ሞጋች ዜጎችን በማፈን፤ የማሰብ ነፃነትን መግደል አይቻልም !
መንደርደሪያ
በኢትዮጵያ፤ በአብይ አህመድ የሥልጣን ዘመን፤
ማሰብ ክልክል ነው !
መጻፍ ክልክል ነው !
መናገር ክልክል ነው !
መሰብሰብ ክልክል ነው !
ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ ክልክል ነው !
ሁለቱ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ ድርጅቶች፤ ህወሃትና ኦህዴድ/ኦነግ በከፈቱት ጦርነት፤ ከ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን ተፈናቅለው፤ ድርቅና ረሃብ በዜጎቻችን ላይ ጥርሱን እየሳለ፤ ት/ ቤቶች፤ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ወድመው፤ ዜጎቻችን ያለ መጠለያ፤ ሕፃናት ያለ ትምህርት፤ የታመሙ ሰዎች ያለ ህክምና፤ የኑሮ ውድነት ህዝቡን እንደ እሳት እየለበለበ፤ አብይ አህመድ ፓርኮችን አሠርቼላችኋለሁ ተዝናኑ ይላል፤ የዘርና የጎሣ: የጦር አበጋዞች፤ ባደረጉት ተደጋጋሚ ጦርነት፤ ኢኮኖሚዋ በደቀቀ አገር፤ በብዙ ቢልየን የሚቆጠር ብር አውጥቼ ቤተ መንግሥት አሠራለሁ ሲለንና፤ ንጉሥ የመሆን ቅዠቱን ስናስብ፤ በሕዝብ መቃብር ላይ ከበሮውን እየደለቀ የሚጨፍር አምባ ገነን መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል::
አብይ አህመድ፤ በተፈናቀሉ ዜጎቻችን: ስቃይና መከራ፤ ልቡ ጮቤ የሚረግጥ፤ የአዛውንት ሃዘን ትካዜ: ሙዚቃው፤ በእናቶች ምሬትና ለቅሶ: የሚጨፍር፤ በሕፃናት ትኩስ ዕንባ: አከላቱን የሚታጠብ፤ ከአፉ በሚወጡ ቃላት: ማር ለውሶ: መርዝ የሚያጎርስ፤ ለሥልጣን ካለው ጥም የተነሳ የአባይ ግድብ የሞላውን ውሃ ቢጠጣ እንኳን የማይረካ፤ በጥቅሉ በሰዎች ስቃይ የሚደሰት ፍጡር ነው::
በኢትዮጵያ፤ በአብይ አህመድ የሥልጣን ዘመን የተፈቀዱት፤
ሙስና (ንቅዘት)፤ ሌብነትና የሥልጣን ብልግና
ጦርነት፤ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀልና ማስራብ
ህዝብን በኑሮ ውድነት መለብለብ
ህዝብን በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት ለያይቶ ማባላት
የዘርና የጎሣ ግንብ መገንባት…… ወዘተ ናቸው ::
እህታችን መምህርት መስከረም አበራ፤ አንጋፋው ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱና፤ ጋዜጠኛ ሠለሞን ሹምዬን ያፈነው፤ አጠያፊው የብልግና ቡድን፤ በአስቸኳይ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ይልቀቅ !!
ሁላችንም ዝም አንልም በቃ !
ነፃነት: እኩልነትና ወንድማማችነት !
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!