የአብይ ትዝብት በአብይ ፆም – ከእውነቱ ፈረደ

Abiy wshetይህ የትዝብት ጽሁፍ በጥያቄና መልስ ላይ የተመሰረተ ነው።ጠያቂው እውነቱ ፈረደ ሲሆን ተጠያቂው አዲሱ የአሕአዴግ ጠ/ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ዶር አብይ አህመድ ና ተፎካካሪ ነን ባዮች ናቸው።

ጥያቄ- ሊቀመንበርና ጠ/ሚንስትር ሆነው በመመረጥዎ እንኳን ደስ አለዎት፤ግን የማን ሊቀመንበርና በማን የተመረጡ ጧሚንስቴር ነኝ ብለው ያምናሉ?

መልስ – ዶር አብይ — እኔ ኢሕአዴግ የመረጠኝ ፣የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ነኝ።ጠቅላይ ሚኒስትርነቴም በኢሕአዴግ ምክር ቤት በተከናወነ ምርጫ ያገኘሁት ነው።
ተፎካካሪ -፣የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ቢሆኑም በሕዝብ ትግል የመጡ በመሆንዎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና የምርጫው ውጤት ነዎት ፤ስለሆነም በኢትዮጵያ ሕዝብ ተመርጠዋል ብለን እናምናለን።
ዶር አብይ-እናንተ ካላችሁ ይሁን፤እኔ ግን ለህሊናዬ መዋሸት ስለሚከብደኝ በኢሕአዴግ ከኢሕአዴግ ነው የተመረጥኩት (ክርስቲያን መሆኔንም አትዘንጉት፤በአብይ ጾም አታስዋሹኝ)።

ጥያቄ የእስረኞች መፈታት ፣የማእከላዊ እስር ቤት መዘጋት የእርሰዎ ጥረት ነው ብለው ያምናሉ?አስቸኳይ ጊዜ አዋጁስ ቢነሳ የሚመሰገኑት እርሰዎ መሆን አለብዎት?

መልስ- ዶር አብይ – በሽህ የሚቆጠሩ እስረኞች በአቶ ሃይለማርያም ጊዜ ተፈተዋል፤ማእክላዊም የተዘጋው በእሳቸው ጊዜ ነው።ይህ ደግሞ የኢሕአዴግ ውሳኔ ነው።ኢሕአዴግ አሰረ፣ኢሕአዴግ ፈታ።እኔ ሥራዬን በአግባቡ መቼ ጀመርኩና ነው?ወዴት ጠጋ ጠጋ!?በኮማንድ ፖስቱ ውሳኔ የታሰሩ ለኮማንድ ፖስቱ በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት መፈታት ያለባቸው ይፈታሉ፤ይህ ኮማንድ ፖስቱ ሲቋቋም የተደረሰበትና የተደነገገ አሰራር መመሪያ አለ።ብዙም ልትደነቁ አይገባም። ተፎካካሪ- እኛስ ተደንቀናል፤ገና ሥራ ሳይጀምሩ ሰዎችን ካስፈቱ የቀድሞችም ቢሆኑ የተፈቱት የእርሰዎ የውስጥ እጅ (ግፊት)ቢኖርበት ነው ብለን እናምናለን፤ስለሆነም እርሰዎን ነው ማመስገን የምንፈልገው።እንኳንስ ይችን የዝምብ ጠንጋራም እናውቃለን።

ዶር አብይ –አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቋቋመበትን ምክንያት ሲያጠናቅቅ ይነሳል።አሁን ደግሞ የተሻለ መረጋጋት (በእናንተ ትብብር)ስላለ በቅርቡ እንደማነሳ በኢሕአዴግ ምክር ቤትም ሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ የሚወሰን ይመስለኛል።

ተፎካካሪ – ቢሆንም ፣ቢሆንም ዋናው ሞተሩ እርሰዎ ነዎት፤ያለእርሰዎ ምንም መልካም ነገር አይመጣምና ክብርና ምስጋና ለእርሰዎ ይሁን!እኛ በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ያለነው በስም ተቃዋሚዎች ሳንቀር ብዙዎቻቻን እርሰዎን የኢትዮጵያ ሙሴ አድርገን ቆጥረንዎታል።

ዶር አብይ – መታወቅ ያለበት ነገር እኔ የኢሕአዴግ አባል እንጂ የተቃዋሚ ድርጅት አባል አይደለሁም፤የኢሕአዴግ የሥራ አመራር በመሆን ስርዓቱን ሳይሆን አሰራሩን ለመለወጥ የምፈልግና የምሞክር ለኢሕአዴግ የለውጥ ሃዋርያ መሆኔ ሊታወቅ ይገባል።

ጥያቄ በኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት ያለዎት እምነት እስከምን ድረስ ነው?

