እርግማን ወይስ አለመታደል እጣ?
ውድ ክቡርነትዎ:-
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ወደ ብርሃን እመራለሁ በማለት ፈጣሪን ምስክር አድርገው ለራሶና ድምፅ ለሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ገብተው የስልጣን ኮርቻ ላይ ከተቀመጡ አራት አመታት አለፎት:: ከሚያዝያ 2010 እስከ ሰኔ 2013 እና እስከ መስከረም 2014 አስፈላጊና አጥጋቢ የፖለቲካዊ ለውጥ አለማምጣቶት ሲጠየቅና ሲተች ይሰጡት የነበረው መልስ የሕገ መንግስት ለውጥ ለማድረግ ዲሞክራቲክ ምርጫ መደረግ አለበት ነበር:: ምንም እንኳ ኢሐደግ ለ30 አመታት ይጠቀምበት የነበረውንና አሁንም የእርሶ መንግስት የሚጠቀምበትን በጎሳ ከፋፍሎ ለመግዛት ያመቻቸውን ሕገመንግስት ትክክል አለመሆኑን ዲስኩር ቢሰጡትም በአብዛኛዎቹ ክልሎች ምርጫ ከተደረገበት ከሰኔ 2013ና በሐረር በደቡብ ሕዝቦችና በሱማሌ ክልሎች ምርጫ ከተደረገበት ከመስከረም 2014 ጀምሮ ሕገመንግስቱ ተሻሽሎ ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንቅ የሆነውን የጎሳ አሰላልፍ ፖለቲካን ለማስወገድ ያደረጉት ጥረት ፍፁም አልታየም:: ምነው ቢባል: የሚሰጡት መልስ ትረካና እንደ አሸን እንደፈሉ እግዚአብሔርን ለንዋይ ክብረታቸው እንደሚጠቀሙ መፅሐፍ ቅዱስ ማስተማር ይቅርና የተስተካከለ ሰዋስዉ የያዘ ዓረፍተ ነገር መስራት እንደማይችሉ አጭበርባሪ የኢትዮጵያ “ሐዋርያቶች” ነው:: ስልጣን ላይ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ 28 አመት የበሰበሰ ስርዓትን በሶስት አመት ማፅዳት ስለማይቻል ጊዜ ይሰጣቸው እያልኩ እከራከርሎት ነበር:: በተመሳሳይ እርሶም እውነተኛ ሆነው የኢትዮጵያ አንድነትና የሕዝቦቿ ህብረት ለኢትዮጵያ ህልውና ዋናና ወሳኝ መሆኑን በግልፅና በድርጊት ማቅረብ ነበረቦት:: መናገርና ማስፈፀም የተለያዩ ነገሮች ናቸው:: ኢትዮጵያ ተናጋሪዎች አስመሳዮችና ፎጋሪዎች እጅግ ሞልቷታል:: ወያኔ : ኢሐደግ : የኦሮሞ : የአማራ : የትግራይ : የወልይታ ወዘተ ፅንፈኛ : ሽመልስ አብዲሳ : እስክንድር ነጋ : ጀዋር መሐመድ : በቀለ ገርባ : ልደቱ አያሌው : የኢትዮ 360 ወሬኞች : የእዲስ አበባው እሳቶች : ስልጣን የተጎናፀፉ ኢዜማዎች : ስማቸውን የቀየሩ የጥንቱ ኢሐደጎች የዛሬ ብልፅግናዎች በአገራዊ ስብስብ ላይ ኢትዮጵያ እያሉ የሚደልሉን : በየበረታቸውና በየክልል ማድቤታቸው ጠባብ ጎሰኝነትን የሚያራምዱ ኦሮሞዎች አማራዎች ትግራይዎች ጉራጌዎች ሲዳማዎች ወዘተ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንነትን እያበሰበሱ ያሉትን ትሎች ማቆም ባለመቻሎ የአመራር ስሎትንና