በዓለማችን  ዘመናዊ አናርኪሲዝም  እያቆጠቆጠ ይሆንን ? – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ከተፈጥሮ አንፃር ፣  አዲስ ና ድብቅ ነገር ያለመኖሩ ይታወቃል ። መፅሐፍ ቅዱስ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ  12 ይኽንን እውነት በእየሱስ አንደበት  ገልፆልናል ፡፡

1  በዚያን ጊዜ የሕዝብ አእላፍ እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ተሰብስበው ሳሉ ፤ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር ፣ አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው ።

2  ነገር ግን የማይገለጥ የተከደነ ፤ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም ።

3  ስለዚህ በጨለማ የምትናገሩት ሁሉ በብርሃን ይሰማል ፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ  የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይሰበካል ።

እውነት ነው ፤ ምንም ድብቅ ነገር ፤ ምንም ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ፣ አዲስ ነገር ፣  በዚሀ ዓለም የለም ። ለጊዜው ነው እንጂ ሁሉ ይገለጣል ። ደብቀን ዘላለማዊ ምሥጢር የምናደርገውም የለም ። ምስጢራዊ የጓዋዳ ወሬአችንንም ፣ ተንሾካሽከን በእኛው ብቻ ልናስቀረው አንችልም  ፡፡ ለጊዜው ምሥጢር ይሆናል እንጂ ፤ ኋላ ህዝብ ይሰማዋል ።

ደሞስ ምን አዲስ ነገር አለ ? ከተፈጥሮ አንፃር ካየነው ከቶም ምንም አዲስ ነገር የለም ። ትላንት በላፈው ትውልድ ተፈጥሯዊ የሆነው ድርጊት በዚህ ትውልድም እየተፈፀመ ነው  ።  ሁሉም ነገር ። ሠናዩም ሆነ እኩዩ…ሁሉም  እየተፈፀመ ነው ። የመተግበሪያው መንገድ የራቀቅ ሆኖ እንጂ የሰው ተፈጥሯዊና ዓለማዊ ድርጊቱ ያውና አንድ ነው ። በሹካ በለህ በእጅ ፣ በእሥትሮ ጠጣህ በመዳፍህ ጨልፈህ ፣ በዲንጋ ገደልክ በሥናይፐር …  ያው አዘለና አቀፈ ነው ። በዛም ሆነ በዚህ ድርጊቱ ፍጻሜ አግኝቷል  ።

አየህ ፣ የትላንቱ ሰው በመዳፉ ይጠጣ ነበር ። ከምንጭ ወይ ከወንዝ ። የዛሬው ሰው ደግሞ ከቧንቧ በኒኬል ወይ በብርጭቆ እየቀዳ  ይጠጣል ። ሁለቱም በዚህም ሆነ በዛ ወኃውን ይጠጡ ነበር ። በቃ ። ልዩነቱን የፈጠረው የሰው ጥበብ ነው ። በሚጥር ና በሚግር ሰው ፈጠራ የሰው ኑሮ ዘምኖል ። ጥበበኝነት ከዘመኑ ጋር እያደገ መምጣቱ ባይካድም ፣ የሰው ጥበቡ አጥፊነትንም ደምሮ መያዙን ልብ በሉ ።… የኢንተርኔት የዝሙት ገብያንና የየሰውን ቂልነትና መጃጃል አሥተውሉ ። አይኑንን ከፍቶ በጠራራ ፀሐይ ህልም የሚያልመው ሰው ጥቂት አይደለም ። ከወጣት እስከ ሽማግሌ ። ይኽንን   ባለ ኢንተር ኔት ካፌዎቹን ጠይቋቸው ፡፡ የአብዛኛው ኮፒዊተራቸውን ታሪክ የያዘው ብልግና እንደሆነ ይነግሯችኋል ፡፡ …

ኮፒዊተርን ጨምሮ ፤ በዚህ ዓለም ብቅ ብለው ብዙ  የፈጠራ ሥራ ሠርተው ያለፉ ሰዎች   አሥታዋዮች ፤ ትሁታንና ጠቢባን ነበሩ ። አብዛኞቹም ፣  ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚያዩ ግብዝነት የማይነካካቸው እንደሆኑ ታሪካቸው ይመሰክራል ። እንደውም አንዳንዶች በፈጠራቸው ያልተጠቀሙ ፤በድህነት ተኮራምተው የሞቱ ፤ መሆናቸውን ሥናውቅ ለእነዚህ የጥበብ ሰዎች እናዝናለን  ። እንዚህ የፈጠራ ሰዎች ዛሬ በበለፀጉት አገራት ትልቅ ከበሬታ አላቸው ፡፡ የእድገታቸው ምንጭ ናቸውና ያከብሯቸዋል ፡፡