መልስ ዶር አብይ –

በእርግጥ በድርጅቴም(ኦፒዲኦ/ኢሕአዴግ)ሆነ በግል አመለካከቴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋነኛ ቅራኔ የነበረው፣ለኢሕአዴግም የትግል ምክንያቱ በብሔር ብሔረሰብ ዙሪያ ያለው ችግር ነው ብለን ታግለናል፤አሁንም እምነታችን ከዚያ የተለዬና የራቀ አይደለም።በዚያም ታግለንበት አሸንፈናል።በመንግሥትነት ይህንን አሳባችንን በሕገመንግሥቱና በፌዴራል አወቃቀር

በመጠቀም አስከብረናል።የአገራችንም ገዢ ሃሳብ ባለቤት ሆነናል።ከዚህ በዃላ ልማትና ሰላም ላይ ነው ትኩረታችን።አዎን በኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት ፅኑ እምነት አለኝ።ይህ እምነት የእኔ ብቻ ሳይሆን የአቶ ሃይለማርያምም ጭምር ነው። ታዲያ የእኔ ብቻ በማድረግ ለምን ትደነቃላችሁ።አያምንም ብላችሁ ጠርጥራችሁኝ ነበር?መቼም እናንተ የዝምብ ዓይናማ ትለዩ የለም?

ተፎካካሪ – እርሰዎ በጣም ትሁት በመሆንዎ እንጂ እውነቱን ያውቁታል።የሌሎች ሁሉ ማስመሰል ነው።የእርስዎ ግን ከልብ መሆኑን መረዳት ከባድ አይደለም።ለዚህ ነው እርሰዎን የብሔር ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን የአንድነታችን ተስፋና ምልክት ነዎት የምንለው።

መልስ-ዶር አብይ – እናንተ ነብዮች ናችሁ ልበል?ገና በ7 ዓመቴ ተመረኩ፤ትንቢትም በቅርቡ ነበረኝ፣ዛሬም ደግሞ ይኸው ከእናንተ አንደበት መልካም ትንቢት ሰማሁ፤ለመሆኑ የየትኛው ቸርች ነብያት ናችሁ?

ጥያቄ በንግግረዎ ላይ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ የሚል ቃል ብዙ ጊዜ ይሰማል፤ይህ የኢሕአዴግ አዲሱ አቋም ነው ?ወይስ የግለዎ?

መልስ ዶር አብይ — እኔ እስከማውቀው ኢሕአዴግ የታገለው ከኤርትራ መለስ ላለችው ኢትዮጵያ ነው።እስከአሁንም ይህችን ኢትዮጵያን ጠብቀናታል።በእርግጥ አቶ መለስ ይህንን ቃል አይጠቀሙም ነበር።ለምን ለሚለው መልስ የለኝም።አቶ ሃይለማርያም ግን ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ብለዋል።ልዩነቱ እኔ በአንድ ንግግር ብቻ ብዙ ጊዜ አትዮጵያ የሚል ቃል ተናግሬያለሁ።አንድ ነገርም ስለእናንተ ሰምቻለሁ።ዶር አብይ ከ40 ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ አለ ብላችዃል፤ምን አቆጣጠራችሁ?አንዴም ልበል አርባ ጊዜ ዋናው መልእክቱ ይመስለኛል።እናንተ ግን ለምን ከራሳችሁ ጋር ትቃረናላችሁ?ስለ ኤኮኖሚው እድገታችን ቁጥሩን ከፍ አድርገን ስንናገር አልተደሰታችሁም፤አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል አብዝተን ስንናገር በጣም ድጋፍና ውዳሴ አዥጎደጎዳችሁ፤ለመሆኑ ደሃ ኢትዮጵያን ነው የምትናፍቁት?የስሟን መነሳት እንጂ እንደአገር መኖሯን መፈለጋችሁን እጠራጠራለሁ።የውጭ ጠላቶቿም እኮ በስሟ ይጠሯታል።ምን ብዬ እንድጠራት ጠብቃችሁ ነበር?

ተፎካካሪ- ስለኢትዮጵያዊነት ተቃዋሚ ተፎካካሪ ነን የሚሉት እንኳን እንደ እርሰዎ ልብ የሚማርክ የተናገረ የለም።ይህም ሃቅ በእኛ በኩል እርሰዎ የኢትዮጵያ ጠበቃና አዳኝ ነዎት እንድንል አሳምኖናል።

ዶር አብይ አመሰግናለሁ።የእኔ የተለዬ መሆኑን ምንም የተግባር ሥራ ሳታዩ አመናችሁ?ይቅርታ ለካስ እናንተ ነብይና የዝንብ ዓይን እንኳን መለየት የምትችሉ ናችሁ!

ጥያቄ ኤርትራን በተመለከተ ያደረጉት ንግግርና ጥሪስ?

መልስ ዶር አብይ — ይህ ምን ያስደንቃል?በአቶ ሃይለማርያም ጊዜ የነበረና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ የኢሕአዴግ አመለካከትና አቋም ነው።የእኔ ብቻ አይደለም።

ተፎካካሪ – አይመስለንም።ይህ የእርሰዎ ልዩ ማስተዋልና የጥበብ ውጤት ነው።ኤርትራ ያለ ኢትዮጵያ መኖር አትችልምና መልካም አስበዋል።

ዶር አብይ – የእኔ እንኳን አንዱ ያለሌላው መኖር አይችልም ከሚለው ላይ በመነሳት አይደለም የተናገርኩት። (ይኸው 27 ዓመት ኖርን አይደለም?)ታሪክ፣ መልካም ጉርብትና ያቀራርቡናል፣ለጋራ ጥቅማችንም ይበጃል ከሚል ነው።ግን የኢሳያስን መልስ ሰማችሁት አይደል?ይህንን የምለው አንተ የተናገርከው ሁሉ ትክክል ነው እንዳትሉ ለማሳሰብ ነው።

የሰሞኑ የቢቢሲ ኢንተርቪዉ(ከግንቦት 7) እጅግ ግራ አጋቢ ሆነብኝ።ባንድ በኩል ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት፣ ኢህአዴግ አስገነጠላት፣እያላችሁ ኢትዮጵያዊነትን አዋርዳችኋል በማለት ትኮንኑናላችሁ።በሌላ በኩል ደግሞ ከኢሳያስ ጋር በመቆም ባድመን አስረክቡ ትሉናላችሁ።ታዲያ አስገነጠለ ከምትሉትና በናንተ መሀል ያለዉ ልዩነት ምንድር ነዉ? የቆዳ ስፋትና ጥበት ካልሆነ በስተቀር።እዉነትና ንጋት እያደር ይገለጣል ይሉ የለ።

ጥያቄ ከተፎካካሪዎች ብለው ከሚጠሯቸው በኩል የሚያገኙትን የድጋፍ መልእክት እንዴት አዩት?

ዶር አብይ – በአንድ በኩል አስደስቶኛል፤በሌላው በኩል አሳዝኖኛል።የተደሰትኩት 27 ዓመት ሙሉ የኢትዮጵያ መንግስት ማለት ይተናነቃችሁ የነበራችሁ ዛሬ የኢትዮጵያ መንግስት በማለታችሁ ተደስቻለሁ።

ያዘንኩበት ሌላው ምክንያት ከእውነትና ከዴሞክራሲ አንጻር የነገሮችን አመጣጥ ለማዬት ስሞክር ነው፤

ላብራራው

እኔ ገና ሥራ ሳልጀምር ያልሰራሁትን ሠርተሃል፣ይህንንም ሌሎቹንም ለመሥራት ተነስተሃል፣ባለፈው የተሠራ ጥሩ ነገር ካለ

ያንተ እጅ አለበት፣ሲሉ ስሰማ እነዚህ ተፎካካሪዎች(ተፎካካሪዎች ለማለት ያስደፈረኝ ተቃዋሚዎች ስላልመሰሉኝ

ነው)የፖለቲካ ሰዎች ወይንስ እንደ ጥንቆላ የሚቃጣቸው ናቸው ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ።ሌላው ደግሞ ሌሎች የሠሩትን