ችሎታዎን መጠራጠር ደረጃ ደርሻለሁ:: አዎን ! በእርግጥ እኔ በውቅያኖስ ላይ ጠብ ያልኩ ቀለም እንደሆንኩ ቆጥረው የውቅያኖስ ውሃን መልክ መለወጥ የማልችል ጠብታ ብሆንም እንድ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሚሰማኝን ሃሳብ ለእርሶ ለማሳወቅ አልቦዝንም:: ይህንንም ስል እርሶ የእኔን ግልፅ ደብዳቤ በቀጥታ ያነቡታል የሚል ብዥታ የለኝም:: ግን ከሎሌዎቾ መሃል አንዱ አይቶትና አንብቦት ቱስ ሊልሎት ይችላል የሚል ተስፋ ስላለኝ ነው:: እንደሚረዱት ከሕይወት ቀጥሎ ለሰው ልጅ ለመኖር ምርጥና የበለጠ ነገር ተስፋ ነው:: ሕይወት ምስቅልቅል ያጋጠማት ቢሆንም የሰው ልጅ ሲኖር ነገ ከዛሬ የተሻለ ይሆናል በማለት ተስፋን ስንቅ አድርጎ ዛሬ የደረሰበትን ስቃይና መከራ በተቻለው አቅም ለመወጣት ይሞክራል:: የኢትዮጵያ ሕዝብም ላለፉት 30 አመታት ያሳለፈው የመከራ ዘመን በዶ/ር አቢይ አህመድ አመራር ዘመን የስቃዩ ሸክም ይቃለልኛል ብሎ ተስፋ በማድረግ እየተጠባበቀ ይገኛል:: ታድያስ እርሶ ይህንን የሕዝብ ተስፋ ያሳኩለታል ወይስ እንደ ሃይማኖት አጭበርባሪ የዘመኑ የኢትዮጵያ “ሐዋርያቶች” እግር የሌለውን እንደሸንኮራ አገዳ እግር ታበቅላለህ በሚል የውሸት ሰበካ እየደለሉት ጊዜውን ይገፉታል? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላለፉት ሁለት ትውልዶች በእራሷ ልጆች ይህንን ዓይነት ስቃይና መከራ ይደርስባታል የሚል ግምት አልነበረኝም:: በእርግጥ እኔ ከኢትዮጵያ ወጥቼ የዛሬ 50 አመታት ወደአሜሪካ ስመጣ ይህንን ያህል ጊዜ በባእድ አገር አሳልፋለሁ የሚል ግምትም አልነበረኝም:: ትምህርቴን ስጨርስ ተመልሼ አገሬንና ሕዝቤን አገለግላለሁ ስል በወጣሁ 2 አመት ደርግ ገብቶ በሶስት አመት ቀይ ሽብር በማለት ተቃዋሚዎቹን መግደልና የተማረውን ክፍል በማውደም አገሪቱን የእውቀት መሃን አደረጋት:: ደርግን በቅርብ ባላውቀውም ከባህር ማዶ ሆኜ ሳስተውለው ችግሩ አትቀናቀኑኝ እንጂ የአገር አንድነትን ሳያስነካ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ህብረት በማያወላውል ደረጃ ኢትዮጵያዊነትን ከማስከበር ወደሗላ የማይል ነበር:: በዚህ ሊደነቅ ይችላል:: ግን ስህተቱና ውድቀቱ ሰብአዊ መብት እክብሮ የሕግን በላይነት ሥነስርዓት አለመጠበቁና አለማስጠበቁ ነው:: እርሶ ያደጉበት ኢሐደግ ግን የኢትዮጵያን ማንነት ያረከሰ : ቅድመ አያቶቻቸው አያቶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቧ ህብረት ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰውና ሕይወታቸውን ሰውተው ያቆሟትን አገር የዛሬ የኦሮሞ የአማራ የትግራይ የሲዳማ የወላይታ የጉራጌ ወዘተ ጎሰኛ ጎጠኛና ፅንፈኛ ታሪክ እንደሌላት ለማድረግ ሲሞክር በጎሳ እንደማያምኑ አቋም ይዘው ጠንካራ እርምጃ አለመውሰዶ የአመራሮን ስልትና የአመራር ቁርጥነቶን ያጠያይቃል:: የወደቀው ወያኔ ጁንታ እርዝራዥ ያነሳውን አግባብ የሌለውን ጦርነት የተጋፈጠውን ጀግናውን የኢትዮጵያን ጦር ወኔ ለመቀስቀስ ወደ ጦር ሜዳ የሄዱበትን ውሳኔ እያደነቅሁኝ ችግሮችን ለመጋፈጥ ልምድ አድርገው የወሰዱት አካሄድ ችግሮች በተነሱበት ቦታ ተገኝተው መፍትሔ መፈለግ ሳይሆን ችግሮችን አልሰማሁም አላየሁም : እኔ ሌላ ቦታ ነበርኩ የሚል ሽፋን ለመፍጠር ይመስላል:: ኧረ በእርሶ አመራር ዘመን በጎሳ ላይ የተመሰረተ ጥቃት የስንቱን ኢትዮጵያውያን ሕይወት አሳጣ:: በተለይ በኦሮሞ ክልል ውስጥ የኦሮሞ ደም የሌላቸው በትውልድ ኦሮሞ የሆኑ በክልሉ ውስጥ የተወለዱ ኢትዮጵያውያን ላይ በስመ አማራ የሚፈፀመውን ግድያ እንዴት ያዩታል? እኔ የምኖርበት አገረ አሜሪካ እንኳን በእሜሪካ የተወለዱ ዘረ ኢትዮጵያውያን ልጆቼ ይቅሩና እኔ መጤዋ የአሜሪካ ዜግነት ያገኘሁ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የዜግነት መብቴ ይከበራል:: ታዲያስ እንዴት ነው ኢትዮጵያዊ በኦሮሞ ክልል ውስጥ ኢትዮጵያዊነቱ የማይከበረው? ይህንን መሰረታዊ የዜግነት መብት በየክልሉ የማይስከብር መንግስት እንዴት የኢትዮጵያ መንግስት ነኝ ብሎ ስልጣን ላይ መቆየት ይችላል? ምንም እንኳ በየክልሉና በየጎሳው ውስጥ ጠባብነት ጎሰኝነትና ፅንፈኝነት ቢንፀባረቅም : ዛሬ በኦሮሞ ክልልና የዛሬን ስልጣንን የእኛ ተራ ነው በማለት ከሚመፃደቁ የኦሮሞ ብልፅግና ፖርቲ አባላት የስልጣን ብልግና ጋር የሚወዳደር ዝቅጠት የለም:: ይህ ፓርቲ የእርሶ የስልጣን ኮርቻ መጎናፀፊያ ፈረስ ነው::
ይህ ፈረስ ካልተገራ የተጫነበትን የስልጣን ኮርቻ መሸከም ያቅተውና ግራ ገብቶት ሲወናጨፍ ከኮርቻው እርሶን ጥሎ እሱም መሄጃ ጠፍቶት ወደ ውድቀት ገደል መከስከሱ አይቀርም:: ይህንን አጉል ሂደት የኦሮም ክልል አመራር መሪ ሽመልስ አብዲሳና እንዳንድ ጠባብ የኦሮሞ ጎሰኞች በኦሮሞ ሸንጎ ላይ የሚናገሩትን ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አንድነት ንግግር በማዳምጥ መገንዘብ ይቻላል:: ይህንን ስል የሌሎች ክልሎች አመራሮች ከጎሰኝነትና ከፅንፈኝነት ነፃ ናቸው ማለት እይደለም:: በተመጣጣኝ ደረጃ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላሉበት ሰቆቃ ተጠያቂዎች ናቸው:: የጎሳ ፖለቲካና ፅንፈኝነት አገራችንና ሰፊው ሕዝባችንን ለአላስፈላጊ ስቃይ ርሃብ ብጥብጥ የኑሮ ውድነትና መከራ አጋልጠዋል:: ግን የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ (የያዘውንና የሚያንፀባርቀውን የተረኛነት ስሜት ካላስወገደ የብልግና ፓርቲ ሊባል ይቻላል) እርሶ የወጡበትና የሚመሩት ስለሆነ ለመላው በአገሪቱ ላይ ለሚያንዣብበው የጎሰኝነትና የፅንፈኝነት ፓለቲካ በዋንነት መጠየቅ ይገባዋል የሚል አስተያየት አለኝ:: የእራሶ ፖለቲካ ፓርቲ ላይ ኢትዮጵያዋነትን ካላዳበሩ እንዴት በጎሳና በቋንቋ የተመዳደበውን ሕዝብ ወደ አንድ ኢትዮጵያዊነት ሊያመጡ ይችላሉ? እውነተኛ የእስተሳሰብ ለውጥ ከግለሰብ ጀምሮ ቤተሰብን አስተምሮ ማህበረሰብን አካቶ አገራዊ አንድነትን ይገነባል:: በአሁን ሰዓት የእርሶ አመራር በአገራዊ አንድነትና በሕዝብ እኩልነት ተስፋ ሰጭና አጥጋቢ ስራ ሰርቷል የሚያሰኝ ውጤት አላሳየም:: ሁላችንም እንደምናውቀው ጁንታው ወያኔ የጀመረውን ኢፍትሀዊና ትክክል ያልሆነ ጦርነት በአገራችን ላይ ሲጀምር የአገር ሕዝብ በአንድነት ሆይ ብሎ ለመሰዋእትነት ከጎኖ ቆሞ ነበር:: ይህ ወኔ የተሞላው የሕዝብ ንቅናቄ ጎሰኝነትና ፅንፈኝነትን ለመዋጋት ለእርሶ መነሻ መሆን ነበረበት:: አልተጠቀሙበትም:: ምክንያቱን ስፈልግ ድንገት እርሶ ይህንን የ30 ዓመት የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ለስልጣን ማቆያ ይጠቀሙበታል ወይስ በርሶ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉትን አባላት ከጠባብ ጎሰኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት መለወጥ አለመቻሎ ይሆን የሚሉ ጥያቄዎችን አሰላስላለሁ:: ችግሩ እርግማን ወይስ አለመታደል?
ይህችን ትንሽ ግልፅ ደብዳቤ ስፅፍሎት እንደ ትውልደ ኢትዮጵያ ለተወለድኩባት ውድ እናት አገሬና እርግማን ወድቆበት ወይም አለመታደል ሆኖበት ከትውልድ ወደ ትውልድ የችግር ቁራኛ ሆኖ እንኳን ምቾት ሊያስብ ቀርቶ የእለት ጉርሻውን እንዴት እንደሚያገኝ ግራ የተጋባውን የአገሬን ሕዝብ ከዚህ ከማይቆም ሰቆቃ ለማውጣት ማስታወሻ ወይም ማነሳሻ ይሆኖታል በሚል ግምትና እኔም ሁለት ሳንቲም ዋጋ ያላትን አስተሳሰቤን ለማጋራት በመፈለግ ነው:: አንድነትን ያጠናክራሉ:: እኩልነትን ያሰፍናሉ:: ማንኛውም የኢትዮጵያ ተወላጅ የትም የኢትዮጵያ ክፍል ሆዶ ለመኖር ለመስራት ለመነገድ እምነቱን ያልአንዳች ፍራቻ ለማካሄድ የሚችልበትን መንገድ ይቀይሳሉ የሚል ተስፋ በርሶና በአስተዳደሮ በመተማመን ነው:: ባለፉት አራት አመታት የሰሯቸው አምራቂ ስራዎች ሊካዱ አይገባም:: ምንም እንኳ ትዝብቶቼ በስእልና በኢንተርኔት ባየሗቸው ቢሆንም ያየሗቸው አንድ አንድ የልማትና የማስዋብ ስራዎች ጥሩ ናቸው:: ግን በሰዎች የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ላይ ማለትም ከመንደርኝነት ወደ እውራጃነት ከጎሰኝነት ወደ ሰውነት