May 5, 2022
18 mins read

የጭካኔ ጥጉ የቱን ያህል ይረዝማል? – እውነቱ ፈረደ

Shine 1ይህች ጽሁፍ ቀጥተኛ ጥያቄዎችን እያነሳች ምን ያህል እዉትን ለመጋፈጥ መፍቀዳችንን እንድንመሰክር የምታበረታታን ናት።

የጭካኔ ጥጉ የቱን ያህል ይረዝማል ?ክብደቱስ ምን ያህል ይሆን ?ህፃናትን ሆን ብሎ ማስራብና ዋይ ዋይ እያሉ ወደ ሞት እዲጟዙ ማድረግ የሚያሾም የሚያሸልም በረከት ወይስ የሚያዋርድ መርገምት? ቅዱስ መጸሐፍ እንዲህ ይላል፤-“ህፃናትን ወደኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸዉ, አትከልክሏቸዉ,” ከዚህ የምንረዳዉ እግዚአብሄር በህፃናት ደስ እንደሚሰኝ እየሱስ ክርስቶስ ሲመክር ነዉ።እኛ ግን እንደክርስቶስ  ምሳሌነት የኢትዮጵያን ህፃናት ዘር ሳንለይ ያድጉ ዘንድ ተንከባከብናችዉ ? መንከባከቡ ቀርቶ በህይወት እንዲኖሩ ፈቀድንላችዉ ወይስ ቀጠፍናቸዉ?

ሃቁ የቱን ያህል ቢመረንም በደል ስለደረሰባቸዉ የአገራችን፡የትግራይ ፣የአማራ፣የአፋር፣የኦሮሞ፣የቤንሻንጉል የኦሞ — ….ወዘተ ህፃናትና ከነህይወታቸዉ በእሳት ስለተቃጠሉት ወገኖቻችን ሳናነሳ አንለያይም።

የአንድ ቱንዚያዊ ህይወት(Mohamed Bouazizi-17 dec 2010) በእሳት መቃጠል የመንግስት ለዉጥ እንዳስከተለ አታዉቁምን? የኛዎቹ ግን የአንድ ደቂቃ ብሄራዊ ሀዘን ሳይደረግላቸዉ መዘንጋታቸዉን ሳስብ ምንኛ ጭካኔ ዉስጥ እንዳለን እረዳለሁ።ለኢትዮጵያም አገሬ አዝናለሁ።

እናት የልጆቿን እልቂት በምን አንጀት ትችላለች ? እናንት የትግራይ እናቶች እንባችሁ ከአይናችሁ ብቻ ሳይሆን ከመሀፀናችሁ እንደ ዥረት ሲንፈቀፈቅ እንዴት ቻላችሁት?ለራሄል እንባ ምላሽ የሰጠ ሃያሉ አምላክ ስለ ትእግስቱ ና ምህረቱ እንጂ ፈጥኖ እንደሚፈርድ አትጠራጠሩ ። በዘረኝነት የተጋረዳችሁ ያገሬ ልጆች ግብዝ አትሁኑ መፅሀፍን አንብቡ።

የትግራይ ፣የአማራ፣የኦሮሞ፣የቤንሻጉል፣የአፋር— የሌሎች አካባቢዎች ህፃናት የማንና ፣ማን ናቸዉ? የኢትዮዽያ ልጆች አይደሉምን? እነዚህ የአገራችን ህፃናት አምላክ የሚወዳቸዉ አይደሉምን ? መላእክትስ ከሰማያት ወርደዉ የሚራሩላቸዉ አይደሉምን? እና ለምን፣ እኮ ለምን- በረሀብ አለንጋ ሲቆሉና በጥም ሲንገላቱ፣ለአንዲት ቀንም ቢሆን የመኖር ተስፋ ሊኖራቸዉ ከቻለ ብሎ ያልተወለዳቸዉ የዉጬ አለም ህብረተሰብ የለገሳቸዉን ምግብና መድሀኒት እንዳይደርሳቸዉ በታንክና በድሮን መንገድ ዘግታችሁ ጉሮ ወሸባዬ አላችሁ? ለምን ?

በህፃናት እሬሳ ላይ ፊልድ ማርሻል ጀነራል ሌላም ሌላም እየተባባላችሁ አልተሿሸማሁም?ለምን ስለምንስ ብላችሁ ለኢሳያስ፣ ለሱማሌ፣ ለአረብ ቅጥረኛ ወታደሮች የትግራይን ህፃናት ያልፀና አንጀት ቀስፋችሁ ያዛችሁ።ለኢሳያስ የሸለማችሁት ካባ ምን እንዲያደርግላችሁ ነበር?