ሁሉ ለእኔ መስጠት ውሽትን ያሳያልና፤ስለእውነት አዘንኩ።

ከሳምንታት በፊት እኛን እኔንም ጭምር አድር ባይ ፣ተለጣፊ ይሉን ነበር።አሁን ግን ሁሉም ተቀየረና ተራማጅ ተባልን።

ታዲያ ይህን አቋም ምን ይሉታል? ።ሌላው ያሳሰበኝ የዴሞክራሲ ጉዳይ ነው፤ይኸውም ተፎካካሪዎቻችን ይህንን የአቋም

ለውጥ (እኛን የመደገፍ ጊዜ ስጧቸው ማለት ፣ዛሬውኑ ውረዱ፣ዓይናችሁ ላፈር እንዳልተባልን) ያደረጉት ለመሆኑ

ም/ቤታቸውን፣ወይም ሥራ አስፈጻሚ አካላቸውን ሰብስበው ተወያይተውበት ነው? ወይስ የአንድ ሰው ውሳኔ?በእኔ ግምት

ከጊዜው አንጻር ፍጥነታችሁን ስመለከት ተሰብስባችሁ የወሰናችሁት አይመስልም።በሁኔታችሁ አይ ዲሞክራሲ ብዬ አዘንኩ።

ግምቴ ትክክል መሆን አለመሆኑን የየድርጅቶቹ አባላት ህሊና ይፍረድ።ምነው የእኛን ስብሰባ ብታዩት፣ እኔ ስመረጥ

የነበረው ክርክር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ስናደርግ የነበረውን ክርክር ብታዩ መልካም ትምህርት ይሆናል ብዬ

አምናለሁ።ተከራክረን እንጂ በጆሮ ብቻ ሰምተን አልወሰንም፣አቋምም አንወስድም።ለማንኛውም በቪዲዮ የተቀረጸ በመሆኑ

ወደኛ ስትመጡ እንድትመለከቱት ይደረጋል።አለያም ባትወዱትም ከበረከት ስምኦን ጋር መድረክ ይዘጋጅላችዃል።

ተፎካካሪ- ስለ ሰጡን ምክርና ትችት ከልብ እናመሰግናለን።ሃቀኛ ሰው በመሆንዎ ነው የወደድንዎት።በረከት ስምኦንን ካዘጋጁልን እርሰዎ ካሉ እሰዬው ነው።

ዶር አብይ – ሳልዘነጋው የምለው አለኝ።ዶር ፍስሃ የሚባለው ማነው?ምን እያደረገ ነው?የምሰማው እውነት ነው?እኔም ሆንኩ ኢሕአዴግ ገና አንድ እርምጃ ሳንራመድ እሱ ኤምባሲዎችን ለማነጋገር ኮሚቴ አቋቁሟል ማለትን ስሰማ በጣም ገረመኝ።የዲያስፖራ ስባሰገዶችን ይዞ ሊመጣልን ይባክናል አሉ።በእሱ በኩል የእኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ እየተሠራ ነው ማለት ነው። ይህን ማድረጉ ያሰብነውን ለፕሮፓጋንዳ ሥራችን ወጭ ሊቀንስልን ይችል ይሆናል፣በተጨማሪም ሌሎቹ ፊታቸውን ወደ አገር ቤቱ እንዲያዞሩና እንዲተባበሩን ምሳሌ ሊሆን ይችላል።ባለውለታችን ነው።የትግሬ ወያኔ መንግሥት እያለ የሚያጥላላንና የሚጠየፈን አንዱ በዘር ላይ የተመሰረተ ድርጅት ተወካይ እንዴት በአንድ ጊዜ ተገልብጦ የእንተዋወቅ ደብዳቤ ሲልክልኝ ከመገረም አልፌ አስቆኛል፤ተቃዋሚ ነኝ የሚለው በየፊናው ቀድሞ ለመግባት ሲራኮት ማየቱ ደስ ቢያሰኘኝም ዓላማ ቢስ በመሆኑ አሳዝኖኛል።እንዲህ ያለው ዓላማ ቢስ ብናስጠጋውም ጥቅም አይሰጥም፤ነገ ሌላ ሲመጣ ጨርቁን ጠቅልሎ ይከዳል።

ሌላው መዘንጋት የሌለበት እኔ አብይ የምመሰርተውና የምመራው ካቢኔ አገር ቤት ውስጥ ካሉት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና ሕገ መንግሥቱን ከሚደግፉት መሃል ነው።ስለዚህ ሕገመንግሥቱን መደገፍ አንዱ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ መረሳት አይኖርበትም።እኔም ምዬ ቃል ኪዳን የገባሁት ሕገመንግሥቱን አክብሬ ለማስከበር እንጂ መቀየር ቀርቶ ለማሻሻል አይደለም፣ያንን ለማድረግ መብትና ስልጣንም የለኝም።