በአልበለፀገቸው አፍሪካ ግን የፈጠራ ባለሙያዎች አይከበሩም ፡፡ አይደገፉም ፡፡ አይበረታቱም ፡፡ ወጣት ከሆኑ ወደ አውሮፓና አሜሪካ መሰደዳቸውና ዜግነታቸውን መቀየራቸውም አይቀሬ ይሆናል ፡፡ ድሮም ሆነ ዛሬ ፣ ባልበለፀጉት አገራት ፣ በአፍ ካራቴ ፤ ብላክ ቤልት ያላቸው ፣ ከፈጠራ እና ከጥበብ ሰዎች የላቀ ምቾትና ድሎት  እንደሚኖሩ ይታወቃል ፡፡ በአፍሪካ በአመዛኙ ግብዝና በትብኢት የተሞሉ ሰዎች በመንግስት ወንበር ላይ ልክ እንዳዋቂ ቁጭ ብለው ሲዘባነኑ ነው የሚስተዋለው ፡፡ የጉልበት ፤ የጠመንጃ አገዛዝ ነው ያለው ፡፡ ህዝቡ በድንቁርና ፣ በርሃብ ፣ የተነሳ በመንጋ እንዲስብ በመደረጉ ለዕውቀት የሚሰጠው  ግምት እጅግ ዝቅ ያለ ነው ፡፡  የመንጋ አሥተሣሠብ በነገሰበት ፣ ያልበለፀገ አገር ውሥጥ ባለ ጠብ መንጃዎች  እንደ ጥንታዊያኑ ፈሪሣውያን ግብዝ ሆነው ቢገኙ  ምን ያስገርማል ?  የትም አፍሪካ አገር ብትሄድ ” አፍ ያለው ጤፍ ይቆላል ፡፡ ” እንደሚባለው ፣ እነዚህ ፈሪሣዊያን በአፋቸው ጤፍ ሲቆሉ ብታይ አንተ ብትገረምም ፣ “ጤፍ አይደለም ሸንብራ ነው ፤ የሚቆሉት ፡፡ ” ብለው የሚከራከሩ መዓት ደጋፊ ሥላላቸው ጤፍ ከመቁላት ልታግዳቸው ከቶም እንደማይቻለህ ተረዳ  ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትዝብት - ደርሶ መልስ ዲያስፖራ (ኢትዮጵያ ደርሶ የመጣ ዲያስፖራ የሚነግራችሁ እውነት) (አንደኛ)

ዛሬም ፤  ይኽቺ ዓለም ፤  እንደትናንቱ     ፣ በነጭ ቀጣፊዎች ና   በጥቁር ውሸታም እኩዩ ምግባር  ክፉኛ እየተበጠበጠች እንደሆነም እወቅ ።  ዓለም  ሠላም የራቃት ቀጣፊ ና ውሸታም በሽብር የሚያምኑ አናርኪስቶች የፖለቲካው ፊት አውራሪ ሆነው በመገኘታቸው ነው ፡፡

በታሪክ  ሠረገላ ወደኋላ ጋልበህ ብታሥተውል ፤ ቀጣፊ ና ውሸታሞች ናቸው የዓለም ሠላም ጠንቅ ፡፡ የዓለምን ሠላም በመጀመርያ ያናጉት አናርኪስቶቹ እንደሆኑ ታሪክ ይነግረሃል ፡፡ ( አናርኪስቶች ከ19 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም ላይ በተደረገ ሽብርና የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ጉልህ ሚና ነበራቸው በፈረሳይ አብዮት ፤ በሶቬት ህብረት  እና በስፔን የእርስ በእርስ ጦርነት በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈዋል ፡፡ … )

ከዚህም በላይ ፣ አናርኪስቶች ፤  በውሸት እና በሽብር ዓለምን አወዛግበው ፤  አንደኛው የአለም ጦርነትን እንዲቀሰቀስ  አድርገዋል ፡፡ አንደኛው የዓለም ጦርነቱ  ሐምሌ 28/ 1914 ዓ/ም ተጀምሮ ጥቅምት 11 / 1918 ዓ/ም እአአ እንዲያበቃ አንድ ቁጥር መንስኤዎቹ እነሱ ነበሩ ፡፡ ይህንን ጦርነት  የቀሰቀሰው የአናርኪስቶች የሽብር ትውራ ነበር ። የአውሰተሮ ሀንጋሪ መስፍን አርክዱክ ፍርዲናንድ በእነዚህ የሽብር ቡድኖች ነበር የተገደለው ፡፡ እናም ለጦርነቱ አንዱ መንሴ ይህ የሽብር ድርጊት ነበረ ፡፡

