይላል ወገን አስችሎት፣

አገር ሲጋለጥ ለውጭ ጠላት።

እምቢ በል ጀግና እምቢ በል ተነስ፣

አገርህ ሲናድ መኖሪያህ ሲፈርስ።

አዲሱ ትውልድ አንተ ተማሪ፣

የወደፈቱ አገር ተጠሪ፣

ታሪክ አንባቢው ሁን ታሪክ ሰሪ።

አንጋፋው ትውልድ፣ታላቅ ወንድምህ ነበረ ታጋይ፣

በየከተማው፣በየገጠሩ፣በየመንገዱ በተራራው ላይ

ለአገር የሚሞት፣እምቢ አሻፈረኝ ለአምባገነኖች አልገዛም ባይ፣

አርማውን አንሳ አትሁን አድርባይ።

በዘር በክልል ሳትከፋፈል፣

ላስተማረህ ሕዝብ ውለታ ክፈል።

 

ያሁኑ ትውልድ ያገሬ ወጣት፣

ካንት ይጠበቃል ቁም ነገር መስራት።

የትውልድ ግዳጅ አንተም አለብህ፣

ስታውደለድል ቀኑ አይምሽብህ።

ተስፋህ ሲጨልም መብትህ ሲገፈፍ፣

ተቃውሞ አሰማ ውጣ ተሰለፍ።

አንተ ገበሬ ያገር ምሰሶ፣

መሬትህ ሲሸጥ ሲሄድ ተገምሶ፣

ምርትህ ሲሳሳ ጎተራህ ሲነጥፍ፣

በማዳበሪያ ስም ስትዘረፍ፣

በራብ አለንጋ ልጅህ ሲገረፍ፣

እምቢ አሻፈረኝ ብለህ ተሰለፍ።

አንተ ነጋዴ አትርፎ አዳሪ፣

በርካሽ ዕቃ ተፎካካሪ ፣

መጥቶ ሲያስወጣህ ከንግድ ስራ፣

ከምትበሳጭ ከምታወራ፣

ቆርጠህ ተሰለፍ በትግሉ ጎራ።

ሳትከዳዳ ሳትከፋፈል፣

ባትዋጋ እንኳን ግብር አትክፈል.::

አንተ የጦር ሰው አንተ ወታደር፣

እንደ ዱር አውሬ ለሆድ አትደር፣

ክብርና ጸጋ ሲኖር ነው አገር።

ለአንድ ድርጅት አትሁን አሽከር፣

ካለፈው ጊዜ ከደርግ ተማር፣

በወገኖችህ እንድትወደድ እንድትከበር፣

እንዳትበተን እንዳትቸገር፣

ለዴሞክራሲ ለእኩልነት፣

ታገል አንድ ላይ በኢትዮጵያዊነት።

ያገሬ ምሁር የለውጥ ጠንሳሽ፣

ለዲሞክራሲ ለጥቃት ደራሽ;

ያምባገነኖች ጭቆና ደምሳሽ፣

ሳትከፋፈል ሁን ታሪክ አዳሽ።

አንት የኪነት ሰው፣አንት ጥበበኛ፣

አንተ ሰዓሊ አንት ሙዚቀኛ፣

አንተ ደራሲ አንት ጋዜጠኛ፣

አትሁን አድርባይ አትሁን ጎጠኛ።

መሣሪያ አትሁን ለዚህ ዃላቀር ለዚህ ተረኛ፣

ከገንዘብ በላይ፣ከዝና በላይ ሁን አገር ወዳድ ታጋይ አርበኛ።

ሆነህ እንድትኖር በሕዝብ ተወዳጅ፣

አትሁን የዝና ጥቅም አሳዳጅ፣

በዬመድረኩ ያምባገነኖች አወዳሽ ሰጋጅ።

እምቢ በል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአዲስ አበባ ዋና ከተማ እና የወልቃይት ደንበር የኢትዮጵያ እና የቀጠናው የወደፊት የህልውና መሠረት ናቸው

አንተ ታክሲ ነጅ፣አንተ ታታሪ፣

አንተ ላብ አደር አንት ለፍቶ አዳሪ፣

አንች ጉዳተኛ አንች ሴት አዳሪ፣

አትቀበሉት ይህን ከፋፋይ አገር ሰባሪ።

በቢሮክራሲው የምትሰራ ጥሪውን ስማ፣

ለስልጣን ለሃብት ከምትሻማ፣

ሕዝብ በጉቦ ከምትዘርፍ ከምትቀማ፣

አገር ሲቆስል አገር ሲደማ፣

አንድ ላይ ሆነህ ተቃውሞ አሰማ።

እምቢ በል ሜጫ እምቢ በል ሶዶ፣

ሁሉም ተወስዶ ሁሉም ተሰዶ፣

እንዴት ያስችላል አገር ተንዶ።

አትገዛቸው በላቸው እምቢ፣

ጋምቤላ አሶሳ ለቀምት ግምቢ።

ማዕድን ወርቅህ ተበዘበዘ፣

አንድም ሳይተርፍ ወጣ ተጋዘ፣

ልጅህ ተርቦ እዬታረዘ።

እንዲመቻቸው ለሚፈልጉት፣

አንድነትህን ክትፎ አደረጉት።

ዘርና ክልል እንቢ በላቸው፣

አንድ ሁንና፣ባንድ ቁምና ተቋቋማቸው።

ጫካውም አምጽ አውሬውም ተነስ፣

የበቀልክበት፣የምትኖርበት አገርህ ሲፈርስ።

ያገሬ ዝሆን ያገሬ ሰሳ፣

ያገሬ ነብር ያገሬ አንበሳ፣

ጠላት ሲያድንህ አንተም ተነሳ፣

ድምጽህን ይስሙት እምቢ በል አግሳ።

እምቢ በል ጀግና አገር ወዳዱ፣

የጥቅም ባሪያ፣ፈሪ ሆዳሙ ይታያል ጉዱ፣

ዘረኛ ባንዳው ይታያል ጉዱ።

በዘር በክልል ሳትነታረክ፣

አንድ ሁንና በአንድነት መድረክ፣

ተያያዝና እጅ ለእጅ፣

አገር አቆየው ለልጅህ ልጅ፣

ክልልና ዘር ይጎዳል እንጅ፣ምንም አይበጅ።

አማኝ አላማኝ፣እስላም ክርስቲያን በአንድ ተሰለፍ፣

ሕዝብ ለማዳን አገር ለማትረፍ።

ለውጭ ጠላት ቀዳዳ አትክፈት፣

ለእርስ በርስ ውጊያ ለባሰ ድቀት።

አትነታረክ አትፎካከር፣

ላላየኸው ቤት ለሰማይ መንደር።

ከሁሉም እምነት ከሁሉም ነገር፣

ከሃይማኖት ፊት የኖረች አገር፣

ትልቅ ብልጫ አላት የያዝካት አገር፣

እናት ኢትዮጵያ ጥንታዊት አገር።

እምቢ በል!  እምቢ በል!  እምቢ በል!!!

አገሬ አዲስ

መስከረም 2003 ዓ ም.(ሴፕቴምበር 2010)

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share