እኔ ወደዃላ ሄደን ሂሳብ አናወራርድም አልኩ እንጂ የፒሪንስፕል አልባነት ፣መገለባበጥ፣አድርባይነትን እቀበላለሁ ኢሕአዴግን በሠራው ወንጀል እጠይቃለሁ አላልኩም።ድርጅቴን ከነወንጀሉ አክብሬ ሌላ ወንጀል ውስጥ በግላጭ እንዳይገባ እከላከልለት እንደሁ እንጂ ፣ሂሳብ መወራረድ ከመጣማ እኔስ መች ይቀርልኛል?።በዚህ እረገድ ባልወደውም ኢሕአፓ ላይ ፕሪንስፕልድ የሆነ አቋም አይቸበታለሁ።የትኛው ብትሉኝ የነእያሱ ማለቴ ነው።አሁንማ ግንቦት ሰባት፣ሸንጎም ሳንጠይቃቸው የእኛ ሆነዋል ማለት ይቻላል።ለመጠጋጋት ዳር ዳር እያላቸው ነው።በሌሎች ጀርባ እንግባ እያሉ ነው።ሁሉም ተቃዋሚ ሳይሆኑ የአንድ ክፍል ተፎካካሪዎች ሆነናል።ኢሕአዴግንና ሕገመንግሥቱን ለመለወጥ ሳይሆን ለማሻሻል ተሰልፈናል።

ተፎካካሪ- ለኢሕአዴግ ም/ቤት ያደረጉት ንግግር እኛንም መስጦናል፤እርሰዎንም እንድንቀበል አድርጎናል።ባለፈው ስህተቶቻችንም ሆነ በአዲሱ የመገለባበጥ አቋም ብዙ አይታዘቡን፣አያሸማቁን(እርሰዎም እንደ አቶ መለስ አካፋን አካፋ ካልተባለ አይበሉ)

ደር አብይ ስለተቀበላችሁኝ አመሰግናለሁ ።ስዬ አብርሃምን እኮ እንደ ጀግናና አዋቂ ቆጥራችሁ በአዳራሻችሁ ሲገባ ቆማችሁ ያጨበጨባችሁለት፤ሳይውል ሳያድር ደግሞ አወገዛችሁት።ጻድቃንን ታወግዙና በ,ሌላው ጊዜ እንደገና ከፍ አድርጋችሁ መጽሃፉን ትቸረችሩ ገባ፣በኢንተርኔት ትቀባበሉት ጀመር። ከቶ ምን ያሻላችዃል?ነግ በኔ ብዬ በትዝብት እያዬዃችሁ ነው።

ጥያቄ በመጨረሻ ላይ የሚሉት አለ?

ዶር አብይ እስኪ ደግሞ የአንተን የጠያቂውን አስተያዬት እንስማ?

ዶር ተፎካካሪ በእርግጥ ልክ ነው፤የእውነቱ ፈረደን ማጠቃለያ እንስማ።

የእውነቱ ፈረደ አስተያዬት–

የጎባጣ ሰው ሎሌ አጎንብሶ ይሄዳል ይባል የለ! እኔ መጠየቅ ስለምወድ ሎሌውን አንተ ጎባጣ ሳትሆን ለምንድን ነው የምትጎብጠው ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ ፣-ጌታዬ እኔን ከሙሉ ቁመቴ ጋር ቢያዩኝ ሞራላቸው ይነካል ፣ከዚያም ከሥራዬ ሊያባርሩኝ ይችላሉ ብዬ በመፍራት ነው ከሳቸው በበለጠ ጎብጬ የምሄደው አለኝ።