ከክልልነት ወደ አገራዊነት ከመለያየት ወደ አንድነት ከእኔነት ወደ እኛነት ከብቸኝነት ወደ ጋራነት ከትንሽነት ወደ ትልቅነት ከቄሮና ከፋኖ ጠባብነት ወደ ኢትዮጵያ ወጣትነት ማስተማርና መቀየር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል:: ከመገንባት ይልቅ የተገነባውን የሚያፈርስ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን የሚያራምድ ለሰው ልጅ ከማሰብ የሰውን ልጅ የሚያርድና የሚያቃጥል ትውልድን ከእንሰሳነት ወደ ሰው ልጅነት መለወጥ ካልተሰራበት አጥፊና አፍራሽ ወራሽ ይመጣል::
ይህም ለውጥ መጀመር ያለበት በኦሮሞ በአማራ በትግራይ በሱማሌ በጋምቤላ በደቡብ ሕዝቦች በሲዳማ በቤንሻንጉልና ጉሙዝና ብተቀሩት ክልሎች ብልፅግና ፓርቲ አባላት ላይ ነው:: ለ60 ዓመታት ያለውን ርሃብ መቋቋም ሳትችል ሕዝቧን በልመና ስንዴ በምትቀልብ አገር የሚኖር ስለጎሳ መብት ባንዲራና ድንበር ማውራት የጉዳዮችን ቅደምትነትን አለመከተል ይሆናል:: ይህ የጎሳ ፖለቲካ ውዝግብና የእኔ ጎሳ አገር ለመግዛት ተራው ነው የሚል ስሜት እንዲህ ከቀጠለ በ1994 አመተምህረት በሩዋንዳ የተደረገውን አይነት የሰው ጅምላ ጭፍጨፋን ሊያመጣ ይችላል:: ይህ ማንኛውንም የኢትዮጵያ ጎሳን ከፍ አያደርገውም:: እልቂቱ አስከፊ ይሆናል:: ሩዋንዳ ከኤፕሪል 1994 እስከ ጁን 1994 በዘጠኝ ሳምንት ውስጥ አንድ ሚልዮን ሩዋንዳዊያኖችን አጥታለች:: ይህንን ያህል አሳዛኝ የሰው እልቂት በአገራችን እንዲፈፀም የሚመኙ እርኩሶች በየጎሳው ውስጥ ይኖራሉ:: ይህንን አይነት ግፍ የሚመኙት በግርግር የግል ሃብት ለማከማቸት የሚፈልጉ ወይም የሰው ልጅ ስቃይ የሚያስደስታቸው የሰይጣን ቁራጮች ናችው:: በተለይ በአስተዳደርና በአመራር ውስጥ ተሰግስገው ችግር የሚያምሱትን መንጥረው ካላስወገዱ የሚመኙትን ለውጥ ለኢትዮጵያ ቀርቶ እርሶ ስልጣን ላይ ለመቆየት ያስቸግሮታል:: ይህንን ወቀሳ ሳቀርብሎት ከበፊቱ ዛሬ ለእርሶ ያለኝ ድጋፍ ትንሽ ቢቀንስም ተስፋዬ ቢሟሟም የኢትዮጵያን አንድነት በማስጠበቅ የዜጎቿ እኩልነትና መብት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በማስከበር ውጤታማ እንዲሆኑ መመኘቴን አላቆምም:: ግን ከሩዋንዳ መማር ተገቢ ነው:: ባለፉት 27 አመታት ሩዋንዳ ከዚያ አሳዛኝ ክስተት ወጥታ ዛሬ ሰላማዊ የለማችና ቆንጆ አገር የሆነችው ሩዋንዳዊነት እንጂ የሁቱና የቱትሲ ጠባብ ጎሰኝነት በአገሪቱ ቦታ እንዳይኖረው የማያወላውል ጠንካራና ወሳኝ እርምጃ ያለው አስተዳደር ስለወሰደ ነው:: በመወላወል የአገር አንድነት የሕዝብ ህብረት አይገነባም:: ክልል ሲኬድ ስለክልል ጎሳ መብትና የበላይነት ተወርቶ : ሰፊው ኢትዮጵያዊያን ፊት የኢትዮጵያና የኢትዮጵዊነት ቱልቱላ በመንፋት አገር አትለማም :: ህልውናዋ በተረትና በሰበካ አይጠበቅም:: ኦሮሞ አማራ ትግራይ ጋምቤላ ወዘተ ክልል ስንሄድ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያለማቋረጥ ማውራት ሃቀኝነት ነው:: በክልል ደረጃ ስለክልል ልማትና እድገት መነቃነቅ ተገቢ ነው:: ግን በክልል ደረጃ የዚያ ጎሳን ከኢትዮጵያዊነት በላይ አድርጎ ማቅረብ : የዚያ ጎሳ ሕዝብ የተለየ በደል እንደደረሰበት መዋሸት ከአመራርና ከባለስልጣናት የሚጠበቅ አይደለም:: ኢትዮጵያ ውስጥ ጎሳ ለጎሳ የተበዳደለው ነገር የለም:: በዳዯቹ መሪዎችና በስልጣን ላይ ተወዝፈው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ከርሳሞች ናቸው:: ይህንን ግልፅ አድርጎ ማስተማር በሃሰት ፕሮፓጋንዳ የተወናበደውን ሕዝብ እውነቱን እንዲያውቅ ይረዳል:: በእነጀዋር መሐመድ በእነልደቱ አያሌው በእነ እስክንድር ነጋ በእነበቀለ ገርባ በሽመልስ አብዲሳ በጌታቸው ረዳ አይነት ውሸታሞች የተታለለውን ሕዝብ መመለስ የሚቻለው እርሶ ለፓለቲካ ምቾት ሳያስቡ በየጊዜው እየወጡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንዱ ጎሳ ሕዝብ ሌላውን የበደለው ነገር እንደሌለ ሲያስተምሩ ነው:: ሌላ የምመክሮት በዚህ የውሸት የጎሳ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት አንድ አካባቢ ላይ ሕዝብ ሲገዳደል አላየሁም አልሰማሁም ከማለት ሄደውም ሆነ በሬድዮ በቴሌቭዥን ወጥተው ሕዝብን ማረጋጋት ማፅናናት የታላቅ መሪ ምልክት መሆኑን እንዲያውቁት ነው:: አያውቁትም እልልም:: ግን ሁኔታዎች በተከሰቱበት ሰአት በተደጋጋሚ ዝምታን ስለመረጡ ነው:: በችግሩና በስቃዩ ወቅት ሕዝብ የሚጠብቀው አለሁላችሁ:: ስቃያችሁ ስቃዬ ነው:: ሃዘናችሁ ሃዘኔ ነው የሚል መሪን ነው:: ጥሩ ምሳሌ ብንል የወታደር ልብሶን ለብሰው ጦር ሜዳ ሲሄዱ ወታደሩና የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማውን ወኔ ማስታወስ ተገቢ ነው:: ታላቅ መሪ የሕዝብ አለኝታ የሕዝብ ኩራት ነው::
ዛሬ አገራችና ሕዝባችን ለተጋለጡበት የፖለቲካ ውስብስብ ዋና ምክንያት አድርገው ሲያቀርቡት የነበረው ለጊዜው አገሪቷ የምትተዳደርባት ሕገመንግስትን ነበር:: እርሶ ማምጣት ለሚፈልጉት ለውጥ ሕገመንግስቱ እንቅፋት ከሆነ አሁን ምርጫ ተደርጏልና ለምን ለመቀየር እልተሞከረም? አይሞከርም? ከባህር ማዶ ሆኜ ስገነዘብ የኢትዮጵያን የጠቅላይ ግዛት ስነ መልክአ አከፋፈል አጥፍቶ የክልል እስላለፍን ያመጣው በጁንታው ወያኔ የሚመራው ኢሕአዴግ ሕዝብን ጠይቆና አማክሮ ሳይሆን በአምባገንነነት ተሞልቶ ነው::