በዚህ በአንደኛው የአለም ጦርነት 20 ሚሊዮን የዓለም ህዝብ አልቋል ፡፡ 21 ሚሊዮኑ ደግሞ ከባድና ቀላል የመቁስል አደጋ ደርሶበታል ፡፡ ዛሬም በዓለማችን  በሽብር ፣ በግድያ ፣ በጭካኒያዊ ድርጊት ንፁሃን እንደ ቅጠል ይረግፋሉ ፡፡  ወደስልጣን ለመምጣት የሚፈልጉ የአፍሪካ ቅጥረኛ አናርኪስቶችም  ግድያና ማፈናቀሉን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል ፡፡  የደሃው ህዝብ ሰቆቃ ፈፅሞ የሚገዳቸው እንዳይደሉም በገሃድ እየታየ ነው ፡፡  ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትግራይን መስቀል ስለመሸከም (ተመስገን ደሳለኝ)

ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ፤ በቀጣፊው  ሂትለር ምላስ የተስፋፋ እና  በቀጣፊ ምላሱ መንጋውን ጀርመናዊ አነሳስቶ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነትን ያባባሰ ነው ፡፡ በዚህ ጦርነትም 3 % የዓለም ህዝብ አልቋል ። ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ህዝብ ፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የጦርነቱ ሰለባ ሆኗል ፡፡ 2.3 ቢሊዮን ( ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን )  ነበር ፤ የዓለም ህዝብ በ1940 ዓ/ም እኤአ ፡፡ ( ጦርነቱ በ1939 መስከረም አንድ ቀን ተጀምሮ ፤ መስከረም 2 ቀን 1945 ዓ/ም አበቃ ፡፡ እኤአ ፡፡ )

ይኸው ዛሬ አራተኛ የሚባል የሌለው 3ተኛው የዓለም ጦርነት እንዲጀመር ፤ የማይቆም የሰው ልጅ ደም እና እንባ እንዲፈስ ፣ የዛሬው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ፣ በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ነው ። ” በቃ ! ጦርነቱ ይቁም ። ዩክሬን የኔቶ ዓባል አትሆንም ! ” ማለት ይችሉ ነበር ። ክቡር ፕሬዝዳንቱ  ፡፡ የኒኩለር ባለቤት ከሆነ ኃያል አገር ጋር እብድ ፣ እብድ ከሚጫወቱ የሠላም አማራጭ  ቢከተሉ ኖሮ ሚሊዮን ዩከሬናዊያን ዛሬ ፤ ከሞቀ ጎጆቸው አይፈናቀሉም ነበር ። ምን ያደርጋል ፤ የአሜሪካ የናጠጡ ቱጃሮች ሥለ ቢሊዮን ዶላራቸው እና ስለምቾት ና ድሎት እንጂ ፣  ሥለተርታው የዓለም ህዝብ  ህይወት እና ኑሮ የሚገዳቸው አይደሉምና  ከእሳቱ በብዙ ሺ ኪሎሜትር ርቀው ቤንዚል እየላኩ የጦርነቱን እሳት ያፋፍማሉ  ። ትዕቢታቸው እንደ ናቡከደናፆር በመሆኑም መስሜያቸው ጥጥ ነው  ።

ዛሬ በዓለም ኃያላኖች ዘንድ የናቡከደናፆር  ተዕቢት በመንገሱ ሠላም ጠፍቷል ።  ሁሉም ኃያላን በተለይም የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መሪዎች በሰው ቁሥል እንጨት የሚሰዱ ትዕቢተኞች ናቸው ። ሚሊዮን ዩክሬናዊ ቢያልቅ ደንታም የላቸውም ። ትህነግ በማለት ፤ ራሱን በገንጣይነት የሰየመው ፤ ” በጠብ__መንጃ ” የሚያምን ዘረኛ ቡድን ፣ በገዛ አገሩ ዜጋ ያውም በጎረቤቶቹ ላይ ጠብ መንጃውን በማንሳት ድንገተኛ ጥቃት ሲሰነዝር ፣ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታት  እንዴት በየሚዲያቸው ፣ የውስጥ ችግራችንን እንዳጫጫሱት አስተውሉ ፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ ድርጊታቸውን ትታዘባላችሁ ፡፡ ቱጃሮቹ የአሜሪካ መሪዎች  ጨካኝነታቸውን እና የእብድ ገላጋይነታቸውን በተጨባጭ በዩክሬን ሀብት ውድመት መረዳት ይቻላል  ። አማራና አፋር ክልል ገብቶ ወያኔ ንፁሐንን እሥከ ቤት እንስሳቱ ሲጨፈጭፍ ና ንብረት ሲያወድም ” እሰይ  ! ደግ አደረገ  ! …” ነው እኮ ያሉት ። ከዳቢሎሳዊ ድርጊቱ ጎን በግላጭ  ነው ፤ የተሰለፉት ። ዛሬም እንደዛው ፡፡ በእብድ ገላጋይነት ተሰማርተው ይገኛሉ ፡፡

እናም ይኽቺ  ዓለማችን ፣ ፈጣሪያችን ፤ ከትዕቢት የፀዳ ፣ በትህትና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ መሪ እዛና እዚህ ቀብቶ ካልሰጠን በቀር ዓለም በእብድ ገላጋዮች ወደተረትነት ለመቀየር ዳርዳር እያለች መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ፡፡ ከአሜሪካ የእብድ ገላጋይነት አንፃርም ፣ አራተኛ በሌለው ጦርነት ዓለም እንዳትጠፋ እንሰጋለን ።…

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ መሬት ችብቸባ፤ በታሪክ እይታአጼ ዮሐንስና አጼ ካሌብ ቢኖሩ አንዴት ያዝኑ!

ዓለም ዛሬ ከእብድ ገላጋይ መሪዎች ይልቅ ፣ እውነተኛ ትህትናን የተጎናፀፉ አርቆ አሳቢና አስተዋይ  መሪዎች  እጅግ ያስፈልጓታል ፡፡  ከሌላው የተሻለ ዕውቀት ያላቸው ሆኖም እውቀት አለኝ ብለው የማይመፃደቁ ” ገና ምንም አላወቅሁም ። ለእናንተ የበዛ የመስላል እንጂ እውቀቴ ፤ ለእኔ ኢምንት ነው ። ይልቁንስ እኔ የማላውቀው እውቀት በእያንዳንዳችሁ  አእምሮ ውሥጥ አለ ። እና በማወቅ አንፃር የማላውቀው ሥለሚበዛ እኔ ከእናንተ ወይም ከዜጎች  የሚበልጥ አእምሮ የለኝም ። ” የሚሉ ። ከሚመሩት ህዝብ ለመማር ዝግጁ የሆኑ ፤  የህዝብን ኑሮ ለማጣፈጥና ህይወቱ በአበሳ ብቻ  የተሞላ እንዳይሆን ፤ ድህነትን ና ድንቁርናን  ለማጥፋት  ሌት ተቀን የሚጥሩ  መሪዎች የዛሬዋ  አለማችን ያስፈልጋታል ፡፡

ዓለም ወደዳግም ትንሠኤ ፣ ወደሠላም መንገድ ፤ የሚወስድ እንደ ክርስቶስ  ” ሠላም ለእናንተ ይሁን ! ” የሚል ፤  አስተዋይ መሪ  በየአገሩ እንዲኖራት  ብትመኝም ፣ እስከዛሬ   ለማግኘት አልታደለችም ።

በዓለም ደረጃ ኃያላን የሆኑ የመንግሥታት መሪዎች ፤ በአመዛኙ ፤ ከውይይት ይልቅ ባላቸው አውዳሚ የጦር መሣሪያ ኃያልነት በትዕቢት የተሞሉ ናቸው  ። ስለሰላም ሳይሆን ሥለሚሸጡት መሣሪያና ሸቀጥ ብቻ ነው የሚጨነቁት ፡፡ የህዝብ መፈናቀል ፤ መራብ ፤ መታረዝ ከቶም የማይገዳቸው ናቸው ፡፡ የዓለም ህዝብ ፤ ራሳቸውን ዝቅ ፣ ዝቅ የሚያደርጉ ግን ደግሞ በእግዚአብሔር ጥበብ የበለፀጉ መሪዎችን  ፤ ፈጣሪ  ፍቃዱ ሆኖ እሥካልሰጠው ግዜ ድረስም ፤ ዓለም የሤጣንን ሃሳብ በሚያራምዱ ጥቂቶች ወይም  ” ገንዘብ ወይም ሞት ! ” በሚሉ  የኃያላን መንግሥታት መሪዎች ፤ ሠላሟ መደፍረሱ ና ክብሩ ሰው ፤ እንደ ውሻ በየሜዳው ለዘላለም ማንቀላፋቱ ከመቸውም ከፍለ ዘመን በከፋ መልኩ ነገም ይቀጥላል ፡፡ ሁሉን ቻዩ ፈጣሪያችን እስካላቆመው ጊዜ ድረስ ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share