እኔን ግን የገረመኝ ሎሌው ለእንጀራው ፈራ ልበል እነዚህ የዲያስፖራ ተፎካካሪዎች ግን ኢሕአዴግ አልቀጠራቸው፣ከሥራ አይባረሩ፣አይታሰሩ፣ለምን እንዲህ እምነተ ቢስና ብኩን ሆኑ?ያ ሳይወድ በግዱ አጎንብሶ የሚሄደው ሎሌ ድርጊታቸውን አይቶ እናቱ የሞተችበትም ወንዝ የሄደችበትም እኩል ያለቅሳል ብሎ ተርቶ ሳቀባቸው። በሎሌያቸው ሳቅ ተገርመው የሳቀበትን ምክንያት ለማወቅ ወደ ላይ ሲንጠራሩ ዕድሜ ልካቸውን ጎብጠው የኖሩት ሰው ሳያስቡት ቀጥ ብለው ለመቆም ቻሉ። የዘንድሮ አድር ባይነት ጎባጣውን ሲያቀና የቀናውን ጎባጣ ማድረጉ የሚገርም ነው።

እንደፈላስፋዎቹ አባባል እውነት ከሁለት ወንዝ፣ከሁለት ወገን ንግግርና ክርክር የምትወጣ ውጤት ናት።እኛ ግን እውነትን በምን ሁኔታ እናግኛት?በዚህም ውሽት በዚያም ውሸት!ዜሮ +ዜሮ=ዜሮ(0+0=0)

አንድ ነገር ላጫውታችሁ-በዱሮ ጊዜ ከዲሞክራሲ ፈላስፎች በፊት የነበሩ ግሪካውያን እንዲህ ይሉ ነበር፣ መንግሥትን እኛ ያመጣናቸው በመሆኑ ቢያጠፉም እኛ ልንተቻቸው አይገባም፤በእኛው ተመርጠዋልና።

!ይህንን አባባል የዘመኑ ሰውና የግሪክ ፈላስፎች አጣጥለውታል።የሚገርመው ግን በ21ኛው ክ/ዘመን ፖለቲከኞች ነን እያልን ሰሞኑን የምናስተጋባውን ጫጫታና ፈንጠዝያ ግሪኮች ቢያዩ እንዲህ ይሉን ነበር “እኛ ግሪኮች ከስህተታችን ተምረን ስንታረም እናንተ ግን ምን ሆናችሁ ነው የእኛ የጥንት አስተሳሰብ ላይ ያላችሁት?”

በዚህ ላብቃ መሰለኝ፣

ለማንኛውም ሚዛናዊ ነገር ልንገራችሁና ልሰናበታችሁ።- ታሪኩ እንደሚያሳዬው ዶር አብይ አዎን ኢሕአዴግ ያሳደገው የኢሕአዴግ አባል ነው።ባለፉት ዓመታት ውስጥ በኢሕአዴግነት የሠራው ክፉም መልካምም ሥራ ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ። ሆኖም ግን ሰው ነውና ነጻ አዕምሮ ኖሮት ከህሊናው ጋር ተሟግቶ ከእንግዲህ ስሙን በመልካም ሥራ ለማስጠራት አስቦ ይሆናል።የጠቅላይ ሚንስትር የሥራ ክንውን ደግሞ በተግባር የሚታይ የብዙዎች የጋራ ሥራ ውጤት እንጂ በቃልና በጽሁፍ ብቻ የሚገለጽ የስነፅሁፍ ውድድር አይደለም።ክንውን ደግሞ በጊዜ ውስጥ የሚታይ ስለሆነ ” እስኪ በጊዜ ገደብ ውስጥ እንመልከተው” የሚሉ ቢኖሩ ብዙም አያሳማቸውም።በአንፃሩ የተጀመረዉ ከኢሕአደግ ፍልስፍናና መንግስት የመላቀቅ ትግል ፣ የህብረተሰቡ የዘላቂ ለውጥ ፍለጋ ትግል መቀጠል አለበት ሊሉ ይገባል።የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ይባል የለ፣ ለውዳሴው እረጋ ማለቱ ይጠቅማል።አለበለዚያ የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል የሚለው ተረት እንዳይፈርድብን።ሁላችንንም ከዚያ ይጠብቀን!!

ኢትዮዽያ ለዘላለም ትኑር!!!

04/11/2018

Leave a Reply

Your email address will not be published.

ogali
Previous Story

ሰላቶ ከዶጋሊ እስከ አሻድሊ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

Shine 1
Next Story

የጭካኔ ጥጉ የቱን ያህል ይረዝማል? – እውነቱ ፈረደ

Latest from Blog

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ንብረቱ እንዲወረስ የሚደነግግ አዋጅ ቀረበ

ዮሐንስ አንበርብር በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት የመውረስ ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ 10 ዓመት ወደኃላ ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው፣ ንብረት በመንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ድንጋጌ የያዘ
Go toTop