እስቲ ልጠይቃችሁ፣መልሱን ለራሳችሁና ለህፃናት ልጆቻችሁ በግልፅ መልሱላቸዉ።ስንቶቻችሁ ናችሁ በተለይ የአለም የምግብ ድርጅት ለህፃናቱ ለህወታቸዉ ማቆያ የላኩትን ምግብና መድሀኒት ማሙሽና ማሚቱ እንዳይደርሳቸዉ መንግስትና የኢሳያስ ጦር ሲጨክኑባቸዉ የተቃወማችሁ? መቃወም እንኳን ብትፈሩ፣

(ግን እኮ የመይሳዉ፣ የአባ ዳኜዉ፣ የአሉላ፣ የባልቻ ፣የጎበና የሌሎች ስመ ጥሩዎች የኒዚያ የጀግኖቹ ልጆች ነን ትሉ አልነበረምን ?) ዝም ማለት ስትችሉ ዝም አላችሁ ወይስ ከግፈኞች ጋር በመቆም በእነዚያ እምቦቅላዎች ላይ ፈረዳችሁ??

ድፍረት አይሁንብኝና ያገሪን የሀይማኖት መሪዎች ጳጳስ፣ቄስ ፣ሼክ ፣ፖስተር፣ሌሎችም ፣ፈጣሪያችን የሚወዳቸዉን ህፃናቶች የምድር መንግስታትና በዘረኝነት የታበዩ ተባባሪዎቻቸዉ በረሀብ ፣በበሽታ ሲፈጇቸዉ ምን አላችሁ? እንደ

ራሄል የመረረ ለቅሶ ባታለቅሱላቸዉ እንኳን፣ አንዲት ጠብታ እንባ እንዴት ነፈጋችኋቸዉ ? አይ ጵጵስና አይ ፓስተርነት አይ ሼክነት ?(ይህን ስል ለግለሰብ ያደሩትን እንጂ ለእዉነት የቆማችሁትንና ምህረትን የምትለምኑትን አይደለም።) ሁሉም እራሱን ይመርምር።

ከእንግዲህ የአገሬ ህፃናት ማንን ተስፋ አድርጋችሁ ፣በማን እጅ እንጠመቃለን ብላችሁ:ትወለዳላችሁ? አልወለድም ብላችሁ አምፁ ።ለቀጣይ ህይወታችሁ በማይሳሳ ትዉልድ መሃል ምንስ ታደርጋላችሁ? ይህ ትዉልድ እናት አገር ኢትዮጵያ እንደ እንደራሄል እንባዋን ታንባ ብሎ ፈርዶባታልና።

ለቂም በቀል በሚያዘጋጃችሁ የፖለቲካ ስርአት ዉስጥ መኖር ምን ይጠቅማችኋል? ምኑስ ይናፍቃችኋል ?

አዉቃለሁ– በለምለሙ የአገራችሁ ሜዳ ላይ መቦረቅ፣ አባሮሽ መጫወት ፣ባልና ሚስት መጫወት፣ ቡሄና አበባይሆሽ፣ቆርኪና ብይ መጫወት ፣ከዬኔታ ጋር ዳዊት መድገም ፣አንዳንዴም ስታጠፋ ያች የምታመዋ የዬኔታ አርጩሜ ፣በመዋለ ህፃናት ከእኩዮቻችሁ ጋር መደስት፣ወደ ትምህርት ቤት በሄዳችሁበት የመጀመሪያ ቀን የእናቶቻችሁን ቀሚስ አልለቅ ብላችሁ ያለቀሳችሁት ሙልቅቅ ያለች ለቅሶ፣የመሳሰሉት ሌላም ሌላም የሚናፍቅና የሚመኙት ነዉ ።

ግን እኮ ይህ ሁሉ የሚኖረዉ የሚወዳችሁ ህብረተሰብ የሚንከባከባችሁና ሰላማችሁ እንዲበዛላችሁ የሚተጋ የሰላም መንግስትና ስርአት ሲኖር ነዉ።እስቲ መለስ ብለን የኛን የልጅት ጊዜ እናስተዉል ፣በየሰፈራችን የሚኖረዉ ሰዉ የትውልዱ ስፍራ ቢቆጠር ከሁሉም ኢትዮጵያ አካባቢ ነበር ።ለነገሩማ እንደዛሪዉ በዘር ሳንካለል የተደበላለቅን አልነበርን? የእከሌ ልጅ የማን ዘር ሳይባል መንደርተኞዉ ሁሉ እንደ ታላቅ እህትና ወንድም ፣እንደአባትና እናት ሆኖ ያሳድገን ነበር።