የእርሶ አስተዳደር በእርግጥ ዛሬ ያለውን የጎሳ ፓለቲካ አስወግዶ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያዊነት ማድመቅ ከፈለገ መጀመሪያ ፀረ አንድነት ፀረ ኢትዮጵያ ፀረ ህብረት የሆነውን ሕገመንግስት ለሕዝብ ምክር ቤት እቅርቦ ይህ ሕገመንግስት ካመጣው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ የበለጠ ስለሆነ እንዲሻሻልና እንዲቀየር ማድረግ ይገባዎታል:: ሕገመንግስት ስነስርአት ላለው ለሕግ የሚገዛ መብቱን ለማስከበር ግዴታውን የተረዳ የሌላውን መብት ለሚያከብር ሕዝብና መንግስት የጥሩ አስተዳደር መመሪያ ነው:: ግን ከዚህ በፊትም ሆነ በእርሶ አገዛዝ ዘመን ሕገመንግስት ውስጥ የተፃፉትና የተቀመጡት አንቀፆች ምን ያህል በስልጣን ላይ በነበሩትና ባሉት ይጠበቃሉ ይከበራሉ? ይህንን ልንከራከርበትና ልንወያይበት እንችላለን:: ደሃውን ሰፊ ሕዝብ ተጠያቂ ያረጋል እንጂ ባለስልጣናት አያከብሩትም:: በእርግጥም ጠባብ ጎሰኝነትን የሚያራምድና የሚያጎላ ሕገመንግስት የኢትዮጵያን ህልውና ከማስጠብቅና የሕዝቧን እንድነት ከማስከበር ጋር ይጣጣማል ማለት አይቻልም:: ለዚህም ነው ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቦቿ ህብረት የመጀመሪያ እርምጃ መሆን ያለበት በወደቀው ኢሕአዴግ የተቀየሰውን አገር አፍራሽና ሕዝብን በጎሳ ከፋፋይ ሕገመንግስትን መለወጥ ነው:: ባለው ሁኔታ ባለተረኛ ጎሳ የበላይነትን እንዲያቅራራ ከማድረግ በስተቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አመጣለሁ ማለት “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ ” የሚለውን ተረት መተረት ይሆናል:: ከላይ እንደጠቆምኩት በእርግጥ ኢትዮጵያን የተረኛ ጎሰኛ የስልጣን ብልግና ማሳያ እንዳትሆን ከፈለጉ አጠገቦ ያሉትን የጎሳ አቅራሪዎችን ማስተንፈስ ወይም ማስወገድ ያስፈልጎታል:: ትረካውን ትምህርታዊ መግለጫዎንና ሰበካውን አቆይተው በግልፅ ጠባብ ጎሰኞችን በጠባብነታቸው እየጠሩ ይህ የጎሰኝነት ፖለቲካ ዞሮዞሮ ራሱን ጠባቡን ጎሰኛ እንደሚጎዳ በማስገንዘብ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ማድረግ ይገባዎታል:: ይህንን ካደሩጉ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከደረሰባቸው እርግማን ወይም አለመታደል እጣ ማውጣት ይችላሉ:: ጎሰኝነት ለሩዋንዳ ሁቱስና ቱትስዎች ያመጣው በደም መፋሰስና በሕይወት መጥፋት ልብ የሚሰብር ሃዘን እንጂ ጥቅም እንደሌለ ሁላችንም መገንዘብ ይኖርብናል::
ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድላቸው::
ከአልማዝ አሰፋ
[email protected]