እረ ለመሆኑ ምንስ ብትከፉ እናት አገርን ለገነጣጠለዉ እናንተ ኢሱ ለምትሉት ኢሳያስ ፣ለፀረ ኢትዮጵያ የሶማሌ ወራሬዎች፣ ለአረብና ለቱርክ ድሮኖች የትግራይ ህፃናቶችን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ?ይሁዳ ለገንዘብ ሲል ጌታዉን ከዳ፣የኞዎቹ ደግሞ እነርሱ ለማይቀመጡባት የአሽከርነት ቦታ እንኳን ለማያገኙባት ለግለሰብ ወንበር ሲሉ ህፃናትን ከዷቸዉ።

ከወያኔ ጋር መዋጋት አንድ ነገር ነዉ፣ ግን ነፍስ ያላወቁ ጨቅላ ህፃናት ላይ የረሀብ እሳት ማንደድ የጭካኔዎች ጥግ ካልተባለ ሌላ ምን ይባል ይሆን?

ስሙን ለመጥራት የማልፈልገዉ አክቲቪስት ነኝ ባይ ” የጭካኔን ጥግ አሳይዋቸዉ” ብሎ ከሰበከዉ ጋር ተስማማችሁ ማለት ነዉ ? ይህ ታሪክን የከዳ ግለሰብ ሲደላዉ አማራ የለም የሚል :ዛሬ ደግሞ ሌላ መሆኑን ለምን መዘንጋት ፈለጋችሁ? short memory የተባለዉን አረጋገጣችሁት ማለት ነዉ።

እረለመሆኑ በቅርቡ የስርአቱ ቁንጮ ሲጠራችሁ ግልብጥ ብላችሁ አዲስ አበባ ከመሄዳችሁም በላይ ንጝሩን ለመስማትና “ቡራኬ” ለመቀበል ገንዘብ ከፍላችሁ አዳራሹን አልሞላችሁትም?

እናንተስ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የተደራጃችሁ እርዳታ አሰባሳቢ ድርጅቶች’ በጎ ፈንድ ሚ ‘GO FUND ME አማካይነት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የምትሰበስቡ በርግጥ ብዙ መልካም የሚያስመግን ስራ ሰርታችኋል በቅርቡ እንኳን ወደ ደቡብ ጌዲዮ አካባቢ ተጉዛችሁ ለተፈናቃዩ መጠለያ ሰራችሁ ለሕፃናቱ ተስፋ ሰጣችሁ። በርቱ እላለሁ። ግን እኔ ለጥያቄ ይበቃል ብዬ የገመትኩትን ላንሳ።

በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ያላችሁ ኢትዮጵያዊ የግብረሰናይ ድርጅቶች፣የተጎዱ ኢትዮጵያን እንርዳ ብላችሁ ለመልካም ስራ ስትሰበሰቡ የትኛዉ ህዝብ ነዉ ወደ አእምሮአችሁ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የሚመጣዉ? እኔ የሚመለከተኝ የክልሌ እንጂ ሊላዉ አይደለም ብላችሁ ታስባላችሁን? አማራዉ ለትግሪዉ አና ለሌሎችም፣

ትግሪዉም ለአማራዉና ለሌሎችም፣ ኦሮሞዉም ለሁሉም፣ እንዲህ እያላችሁ ነዉ የምትነሳሱት? ወይስ ለኔ የኔ ብቻ ሆነናል? አንዱ ክልል ሲራብ ሌላዉ እንደራሱ ካልተሰማዉ ጉዞአችን ወዴት ነዉ? አስቡበት።

አሁን ያለንበት ወር የፋሲካ(ጌታ ህፃናትን አጥብቆ እንደሚወድና እንደሚራራላቸዉ አስተዉሉ)እንዲሁም የረመዳን ወቅት ነዉ ።እንግዲህ ባላችሁ መጠን በምግብ በመጠጥ ልትብነሸሹ ነዉ።ይህ እንደየ ልምዳችንና ባህላችን ማድረጋችሁ መልካም ይመስለኛል።ግን በዚህ ጊዜ በየትኞዉም ኢትዮጵያዊ ግዛት በዋናነት በኢሳያስና በአብይ እንዲሆም በሌሎች ለመደራደርያነት፣ በማያዣነት፣ ለተያዙ እምቦቀቅላ ህፃናት የሰቆቃ ኑሮን በዝምታ ነዉ የምታልፋት ወይስ ምን አስባችኋል?

አንድ ማስተዋል ልንገራችሁ, —

የራሄል እንባ ወደ ፈጣሪ ደርሶ ፍርድን እንዳመጣ ሁሉ፣ኢትዮጵያም ለህፃናት ልጆቿ በእሳት ለተቃጠሉት ልጆቿ፣በባለጌ ስድ አደጎች ለተደፈሩ ወጣቶች፣ እናቶችና መነኩሴዎች፣ የገዳም ሰዎች፣ወደ ገደል ወደ ወንዝ ለተወረወሩት፣በአደባባይ ለተሰቀሉ ፣ ለተቃጠሉ የእምነት ቤቶች በቓንቓችዉ ምክንያት ብቻ ለተፈናቀሉ ፣ለተሰደዱ በሊቢያ በረሀ ስለእምታቸዉ ሰማእት ለሆኑ፣ በየእስር ቤት ለሚማቅቁ ፣ለሌሎችም የዘር ፓለቲካ ስርአቱ ሰለባ ለሆኑት ሁሉ ቸሩ አምላክ እስከ አሁን እንደታገሰን ጨርሶ እንዲምረን የምንፀልይበት ጊዜ ላይ ናት ።እስቲ ሁላችንም ወደልቦናችን ተመልሰን እንርዳት።

ይህን ፅሁፍ ስታነቡ ድርጊቱ ተፈፅሟል ወይስ አልተፈፀመም ላይ ከማቶከር ይልቅ በማን ተፃፈ ለምን ተፃፈ የሚለዉ የመጀመሪያ ትኩረታችሁ ሊሆን አይገባም ። የፅሁፍን ጭብጥ ትስታላችሁና።

የዘር ተዋናዮች መድሃኒትና ምግብ የነፈጋችዃቸዉ ህፃናት በሚወዳቸዉ በክርስቶስ እቅፍ ዉስጥ ሆነዉ በህፃን አንደበታቸዉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ ከመላክት ጋር እየቦረቁ የደስታና የሰላም ህይወት እየኖሩ ናቸዉና ፣

እናት አለም ኢትዮዽያ ከእንግዲህ ስለነሱ አታልቅሺ ። እንባሽ በአይንሽ አይታይ ። ይልቁንም ልምከርሽ ፣ ማንባት ካለብሽ በገዛ ወገኖቻቸዉ ላይ የወጭ ወራሪ ጦር አምጥተዉ የጭካኔን ጥግ ላሳዩት ለኢሳያስና ለአብይ ተባባሪዎች ነዉ።

መደምደሚያ፣

ለዚህ ፅሁፍ መደምደሚያ ይሆናል ብዬ ያሰብኩት የሚከተለዉ ነዉ።እናንተስ ትማማላችሁ?

በዚህ ትዉልድ ያለን ትዉልዱን የመንከባከብና የማሸጋገር ሀላፊነት ያለብን በሰብአዊነታችን ከስረናል። ተጨካክነናል።

የአገራችንን ሉአላዊነትና ዘላቂነት ኪሳራ ላይ ጥለናል።ለሕዝብ በተለይም ደካማዎችን ህፃናትን ይጠብቃል የተባለዉ መንግስት የመፍትሄ ሳይሆን የችግር መንስኤ በመሆኑ ከስሯል።

የባላገሩ(tv) አይድል፡ላይ በመድረክ ቀርበዉ በእንባ ተሞልተዉ ያንጎራጎሩትን ህፃን ቅዱስና ታዳጊ አፎንያ አስታዉሱ(ዩቲዉብ)

አፎንያ፡–ለህፃን ቅዱስ ልትል የምትችለዉ የማፅናኛ ግጥም (እንግርጉሮ)ይህን ይመስለኛል፧

“ምንም ህፃን ብሆን እንደሴትነቴ እንባህን ለማበስ አለኝ ብልሀት፣

ይህ ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ዳግም እንዳታለቅስ እሸሽገሀለሁ በመሀፀኔ ዉስጥ።

መልካም ጊዜ መጥቶ ኢትዮጵያ እናታችን እስክትሆን ደስተኞ ፣ እንባህ ለምን ይፍሰስ ዉለታ ለማያዉቅ ለትዉልድ ደመኞ ። እኔ አንተን አርግዤህ፣ በመሐፅኔ አኑሬህ ሸሽግሀለሁ፣

አደራ ጠባቂ እምዬን የሚወድ፣ ትዉልዱ ሲመጣ አንድ ቀን -አምጬ እኔ ወልድሀለሁ። ያሳላፈካቸዉን የለቅሶ መድረኮች በምጥ ስቃይ ጩኸት ፣ለናት አገሬ ስል እኔ ከፍልሀለሁ።

ከዚያ በኋላማ ለቅሶዉ ሳቅ ይሆናል

ስንት አሳልፈናል፣

ስንት አሳልፈናል

ስንት አሳልፈናል።

 

ከዚያ በኋላማ ለቅሶዉ ሳቅ ይሆናል

እዉነቱ ፈረደ፣

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop